1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፓሪሱ ረቂቅ ስምምነት

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 5 2008

የዛሬ ስድስት ዓመት ኮፐንሃገን ላይ ብዙ ተጠብቆ ተሳታፊዎችና ተደራዳሪዎች ባዶ እጃቸዉን መመለሳቸዉ እነሱን ብቻ ሳይሆን ጉዳዩን ጉዳዬ ብሎ የሚከታተለዉን ወገን ሁሉ ያሳቀቀ አጋጣሚ ነበር።

https://p.dw.com/p/1HNr1
Frankreich Cop21 Klimagipfel in Paris Klimaabkommen beschlossen
ምስል Getty Images/AFP/F. Guillot

የፓሪሱ ረቂቅ ስምምነት

ባሳለፍነዉ ሳምንት ማለቂያ ላይ በተቃራኒዉ ፓሪስ ወደእሷ ያንጋጠጡ እንዳያፍሩ ሰግታ፤ ተጨንቃ፤ ተሯሩጣም ሆነ በለስላሳዉ ዲፕሎማሲዋ ሸምግላ የየግል ጥቅማቸዉን አስቀድመዉ ሲጓተቱ የነበሩትን አቀራርባ ከባዶ እጅ አድናቸዋለች። ለዚህም ሞቅ ያለ ጭበጨባ ተችሯታል። ጤና ይስጥልኝ የዝግጅታችን ተከታታዮች እንደምን ሰነበታችሁ? በሽብር ጥቃት ከደረሰባት ድንጋጤና ጉዳት ሳታገግም ዓለም አቀፉን የተመድ የአየር ንብረት ለዉጥ ተመልካች ጉባኤ COP 21ን ያስተናገደችዉ ፈረንሳይ ዋና ከተማዋ ከሰማይ ጠቀሱ ማማዋ ቀጥሎ የሚታወስበትን ፖለቲከኞቹ «ታሪካዊ» ካሉት ስምምነት እንዲደርሱ ማግባባቱ ተሳክቶላታል።

ለሁለት ሳምንታት የዘለቀዉ የፓሪሱ የተመድ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለዉጥ ተመልካች ጉባኤ በመጨረሻዉ ዕለት ማለትም ባለፈዉ ቅዳሜ ምሽት የዉጥረት እና ጭንቀት ድባብ ዉጦት እንደነበር ነዉ የተሰማዉ። ከ196 ሃገራት የተዉጣጡት 50ሺህ የጉባኤዉ ተሳታፊዎች ተደራዳሪዎቹ ከምን ላይ ይደርሱ ይሆን በሚል የየመጡበት ሀገር ስም ከተለጠፈበት ጀርባ እየተቁነጠነጡ ለረዥም ሰዓታት ጠብቀዋል። ቀኑ ሳይጠናቀቅ በጥድፊያ የተደረሰዉን የድርድር እና ዉይይት መቋጫ ማምሻዉ ላይ የፈረንሳይ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሎሮ ፋቢዮ በእፎይታ ይፋ አደረጉ።

Frankreich Cop21 Klimagipfel in Paris Klimaabkommen beschlossen
ምስል Reuters/S. Mahe

«አሁን የጉባኤዉን ተሳታፊ ወገኖች «የፓሪስ ስምምነት» የተባለዉን ረቂቅ ዉሳኔ እንዲያፀድቁ እጋብዛለሁ። አዳራሹን በመላ እያማተርኩ ነዉ፤ አዎንታዊ ምላሽ አያለሁ። ምንም ተቃዉሞ አልሰማሁም። ስለዚህምየፓሪስ ስምምነት ለአየር ንብረት ተቀባይነት አግኝቷል።»

በትንሿ መዶሻ አሉ ፋቢዮ ታላቁን ዉሳኔ አስረገጥንበት። ተጨበጨበ። ጭብጨባዉ ምናልባትም ለረዥም ጊዜያት የየግል ጥቅማቸዉን እያሰቡ የሚከራከሩ ወገኖች የመስማማታቸዉ ግልግል ያስከተለዉ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም በፓሪሱ ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ የተገኘዉ ዉጤት አሁንም የምድራችንን ሙቀት ተመራማሪዎቹ በቂ በሚሉት ደረጃ ሊያስቀንስ የሚችል እንዳልሆነ ትችቱ ወዲያዉ ነዉ የተሰማዉ። ረቂቅ ስምምነቱ በዋናነት ሃገራት በሙሉ ወደከባቢ አየር የሚለቁትን የሙቀት አማቂ ጋዝ መጠን ለመወሰን መቁረጣቸዉ እና ለመቀነስም ዝግጁነት ማሳየታቸዉ፤ የዓለም የሙቀት መጠንም ከ2 ዲግሪ እንዳይበልጥ እንደዉም ከዚያም በታች ቢቻል የሚሉ አሉ ለዚህም ርምጃዎች ይወሰዱ የሚለዉ ላይ መስማማታቸዉ፤ በየዓመቱም የታዩ መሻሻሎች እንዲቃኙ መወሰናቸዉ፤ እንዲሁም በአየር ንብረት ለዉጥ ለተጎዱትን አዳጊ ሃገራት በየዓመቱ ከ2020ዓ,ም ጀምሮ የ100 ቢሊየን ዶላር ርዳታ ለመስጠት መስማማታቸዉን ያካትታል። ዝርዝር ስምምነቱ እና አፈፃፀሙ ደግሞ እያንዳንዱ ሃገር በየግሉ መክሮ የሚወስነዉ ይሆናል። ለዚህም ገና ወራትን መጠበቅ ግድ ነዉ።

Frankreich Cop21 Klimagipfel in Paris Klimaabkommen beschlossen
ምስል Getty Images/AFP/F. Guillot

ያም ሆኖ ግን እንደተንታኞች ምዘና ከሆነ ሃገራት የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀትን በተገቢዉ መጠን የማይቀንሱ ከሆነ የምድር ሙቀት ከዘጠና አምስት ዓመታት በኋላ 4,5 ዲግሪ ይደርሳል። እስካሁን ባለዉ አካሄድት ከቀጠለም በተጠቀሰዉ ጊዜ 3,6 ዲግሪ መድረሱ አያጠራጥርም። ፓሪስ ላይ በተደረሰዉ ስምምነት መሠረትም እንኳ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2100ዓ,ም 2,7 ዲግሪ ይደርሳል።

ዩናይትድ ስቴትስ ዓለም ከዚህ ስምምነት እንዲደርስ ለፍቻለሁ ትላለች። ላሳዩት ትብብርና ተሳትፎም ሌሎች ሃገራትንም ያመሰገኑት ፕሬዝደንቷ ባራክ ኦባማ፤ ለፓሪሱ ዉጤት የአንበሳዉ ድርሻ የእሳቸዉ አስተዳደር መሆኑን ለዜጎቻቸዉ ሳይገልፁ አላለፉም።

«ሁለት መቶ ገደማ የሚሆኑት ሃገራትን ትልቅም ሆነ ትንሽ፤ የበለፀጉም ሆኑ በማደግ ላይ ያሉ፤ ለመላዉ ዓለም ስጋት የሆነዉን ችግር ለመጋፈጥ በጋራ የሠሩ ሕዝቦችም ላመሰግን እወዳለሁ። ዓለም እንደአንድ ሲቆም በጋራ ማድረግ የምንችለዉን አሳይተናል። ዛሬ የአሜሪካን ሕዝብ ሊኮራ ይችላል፤ ምክንያቱም ይህ ታሪካዊ ስምምነት የአሜሪካን አመራር መታሰቢያ ነዉ፤ ባለፉት ሰባት ዓመታት ዩናይትድ ስቴትስ በመለወጥ ላይ ያለዉ አየር ንብረት የሚያስከትለዉን አንዳንድ ተፅዕኖ ለመለወጥ የአየር ንብረት ለዉጥን ለመግታት በሚደረገዉ ጥረት የዓለም መሪ ወደመሆን አሸጋግረናል።»

በአንድ በኩል 196ቱ ሃገራት የአየር ንብረት ለዉጥ መኖሩን በአንድ መንፈስ መቀበላቸዉ አንድ ነገር መሆኑን አቶ ዮናስም ሆኖ ሌሎች ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች አፅንኦት ይሰጡታል። በአንፃሩ ለከባቢ አየር ብክለትም ሆነ እሱን ተከትሎ ለመጣዉ የአየር ንብረት ለዉጥ ከፍተኛ አሉታዊ አስተዋፅኦ ያደረጉ ሃገራትን የጥፋታቸዉን ያህል ለማረምም ኃላፊነት እንዲወስዱ የሚያደርግ ዓይነት አለመሆኑ ግን ጥንካሬዉን ያጎድለዋል ባይናቸዉ።

Frankreich Klimagipfel in Paris PK Obama
ምስል Reuters/K. Lamarque

የፓሪሱ ስምምነት ዓለማችንን የአየር ንብረት ለዉጥ ካስከተለባት አስጊ መዘዞች ለመታደግ እድሎችን የሚያመቻች ረቂቅ ዉል ነዉ በሚል ከአሁኑ የሚያሞካሹት ወገኖች ያ የኮፐንሃገኑ ክስረት እንዳይደገም ፍርሃት ያደረባቸዉ ሳይሆኑ እንደማይቀሩ ነዉ ተቺዎች የሚናገሩት። ድርድሩና ዉይይቱ ቀላል ጊዜና አቅም አይደለም የጨረሰዉ። እንቅልፍ አልባ ሌሊቶች ሳይቀሩ አልፈዋል። ጉባኤዉ ዓርብ ይጠናቀቃል ቢባልም ከስምምነት ዉሳኔዉ የተደረሰዉ ግን ቅዳሜ ማታ ነበር። የኮፐንሃገኑ ትዝታ እያሳቀቃቸዉ ወደስምምነት የተገፉት ወገኖች ሁሉም በተናጠል ሲታዩ ደስተኞች ሆነዋል ማለት አይቻልም።

የአየር ንብረት ለዉጥ ለመግታት ሊወሰድ የሚገባቸዉን ርምጃዎች ያካተተዉን የፓሪሱን ረቂቅ ስምምነት በጭብጨባና ደስታ የተቀበሉት በርካታ ሃገራት ዉዳሴም እየቸሩት ነዉ። ጀርመን ለመፃኢዉ ሰብዓዊ አኗኗር መልካም አጋጣሚ ነዉ ስትል፤ ቻይና እንከን አልባ የሚባል ባይሆንም አንድ ርምጃ ወደፊት መሆኑን ግልፅ አድርጋለች። ለተመድ ዋና ፀሐፊ ባን ጊሙን ከብዙ ድካም በኋላ የተገኘ ስኬት ነዉ ረቂቅ ስምምነቱ። በረቂቅ ስምምነቱ የተካተተዉ ሁሉ ተግባራዊ መሆን መቻሉ ግን ጥያቄ ነዉ። የፓሪሱ ረቂቅ ስምምነት በቀጣይ ወራት ሃገራት በየግላቸዉ መክረዉበት የሚያፀኑት ቢሆንም ለጊዜዉ ከምንም አንድ ነገር ተብሎ በብዙዎች ተወስዷል። የብዙዎቹ ስጋትም ስምምነቱ ከፀደቀ በኋላ ለተግባራዊነቱ የሚደረገዉ ክትትል በግልፅ አለመቀመጡ ክፍተት ይፈጥር ይሆን የሚለዉ ነዉ።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ