1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን የፀጥታ እርምጃዎች

ማክሰኞ፣ ጥር 5 2007

ባለፈው ሳምንት ፓሪስ ፈረንሳይ ውስጥ የተፈፀመው የሽብር ጥቃት በመላ አውሮፓ የፀጥታ አጠባበቅ ጉዳይ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው አድርጓል ።

https://p.dw.com/p/1EJaM
Trauermarsch in Paris 11.1.2015
ምስል Reuters/Platiau

የህብረቱ አባል ሃገራት የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮችም ችግሩን በጋራ መከላከል በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ፓሪስ ውስጥ ከትናንት በስተያ መክረው የመረጃዎችን ልውውጥ ለማጠናከር ተስማምተዋል። ጀርመን በበኩልዋ የሽብር ጥቃትን መቋቋም ያስችላል ያለችውን አዲስ ህግ ልታወጣ ተዘጋጅታለች ።
ፓሪስ ፈረንሳይ ውስጥ የደረሱትን የሽብር ጥቃቶች ያወገዙት የዓለም መሪዎች ባለፈው እሁድ በዋና ከተማይቱ በተካሄደውታላቅ ሰለማዊ ሰልፍ በመካፈል ለፈረንሳይ ህዝብ ያላቸውን አጋርነት አሳይተዋል ። የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ የጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ኬምረንን ጨምሮ ከ40 በላይ የመንግሥታት መሪዎች ና ቁጥሩ 3.7 ሚሊዮን የተገመተ ህዝብ የተካፈለበት ሰልፍ በጥቃቱ የተገደሉት 17 ሰዎች የታሰቡበት ብቻ ሳይሆን ሃሳብን በነፃ የመግለጽ ነፃነት ላይ የተቃጣውን ጥቃት ያወገዘ ጭምር ነበር ። የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ብዙዎችን ለአንድ ዓላማ በህብረት ያስቆመው ሰልፉ ይህንኑ መልዕክት አስተላልፏል ብለዋል ።
« ያ የሚያመለክተው ለነጻነት ለእኩልነትና ለወንድማማችነት የሚቆሙ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን ነው ። እናም የፈረንሳይ ታሪካዊ ወዳጅ እንደመሆናቸን እኛ እንደ ጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክ ድግፍ ማድረግ እንደምንፈልግ ዛሬ መናገር በመቻላችን ክብር ይሰማናል ።በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ከፈረንሳይ ህዝብ ጎን በመቆም ጽናቱን እንዲሰጣችሁ ከልብ እንመኛለን ።»


ዓለም በህብረት ያወገዛቸው ያለፈው ሳምንቶቹ የፓሪስ ጥቃቶች አውሮፓውያንን በእጅጉ ማሳሳበቸው ቀጥሏል ። የአውሮፓ መንግሥት ከጥቃቱ በኋላ በተናጠልም ሆነ በጋራ የፀጥታ እርምጃዎቻቸውን አጠናክረዋል ። በፈረንሳይ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነው የተባለው ካለፈው ረቡዕ አንስቶ እስካለፈው አርብ ፓሪስ ውስጥ የተፈጸመው የአሸባሪዎች ጥቃት ፈረንሳይ ውስጥ ዳግም ሊደርስ ይችላል የሚለው ስጋት አሁንም እንዳለ ነው ። በዚህ ሰበብም ፈረንሳይ ጥቃት ሊፈፀምባቸው ይችላል ተብለው የሚያሰጉ አካባቢዎችን የሚጠብቁ 10 ሺህ ወታደሮች ከዛሬ ጀምሮ አሰማርታለች ። ታጣቂዎች ባለፈው ረቡዕ አወዛጋቢ ምፀታዊ ምስሎችን የሚያወጣውን የሻርሊ ኤብዶ ጋዜጣ የፓሪስ ቢሮ ያለ አንዳች ችግር ሰብረው በመግባት የጋዜጣውን ሠራተኞችና ፖሊሶችን በአጠቃላይ 12 ሰዎችን መግደላቸው አስደንግጦና አስቆጥቶ ሳያበቃ በማግስቱ እዚያው ፓሪስ ሌላ ታጣቂ ፖሊስ መገደሉ ይኽው ተጠርጣሪ በሚቀጥለው ቀን አርብ የይሁዲዎች የሸቀጣሸቀጥ መደብር ውስጥ ሰዎችን አግቶ ከመካከላቸው 4ቱ መገደላቸው ፈረንሳይ ብቻ ሳትሆን በአጠቃላይ የአውሮፓ መንግሥታት የፀጥታ አጠባቃቸውን ዳግም እንዲፈትሹ አስገድዷል ።ባለፈው እሁድ እዚያው ፓሪስ ውስጥ የአውሮፓ ህብረት የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባካሄዱት ምክክር አሸባሪዎችን መከታተል የሚያስችሉ መረጃዎችን ለመለዋወጥ ተስማምተዋል ። የፈረንሳይ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ቤርናር ካዘነቭ ምክክሩ በተካሄደበት እለት እንዳስታወቁት ሚኒስትሮቹ ከተስማሙባቸው ጉዳዮች አንዱ በተለይ በአንዳንድ የአውሮፕላን ተጓዦች ላይ ክትትል ማድረግን ይጨምራል ።
«በርግጥ በተጨባጭ መስፈርቶች መሰረት በተወሰኑ መንገደኞች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማካሄድ እንደሚገባ ሁላችንም ተስማምተናል ። እርግጥ ነው ይህ ሁሉ የሚከናወነው መሰረታዊ መብቶችን በማክበር ነው ።

Trauermarsch in Paris 11.1.2015
ምስል Reuters/Gaillard


የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን በተለይ የመንገደኞችን መረጃ ልውውጥ ተግባራዊ እንዲሆን ቢያበረታታም የአውሮፓ ፓርላማ ግን የግለሰቦችን ምስጢር የመጠበቅ መብት እንዳይነካ በሚል ስጋት እርምጃውን አግዶት ነበር ። ሆኖም የህብረቱ አባል ሃገራት ፖሊሶችና የደህንነት መስሪያ ቤቶች አሸባሪዎችን ለመከታተልና ለማዳን እንዲችሉ የመንገደኞችን ስም ዝርዝሮች የያዙ መረጃዎችን የሚለዋወጡበት አሰራር አለ ።ካዘነቭ የእነዚህ መረጃዎች ትኩረት በሰዎቹ ማንነት ላይ ብቻ የተወሰነ መሆን አይገባውም ይላሉ ። «እነዚህ የመረጃ ልውውጦች የውጭ ተዋጊዎቹ የሚጠቀሙባቸውን የገንዘብ ዝውውሮች ድጋፍን ጭምር ሊያካትቱ ይገባል ።አደጋ ሊጥሉ ስለ ሚችሉ ወገኖችም የመረጃ መለዋወጥ ያስፈልጋል ። ታላላቅ መንግሥታት የደህንነትና የፀጥታ መስሪያ ቤቶች የትኛዎቹን አደገኛ ሰዎች በየሃገሮቻቸው እንደሚከታተሉ ርስ በርስ መረጃ ሊለዋወጡ ይገባል ።»
»
አባል ሃገራት አሸባሪዎችንና የአየር ተጓዦችን የተመለከቱ መረጃዎችን በመለዋወጥ ረገድ ፈጣን እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ያሳሰቡት ካዘነቭ ህገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርም የሚተኮርበት አንዱ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል ።
«ህገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን ለመከላከል እየሞከርን ነው ። በዚህ ጉዳይ ላይ አፅንዖት አደርጋለሁ ፤ በአውሮፓ ደረጃ በህገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ መካሄድ ይገባዋል ። በጉዳዩ ላይ የመረጃ ልውውጥና የጋራ ዘመቻዎች ተግባራዊ መሆን ይገባቸዋል ።»
የአውሮፓ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች እነዚህን በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ተባብሮ በመሥራት መረጃዎችን ለመለዋወጥ ሲስማሙ ጀርመን ደግሞ የሽብር ጥቃትን ይከላከላል ያለችውን አዲስ ህግ እንደምታወጣ በቅርቡ አስታውቃለች ። የጀርመን ፌደራል የፍትህ ሚኒስትር ሃይኮ ማስ እንደተናገሩት ህጉ በተለይ ለሽብር የሚሰማሩና ከአሸባሪዎች ጋር የሚተባበሩ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ን ነው ።

Trauermarsch in Paris 11.1.2015
ምስል Kitwood/Getty Images


«ራሳችንን ከሽብር ጥቃት ለመከላከል አዲስ ህግ ያስፈልገናል ። ይህ ካለፉት ሳምንታት ወዲህ እየተዘጋጀ ነው ።ይህም የተባበሩት መንግሥታት የውጭ ተዋጊዎች ኃይሎች በሚል ርዕስ ያሳለፈውን ውሳኔ ተግባራዊ የሚያደርግ ነው ። ወደ ውጭ በመሄድ በጅሃድ ጦር ተሳታፊ ለመሆን አስበው የሚጓዙ በሽብር ጣቢያዎች በሚካሄድ ማንኛውም እንቅስቃሴ የሚካፈሉ ወይም ደግሞ ወይም ደግሞ በቀጥታ የሽብር እርምጃ በመውሰድ የሚተባበሩትንም እንዲቀጡ እናደርጋለን ።በሁለተኛ ደረጃ ሽብር ለማካሄድ መጠኑ አነስተኛም ቢሆን ገንዘብ ማዋጣት አሸባሪዎችን መርዳት ስለሚሆን ይህም የሚያስቀጣ ይሆናል ። ከአውሮፓ አጋሮቻችንና ከባልደረባዬ ከቶማስ ደ ሜዜር ጋር ይህንን እያዘጋጀን ይህንኑ በዚህ ወር ውስጥ ይፋ እናደርጋዋለን ። »
ባለፈው ቅዳሜ ለሊት ሰሜን ጀርመን ሃምቡርግ ውስጥ በሚገኝ የሻርሊ ኤብዶን የካርቱን ምስሎች በሚያሳትም ሃምቡርገር ፖስት የተባለውጋዜጣ ቢሮ ጥቃት ተፈፅሞበታል ።በጥቃቱ ግን የተጎዳ ሰው የለም ።ይኽው ጥቃቱ ከፓሪሱ ጥቃት ጋር ግንኙነት ይኑረው አይኑረው ገና አልተረጋገጠም ። ከፓሪሱ ጥቃት ወዲህ አንዳንድ የጀርመን የጋዜጣ ድርጅቶች የፖሊስ ጥበቃ እየተደረገላቸው ነው ። በጀርመን የአሸባሪዎችን ጥቃት ለመከላከል ይወጣል ከተባለው ህግ ጋር በሽብር ተጠርጣሪ ያልሆኑ ግለሰቦችን የስልክና የኢንተርኔት ግንኙነቶችን የያያዙ መረጃዎችን ለ6 ወራት ማስቀመጥን የሚፈቅደው ህግ እንደገና ተግባራዊ ሊሆን ይችል ይሆን የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም ። የጀርመን የፍትህ ሚኒስትር ግን ይህ አስፈላጊ ሆኖ አይታያቸውም ።
«ይህ ለኔ አይታየኝም ። ከዚህ ጥቃት በኋላ የግለሰቦችን መረጃዎች እንደገና ማከማቸቱ ትርጉም የሚኖረው አይመስለኝም ።በመጀመሪያ በፈረንሳይ መረጃዎችን የማከማቸቱ አሠራር አለ ሆኖም ይህ አሰራር ግን አደጋውን ከመድረስ አላገደውም በሁለተኛ ደረጃ የአውሮፓ ፍርድ ቤት ይህን ዓይነቱ አሰራር የግለሰቦችን መብት የሚጥስ ነው ሲል ውሳኔ አስተላልፏል ።

Bundesjustizminister Heiko Maas in Berliner Moschee 9.1.2015
ምስል picture-alliance/dpa/Rainer Jensen
Thomas de Maiziere und Heiko Maas
ምስል picture-alliance/dpa/R. Jensen

በአሁኑ ጊዜ እኔም ሻርሊ ነኝ እያልን የፕሬስ ነፃነትን ለማስጠበቅ ቆመናል ። የግለሰቦችን የስልክና የኢተርኔት ግንኙነቶችን የያዙ መረጃዎችን በማከማቸት የጋዜጠኞችን መረጃዎችንም በሙሉ ሰብስቦ በማስቀመጥ የፕሬስ ነፃነትን እንገድባለን ። ይህ አብሮ የሚሄድ አይደለም ። መረጃዎችን ሰብስቦ ማስቀመጡ አይረዳንም ። መሰረታዊ ሰብዓዊ መብቶችን የሚጥስ ነው ። ስለዚህ እኔም እንደገና መመለሱ አይታየኝም ።»
የጀርመን ባለስልጣናት እንደሚናገሩት በአሁኑ ጊዜ በጀርመን የሽብር ጥቃት ያን ያህል አሳሳቢ አይደለም ። የየፌደራላዊት ሪፐብሊክ ጀርመን ህገ መንግሥት ጠባቂ መሥሪያ ቤት ፕሬዝዳንት ሃንስ ጆርጅ ማሰን አልቃይዳ ራሱን የሶሪያና የኢራቅ እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራው IS ለጀርመንም ጠላቶች መሆናቸው የታወቀ መሆኑን ተናግረው የሽብር ጥቃትም ማካሄድም እንደሚፈልጉም አስታውቀዋል ።ሆኖም የጀርመን የፀጥታ ጠባቂ አካላት ጥቃቶችን አስቀድሞ መከላከል የሚያስችላቸው ብቃት እንዳላቸው ነው ሚኒስትሩ ያስረዱት ። ከዚሁ ጋር ግን ሚኒስትሩ የአሸባሪዎች መሸጋጋሪያ ሆና በማገልገል ላይ የምትገኘው ቱርክ አሸባሪዎችን ለመከላከል በሚካሄደው እንቅስቃሴ ተባባሪ እንድትሆን ማድረግ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል ።
«እስካሁን ድረስ ቢያንስ 550 የሚሆኑ ወጣቶች ከጀርመን ወደ ሶሪያና ወደ ኢራቅ ሄደዋል ።አብዛኛዎቹ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት በቱርክ በኩል ነው የተጓዙት ። ቱርክ ለኛ ቁልፍ የሆነች ሃገር ናት ።በዚህም ምክንያት በኔ አመለካከት ከቱርክ ባለሥልጣናት ጋር በመተማመን ላይ የተመሠረተ የቅርብ ግንኙነት በጣም አስፈላጊ ነው ። ቱርኮች በሃገራቸው በኩል ወደ ሶሪያ የሚደረጉ ጉዞዎችን እንዲያስቆሙ እንጠይቃለን ። ይህ በከፊል ተሳክቷል ። ሆኖም በቱርክ አድርገው ወደ ሶሪያ የሄዱት ሰዎች ቁጥር 550 ከፍተኛ ነው ።በዚህ ሰበብም ቱርክ ተጨማሪ እርምጃዎችን መውሰዷ ከምንም ጊዜውም በላይ አስፈላጊ ነው ። »
በሻርሊ ኤብዶ ላይ የተፈፀመው የሽብር ጥቃት በፕሬስ ነፃነት ላይ የደረሰ ጥቃት ነው የሚሉት የጀርመን ፖለቲከኞች ይህ ነፃነት እንዳይታፈን በህብረት መቆም እንደሚገባ አሳስበዋል ።

ኂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ