1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ «ኤሌክትሮኒክ» ሲጋራ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 2 2006

እ ጎ አ ካለፈው ጥር ወር መግቢያ ወዲህ፣ በዩናይትድ ስቴትስ ፣ ኒው ዮርክ፤ ቢል ደ ብላሲዮ የተባሉት የዴሞክራቱ ፓርቲ አባል የከተማይቱን የከንቲባነት ሥልጣን ከመረከባቸው በፊት፤ ከዚያ በፊት ፣ 3 ጊዜ ተመርጠው እ ጎ አ ከ ጥር 1፤ 2002

https://p.dw.com/p/1CYtF
ምስል picture-alliance/dpa

እስከ ታኅሳስ 31, 2013 ያገለገሉት ከንቲባ ማይክል ሩበንስ ብሉምበርግ፣ ከሚታወቁባቸው ድርጊቶች አንዱ በሲጋራ ማጨስ ላይ ባደረጉትጠንከር ያለ ዘመቻ ነው። 8 ሚሊዮን ኑዋሪዎች ባሏት ግዙፍ ከተማ፤ ሕግ ሆኖ እንዲጸድቅ ባበቁት ደንብ መሠረት ፣ ካለፈው ግንቦት ወዲህ፤ ሲጋራ መግዛት የሚፈቀድላቸው ወጣቶች፣ ዕድሜአቸው 18 ሳይሆን በ 21 እንዲወሰን ነው የተደረገው። በሲጋራ ላይ ከፍ ያለ ቀረጥ በመጣልም ከሀገሪቱ መስተዳድሮች ቀዳሚውን ቦታ የያዘች ኒውዮርክ ናት። የከተማይቱ አስተዳደር አንድ ጥናት እንደሚጠቁመው ከሆነ፣ የሲጋራ አጫሾች ቁጥር ባለፉት 10 ዓመታት ከ 21 ከመቶ ወደ 14,8 ከመቶ ነው ያሽቆለቆለው። በዚህ ምዕተ ዓመት በዓለም ዙሪያ አንድ ቢሊዮን ሰዎች ሲጋራ በማጨስ ሳቢያ ሕይወታቸው እንደሚያልፍ የገለጡት ብሉምበርግ ፣ ኒው ዮርካውያን ከዚሁ የሰለባዎች ብዛት ጋር እንዲደመሩ አለመሻታቸውን ነበረ የገለጡት።

Infografik Elektronische Zigarette Englisch

ከሰው ሰው ለማይተላለፉት በሽታዎች መንስዔ በመሆን ከታወቁት በዋነኛነት የሚጠቀሰው ትምባሆ ነው። ባለፈww በ 20ኛው ክፍለ ዘመን ከትምባሆ ጋር በተያያዘ ጠንቅ አንድ መቶ ሚሊዮን ሰዎች መሞታቸው ይነገራል። ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በትጋት የሚበጅ እርምጃ ካልወሰደ በ 21ኛው ክፍለ ዘመን፤ በሚሊዮን የሚቆጠር ሳይሆን፣ አንድ ቢሊዮን ህዝብ በትምባሆ ሳቢያ ያልቃል የሚል ግምት ነው ያለው። እንዲያውም፣ እ ጎ አ በ 2030 ፣ በትምባሆ ሳቢያ ሕይወታቸውን ከሚያጡት መካከል 80 ከመቶውእጅግ በደኸዩት የእስያ ፤ አፍሪቃና ደቡብ አሜሪካ የሚኖሩ ዜጎች እንደሚሆኑ ነው የተገለጠው።

ትምባሆ በተለያየ አዘገጃጀት ገበያ ላይ እየዋለ ፣ የዚህ ጠንቀኛ ንጥረ ነገር ሰለባ የሆነውና የሚሆነው መጠን ቀላል እንዳልሆን ቢታወቅም ፣ ልማዱ ፣ በሱስ ስለሚታገዝ እንደዋዛ የሚገታ አይመስልም።

በዚህ ላይ እንደ ሥነ ቴክኒኩ ዕድገት ፣ ለዚህ ልማድ ለየት ያለ ዘዴ ለመፍጠር ይሁን አይታወቅም «የኤሌክትሮኒክ ሲጋራ » ወይም ባጭሩ (ኢ-ሲጋራ ) የሚባለው ገበያ ላይ ከዋለ ጥቂት ዓመታትን አስቆጥሯል። ሁለቱ ፣ ማለትም ከትምባሆ የሚቀመመው ሲጋራና የኤሌክትሪክ ሲጋራ ምንድን ነው ልዩነታቸው?በደቡብ ጀርመን ፤ በባደንቩርተምበርግ ፌደራል ክፍለ ሀገር በምትገኘው በሃይድልበርግ ከተማ፤ የጀርመን የካንሠር ምርምር ማዕከል ባልደረባ፤ ሀኪምና ተመራማሪ ፣ የትምባሆ ቁጥጥርና የካንሠር መከላከያ ክፍል ኀላፊ የሆኑትን ዶክተር ማርቲና ፖኧችከ-ላንገርን ጠይቄአቸው ነበር።

«የትምባሆ ሲጋራ ፣ ትምባሆና ሌሎች ተጨማሪ ቅመማት፣ ወረቀትና አፍ ላይ እሚደረገው የሲጋራ ጫፍ ላይ ያለውን ማጣሪያ የሚያጠቃልል ነው። እርሱም ወረቀትና ትምባሆ ያለበት ጫፍ በእሳት የሚቀጣጠል ፣ በማጣሪያው በኩል ያለው ጫፍ ደግሞ ጭሱ ወደውስጥ የሚተነፈስበት (የሚማግበት) ነው ። ኢ -ሲጋራ፣ ፕላስቲክ ፣ የብረታ ብረት ክፍሎች፣ ባትሪና ፣ የተቀመመ ፈሳሽ ንጥር (ኬሚካል) ያለው ነው። ልዩነታቸው በአጭሩ፣ አንዱ የኬሚካሎች ቅመማ ሌላው የትምባሆ የቅመማ ንጥር ያለው መሆኑ ነው»።

«ሲጋራ ማጨስ ለሞት ሊዳርግ ይችላል !» የሚለው መፈክር ፣ በትምባሆ ወይም ሲጋራ ፓኮዎች ላይ ተጽፎ ይነበባል። የኤሌክትሪክ ሲጋራ የሚሰኘው በጤና ላይ ጉዳት ያስከትላል የሚል ማስጠንቀቂያ አይታይበትምና አደገኛ አይደለም ማለት ነው? ዶክተር ማርቲና ፖኧችከ - ላንገር እንዲህ ይላሉ።

E-Cigarettes Elektrische Zigarette
ምስል Getty Images

«የ-ኢ (ኤልክትሪክ) ሲጋራዎች ፣ ገበያ ላይ መዋል የጀመሩበት ጊዜ ቅርብ ነው። ስለዚህም፣ በዚህ ላይ ማስታወቂያ ወይም ማሳሰቢያ መሰል ነገር ለማሥፈር ፣ ጊዜው ገና ነው። ጤናን በማወኩ ረገድ፣ ያለው ተጽንዖ እስከምን ድረስ እንደሆነ፤ ግምቱም ሆነ ምልክቱ አይጠፋም፤ የተቀመመው ንጥረ ነገር ወደውስጥ በሚተነፈስበት ጊዜ ወደ ሳንባ መግባቱ የማይቀር ነው። አጠር ላለ ጊዜ በተደረገ ክትትል፣ማሳል ፣ ዐይን ማቅላት፣ ራስ ምታት ማስከተልም ሆነ ራስ ማዞር፤ ማቅለሽለሽ፤ ድካም ፤ እንቅልፍ ማጣትና የመሳሰለውን ሊያስከትል እንደሚችል ፣ የተመዘገበ፣ የተደረሰበት ጉዳይ ነው። በረዥሙ ሲታይ ግን ምን ዓይነት ሳንክ ሊያስከትል እንደሚችል ገና በግልጽ የታወቀ ነገር የለም እነዚህ ቅመሞች ለዚህ ጉዳይ መዋል የጀመሩት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ነው። »

ኢ- ሲጋራ፣ በጤና ላይ የሚያስከትለው ጠንቅ በተለይ ካንሠርን ለመሰለ አደገኛ በሽታ የሚዳርግበት

ሁኔታ ይኖር ይሆን? ከሆነስ በየትኛው ወይም በየትኞቹ የቅመማት ንጥር ነው ሊከሠት የሚችለው?

«በኢ-ሲጋራዎች ከሚገኙ ፈሳሽ ቅመማትም ሆነ ንጥረ ነገሮች በጥቂቱም ቢሆን፤ ኒትሮሳሚንስ፤ ራኮሲን፤ እነዚህ ከትምባሆ የሚገኙ ናቸው--በተጨማሪም ፎርማልሃይድ ወይም ሜታናል፣ አክሮሊን፤ እንዲሁም ጠጣር የብረታ ብረት ዓይነቶች፣ ኒኬል፣ ወይም ክሮም እንደሚገኙ ይታወቃል። እዚህ ላይ መጠቀስ የሚገባው፣ እነዚህ የተወሱት በአነስተኛ መጠን ነው የሚገኙት።

እስካሁን ድረስ፣ በ ኢ-ሲጋራዎች ላይ፣ በቂ ጥናት አልተደረገም። በመጠኑ ከተደረገው ጥናት በመነሣትም ኢ-ሲጋራዎች፣ ለጤንነት አሳሳቢ ስለመሆናቸው መናገር እንችላለን። በተለይ ለሚያጨሱ ሰዎች ! በይበልጥ ደግሞ ለልጆችና ለለጋ ወጣቶች!።»

Michael Bloomberg
ምስል picture alliance / AP Photo

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፣ የዩናይትድ ስቴትስ የምግብና የመድኃኒት አስተዳደር ፣ የኤሌክትሮኒክ ሲጋራ በተለይ ሊማለሉ በሚችሉ ከ 13 እስከ 17 ዓመት ዕድሜ ባላቸው ወጣቶች ዘንድ ሊያስከትል የሚችለው አደጋም ሆነ ሳንክ ፤ ይህና ሌሎች 45 የምርምር ፕሮጀክቶች ጥናት እንዲካሄድባቸው 270 ሚሊዮን ዶላር መመደቡ ተመልክቷል። የጥናቱ ውጤት፣ እ ጎ አ ከ 2018 ዓ ም በፊት ተጠናቆ ስለማይቀርብ ፣ የ ኤሌክትሮኒክ ሲጋራ አምራቾች ያላንዳች ሳንክ ምርታቸውን መሸጣቸውን እንደሚቀጥሉ ነው የሚታሰበው። የኤሌክትሮኒክ ኢንዱስትሪው በዚህ ዓመት ብቻ፣ በዓለም ዙሪያ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ «ኢ -ሲጋራ» ይሸጣል ተብሎ ነው የተገመተው። በዓለም ታላላቅ የትምባሆ ኢንዱስትሪዎች በመደገፍ ፣ የኤሌክትሮኒክ ሲጋራ ኢንዱስትሪው፣ ገበያውን በእጅጉ በማስፋፋት ላይ ይገኛል። ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ፣ ቁጥራቸው ከ 14 ሚሊዮን የሚበልጥ ጎልማሶች ወደ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ በ 13 እና 19 ዓመት የዕድሜ ዕርከን ላይ ያሉ ፣ እንዲሁም በ 20ኛዎቹ ዓመታት የሚገኙ ወጣቶች፣ የኤሌክትሮኒክ ሲጋራ አዘውታሪዎች ናቸው ። በዚህ የሚጠቀሙ የ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎች መጠንም ፣ ሃቻምና፣ በአንድ ዓመት ውስጥ በእጥፍ መናሩ ነው የተመለከተው።

የተባበሩት መንግሥታት ፤ የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት እ ጎ አ ከ 2013 እስከ 2020 ከሰው ወደ ሰው የማይተላለፉ በሽታዎችን፣ አስቀድሞ ለመከላከልና ለመቆጣጠር እርምጃ መውሰድ የሚያስችል ዓለም አቀፍ እቅድ ያወጣ ሲሆን፤ አንዱ ዓላማ፣ እ ጎ አ እስከ 2025 በትምባሆ መጠቀሙ ፣ ከሞላ ጎደል በ 30 ከመቶ እንዲቀነስ ማብቃት ነው። እንደ የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት አመለካከት፤ በትምባሆ ሳቢያ ፤ ሰዎች ዕድሜያቸው የሚያጥርበት አደጋ እንዲቀነስ የተቻለውን ሁሉ ማድረግ፣ የመንግሥታት ሁሉ አጀንዳ ሊሆን ይገባል።

ከትምባሆ በሚቀመም ሲጋራ፤ ከባድ ሱስ ያለባቸው ሰዎች ቀስ በቀስ እንዲቀነሱና ምናልባትም እርግፍ አድርገው እንዲተውት ሊያግዝ ይችላል ተብሎ እንደ አማራጭ የቀረበው የኤሌክትሮኒክ ሲጋራ የተለያዩ የቅመማ ንጥሮች የሚቀርቡበት በመሆኑ ፤ እርሱም ለጤና ጠንቅ አይሆንም ብሎ ማሰብ የዋሕነት መሆኑን ፤ በጀርመን የካንሠር ምርምር ማዕከል ከዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት የተቀናጀው የትምባሆ ቁጥጥርና የካንሠር መከላከያ መማሪያ ኀላፊ ዶክተር ማርቲና ፖኧችከ -ላንገር ያስገነዝባሉ።

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ