1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ «BMW» 100ኛ ዓመትና የመጀመርያዉ የጀርመን መኪና በኢትዮጵያ

ዓርብ፣ መጋቢት 2 2008

«BMW» በመባል የሚታወቀዉና በዓለም ከፍተኛ ቃዋቂነትና ተወዳጅነትን ያተረፈዉ የጀርመኑ የተሽከርካሪ ኩባንያ በያዝነዉ ሳምንት ሰኞ የተመሠረተበትን 100 ኛ ዓመት በደማቅ አቅብሮአል። በኢትዮጵያ የመጀመርያዉ የጀርመን አዉቶሞቢል በስንት ዓመተምህረት እንደገባ ያዉቃሉ?

https://p.dw.com/p/1IAT8
Deutschland BMW Feier zum 100. Jubiläum in der Allianz Arena München
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Schrader

የ «BMW» 100ኛ ዓመትና የመጀመርያዉ የጀርመን መኪና በኢትዮጵያ


በጎርጎርዮሳዊ 1916 ዓ,ም መጋቢት ሰባት የባየር አዉሮፕላን ሞተር አምራች ኩባንያ ሆኖ ነበር የተመሰረተዉ፤ የዛሬዉ ታዋቂዉ የጀርመን ተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ «BMW» አንድ መቶኛ ዓመቱን ሲያከብር ዝግጅቱ በተካሄደበት በሙኒክ በሚገኘዉ የኦሎምፒክ አዳራሽ 2000 ሺህ ተጋባጭ እንግዶች ተገኝተዋል። ይህንኑ ዝግጅት ከ30 ሺህ በላይ የሚሆኑ የመኪና አምራቹ የ«BMW» ሰራተኞች ዝግጅቱ ከተካሄደበት አዳራሽ ቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘዉ ግዙፍ ስታድዮም ለሦስት ሰዓታት በቀጥታ ተከታትለዉታል።

BMW Vision Next 100
ምስል picture-alliance/dpa/S. Hoppe


ግዙፉ የጀርመን መኪና አምራች ኩባንያ በጎርጎርዮሳዊ 1916 ዓ,ም መጋቢት ሰባት የባየር አዉሮፕላን ሞተር አምራች ኩባንያ ሆኖ ነበር የተመሰረተዉ። በ 1922 ዓ,ም ኩባንያዉ በመቀጠል ሞተር ሳይክልና የመኪና ሞተሮችን በማምራት «BMW» የተሰኘዉን የአህፅሮት ስሙን ይዞ ሥራዉን መቀጠሉ ተመልክቶአል። የጀርመኑ «BMW» የተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ በዓለም ዙርያ በ14 ሃገራት 30 የመኪናና እና የሞተር ሳይክል ማምረቻ ፋብሪካ የተከለ ሲሆን፤ ኩባንያዉ በዓመት 80 ቢሊዮን ይሮ ገቢን ያገኛል። ምንም እንኳ ኩባንያዉ በዓለም ዙርያን ተወዳጅነትና ታዋቂነት ያግኝ እንጅ ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት በፊት አምራች ኩባንያዉ አስገድዶ ሰራተኞችንና በናዚ ማጎርያ ጣብያ የሚገኙ ታሳሪዎችን ጉልበት በዝብዞአል የሚለዉ ጥናት ገሃድ መሆኑ ድርጅቱ ታሪክ ላይ ጥቁር የታሪክ ጠባሳን መጣሉ አልቀረም። በአዲስ የተሾሙት የኩባንያዉዋና ሥራ ስኪያጅ ሃራልድ ክሩገር በኩባንያዉ 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ስነስርዓት ላይ ኩባንያዉ በጀርመን ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት በፊት በሦስተኛ ስርወ መንግሥት ኩባንያዉ በሽዎች የሚቆጠሩ አስገድዶ ሰራተኞችን ጉልበት መበዝበዙን በተመለከተ ኃዘናቸዉን እንዲህ ነበር የገለፁት ።

Bildgalerie 100 Jahre Automobiler Fortschritt 75. Auto-Salon, Genf
ምስል picture-alliance/dpa/BMW AG


« በኩባንያዉ ታሪክ ዉስጥ ከባድና አስቸጋሪ ጊዜዎች ነበሩ። እናም በዚህ ምክንያት ኩባንያዉ በዚህ ጉዳይ ላይ የተሰማዉን ኃዘን ከልቡ ይገልፃል። በጎርጎርዮሳዊዉ 1983 ዓ,ም «BMW» እና የጀርመን ታሪክ በሚል በወጣዉ ጽሑፍ ፤ የመኪና አምራቹ ኩባንያ «BMW» የድሮ ታሪኩን በይፍ በግልፅ ለክርክር ሲያወጣ የመመጀመርያዉ የጀርመን ድርጅት ነዉ»
መኪናን በጥራትና በጥንካሪ በማምረት ምልክትና ባህላቸዉ ያደረጉት ጀርመናዉያን ፤ ተሽከርካሪዎቻቸዉ ከዓለም ቀዳሚ ቦታን የያዘ ነዉ ያሉን በጀርመን የመኪና ኩባንያ ዉስጥ የሚያገለግሉት ዶክተር ፀጋዬ ደግነህ፤ በጀርመን መኪና መመረት የተጀመረዉ በጎርጎረሳዉያኑ 1886 ዓ,ም ነዉ ሲሉ ታሪኩን ያስረዳሉ።


«የጀርመን አዉቶሞቢል ምርት ታሪክ በጣም ረጅምና በዓለምም ቀዳሚዉ ነዉ። የመጀመርያዉ የጀርመን አዉቶሞቢል በጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር 1886ዓ,ም ነዉ ተሰርቶ የወጣዉ። እሱም ፍሪድሪሽ ቤንዝ በሚባል ሰዉ ስም ነዉ የወጣዉ። ይህ አሁን ካርል ቤንዝ መርቸዲስ ቤንዝ እየተባለ የምናያቸዉ መኪናዎች መጀመርያ መኪናን በሰራዉ በቤንዝ ስም የተሰየመ ነዉ። ቀደም ሲል የመኪና ምርቱ ጥቂት ነበር። ከዝያ በኋላ በየጊዜዉ የተለያዩ መኪናዎች የተለያዩ ስሞችን እየያዙ መጡ። የባየር ሞተር ሥራ ማለት «BMW» የተሰኘዉም የመኪና ኩባንያም እንግዲህ የተሽከርካሪ ሞተሮችን ሲያመርት መቶኛ ዓመቱን ይዞአል ። በጀርመን የመኪና ኢንዱስትሪ በተለይም በ1940 ዎቹ አካባቢ በመንግስት ይዞታ በመንግስት ቁጥጥር ሥር ወድቆ ነበር። ይህ ደግሞ ሁሉንም ስመ ጥር የሆኑትን የመኪና አምራቾች በሙሉ አጠቃሎ ይዞ ነበር። ከሁለተኛ ዓለም ጦርነት በኋላ ደግሞ እንዳለ የመኪና ኢንዱስትሪዎቹ በብዛት ተደምስሰዉ ነበር ማለት ይቻላል፤ ማምረት የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዉ ነበር። አሁን ግን ያን ነገር አስወግደዉና ኃይላቸዉን አጠናክረዉ በጥቂት ጊዜ ዉስጥ ማለት በ70 ዓመታት ዉስጥ እንደገና በዓለም ላይ በመኪና አምራችነት ቀዳሚነቱን ቦታ ይዘዉ ይገኛሉ። ለምሳሌ ያህል ካየን በአንድ ዓመት ዉስጥ እስከ 14 ሚሊዮን የሚቆጠሩ መኪናዎች ናቸዉ የሚመረቱት። መርቸዲስ አዉዲ የመሳሰሉት መኪና አምራች ኩባንያዎች በዓመት እስከ ሁለት ሚሊዮን መኪናዎች ድረስ ያመርታሉ። »

Deutschland BMW Isetta Oldtimer
ምስል picture-alliance/dpa/F. Leonhardt


በአጼ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት በ1900 ዓ,ም ገደማ ፤ ጀርመናዊዉ ነጋዴ አርኖልድ ሆልዝ ወደ ኢትዮጵያ መኪና ማስገባቱን ሆኖም ግን ከዚህ ቀደም ሲል አጼ ምኒሊክ ከእንጊሊዝ አገር አንድ መኪና አስመጥተዉ እንደነበር ታሪክ ያሳየናል ያሉን፤ በመጀርመን የመንጃ ፈቃዳቸዉን የያዙት የመጀመርያዉ ኢትዮጵያዊ የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ የልጅ ልጅ አቶ ታደለ ይድነቃቸዉ ተሰማ እሸቴ ናቸዉ።


«በእኛ ሃገር የመኪና አመጣጥ ታሪክ እንደዚህ ነዉ። እንደ ኢትዮጵያዉያን አቆጣጠር በ1900 ዓ,ም ለአፄ ምንሊክ መኪና ለማምጣት አርኖልድ ሆልዝ የሚባል ጀርመናዊ ኢትዮጵያ ዉስጥ በትልልቅ ኢንቪስትመንቶች የተሰማራ ሰዉ ነበር። በዝያን ጊዜ በወርቅ ማዕድን ንግድ እና በሌሎች እንደዉም በባንክም ጭምር ኃሳብ የነበረዉ ይመስለኛል። ቴክኖሎጂ አፍቃሪ የነበሩትን አፄ ምንሊክን ለማስደሰት ይህ ጀርመናዊ ከሃገሩ መኪና ይዞ ለመምጣት ይወስናል። ከዝያም ጥር 15 ቀን 1900 ዓ,ም መኪናዉን ይዞ አዲስ አበባ ገብቶአል። ነገር ግን እሱ አዲስ አበባ መኪና ይዞ ከመምጣቱ 15 ቀናት በፊት ቤንዝ ሌይ የሚባል እንጊሊዛዊ ሌላ መኪና ከእንጊሊዝ ሃገር ከአንድ ጓደኛዉ ጋር ይዞላቸዉ መጥቶ ነበር። የመጀመርያ የምትባለዉ መኪና ኢትዮጵያ የገባችዉ እንግሊዛዊዉ ይዞ የመጣት ነች። ነገር ግን የኛን የመኪና ታሪክ ከጀርመን ጋር በጣም የሚያገናኘዉ ጀርመናዊዉ አርኖልድ ሆልዝ ይዞ የመጣዉ ነዉ። ከነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ፓስፖርት እንዳየሁት ከሆነ ከዝያ በኋላ የካቲት 23 ቀን አፄ ምንሊክ ለነጋድራስ አስታጥቄ ወልደጻድቅ ለሚባሉ ለሌላ ነጋድራስ እና አንድ ኪዳነ ወልድ ለሚባሉ ሰዉዬ ጋር ከነጋድራስ ጋር ለሦስቱ በአንድ ወረቀት ላይ ወደ አዉሮጳ እንዲሄዱ የላኩበት ፓስፖርትን ጽፈዋል። ወደ ጀርመን ተልከዉ የሄዱት ነጋድራስ ደግሞ 1900/ 1901 ወይም እስከ 1902 ከአንድ ዓመት እስከ ሁለት ዓመት ነዉ የቆዩት። ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ እዝያ ቆይተዉ ጀርመን ሃገር በመኪና መንዳትና በጥገና በመሰልጠን የመጀመርያዉ ኢትዮጵያዉዊ ሆነዉ ተመልሰዋል። እሳቸዉ ሲመጡ ደግሞ ግን መርከብ ላይ ሆነዉ የተነሱት ፎቶ ላይ እንደፃፉት« ወደ አዲስ አበባ ስንመለስ ይላል» ከፎቶዉ ጀርባ ፤ ከጀርመን ሃገር ሌላ ሾፊር ለምኒሊክ ይዘዉ መተዋል። እኝህ ጀርመናዊ ከአኖርልድ ሆልዝ ቤተሰብ ጋር ነዉ የመጡት። በዚህ ዓይነት መንገድ ነዉ ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ጀርመን ሃገር የመኪና መንዳትና መጠገን ሥልጠናን ያገኙት። ከጀርመን እንደተመለሱም በቤተ-መንግሥት የመኪኖች ኃላፊ ሆነዉ እስከ 1903 ዓ,ም ሌሎች ኢትዮጵያዉያንን መኪና መንዳትንና ጥገና ሞያን አሰልጥነዋል። ከዝያ በኋላ አፄ ምንሊክ የፍሎኃዎች ሹም አድርገዉ ሾመዋቸዉ ነበር። ስለዚህ የነጋድራስ የመኪና ሹፍርና በኢትዮጵያ የሚጀመረዉ በ1900 ዓ,ም በዝያ በሄዱባት ፓስፖርት ታሪክ ነዉ።»

Buchcover Im Nacke Motorwagen Nach Abessinien zu Kaiser Kaiser Menelik
ለአጼ ምኒሊክ ከጀርመን ስለተላከዉ የመጀመርያ መኪና ታሪክ በጀርመንና ቋንቋ የተፃፈ መጽሐፍ



ግዙፉ የመኪና ኩባንያ «BMW» ያለፈዉን ታሪክ ዘግቶ ወደፊት ለተጠቃሚ የሚያቀርባቸዉን ተሽከርካሪዎች በደረጃቸዉና በጥራታቸዉ የመጠቁ የተሽከርካሪ ናሙናዎች ኩባንያዉ 100 ኛ ዓመቱን ሲያከብር ለተመልካች ቀርበዉ ነበር። በሩ ወደ ላይ የሚከፈትና እንደ ኩላሊት ዓይነት ቅርፅ ያለዉ የረቀቀና በረቀቀ ቴክኖሎጂ የተሰራዉ «BMW VISION NEXT 100» የተሰኘዉ የተሽከርካሪ ናሙና፤ መኪናዉ ራሱ የሚሄድ አልያም ደግሞ በሹፊር የሚዘወር ዓይነት ነዉ። የእዚህ መኪና ናሙና ዋና አቅራቢ አድርያን ፋን ሆይዶንግ በዝግጅቱ ላይ እንዳብራሩት፤ መኪናዉ ባለ መሪ ነዉ።
« መኪናዉ መሪ አለዉ፤ ምክንያቱም የመኪናዉ ሹፊር ተሽከርካሪዉ ወድየት እንደሚሄድ ወይም መሄድ እንዳለበት በራሱ መወሰን እንዲችል ነዉ። እንደሚታየዉ መኪና ዉስጥ በግልፅ በሥነ-ስርዓት የተቀመጠ ነዉ። ሙሉዉን የፊት መስታወት እንደ እስክሪን ልናስበዉ ልንጠቀምበት እንችላለን። »

Deutschland BMW Felge Logo
ምስል picture alliance/dpa/S. Hoppe


ተሽከርካሪዉ ላይ የተገጠመዉ መስታወት ድፍን ምንም የማያሳይ ቢሆንም ቅሉ የመኪናዉ የሚሄድበትን መንገድ የሚያሳይ መስመር በስክሪን ላይ ይታያል። ሹፊሩ ወደፊት መንገዱ ላይ የሚያጋጥመዉን ማንኛዉንም እክል ሹፊሩ ከማየቱ በፊት መኪናዉ ቀድሞ በማወቅ ማስጠንቀቅያን ያስተላልፋል። ይህ ዓይነቱ ተሽከርካሪ ገበያ ላይ መቼ ይዉል ይሆን፤ የ«BMW» የመኪና ኩባንያ ዋና ተጠሪ ሃራልድ ክሩገር የቀረበላቸዉ ጥያቄ ነበር።

« እንደኔ ምኞት ቢሆን ኖሮ ነገ ቢኖር ደስ ይለኝ ነበር። ከዚህ ጋር አያይዘን ግን በመጭዉ 20 እና 30 ዓመታት እድሜ ዉስጥ ይህ ዓይነቱ ተሽከርካሪ ይኖራል የሚል እምነት ነዉ ያለዉ። አንዳንዶቹ የተሻሻሉት የመኪና ቴክኒኮች አስቀድመዉ ሊመጡ ይችላሉ። «BMW» ወደፊት የመኪና ኩባንያ አዲስ ቴክኖሎጂን ለማምጣት ትኩረት ላይ ነን።»
በጀርመን የመኪና አምራች ኩባንያ መርቸዲስ ቤንዝ ዉስጥ የሚያገለግሉት ዶክተር ፀጋዬ ደግነህ የመኪና ጥራት እጅግ መሻሻሉን ይገልፃሉ።

« አሁን ሁሉም ዓይነት መኪናዎች ባህሪያቸዉ እየተመሳሰለ ነዉ። የዉጭ ቅርጹ ወይ አቋሙ ካልሆነ በስተቀር ዉስጣቸዉ የመኪና ባህሪያቸዉ አንድ ዓይነት እየሆነ ስለመጣ አሁን ያለዉ ጥያቄ እንዴት አድርገን ነዉ መኪናዎቹን የተሻለ ማድረግ የምንችለዉ በሚለዉ ላይ ስራዉ የሚያተኩረዉ። በቀዳሚነት የሚቀመጡት እንደ መርቸዲስ፤ አዉዲ «BMW» እንደ ፎልክስ ቫገን የመሳሰሉት የጀርመን መኪና ማምረቻዎች የሚከተሉት ዲጂታላይዜሽን የሚባለዉን ዓይነት መርህ ነዉ። መኪናዎቹ እርስ በርስ መረጃን ይቀያየራሉ፤ ሁለተኛዉ ራሱን ችሎ የሚሄድ መኪና፤ ማለት ያለ ሹፊር የሚሄድ መኪና ማለት ነዉ። እንደዚህ ዓይነት መኪኖች ብዙ ሙከራ ላይ ነዉ ያሉት። አሁን እንደዉም የሚፈበረኩት መኪናዎች ካየናቸዉ አንድ ጠባብ ቦታ ዉስጥ ለማቆም ሹፊሩ ከመኪና ወርዶ በስማርት ስልኩ በመጠቀም ብቻ መኪናዉ ራሱ አዙሮ የሚገባበት ራሱ አዙሮ የሚወጣበት ዓይነት ቴክኖሎጂዎች እየተፈጠሩ ነዉ። እዚህ ላይ አንድ አዲስ ሞዴል መኪና እድሜዉ ሰባት ዓመት ነዉ። ከዚያ በኋላ ሌላ አዲስ በተሻሻለ መንገድ አዲስ አይነት መኪና እየተፈጠረ ነዉ። »

Deutschland BMW Motorrad R 32
ጀርመናዊዉ ሮናልድ ሆልዝ ለአጼ ምኒሊክ ወደ ኢትዮጵያ ስላመጣዉ መኪና ሲያሳይና ሲያስረዳ


በጀርመን የመኪና ኩባንያ በዓለም ዙርያ በርካቶችን እንደሚያሳትፍ የገለፁልን ዶክተር ፀጋዬ በመቀጠል ጀርመን ዉስጥ አንድ ሰባተኛዉ የሥራ ዓይነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከጀርመን መኪና ኩባንያ ጋር የተገናኘ ነዉ ሲሉ ተናግረዋል።


«በጀርመን በአጠቃላይ 750 ሺህ የሚሆነ ሰዉ በመኪና ኩባንያ ዉስጥ ተቀጥሮ ይሰራል። ሌሎችም የዛኑ ያክል ቁጥር ያላቸዉ ሰዎች በተዘዋዋሪ መንገድ ከዚሁ ከመኪና አምራች ኩባንያ ጋር ግንኙነት አላቸዉ። በዚህም የመኪና ምርት አፅናፋዊ በሆነ ሁኔታ ነዉ እየሰራ ያለዉ። የጀርመን የመኪና መገለጫ ደግሞ ጥራቱ ነዉ በዚህም «made in Germany » ያሰኘዋል። ተወዳጅነቱም የዛኑ ያህል የላቀ ነዉ። በኢትዮጵያም ቢሆን ለጀርመን መኪኖች ያለዉ ትርጉም ከፍተኛ ነዉ። ሙሽራ እንኳ ሲያገባ በሙዚቃ ሙሽራዉ መርቸዲሱን ይዞ መጣ ነዉ የሚባለዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ «BMW» አልያም አዉዲን የሚነዳ ሰዉ በመኪናዉ የሚሰጣዉ ዋጋ ትልቅ ነዉ፤ መኪናዎቹም ቢሆን ጠንካራና ረጅም እድሜ አላቸዉ።»

በኛ እድሜ የጀርመንን መኪና ማሽከርከር የንግሥና ያህል ነበር ያሉን፤ አቶ ታደለ ይድነቃቸዉ፤ በኢትዮጵያዉያን ዘንድ የጀርመን መኪና ተወዳጅ ነዉ በዘፈናችንም ቢሆን መርቸዲስ ይጠቀሳል ሲሉ ተናግረዋል።
«እንደ እኔ ግምት አርኖልድ ሆልዝ ከጀርመን ይዞአት የመጣዉ መኪና ቤንዝ ይመስለኛል። ከዝያ በኋላ በጣም በግልጽ የጀርመን መኪኖችን የሚያሳይ ፎቶ ያለዉ 1930 ዎቹ ነዉ ። የቤንዝ አርማ ያለባቸዉ በናፍጣ የሚሰሩ የጀርመን መኪኖች በብዛት ነበሩ። በኛ እድሜ የጀርመንን መኪና ማግኘት ማለት የንግሥና ያህል ነበር። በዝያ ዘመን የማንኛዉም ወጣት ህልም መርቸዲስ አልያም «BMW» መያዝን ነበር። ቤተ- መንግስቱም ከፍተኛ ባለስልጣናትም ታዋቂ ነጋዴዎችም ቢሆኑ የሚይዙት የጀርመንን መኪና ነበር። እንደዉም የደረጃ መግለጫ ምልክትም ሆኖ የነበረዉ የጀርመን መኪና ነበር። እስከ ዛሬም ይህ ስሜት ከኢትዮጵያን አዕምሮ የወጣ አይመስለኝም። የጀርመን እቃ ሲባል የተከበረ ነዉ በጠንካራነቱ የሚታወቀዉ የሚወደደዉ።እና ዛሪም መርቸዲስንና «BMW»ን የማያልም ያለ አይመስለኝም። ታድያ የኢትዮጵያና የጀርመን መኪኖች ግንኙነት ከጀመረ መቶ ስምንት ዓመት መሆኑ ነዉ፤ አሁን»

Deutschland BMW Feier zum 100. Jubiläum in der Allianz Arena München
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Schrader


ስለ ዝግጅታችን ያላችሁን አስተያየት በአድራሻዎቻችን ላኩልን አልያም በፊስ ቡክ ገጻችን ላይ አስተያየቶቻችሁን ጻፉልን። ሙሉዉን ቃለ ምልልስ የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።


አዜብ ታደሰ


ነጋሽ መሐመድ