1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፖላን ድ ባለሥልጣናት ሞትና የካትይን ጭፍጨፋ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 4 2002

ቤሪያ-ጊዜ አላጠፉም።የፖላንድ ዜጎችን ከየእስር ቤቱ እያሳፈሱ ምዕራባዊ ሩሲያ ስሞሌንስክ አጠገብ ካትይን ደን ዉስጥ በተከታታይ አስጨፈጨፉ።

https://p.dw.com/p/Mub2
ከካትይን ጅምላ ቀብሮች አንዱምስል picture alliance/dpa


ፖላንዳዊዉ የአለም አቀፍ ግንኙነት አጥኚ ስላቮሚር ደብስኪ እንደ ብዙዉ የአለም ፖለቲከኛ አዘነዋል።እንደ ፖላንዳዊ እንደ ድፍን ፖላንድ ደንግጠዋል።አንብተዋል። ፀልየዋልም። ደግሞ እንደ ፖለቲካ አስተንታኝ ጠየቁ።«የፖላንድን መንግሥትን የሚወክሉ ሰዎች በሺ የሚቆጠሩ የፖላንድ ወታደሮች በጅምላ በተገደሉበት ሥፍራ መሞታቸዉ ሊገባን አይችልም» እያሉ።ደብስኪ ለራሳቸዉ ጥያቄ-እራሳቸዉ መለሱ «ምናልባት ይሕ ምድር የፖላንዶችን ደም ሳይወድ አይቀረም» ብለዉ።የፖለንድ መሪዎችን ሞት-ከማንነታቸዉ ጋር፣ የጉዞቸዉን-ምክንያት ከታሪካዊ ዳራዉ ጋር፣እያጣቀስን-የገባንን ጥቂት፣ካልገባን ብዙ ጋር አሰባጥረን እንቃኛለን ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

የፖላንድ መሪዎች በ1921 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የፍራንኮ-ፖሊሽ ወታደራዊ ትብብርን ከፈረንሳዮች ፥በ1932 የሶቬት-ፖሊሽ አንዱ ሌላዉን ያለመዉረር ሥምምነትን ከሶቭዮቶች፥ በ1939 የፖሊሽ-ብሪቴን የጋራ የመከላከያ ሥምምነትን ከታሏቋ ብሪታንያ ጋር የተፈራረሙት ሐገራቸዉን ምሥራቅና ምዕራብ አቃርጠዉ ከያዟት ከኮሚስቶችና ከናትሲዎች ጥቃት ለመከላከል ዘዴ ብለዉት ነበር።


የወርሶ መሪዎች፥ በ1932 ከሶቬየት ሕብረት ጋር ዉሉን ሲፈራረሙ ከዚያ በፊት ከፈረንሳይ ጋር የፈረሙትን ሥምምነት አለማፍረሳቸዉ እንዳበገናቸዉ ሰባት አመት የቆዩት ሞስኮ ኮሚንስቶች-ፖላንዶች በ1939 ከብሪታንያ ጋር ሌላ ስምምነት መፈረማቸዉ ይበልጥ አስቆጣቸዉ።ሞስኮዎች ለቁጣቸዉ ማብረጃ መላ ሳያገኙለት የጀርመን ናትሲ ፖላንድን ወረረ።መስከረም አንድ-1939።

ዋና ፀሐፊ ጆሴፍ ስታሊን ከሁለት ሳምንት በላይ አልታገሱም።ቀዩ ጦራቸዉ ምሥራቃዊ ፖለንድን እንዲወር አዘዙ።መስከረም 17-1939።የዎርሶ መሪዎች በስምምነታቸዉ መሠረት ወደ ሰሜን-ምዕራብ፥ ብሪታንያን፥ሽቅብ፥ ወደ ደቡብ ምዕራብ ፈረንሳይን ቁልቁል ቢመለከቱም የደረሰላቸዉ የለም።

Gedenken 70 Jahre Massaker in Katyn Polen
70ኛ አመቱ መታሰቢያምስል picture-alliance/dpa

የሶቬት ሕብረቱ ሕዝባዊ የሐገር ዉስጥ ጉዳይ ኮሚሳር ላቭሬንቲይ ቤሪያ ፓቭሎቪች ቀዩ ጦር መስከረም ፖለንድን ከወረረበት ጊዜ ጀምሮ የተያዙትን የፖላንድ ዜጎች የሚያሥወግዱበትን ብልሐት ማሰላሰል ከጀመሩ ዋል አደር ብለዋል።ቤሪያ የፓርቲያቸዉ ማዕከላዊ ኮሚቴ አንድ እንዲላቸዉ ስታሊን በሚወዱት ቃል-ቋንቋ የከሽኑትን ደብዳቤ ፃፉ-መጋቢት 5 1940።

ስታሊን የመሩት፥ ቤሪያ ራሳቸዉ የተሳተፉበት ማዕከላዊ ኮሚቴዉ እኒያን የጦር ምርኮኞች፥ እኒያን አድሐሪ፥ አቆርቋዥ፥ ቡርዣ፥ሻጥረኛ፥ ፀረ-ሕዝብ ወዘተ ያላቸዉን የፖላንድ ሙሕራን፥ ፖለቲከኞች፥ ፖሊሶች እንዲወገዱ ወሰነ።ቤሪያ-ጊዜ አላጠፉም።የፖላንድ ዜጎችን ከየእስር ቤቱ እያሳፈሱ ምዕራባዊ ሩሲያ ስሞሌንስክ አጠገብ ካትይን ደን ዉስጥ በተከታታይ አስጨፈጨፉ።

የካትይደን ደን የፖላንዶች አስከሬን በተከመረበት-በሰባኛ አመቱ ባለፈዉ ሳምንት ሮብ የገዳይ-ሟች ወራሽ ዉልዶች-እንደ ኦርቶዶክስም፥ እንደ ካቶሊክም ወግ ሙታንን እኩል አሰቡት።የሩሲያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ቭላዲሚር ፑቲን።

«ለዚሕ ወንጀል ምንም አይነት ምክንያት አይቀርብም።በኛ ሐገር አምባገነናዊዉ ሥርዓት ሥላደረሰዉ ዘግናኝ ግፍ ግልፅ የሆነ ፖለቲካዊ፥ሕጋዊና ሞራላዊ ግንዛቤ አለ።ይሕ (አቋም) በጭራሽ አይታጠፍም።»

የፖላንዱ ጠቅላይ ሚንስትር-ዶናልድ ቱስክም ከፒቲን ጎን ቆመዉ ሙታንን ዘክሩ።የፑቲንን ንግግር አድምጡ።መለሱም።

«እንደነዚሕ አይነቶቹ እርምጃዎች እንዲበረክቱ እንፈልጋለን።የተምሳሌያዊነቱን ትርጉም ላጋንነዉ አልፈልግም።ይሁንና እዚሕ ባለዉ ሁኔታ ተንሳሌያዊነቱ ቀላል ግምት የሚሠጠዉ አይደለም።ወደ ካትይን እንድንመጣ መጋበዛችን፥ ሠለቦቹን በጋራ ማሰባችን፥ታሪካዊዉን እዉነታ ለማቃናት የታየዉ ሞራላዊ (ፍላጎት) ጠቃሚ ነዉ።ከዚሁ ጋር የየፖላድ-ሩሲያ ግንኙነትን ይበልጥ ማጠናከር እንፈልጋለን።»

የጋራ-ዝክሩ፥ ጥፋቱን የመቀበል ዝንባሌ-ንግግሩ ከሰባ አመት በላይ ሥር የሰደደዉን የሁለቱን ሐገራት ቂም-በቀልን የሚያለዝብ፥ የሁለቱ ሕዝቦችን የወደፊት ግንኙነት መልካምነትን የሚጠቁ- ተስፋ ብጤ ነበር።ፕሬዝዳት ሌሕ ካችንስኪ ሐሙስ ከወርሶ ፕራግ-ቼክ ሪፐብሊክ የገቡት የካትዬንን ደን ዛፎችን እያወዛወዘ፥ ቀዝቃዛ፥ ጨፍጋጋዉን የስሞለንስክ አየርን እየበረቀሰ-ዎርሶ-ላይ በፈጠረዉ ስሜት እንደተደሰቱ ነበር።

Polen Flugzeugabsturz Trauer Präsidentenpaar
ማሪያና ሌሕ ካቺንስኪ ሞትም አለያቸዉምምስል AP

በርግጥም የሞስኮ መሪዎች ከሰባ አመት በፊት እዚያ ጫካ ዉስጥ ለተገደሉት የፖላንድ ዜጎች ካሳ፣ ይቅርታ፣ መረጃ መስጠቱን ባይቀበሉት እንኳን ሟቾች ጭፍጨፋዉ በተፈፀመበት ሥፍራ በይፋ እንዲዘከሩ መፍቀዳቸዉ፣በዝክሩ ላይ የሩሲያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ቭላድሚር ፑቲን ከፖላንዱ አቻቸዉ ጎን ቆመዉ ሙታንን ማሰባቸዉ ጭፍጨፋዉን እንዲጋለጥ ለታገሉት ለጥብቅ ብሔረተኛዉ ለፕሬዝዳት ካቺንስኪና ለተባባሪዎቻቸዉ ከማስደሰትም በላይ ድል ነበር።

Flash-Galerie Polen Trauer zum Tod von Präsident Lech Kaczynski in Smolensk
ሐዘንምስል AP

ካቺንስኪ ፕራግ ላይ ከአስር ሌሎች የምሥራቅ አዉሮጳ ሐገራት አቻዎቻቸዉ ጋር ሆነዉ ሐሙስ ከዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ የሰሙት የድሮ-አያት-አባቶቻቸዉ በተለይ ከብሪታንያ፥ ከፈረንሳ መሪዎች ጋር ሲፈራረሙ ሲስማሙ የሰሙትን አይነት አበረታች፥ አስደሳች ቃል-መልዕክት ነበር።

«ይሕቺ ግርማ-ሞገስ የተላበሰች ከተማ-ፕራግ በብዙ መንገድ የሠዉ ልጅ ዕገት ቋሚ ሐዉልት ናት።ይሕ ሥነ-ሥርዓት ደግሞ ተቀናቃኝ ሐይላት በሙሉ አዲስ ወዳጅነት መመሥረት እንደሚችሉ የሚያረጋግጥ ነዉ።»


አለም ባንኮኮን ባንድ እግሯ ያቆመዉን የተቃዉሞ ሠልፍ፥ ሱዳን ሊደረግ የታቀደዉን ምርጫ፥ ቢሽኬክን በደም-አስከሬን ያረከሰዉን ሕዝባዊ አመፅ ዉጤት ከመከታተል ትኩረቱ ያነጣበዉን የሐያላን ሐገራት የሥልታዊ ጦር መሳሪያ ቅነሳ ዉል ምክንያት እድምታን ሲከታተል አርብ የስሞለንስክ ከተማ የፑቲን-ቱስክን መልዕክት ገና እያመነዠኸች ነበር።ዎርሶም እንዲሁ።

ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ የአፍቃኒስታኑ ፕሬዝዳንት ኻሚድ ካርዛይ መንግሥታቸዉ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ሥለለዉ ግንኙነት መሻከር ያሉትን በየጣልቃዉ ማሰላሰላቸዉ አልቀረም።ከፕራግ ዋሽንግተን የገቡት ግን ከሩሲያዉ አቻቸዉ ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ጋር ያደረጉትን የሥልታዊ ጦር መሳሪያ ቅነሳ ዉልን ሰነድ፥ ከምሥራቅና ማዕከላዊ አዉሮጳ መሪዎች ጋር ያደረጉትን ዉይይት በጎ ዉጤት ይዘዉ ነበር።ቸር ዜና አንግበዉ-እንደተደሰቱ።

ፕሬዝዳት ዲሚትሪ ሜድቬድ ሥለ ኪርጊስታን ፖለቲካዊ ቀዉስ ብዙ ማሰብ ማሰላሰላቸዉ አልቀረም።ከፕራግ ሞስኮ የገቡት ግን ያዟቸዋል የሚባሉት ጠቅላይ ሚንስትር ቭላድሚር ፑቲን ሥለ ፖላንድ ተጨፍጫፊዎች ያሉትን ያሉበትን ምክንያት ከማስተንተን ጋር ከኦባማ ጋር በፈረሙት ትልቅ ዉል እንደተደሰቱ ነዉ።

ሮብ ካትይን ላይ በሆነዉ፥ ሐሙስ ፕራግ ላይ ባደረጉ-በተደረገ በሰሙት-ባሉት እንደተደሰቱ አርብን የዋሉት ካቺንስኪ ለዘመናት ከታገሉለት የአንዱን ድል እቦታዉ ሔደዉ የሚተክሩበት ጊዜ ሳያጓጓቸዉ አልቀረም።ካችንስኪ የሶቬት ሕብረትንና ሶቬት ሕብረት የምትዘዉረዉን የሐገራቸዉን ኮሚንስታዊ ሥርዓት በመቃወማቸዉ በ1981 ታሥረዋል።

የፖላንድ ከሚንስታዊ ሥርዓት በተወገደበትና ምርጫ በተደረገበት መሐል የነበረዉን የክፍተት ዘመን በፕሬዝዳትነት የሞሉት ሬዝሳርድ ካቾሮቭስክ ሶቬቶችን በመዋወማቸዉ ወገኖቻቸዉ በተጨፈጨፉበት ዘመን በሶቬቶች ታስረዉ፥ ተግዘዉ፥ ሞት ተበይኖባቸዉም ነበር።በሁለተኛዉ የአለም ጦርነት ወቅት ወላጃቸዉን አጥተዉ ያደጉት ወይዘሮ አና ቫለንትይኖቪችም እንደ ካቺንስኪ፥ እንደ ካቾሮቭስክ ሁሉ ሶቭየት ሕብረትና በሶቬት ሕብረት የሚዘወረዉን የሐገራቸዉን ኮሚንስታዊ ሥርዓት ሲተጋሉ ነዉ-ያደጉ የኖሩት።

ቅዳሜ ዎርሶ-ስሞለንስክም ነጋ። ሰወስቱ እዉቅ የሶቬት ሕብረት ተቃዋሚዎች፥ እንደነሱዉ ሁሉ ሶቬት ሕብረትን የተቃወሙ፥ ቀዩን ጦር የተዋጉ፥ የሐገራቸዉን ኮሚንስታዊ ሥርዓት የታገሉ የዘመኑ ፖላንዳዊ ትዉልድ ጀግኖችን ፥ደጋፊ፥ ሹማምንቶቻቸዉን አስከትለዉ፥ በሶቬት ሕብረት የተጨፈጨፉ ወገኖቻቸዉን ለማሰብ ወደ ቀድሞዋ ሶቬት ሕብረት ሶቬት ግዛት ለመጓዝ ከሶቬት ሕብረት አዉሮፕላን ገቡ።

ሶቬት ሕብረት ሲታገሉ ኖረዉ፥ ሶቬት ሕብረትን በመታገላቸዉ ታስረዉ፥ ተግዘዉ፥ ቆስለዉ፥እንደ ጀግና ለመመረጥ፥ ለመሾም-መሸለም የበቁት የፖላንድ መሪዎች አዉሮፕላን ሲሆን የሶቬትን መዉደዳቸዉም ወይም አለመጥላታቸዉ አስተንታኝ ደብስኪን ሊገባቸዉ ካልቻለዉ አንዱ ግን ትንሹ እንቆቅልሽ ነዉ።

ብቻ የስሞለንስክ አየር የሮቡ-ደስታ አልተለየዉም።ግን ይበልጥ ጨፍግጓል።ማን-ይናገር የነበረ?-እሳቸዉ የዚያን ቀን ጧት እዚያ ከነበሩት ብዙዎች አንዱ ነበሩ።ይናገራሉም።

«የሆነ ሠቅጣጭ ድምፅ ሰማን፥ ድምፁ እየጠነከረ፥እየቀረበ መጣ። ወዲያዉ ሐይለኛ ፍንዳታ ከተማይቱን አናወጣት።»

ሶቬት ሕብረትን የሚቃወሙትን ዘጠና ሰባት የፖላንድ ሹማማንት፥ ጀግኖች፥ ወዳጅ-ዘመዶችን ያሰፋረዉ የሶቬት ሕብረት አዉሮፕላን ሶቬት ግዛት ዉስጥ ገደላቸዉ።ከአራት ቀን በፊት-ሮብ መልካም ዜና ያበሰሩት ጠቅላይ ሚንስትር ዶናልድ ቱስክ የአለቃ-ጓዶቻቸዉን ሞት አርጂ ሆኑ።

«አለም እንዲሕ አይነት ነገር ብዙ አያያም።ብዙዎቻችን ጓደኛ ወዳጆቻችን፥ አጥተናል።ትልቁ ሐዘን ግን በርግጥ የሟች ዘመድ ዉላጅ-ወዳጆች ነዉ።»

ፖላንድ ደነገጠች።አነባች።አለምም በርግጥ ብዙ የማያየዉን አየ።አዘነ።ፕሬዝዳት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ።

«የተሰማኝን ጥልቅና የልብ ሐዘን በሩሲያ ሕዝብ ስም ለፖላንድ ሕዝብ እገልጣለሁ።»

የጀርመንዋ መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ቀጠሉ።

«በዚሕ አጋጣሚ በአዉሮፕላኑ አደጋና በፖላንዱ ፕሬዝዳት ሞት ክፉኛ መደንገጤን መናገር ነዉ የምፈልገዉ።ከፌደራላዊዉ የመራሔ መንግሥት ፅሕፈት ቤት ተጨማሪ መግለጫ እሰጣለሁ።»

ሜርክል-ተጨማሪዉን መግለጫ ሰጡ።የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ጎርደን ብራዉን አሰለሱ።

«ፕሬዝዳት ካቺንስኪ ባለቤታቸዉ ማርያና አብረዋቸዉ የነበሩት ሰዎች በአዉሮፕላን አደጋ በመሞታቸዉ መላዉ አለም የደነገጠ፥ያዘነ ይመስለኛል።ፖላንድ ያለፈችበትን አስቸጋሪ ሁኔታ እናዉቃለን።እሳቸዉ (ፕሬዝዳንቱ) እራሳቸዉ የትብብር ንቅናቄ አባል በነበሩት ወቅት የከፈሉትን መስዋዕትነት እናዉቃለን።ለፖላንድ ሐርነትና ነፃነት ያደረጉትን አስተዋስኦም እንገነዘባለን።»

የሌሎች ሐገራት መሪዎች፥ የአለም አቀፍ ድርጅት፥ የማሕበራት ተጠሪዎችም ማዘን-መደንገጣቸዉን አከታትለዉ ገለጡ።የሐይማኖት አባቶች ፀለዩ።ሶቬትን የተቃወሙ፥ የታገሉት የፖላንድ ምርጥ ልጆች ግን በቃ።ከእንግዲሕ ታሪክ ነዉ ዘካሪያቸዉ።ከታሪካዊዉ የሶቬት ሕብረት ምድር፥ በሶቬት ሕብረት አዉሮፕላን የመሞታቸዉ አጋጣሚ ግን የፖለቲካ አዋቂ ደብስኪ እንዳሉት መቼም-ለማምንም መግባቱ አይገባም።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ