1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ1997 የኢትዮጵያ ምርጫ ዉዝግብ ያስከተለዉ ግጭት 5ኛ ዓመት

ሰኞ፣ ጥቅምት 22 2003

---እንዲሕ መሰሉ-ጅምር ደፍርሶ-ሲጦዝ-ሲረግብ አምስት ወራት አስቆጥሮ-የሆነዉ ሆነ።ግጭት፥ ግድያ፥እስራት ፍርሐት-እና ፅልመት።

https://p.dw.com/p/PveK
አዲስ አበባምስል picture alliance/dpa

01 11 10


ኢትዮጵያ የቀይ-ነጭ ሽብር እልቂት-ፍጅትን ተገላገለች ከተባለ ወዲሕ የኢትዮጵያ ከተሞች በጣሙን የርዕሠ-ከተማይቱ አደባባይ አዉራ መንገዶች በሰዉ ደም፥ አካል፥ በሐብት ንብረት ስብርባሪ የጨቀዩበት-ሳምንት አምስተኛ አመት ዛሬ አንድ አለ።ብዙ የተባለ-የሚባልለትን ክስተት ከባለሙያ ጋር ላፍታ እንቃኘዋለን አብራችሁን ቆዩ።

ከሆነዉ የመማር ብልጠት፥ በሆነዉ የማዘን-ቅንነት ወይም ሰብአዊነት፥ የተበለጥኩ ቁጭት፥ወይም ሌላ ብቻ ምክንያቱ ምንም ሆነ-ምን እንደያኔዉ ሁሉ ዛሬም ያኔ የሆነዉ መጥፎ-የሆነበት ምክንያት ለምን ሆነ-ጥያቄ እየተመለሰም-እንደገና እየተጠየቀ ነዉ-።የፖለቲካና የሕግ አዋቂ ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ ከተዳጋጋሚዉ መልስ ጥቂቱን ይደግሙታል።
ዶክተር ለማ በጣሙን ሥለ ምርጫዉ ዝግጅት፥ ዘመቻ-የድምፅ አሰጣት ዛሬ-ያሉትን ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ የዛሬ-አምስት አመት ብለዉት ነበር።ግን የዛሬ-አምስት አመት የዛሬን-ዕለት አንድ ካለዉ-ክስተት በሕዋላ።

«የምርጫዉ ዘመቻ በሁሉም ዘገቦች፥ በሁሉም ዘገባ ለአሕጉሪቱ ምሳሌያዊ ነበር።የምርጫዉ ዕለትም እንደዚሁ በሁሉም መስፈርት አብነታዊ ነበር።ምክንያቱም ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆኑት ድምፅ መራጮች ድምፃቸዉን ሰጥተዋልና።»

እንዲሕ መሰሉ-ጅምር ደፍርሶ-ሲጦዝ-ሲረግብ አምስት ወራት አስቆጥሮ-የሆነዉ ሆነ።ግጭት፥ ግድያ፥እስራት ፍርሐት-እና ፅልመት።ዶክተር ለማ ይፍራ-ሸዋ ቀይ ሽብርን መሠል-ይሉታል።
አዲስ አበባ ሙቶቾዋን-ስትለቅም-ስትቀብር፥ ቁስለኛ-እስረኞችዋን ስታስስ-ስትቆጥር ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ጀርመን ነበሩ።የግጭት ግድያዉን ምክንያት ተጠየቁ።መለሱም።

«በፖሊስ ላይ አምስት የእጅ ቦምቦች ተጥለዉ የተወሰኑ የፖሊስ ባልደረቦችን ገድለዋል።አቁስለዋልም። እነዚያ ሥራ አጥ ወጣቶች ከፖሊስ ላይ ሁለት ጠመንጃ ቀምተዋል።ከሁለቱ አንዱን ሐሙስ አግኝተነዋል።ከሐሙስ ጀምሮ ሁኔታዎች ተረጋግተዋል።በዚሕ መሐል ብዙ ኢትዮጵያዉያን ሞተዋል።ሰዎች በመሞታቸዉ አዝናለሁ።ግን የተለመደዉ አይነት ሠላማዊ ሠልፍ አልነበረም።»

የመጨረሻዉ ምክንያት-ጠቅላይ ሚንስትር መለስ እንዳሉት ሆነም-አልሆነ የምክንያቱ ምክንያት ለአፍሪቃ አብነት ተብሎ የነበረዉ ምርጫ-ዉጤት ነዉ።ዶክተር ለማ እንደሚሉት ከዉጤቱም በላይ ዉጤቱ የፈጠረዉ አጓጓል ስሜት-እና ፍርሐት።

1998 አዲስ ነበር።ግን በአረጌዉ አመት መጥፎ ቅሪት እየተገፋ-የመጥፎዉ ቅሪት ብቀላ እንደተንተከተከ-እንደገነፈለበት አረጀ-በ99 ተተካም።ለአዲስ አመአት-አንድ አመት ፈሪ።የአመአቱ ዋዜማ ኢትዮጵያ ከግንቦት 1997 ማብቂያ በሕዋላ የተጓዘችበትን በተለይ-ከጥቅምት 1998 ጀምሮ የተቀባችዉን እድፍ-የምትለቃለቅበት-ለአዲስ በጎ እዉነት የተዘጋጀችበት መስሎ ነበር።

ለሁለት አመት ግድም ታስረዉ የነበሩ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ተለቀቁ።መልዕክቱም ብሩሕ ተስፋ ፈንጣቂ ነበር።ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ።
አዲስ አመት፥ አዲስ አመአት፥ አዳዲስ ቃላት-አዲስ ተስፋ።ሽፋኑ እንጂ በርግጥ እዉነቱ አሮጌ ነበር።ተስፋዉም ከንቱ።የድሕረ-አመአት-ጉዞ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ከበፊቱም የበሳ-ሆነ።ጠንካራዉ ተቃዋሚ ፓርቲ ተከፋፈለ።የመንግሥት እርምጃም ከፋ።የክፋቱ ክፋት ከአምስት አመት በሕዋላ-ዛሬም የተሻለ ክስተት አይደለም-የተሻለ ተፋ እንኳን አለመኖሩ ነዉ።እንደገና ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ።
ነጋሽ መሐመድ ነኝ-እስኪ ቸር እንመኝ።

ነጋሽ መሐመድ