1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፕሬዝደንት ኦባማ የኢትዮጵያ የጉብኝት ዕቅድና ትችቱ

እሑድ፣ ሰኔ 28 2007

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ በሐምሌ ወር ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙ ተነግሯል። ፕሬዝደንቱ በአፍሪቃ በሚያደርጉት ጉብኝት የአባታቸዉ ሀገር ኬንያን እንደሚጎበኙ ቀደም ብሎ ነበር የተሰማዉ። ቆየት ብሎ ደግሞ ኢትዮጵያንም እንደሚሄዱ ተነገረ።

https://p.dw.com/p/1FsS1
Washington Supreme Court Entscheid über Obamacare PK Obama
ምስል Reuters/G. Cameron

ወደኢትዮጵያ የሚሄዱት ለሁለት ፓላማ ነዉ፤ የአፍሪቃ ኅብረት መሪዎችን ማግኘትና ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋርም ለመነጋገር። የተለያዩ የዜና አዉታሮችም ሆኑ ጋዜጣና ድረገፆች የእሳቸዉ የኢትዮጵያ ጉብኝትን እንደኬንያዉ ሁሉ ሰምተዉ ቸል አላሉትም። ዘጋሪዲያንና ዋሽንግተን ፖስትን ጨምሮ የእሳቸዉ የኢትዮጵያ ጉብኝት ለዴሞክራሲያዊነት የተሳሳተ መልዕክት ያስተላልፋል ሲሉ ትችት ሰነዘሩ። በተለያዩ ሃገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዉያንም ጉብኝቱን በመቃወም የፋክስና ስልክ መልዕክቶችን ወደፕሬዝደንቱ ጽሕፈት ቤት እየላኩ ነዉ፤ ፊርማም እያሰባሰቡ ነዉ። በአንፃሩ የፕሬዝደንቱ ጉብኝት የማይቀር መሆኑን ያስተዋሉ ደግሞ በጉብኝታቸዉ ወቅት ሊያነሷቸዉ ይገባል ያሏቸዉን መሠረታዊ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ ያሳስባሉ። ኦባማ ከአፍሪቃዉ ጉብኝታቸዉ ዝርዝር ዉስጥ በቅርቡ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር እንዳካሄደች የተወደሰችዉ ናይጀሪያን አለማካተታቸዉም በእጅጉ ተነቀፈ። ወዲያዉም ፕሬዝደንቱ በኋይትኃዉስ በሕዝብ የተመረጡትን አዲሱን የናይጀሪያ ፕሬዝደንት ተቀብለዉ እንደሚያነጋግሩ ተሰማ። በርካታ ትችት ቢቀርበትም ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ በስልጣን ላይ እያለ ኢትዮጵያን የጎበኘ የመጀመሪያዉ የአሜሪካን ፕሬዝደንት ይሆናሉ። ዉይይቱን ከድምፅ ዘገባዉ ይከታተሉ።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ