1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፕረስ ነፃነት ቀን፦መነሻዉና እሳቤዉ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 27 2001

ከዶሐ-እስከ ፓሪስ፥ ከሶል እስከ ኒዮርክ እንደተነገረዉ ግን የጋዜጠኞች መብት፥ የፕረስ ነፃነት አሁንም ከባድ ፈተኛ እንደተጋረጠበት ነዉ።

https://p.dw.com/p/Hjvf
የፕረስ ነፃነት ቀን-በርሊን «ልብስ ያለ ገላ መረጃ ያለ ነፃነት---»ምስል picture-alliance / dpa

04 05 09


ሚያዚያ ሃያ-ዘጠኝ 1991 (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮ̎ጳዉያኑ አዎጣጠር ነዉ) ዊንድ ሆክ-ናሚቢያ የተሰበሰቡት አፍሪቃዉያን ጋዜጠኞች ከዉይይት፣ ዉሳኔ ስብሰባቸዉ ዉጤት ይልቅ በአስተጋብኦቱ ደስታ ጮቤ ረግጠዉ ተደንቀዉም ነበር።ከያኔ ተሰብሳቢዎች-ትናንት የዋለዉን የአለም የፕረስ ነፃነት ቀን ለማክበር እድሜ ያደላቸዉ ዘንድሮም አለመደነቅ አይችሉም።ግን በተቃራኒዉ።ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋላችሁ።የአድናቆቶቹ ተቃርኖ-አብነት፤ የፕረስ ነፃነት ቀን-መነሻ፤ እሳቤ-ገቢራዊነቱ መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።
-------

የቀጠሩ አሚር ሼኽ ሐማድ ቢን ኸሊፋ ከግል ሐብታቸዉ አንድ መቶ ሐምሳ ሚሊዮን ዶላር አዉጥተዉ አዲስ አለም አቀፍ ቴሊቪዥን ጣቢያ እንዲቋቋም በ1996 ሲያዙ-ከአምስት አመት በፊት ዊንድ ሆክ ናሚኒያ ተሰብስበዉ የነበሩት የአፍሪቃ ጋዜጠኞች ያደረጉትን ዉይይት ይዘት፥ የዉሳኔያቸዉን እንዴትነት አዉቀዉት፥ደግፈዉት ነበር-የሚባልበት ምክንያት አልነበረም።

የዚያኑ ያክል አሜሩ ያዘዙትን-ሲያዙ የናሚያ ጉባኤተኞችም ሆኑ ሌላዉ ታዛቢ የአሜሩ አለማ እንደ አባት፤ አያት ቅድመ አያቶቻቸዉ፣ እንደ አረብ አቻዎቻቸዉ፥በየሐገር ዉስጡ ሥርጭት መወደስ፣ መሞገስ መመለኩ አልበቃ ብሏቸዉ አለም አቀፍ ጣቢያ አስከፈቱ ከማለት አልፎ-የዛሬዉን እዉነት ለመተነበይ መሠረት የሚያደርጉት ልምድ፥ምልክትም አልነበራቸዉም።ከነበረም-በጣም ሥሥ ነበር።

በትንሺቱ የጋዝ-ቤንዚን ቱጃሪቱ አረባዊት ሐገር መልከዕ-ምድራዊ አቀማመጥ ሥም-አል-ጀዚራ (ደሴት ወይም ልሳነ-ምድር እንደማለት ነዉ) ተብሎ የተሰየመዉ ጣቢያ አለምን ለዘመናት ከተቆጣጠሩት ግዙፍ አለም አቀፍ ጣቢያዎች የሚሰነዘረበትን ትችት ወቀሳ፥፤ ከአረብና ከምዕራብ መንግሥታት በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሚደረግበትን ጫና ተቋቁሞ ለአረብኛና ለእንግሊዝኛ ተናጋሪዉ አለም የነፃ መረጃ ፍሰት አማራጭ መሆኑ ሲረጋገጥ ሥለ መስራቾቹ አለማ የነበረዉ ግምት መላምት በርግጥ ሟሽሿል።

ከአለም የሶቬት ሕብረት መፈረካካከስ፥ የኢራቁ-ጦርነት-ዉጤት፥ከአፍሪቃ ደግሞ የደቡብ አፍሪቃ የጥቂት ነጮች አገዛዝ ማክተም፥ ምናልባትም የሲያድ ባሬ፥ የመንግሥቱ ሐይለማሪያም የዘመነ-ሥልጣን ፍፃሜን ምን-እንዴትነት እያብሰለሰሉ ዊንድ ሆክ የተሰበሰቡት አፍሪቃዉያኑን ጋዜጠኞች ሥለ መብት ነፃነታቸዉ ያደረጉትን ዉይይት የአለምን ትኩረት ጨርሶ የሚስብ አልነበረም።

የአራት ቀን ዉይይታቸዉን በአቋም መግለጫ አሳርገዉ ግንቦት ሰወስት ሲበታተኑ ግን በፊት ያሰቡ-የገመቱት ትንሽ ቀርቶ-ተታቃራኒዉ ትልቅ በጎ ሁነት እዉን ሆነ።የአለም የትምሕርት የሳይንስና የባሕል ድርጅት UNESCO-የአፍሪቃዉያኑ ጋዜጠኞች የአቋም መግለጫ የወጣበትን ዕለት ግንቦት ሰወስትን የአለም የፕረስ ነፃነት ቀን ብሎ ሰየመዉ።ለዊንድ ሆክ ጉባኤተኞች የአስደሳች-ግን የአስደናቂዉ ዉጤት-በአል አስራ-ስምተኛ አመቱ ሲዘከር አምና የፕረስ ነፃነትን በመጋፋት ከአለም ከፍተኛዉን ደረጃ የያዙት የፍሪቃ ሐገራት መሆናቸዉ ነዉ-ያሁኑ አስደናቂ የያኔዉ ደስታ ቅጭት።

ኤርትራ፥ ዚምባቡዌ፥ እና ሶማሊያ የፕረስ ነፃነትን ከሚጥሱ ሐገራት ግንባር ቀደሞቹ መሆናቸዉ በተረጋገጠበት-አመት አምና፥የሕዝባቸዉን ሐብት እየዘረፉ፤ በሐይማኖት፣ በባሕል-ወግ ሸብበዉ የሚረግጡ ነገስታት፤ አምባገነኖች፣ በተንሰራፉበት አለም መሐል የነፃ መረጃ ማሰራጪያ ደሴት-የሆነችዉ ትንሺቱ አረባዊት ልሳነ-ምድር ቀጠር ለፕረስ ነፃነት የሚቆረቆር ተቋም ማዕከልም ሆነች።

«ለመገናኛ ዘዴዎች ነፃነት የዶሐ ማዕከል» የተሰኘዉ ተቋም ምክትል ሐላፊ ቴሪ ስታይነር እድለኞች ነን-አሉ በቀደም።
«እኛ በጣም እድለኞች ነን።ምክንያቱም እዚሕ የቀጠር ባለሥልጣናት ከአንድአመት ትንሽ ቀደም ብሎ ለመገናኛ ዘዴዎች ነፃነት የሚሟገት ማዕከል እንድን መሠረት ወሰኑ።እና በመረጃ ሥርጭት ነፃነት ላይ የሚፈፀም ጥቃትን እንድንከታተል እና እንድንከላከል ጠየቁን።ከዚሕም በተጨማሪ ድጋፍና እርዳታ የሚፈልጉ ጋዜጠኞችና የመገናኛ ዘዴ ተቋማትን እንድንረዳ ጠየቁን።»

Al Dschasira Fernsehstudio in Doha
አል-ጀዚራ አመሰራረቱ ግራ አጋቢ ነበርምስል picture-alliance/dpa

«የዊንድ ሆኩ ዉሳኔ» ተብሎ የሚታወቀዉ የአፍሪቃ ጋዜጠኞች የአቋም መግለጫ ከወጣበት ዕለት ጀምሮ በየአመቱ የሚከበረዉ የአለም የፕረስ ነፃነት ቀን ዘንድሮ ለአስራ-ዘጠነኛ ጊዜ ትናንት ከመከበሩ ከአራት ቀን በፊት ሮብ-የዶኸዉ ማዕከል የሶማሊያ ጋዜጠኞች በአንፃራዊ ነፃነት የሚሠሩበት ገለልተኛ የዜና የገልግሎት ማዕከል ጅቡቲ ዉስጥ ከፍተሎቸዋል።

ባለፉት አራት ወራት ብቻ ሁለት ጋዜጠኞች የተገደሉባት፥ሌሎች የቆሰሉባት፥ራዲዮ ጣቢያዎች የተዘጉባት ሶማሊያ ድንበር የለሽ ዘጋቢዎች እንደሚለዉ የፕሬስ ነፃነት በማክበር ከአለም 154ኛ ላይ ትገኛለች።እስከ ሐቻምና ድረስ ብዙ ጋዜጠኞች ከተገደሉባቸዉ ሐገራት ኢራቅን ተከትላ ሁለተኛ ነበረች።የሶማሊያ ጋዜጠኞችን ፈተና እንደ ባለሙያ እየኖረበት-የሚያዉቀዉ ሙስጠፋ ሐጂ አብዲኑር እንደሚለዉ በዶኸዉ ማዕከል የገንዘብና የሙያ ድጋፍ የተከፈተዉ ዜና አገልግሎትሎት (SOMINA) ለሙያ አጋሮቹ ብዙ ነዉ።

መንበሩን ፓሪስ ፈረንሳይ ያደረገዉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ድንበር የለሽ ዘጋቢዎች እንደሚለዉ አምና እና ዘንድሮ የፕሬስ ነፃነትን በማክበር ከአፍሪቃ ሐገራት የተሻለ ደረጃ ላይ ያለችዉ የ1991ዱን የአፍሪቃዉያን ጋዜጠኞች ጉባኤ ያስተናገደችዉ ናሚቢያ ብቻ ናት።ከአለም ሃያ ሰወስተኛ።የአፍሪቃ ጋዜጠኞች ለአለም የተረፈ ጥያቄያቸዉን ባሰሙበት ወቅት ከይፋ-አዋጅ በመለስ አዲስ ነፃ ሐገር የሆነችዉ ኤርትራ ባንፃሩ የመጨረሻዉን ደረጃ ይዛለች።173ኛ።

1991 ለኢትዮጵያም ሌላ ታሪክ አለዉ። ወታደራዊዉ መንግሥት የተወገደበት በዉጤቱም ለፕረስ ነፃነት የተስፋ ጭላንጭል የበረቀበት አመት ነበር።በአስራ-ስምንተኛ አመቱ አምና ሲከበር ግን የፕረስ ነፃነትን በማክበር አንድ መቶ አርባ-ሁለኛ ሆናለች።በዚያ ዘመን የፕረስ ነፃነትን ማክበር አይደለም ተስፋዉ እራሱ የማይታወቅባት ሐገር ቀጠር ባንፃሩ ባጭር ጊዜ ዉስጥ የአለም የፕረስ ነፃነት ማክበሪያ ማዕከል ሆናለች።የትናንቱን በአል በሰፊ ዉይይትና በትልቅ ጉባኤ ከተከበረባቸዉ ሐገራት አንዷም ሆናለች።እንደገና ቴሪ ስታይነር።
«መናገር የምፈልገዉ ዋናዉ ነገር ይሕ የአለም የፕረስ ነፃነት ቀን-እዚሕ በአንድ የአረብና የሙስሊም ሐገር ሲከበር ያሁኑ የመጀመሪያዉ መሆኑን ነዉ።ይሕ ማለት ትልቅ ነገር ነዉ።ምክንያቱም በአካባቢዉ ለመረጃ ሥርጭት ነፃነት ለሚታገሉ ወገኖች በሙሉ ትልቅና አበረታች እርምጃ በመሆኑ።»

ዩናይትድ ስቴትስና ተባባሪዎችዋ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ሊገነቡላት፥ ሰላም እኩለት ሊያሰፍኑላት ከስድስት አመታት በፊት ጦር ያዘመቱባት ኢራቅ ለተከታታይ አመመታት ብዙ ጋዜጠኞች ከሚገደሉባቸዉ ሐገራት የመጀመሪያዉን ሥፍራ እንደያዘች፣ የፕረስ ነፃነት በማክበር ከአለም አንድ መቶ ሐምሳ ስምተኛዉን ደረጃ ላይ ትገኛለች።ሳዑዲ አረቡያ አንድ መቶ-ሥልሳ አንድኛ፥ ግብፅ አንድ መቶ አስራ-ስድስትኛ እስራኤል (ከግዛቷ ዉጪ) አንድ መቶ አርባ ዘጠነኛ ናቸዉ።

Reporters without borders Logo
የድንበር የለሽ ዘጋቢዎች አርማ

በነዚሕ ሐገራት በተከበበችዉ ቀጠር-ሰሞኑን የተደረገዉ ጉባኤ ሥለ መገኛ ዘዴዎች አቅም፥ሥለ ዉይይት፥ መግባባትና እርቅ መክሯል።የዉይይቱ ርዕሥ የዶሐዉ ማዕከል ምክትል ሐላፊ
ቴሪ ስታይነር እንደሚሉት በጣም ተቀሚ ነዉ።በተለይ ለዚያ አካባቢ።

«በነዚሕ ርዕሶች ላይ ለመነጋገር፥- እዚሕ እንደ አለም ማዕከል፥ ከመላዉ አለም የተዉጣጡ ጋዜጠኞችና የድርጅት ተጠሪዎች ተካፍለዋል።እና እነዚሕ ርዕሶች በጣም አስፈላጊዎች ናቸዉ።በተለይ ደግሞ በዚሕ አካባቢ በነዚሕ ርዕሶች ላይ መነጋገር በጣም ጠቃሚ ነዉ።
-------------------------------
የዘንድሮዉን የአለም የፕረስ ነፃነት እሁድ ሲከበር የኢራንና የሰሜን ኮሪያ ባለሥልጣናት ያሰሯቸዉ ሰወስት የአሜሪካ ጋዜጠኞች እንዲለቀቁ የሚደረገዉ ጥሪና ጥያቄ የአለም መገናኛ ዘዴዎችን፥ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቾችን ትኩረት ስቧል።ከዶሐ-እስከ ፓሪስ፥ ከሶል እስከ ኒዮርክ እንደተነገረዉ ግን የጋዜጠኞች መብት፥ የፕረስ ነፃነት አሁንም ከባድ ፈተኛ እንደተጋረጠበት ነዉ።

dw,Rsf,DCMF

ነጋሽ መሐመድ