1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፕረስ ነጻነት ቀን፤ የታሠሩት 2 ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች

ሰኞ፣ ሚያዝያ 25 2002

ዋና ጽ/ቤቱ በኒው ዮርክ የሚገኘው CPJ በሚል የእንግሊዘኛ ምህፃር የሚታወቀው፤ ለጋዜጠኞች ደኅነነት የሚታገለው ድርጅት፤ ባለፈው ዓርብ ባወጣው መግለጫ ላይ ፣

https://p.dw.com/p/NDac
ምስል picture-alliance / dpa

«የመንግሥትን ንብረት አላግባብ አውለዋል» በሚል ክስ የታሠሩ 2 የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቭዥን ጋዜጠኞች ሁኔታ ያሳሰበው መሆኑን አስታውቋል። ዛሬ ታስቦ በዋለው የዓለም የፕረስ ነጻነት ቀን ፣ ዋና ጽህፈት ቤቱ በፓሪስ፣ ፈረንሳይ ፣ የሚገኘው ድንበር አያግዴው የጋዜጠኞች ድርጅት፣ በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ፣ በሰፊው የፕረስ ነጻነት ፀር ናቸው ያላቸውን አገሮች ጠቁሞአል።

ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች ደኅነነት ተመልካች ድርጅት(CPJ)የኢትዮጵያ ቴሌቭዥንና ራዲዮ ጋዜጠኞች ኃይለየሱስ ወርቁና አብዱልሰመድ መሐመድ፣ የመንግሥትን ንብረት አላግባብ ሳያውሉ አልቀሩም በሚል ክስ ተይዘው መታሠራቸው ያሳሰበው መሆኑንና የምርመራውንና የፍርዱን ሂደት በጥሞና እንደሚከታተል አስታውቋል። በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸው ዋና ጽ/ቤቱ ፓሪስ፣ ፈረንሳይ የሚገኘው ዓለም አቀፉ የድንበር አያግዴው የጋዜጠኞች ድርጅት ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ J. Lordet እንዲህ ብለዋል።

«እስካሁን ፣ ባስቸኳይ እንዲፈቱ ብለን የወሰድነው እርምጃ የለም። ግልጽ መሆን አለብን። በመጀመሪያ የምንጠይቀው፣ ፍትኀዊና ግልጽ በሆነ ምርመራ ፣ የፍርዱ ሂደት እንዲከናወን ነው። ዋናው ነገር፣ እንዚህ 2 ሰዎች፣ ወንጀል በመፈጸም ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል ወይስ ሥራቸውን በትክክል እየሠሩ ነበር? ነው ። እነዚህ ሁለት ጋዜጠኞች የተከሰሱት፣የሃሰት ሰነድን ለውጠው ሊያሻግሩ ሞክረዋል ተብሎ ነው። እኛ አሁን ማወቅ የምንፈልገው፣ ጋዜጠኞቹ፣ በቀጥታ ሥራቸውን በታማኝነት እያከናወኑ እያሉ ነው ወይ ለእሥር የታደረጉት ? ምርመራው ግልጽና ፍትኀዊ መሆኑ በጣም ወሳን ነው።»

ድንበር-አያግዴው የጋዜጠኞች ድርጅት (RSF)ዓለም አቀፉን የፕረስ ነጻነት መታሰቢያ ዕለት አስመልክቶ፣ ዛሬ ባወጣው መግለጫ «በአቶ ኢሳይያስ አፈወርቂና በሚከተሏቸው ጥቂት ጽንፈኞች ብሔርተኞች ቡድን የምትመራው፣ የቀኝ ባህር አዋሳኝዋ ሀገር፣ ኤርትራ በጥቂት ዓመታት ውስጥ፣ በአፍሪቃ መሪ የመገናኛ ብዙኀን እሥር ቤት ሆናለች፣ በአሁኑ ጊዜ፣ 30 ያህል ጋዜጠኞች በ 314 የአሥር ጣቢያዎችና ማዕከላት ውስጥ፣ ተይዘው ይገኛሉ» ሲል አስታውቋል። በተጠቀሱት እሥር ቤቶች ፍጹም ጭካኔ ከተመላበት አያያዝ የተነሣ፣ 4 ጋዜጠኞች ሞተዋል፣ ሌሎች፣ ደብዛቸው እንደጠፋ ነው፣ በ RSF መግለጫ መሠረት!።

RSF፣ ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ፣ እ ጎ አ በግንቦት ወር 2008 ዓ ም፣ ስለታሠሩ ጋዜጠኞች በአልጀዚራ ቴሌቭዥን ተጠይቀው፣ «የታሠሩ ጋዜጠኞች አልነበሩም ፣ የሉምም፣ የተሣሣተ መረጃ አግኝታችኋል» ማለታቸውን RSF በዘገባው ላይ ጠቅሷል። የኤርትራመንግሥት ይኸው ድንበር አያግዴው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት የአንድ ምዕራባዊ ኃያል መንግሥት የስለላ ድርጅት ተላላኪ ነው በማለት ለክሱ ደንታ የሌለው መሆኑን በየጊዜው ሲገልጽ መቆየቱ አይዘነጋም።

በያመቱ፣ በዛሬዋ ዕለት እ ጎ አ ግንቦት 3 ቀን በሚከበረው ዓለም አቀፍ የፕረስ ነጻነት ዕለት ፣ ዘንድሮም እንዳምናው የፕረስ ጠላቶች የተባሉ የ 40 ፖለቲከኞች የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የሚሊሺያ ጦረኞችና የወንጀለኞች ድርጅቶች ሥም ዝርዝር ቀርቧል።

ሶማልያ ውስጥ፣ የስለላ ጉዳይ ኀላፊ ሙሐመድ ዋርሳም ዳርዊሽ፣ በሰፊው ወረራና ብርበራ እንዲካሄድ በማቀድ ህገ-ወጥ በሆነ አሠራር የቀሩት ጥቂት የአገሪቱ ጋዜጠኞችም ቢሆኑ እንዲያዙ አንዳንዴም በጥይት እንዲገደሉ ያደርጉ ስለነበረ ዓይነተኛ የፕረስ ጠላት ተብለው ስማቸው በአኩያን መዝገብ ሠፍሮ ቢቆይም፣ እ ጎ አ ፣ ከታኅሳስ ወር 2008 ዓ ም ወዲህ፣ ስማቸው ከዝርዝሩ ውጥ ተፍቋል።

በናይጀሪያ የአገሪቱ የፀጥታ አገልግሎት ፈላጭ -ቆራጭ በመሆን መሥራቱ፣ በኦግቦና ኦኖቮ የሚመራው የፖሊስ ኃይልም፣ ነጻውን ፕረስ በመተናኮል ወደር ያልተገኘለት ቡድን መሆኑ ተመሥክሯል። በቂ ሥልጠና ያላገኙት ፖሊሶች፣ በጋዜጠኞች ላይ፣ የዐይን ምሥክሮች ሊያዩ በማይችሉበት ሁኔታ፣ የኃይል እርምጃ እንዲወስዱ ማበረታቻ ሲሰጣቸው መቆየቱን የደንበር አያግዴው የጋዜጠኞች ድርጅት መግለጫ ያስረዳል።

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሠ