1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፕሬዚደንት ከ*ለር የልማት ጥሪ ለአፍሪቃ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 21 1997

ከቅርብ ጊዜ በፊት ኢትዮጵያን ጨምሮ አፍሪቃን ለአሥር ቀናት የጎበኙት አዲሱ የጀርመን ርእሰብሔር ሆርስት ከ*ለር በዚሁ ሥልጣናችው ወቅት አፍርቃነኩን መርሕ ማዕከላዊ ጉዳይ ሊያደርጉት እንደሚሹ ከጉብኝቱ ፍፃሜ በኋላ በርሊን ውስጥ በሰጡት መግለጫ አስረድተዋል።

https://p.dw.com/p/E0f7

“በዚህ ሥልጣን ላይ በምቆይበት የአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከአፍሪቃውያኑ የለውጥ አራማጆች ጋር የዘወትሩን ቀጣይ ውይይት ለመገንባት እሞክራለሁ” የሚሉት የዓለምአቀፉ ገንዘባዊ ድርጅት/ኣይኤምኤፍ የቀድሞ መሪ፥ የአፍሪቃው አህጉር የተፈበረኩ እቃዎችንም ለውጭው ገበያ ወደሚያቀርብበት ደረጃ በመሸጋገር ፈንታ እንደተለመደው በጥሬ አላባዎች አቅራቢነት ሚና ብቻ ተገድቦ መቅረት እንደሌለበት ነው የሚያስገነዝቡት። በእርሳቸው አመለካከት መሠረት፥ አውሮጳውያኑም ሆኑ ወይም አሜሪካውያኑ በዓለም የንግድ ድርጅት ውስጥ ገበያዎቻቸውን ክፍት በሚያደርጉበት ጥያቄ ረገድ ሲያቅማሙ የቆዩበት ሁኔታ ነው አሁን መቀየር ያለበት። ዛሬ፥ ፕሮፌሰር ሆርስት ከ*ለር ለአፍሪቃ ያጎሉትን የልማት ጥሪ ነው የምንመለከተው፥

የአፍሪቃው አህጉር መነቃቃትና መራመድ ሰፊ ገበያን ስለሚፈጥር ለጀርመንና ለአውሮጳ ጠቃሚ እንደሚሆንም ነው ፐሮፌሰር ከ*ለር የሚያስገነዝቡት። ግና ያው ኃላቀር አህጉር መልማት እንደተሳነው ከቆየ፣ አፍሪቃውያኑ ፈላስያን በየጊዜው ማዕከላይ ባሕርን እያቋረጡ ወደ አውሮጳ የሚጎርፉ እንደሚሆኑም ነው እርሳቸው አሁን የሚያስጠነቅቁት። እርሳቸው እንደሚሉት የኤክስፖርት ሀገር ጀርመን ዕጣ በግልፁ ገበያ እና በነፃው ንግድ ላይ ነው የሚመረኮዘው፤ አፍሪቃ ምሥቅልቅል ውስጥ ከገባች፣ አፍሪቃውያኑ በዓለም ንግድ ውስጥ ርትኣዊ ድርሻ ካላገኙ፣ አጽናፋዊው የኤኮኖሚ ትሥሥር ትርጓሜውን ነው የሚያጣው። በፕሬዚደንቱ አስተያየት መሠረት፥ በዚህ ረገድ ጀርመን የተለየ አገልግሎት ልትፈጽም ትችላለች፤ አፍሪቃ ውስጥ ለአዎንታዊው የጀርመን ሚና ጉልህ እድል የተደቀነ ሆኖ ነው የሚታየው።

ግን በልማቱ ትብብር ረገድ ፕሮፌሰር ከለር ሂስም ነው የሚያቀርቡት። በእርሳቸው አመለካከት፥ እስካሁን ሲሰጥ የቆየው የልማት ርዳታ፥ ገንዘቡ ለፕሮዤዎች ማንቀሳቀሻ የሚሰራጭበትን ሁኔታ ያማከለ ነበር፤ ግን በአፍሪቃ ሀገሮች ውስጥ ዴሞክራሲ የሚነቃቃበትና ቀልጣፋ የመንግሥት ተቋማት የሚገነቡበት ርምጃ የበለጠውን ትኩረት ማግኘት ነበረበት። እርሳቸው ለራሳቸውም መንግሥት እንዳስገነዘቡት፥ ሐብታሞቹ እንዱስትሪ-ሀገሮች ከጠቅላላው ብሔራዊ ውጤታቸው ነጥብ-ሰባት በመቶውን ለልማትርዳታ እንዲያውሉት የተገባውን ቃል ጀርመንም እርከን በእርከን እውን ማድረግ ይገባታል።

ያፍሪቃን ልማትና የዴሞክራሲ ጥንካሬ ማትኮሪያ ያደረገው የፕሬዚደንት ከ*ለር ማሳሰቢያ፥ ጀርመንን ብቻ ሳይሆን፣ የዓለምንም ኅብረተሰብእ ነው ያመላከተው። የዓለም ኅብረተሰብእ ለአፍሪቃ ሰፊውን ርዳታ እንዲያሸጋግር ጥሪያቸውን ያጎሉት ከ*ለር፥ የተድላ ኑሮ የሚመሩት አውሮጳውያን አፍሪቃ ውስጥ ለአፍሪቃውያኑ ደኅንነት በቅንና በልገሳው መንፈስ ቢንቀሳቀሱ፣ ለአውሮጳ እንደራስ-ከበሬታ የሚቆጠር ሆኖ ነው የሚያዩት። ይህም ሲሆን፣ አፍሪቃውያን የሚያገኙት ርትዓዊው የንግድ ተሳትፎ ነው በረሃብ አንፃር በሚደረገው ትግል ረገድ አንድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚሆነው።

“እኛ ራሳችንን የድሆቹ አጋሮች አድርገን ካልተመለከትን፥ በእነዚያው ሀገሮች ውስጥ የተድላውን ኑሮ፣ ሰላምንና ፀጥታን ማስገኘት የሚቻል አይሆንም” ያላሉ ፕሬዚደንት ከ*ለር። አንደኛ፣ ሁለተኛ፣ ወይም ሦሥተኛ ሳይሆን፣ አንዲት ዓለም በምትሰኘው ምድራችን አፍሪቃውያን ርትኣዊውን ቦታ ማግኘት እንደሚገባቸው፣ የጣምሮች ጎራ ተጣማሪዎች መሆን እንዳለባቸው ይሰማቸዋል።

አስቀድመን እንደጠቀስነው፥ ንግድ ራስአገዝ ለማድረግ የሚያስችል እጅግ ፍቱን እገዛ፣ እጅግ ፍቱን ርዳታ ሆኖ ነው እርሳቸው የሚያዩት። ስለዚህም ነው ርትዓዊው የዓለም ንግድ ተሳትፎ ይዞታ ዓለምአቀፉ ኅብረተሰብእ አፍሪቃ ውስጥ በረሃብና በድህነት አንፃር ለሚያደረርገው ትግል እጅግ ጠንካራ አስተዋጽኦ ነው የሚባለው። በእርሳቸው አስተያየት መሠረት፥ በዶሃ/ቃታር የተጀመረው የዓለም ንግድ ድርጅት ድርድር ዙር፥ እውነተኛ የልማት ድርድር መድረክ ወደሚሆንበት ደረጃ የተሸጋገረ እንደመሆኑ መጠን፣ አሁን ቃላትን በተግባር መተርጎም ነው የጊዜው ጥሪ።

በሌላው በኩል ደግሞ፥ ለአፍሪቃ ልማት የሚቀርበው ርዳታ ለግቡ ክትትል በመዋል ፈንታ እየባከነ እንዳይቀር የሚያደርግ ጥብቅ ቀዳሚ ግዴታ እንዲታከልበትም ነው ፕሮፈሰር ሆርስት ከ*ለር የሚሹት። በዚሁ በእርሳቸው ማስገንዘቢያ መሠረት፥ ጀርመንና ዓለምአቀፉ ኅብረተስእ የልማቱ ርዳታ በማይባክንበት ፍሬአማ መሬት ላይ የሚያርፍ መሆኑን/ማለት ለተጨባጭ ፕሮዤ ማንቀሳቀሻ እንደሚውል፣ ገንዘቡ ለልማት የሚውልበት አካባቢ ጥሩና ምሥጉን አመራር እንዳለበት አስቀድመው ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።

ፕሬዚደንት ከ*ለር እንደሚሉት፥ የአፍሪቃ ፖለቲካዊ ነፃነት የማይነካ ቢሆንም፥ የአፍሪቃን ልዩ ባሕርይ ማመካኛ እያደረጉ ፍትሕን ማጓደልና የራስን ሕዝብ ለበደል ማጋለጥ፥ መወገዝና መወገድ ያለበት አድራጎት ነው። ጥፋትን በስም ጠርቶ እንዲታረም፣ መልካሙ አስተዳደርና ምሥጉኑ አመራር እንዲጠናከር መጠየቅ የዓለም ወንድማማችነት ግዴታ እንጂ፣ የአዲስ ቅኚግዛታዊ ጫና ወይም ጣልቃገብነት አይደለም። አፍሪቃውያኑ መሪዎች በእንዱስትሪ-ሀገሮች ውስጥ የሚታያቸውን ጉድለት፣ ያገማመት ስሕተት እና አለመግባባት በግልጽ እንዲናገሩት እና በዚህም አኳኋን ሁለቱም ወገኖች ግልጽነትን እንዲያጎሉት ሲደረግ ብቻ ነው እውነተኛ ትብብር ሊኖር የሚችለው--ፕሬዚደንት ከ*ለር እንደሚያስገነዝቡት።

ብዙ የአፍሪቃ ሀገሮች የተሸከሙት የውጭው እዳ እንዲቃለልላቸው፣ የእዳ ምኅረት እንዲደረግላቸው የሚያቀርቡትን ጥያቄ የሚረዱላቸው ፕሮፌሰር ከለር፥ የእዳ ምኅረትና የብድር አወሳሰድ ሥርዓት ከኤኮኖሚው ተሐድሶ ለውጥና በድኅነት አንፃር ከሚደረገው ትግል ጋር የተጣመረ መሆን እንዳለበት ነው የሚያስገነዝቡት። በዚህም መሠረት ነው፥ በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ወቅት ጀርመን ለኢትዮጵያ ፷፯ ሚሊዮን ኦይሮ የሚደርሰውን ዕዳ የሰረዘችላት። ጀርመን ይህንኑ እዳ በመሠረዝ፥ ኢትዮጵያ ውስጥ የኤኮኖሚው ተሐድሶ ለውጥ እንዲነቃቃና በድህነት አንፃር የሚደረገው ትግል እንዲጠናከር ለሚደረግበት ርምጃ አስፈላጊው አንቀሳቃሽ ወረት ነፃ እንዲሆን ነው የምትሻው። በዚህ አኳኋን፥ የእዳው ስረዛ ከልማት ግቦች ጋር የተጣመረ ነው ማለት ነው። ፕሬዚደንቱን አጅበው ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙት ጀርመናዊቱ ሚኒስትርዴታ ኬርስቲን ሙ*ለር የእዳውን ስረዛ የተመለተው ውል አዲስ አበባ ውስጥ በተፈረመበት ወቅት እንደገለፁት፥ ከእዳ ክፍያ ነፃ የሚሆነው ገንዘብ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ ለትምህርት ስርጭት ማስፋፊያ፣ ለግብርናው ዘርፍ ልማት ማነቃቂያና በድህነት አንፃር ለሚደረገው ትግል ማጠናከሪያ ነው የሚውለው። አሁን በተገኘው መረጃ መሠረት፥ ጀርመን ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ለኢትዮጵያ በጠቅላላው ወደ ፪፻ ሚሊዮን ኦይሮ የሚጠጋውን ዕዳ ነው የሰረዘችላት። ጀርመን ቴክኒካዊውን የልማት ትብብር ድርጅት ወይም የጀርመኑን የልማት አገልግሎት በመሳሰሉት የልማት ወኪሎቿ አማካይነት ኢትዮጵያ ውስጥ የምታካሂደውን የልማት ትብብር ሥራ ወደፊት በሰፊው እንመለከተዋለን።

ለአንዲት ሀገር ልማት ሰፊው የትምህርት ስርጭትና ጠንካራው የመርሐሙያ ሥልጠና አገልግሎት ቁልፉ መንገድ ሆኖ የሚያዩት ፕሮፌሰር ከ*ለር “ሰዎች ለሰዎች” የተሰኘው የዝነኛው ካርል-ሃይንትስ በ*ም ድርጅት ሃረር ውስጥ የሚያካሂደውን ቴክኒካዊ የሥልጠና ማዕከል ዓይነተኛ አርአያ አድርገው ነው የሚመለከቱት። እርሳቸው ከአዲስ አበባ ተነስተው ወደ ሐረርም በመጓዝ “ሰዎች ለሰዎች” ያቋቋመውን፣ በአሕጽሮት “ኤቲቲሲ” የሚሰኘውን የግብርና ቴክኒካዊ ማሰልጠኛ ኮሌጅ በጎበኙበት ወቅት እንደተገለፀው፥ ሴቶችና ወንዶች ወጣቶች በግብርናው ዘርፍ በኩል ከፍተኛ ዕውቀት እንዲገበዩ የሚያደርገው፣ እንዲሁም በኤሌክትሮኒክ፣ በብረታብረት ብየዳ እና በመኪና ሜካኒክ ጥበብ የ፫ ዓመታት ሥልጠና እየሰጠ በዲፕሎማው ማዕርግ የሚያስመርቀው ተቋም፥ ረሃብንና ድህነትን ለመቅረፍ በሚደረገው ትግል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው ሆኖ ነው የሚታየው። እንዲያውም፣ ራሱ የኢትዮጵያ መንግሥት ይኸው ተቋም ያለውን ከፍተኛ የሥልጠና ደረጃ በመገንዘብ፥ የኮሌጅነት ትውቂያን ከመስጠቱም በላይ፣ አሁን ሀገሪቱ ውስጥ የመርሐሙያውን አገልግሎት ለማሻሻል በሚወሰደው ርምጃ ረገድ ያው የ”ሰዎች ለሰዎች” የግብርና ቴክኒካዊ ማሠልጠኛ ተቋም ዓይነተኛ አርአያ እንዲሆን መርጦታል። ራሳቸው ካርልሃይንትስ በ*ም በፕሬዚደንቱ ጉብኝት ወቅት እንዳስገነዘቡት፥ ከጠቅላላው ሕዝቧ ፹ በቶው ያህሉ በየገጠሩ አካባቢ በሚኖርባት ኢትዮጵያ ከድህነት ለመላቀቅ የሚቻለው፥ የሀገሪቱ ወጣት የትምህርቱ ዕድል ሲከፈትለት ብቻ ነው፣ ያለትምህርት ልማት አይኖርም።