1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ2007 አበይት ፖለቲካዊ ክንዉኖች

ሰኞ፣ መስከረም 3 2008

ኢትዮ-ኢርትራ ድንበር ከ1990 ጀምሮ እንደነበረዉ «ሰላምም፤ ጦርነትም የለም» እንዳሰኘ ጥቀምት ተጋመሰ።ቀዝቃዛዉ ወር ለፍፃሜዉ ዕለታት ሲቀሩት ከወደ ለንደን በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የተሰነዘረዉ ወቀሳ ፖለቲካ የሚከታተለዉን ኢትዮጵያዊ አይን ጆሮን ላፍታ ብሪታንያ ላይ ሳያስለግተዉ አልቀረም።

https://p.dw.com/p/1GWPR
ምስል AP Photo/Mohammed Abd el-Moaty, Egyptian Presidency

የ2007 አበይት ፖለቲካዊ ክንዉኖች

የዘመን ዑደት፤ የቀመር ስሌት ግድ አለና የኢትዮጵያዉን2007 ላይመጣ ሔደ።ግን «ታሪካዊ ጠላት»የሚባባሉት ኢትዮጵያ እና ግብፅ «ታሪካዊ»ስምምነት የመፈራረማቸዉ ታሪክ ሲተረክ ያን ዘመን አለመዘከር አይቻልም።የነፃ ምርጫ ታሪክ ሲወሳ፤ የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ኢሕአዴግ እና ተባባሪዎቹ የመቶ በመቶ ድል አስመዘገቡ የመባሉ ታሪክ መጠቀሱ፤ ታሪካዊዉ ድል ሲጠቀስ፤ ከአርብ አኩለ-ሌት በኋላ ታሪክ የሆነዉ ታሪካዊ ዓመት መነሳቱ እርግጥ ነዉ።ኢትዮጵያዉን በገፍ የመሰደዳቸዉ፤በየደረሱበት የመሞት፤ መሰቃየታቸዉን አሳዛኝ ታሪክን 2007 ከብዙ ቀዳሚዎቹ ወርሶ-በተራዉ አዉሮሶ ከመሰናበቱ ሌላ፤ከቀዳሚ ተከታዮቹ የሚለይበት የለም።ሰላሳ ስደተኞች ባንዴ፤ ባንድ አሸባሪ ቡድን የመቀላታቸዉ ዘግናኝ ታሪክ ግን የዚያ ታሪካዊ ዓመት ታሪክ ነዉ።የኢትዮ-አሜሪካ የዘመናት ታሪክ በፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ታሪካዊ ጉብኝት አዲስ ታሪክ የማከሉ ሐቅም የከቅዳሜ በኃላዉ አምና ብቻ ታሪክ ነዉ።በጎሉ ፖለቲካዊ ክስተቶቹ ላፍታ እንዘክረዉ።

የሕዝብ ተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤቶችየ2007 ሥራቸዉን የጀመሩትበየዓመቱ እንደሚሆነዉ አዲሱንዓመት የመቀበያዉ ድግስ፤ ፌስታ፤ጭፍራ፤ ሽብ-ረብ፤ የመልካም ምኞት መግለጫ፤ የዕቅድ፤ ቃል ኪዳኑ ጋጋታ፤ቀዝቀዝ፤ ደብዘዝ ሲል ነበር።መስከረም ማብቂያ።

ምክር ቤቶቹ ከ2003 ጀምሮ እንደለመድነዉ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲእንደራሴን ብቻ ይዘዉየአዲሱን ዓመት ሥራ አንድ ሲሉ ፕሬዝደንት ሙላቱ ተሾመ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያስተላለፉት መልዕክት ያዉ አዲስ ዓመት ነዉ ባብዛኛዉ ደግ፤ ደጉን አመልካች ነበር።

Äthiopien Mulatu Teshome ist neuer Präsident
ምስል Elias Asmare/AFP/Getty Images

ፕሬዝደንቱ በተለይ ለግንቦት ሥለታቀደዉ ምርጫ የተናገሩት በ546 ተወካዮች መካካል ለወሬ ነጋሪ ባንድ ድምፅ ብቻ የተወከለዉ አማራጭ ፖለቲካ የተሻለ ዉክልና ሳያገኝ አይቀርም የሚል ጭላንጭልም ቢሆን ተስፋ ፈንጥቆ ነበር።

በአዲስ አበባና አስመራ መካካል ከቃላላት እንኪያ ሰላንቲያ ከፍጥጫ፤ ግልምጫ፤ ከጠብ፤ መጎሻሻም ሌላ በአዲሱ አመትም አዲስ ነገር እንደማይኖር የፕሬዝደንት ሙላቱ ንግግር ግልፅ ማረጋገጪያ ነበር።

ኢትዮ-ኢርትራ ድንበር ከ1990 ጀምሮ እንደነበረዉ «ሰላምም፤ ጦርነትምየለም» እንዳሰኘ ጥቀምት ተጋመሰ።ቀዝቃዛዉ ወር ለፍፃሜዉ ዕለታት ሲቀሩት ከወደ ለንደን በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የተሰነዘረዉ ወቀሳ ፖለቲካ የሚከታተለዉን ኢትዮጵያዊ አይን ጆሮን ላፍታ ብሪታንያ ላይ ሳያስለግተዉ አልቀረም።

እርግጥ ነዉ የኢትዮጵያ መንግሥት ብሪታኒያዊዉ-ኢትዮጵያዊዉንታዋቂ ፖለቲከኛ አንዳርጋቸዉ ፅጌን ሰነዓ-የመን ላይ ይዞ ካሰራቸዉ ወዲሕ ብሪታንያ ዜጋዋን ለማስፈታት የሆነ ነገር ማድረጓ አይቀርም ባዮች ወደ ለንደን ማማተራቸዉን ያኔም-ዛሬም አላቋረጡም።

Äthiopien Ministerpräsident Hailemariam Desalegn
ምስል DW/Y. Gebireegziabher

የጥምቅምት ማብቂያዉ ወቀሳ ሰበብ ግን የአንዳርጋቸዉ መታሰር አልነበረም።በብሪታንያ ርዳታ የሰለጠነ፤ የታጠቀና የተደራጀዉ የኢትዮጵያ ፖሊስ ሰላማዊ ሰዎችን በተለይ ተቃዋሚዎችን ይገድላል፤ ያስራል፤ ያሰቃያል፤ ሲቶችን ይደፍራል መባሉ ነበር።የጋዜጠኞችና የመብት ተሟጋቾች ትችት፤ ክስና ወቀሳ ያስደነገጠዉ የብሪታንያ መንግሥት ለኢትዮጵያ ፀጥታ አስከባሪ መርጃ ይሰጠዉ ከነበረዉ ርዳታ 27 ሚሊዮን ፓዉንድ አገደ።በቃ።

በነገራች ላይ ኢትዮጵያ ከብሪታንያ ከፍተኛ ርዳታ ከሚያገኙ የአፍሪቃ ሐገራት ሁለተኛዋ ናት።The Teleheraph እንደዘገበዉ ብሪታንያ ባለፉት 3ት ዓመታት አንድ ቢሊዮን ፓዉንድ ለኢትዮጵያ ረድታለች። ሰባ ሚሊዮኑ «ለአስዳደርና ለፅጥታ ፕሮጄክቶች» የዋለ ነዉ።

የሕዳር አየር ሞቅ ቀዝቀዝ በሚለዉ የሙስሊሞች ተከታታይ ተቃዉሞ ለብ፤ሞቅ እያለ አዝግሞበፖለቲከኞች የምርጫ ዝግጅት፤ ዉይይት፤ ዉዝግብ እየጋመ ለታሕሳስ ሥፍራዉን ለቀቀ።ታሕሳስ አጋማሽ ባሕር ዳር ዉስጥ ለተቃዉሞ ሠልፍ አደባባይ በወጡ ክርስቲያን ሰልፈኞችና ፀጥታ አስከባሪዎች ተጋጭተዉ በትንሽ ግምት 3 ሰዉ ተገደለ።የነበሩ-ይናገራሉ።

ሠልፈኛዉ አደባባይ የወጣዉ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን የምትጠቀምበት ሥፍራ ለመንገድ ማስፋፊያ ተብሎ መከለሉን በመቃወም ነበር።የኢትዮጵያዊያኑ አራተኛ ወር፤ የተቀረዉ ዓለም 2014 ሲጠናቀቅ ከኒዮርክና ናይሮቢ የሰማነዉ የኢትዮጵያ ነፃ ጋዜጠኞች ይዞታ፤ ፕሬዝደንት ሙላቱ ተሾመ መስከረም ላይ ከተናገሩት ፍፁም የሚቃረን መሆኑን የሚያረዳ ነበር።ፕሬዝደንቱ እንዲሕ ነበር-ያሉት።

ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች CPJ-በምሕፃሩ እንዳስታወቀዉ ግን የጎርጎሪያኑ 2014 በርካታ ኢትዮጵያዉን ጋዜጠኞች የታሠሩበት፤ ብዙ መገኛ ዘዴዎች የተዘጉበት፤ ከሁሉም በላይ ሰላሳ ያሕል ጋዜጠኞች የተሰደዱበት ነበር።በምሥራቅ አፍሪቃ የሲፒጄ ተወካይ ቶም ሮሕድስ።

Äthiopien Barack Obama Hailemariam Desalegn PK
ምስል Getty Images/AFP/de Souza

ጥር ባተ።ጣይቱ ሆቴል በእሳት ጋየ።የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር። ኢትዮጵያዉያን እትጌ ጣይቱን እንደሚዘክሩበት ሁሉ ብሪታንያዉያን ደራሲ Evenlyn Waugh እና ጋዜጠኛ Bill Deeds ሥለ ኢትዮጵያ የፃፉትን ያስታዉሱበታል።ሁለቱም በሃያዎቹ የእድሜ ክልል ዉስጥ በነበሩበት ዘመን ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ስትወር ለመዘገብ ኢትዮጵያ በነበሩበት ወቀት ያረፉት ጣይቱ ሆቴል ነበር።1928።

ተቃጠለ።እንደ 1890ዎቹ የተመሠረተዉ የመጀመሪያዉ የኢትዮያ ሆቴል እየተጠገነ መሆኑ ነዉ-ደጉ ዜና።ታሪካዊዉ ሆቴል በእሳት በጋየ ከጥቂት ቀናት በኋላ የእስከያኔዉ ታላቅ ተቃዋሚ ፓርቲ አንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ (አንድነት-ባጭሩ) የጠራዉ ተቃዉሞ ሠልፍ በግጭት በፀጥታ አስከባሪዎች ድብደባ ተበተነ።የፓርቲዉ ተቀዳሚ ምክርትል ፕሬዝደንት አቶ ተክሌ በቀለ።

Äthiopien Addis Abeba Obama Rede Afrikanische Union
ምስል Getty Images/AFP/S. Loeb

የሆቴል ቃጠሎ፤ የድብደባ፤ ወቀሳዉ ዜና ጋብ ሲል ፤«ታሪካዊ ጠላት» የሚባባሉት ኢትዮጵያና ግብፅ ሱዳንን መሐል አድረገዉ የአባይን ዉሐ በጋራ ለመጠቀም «ታሪካዊ» የተባለዉን ዉል ካርቱም ላይ ተፈራረሙ።የሰወስቱ ሐገራት መሪዎች ባፀደቁት ዉል መሠረት ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የምታስገነባዉ የኤሌክትሪክ ሐይል ማመንጪያ ግድብ በዉሐዉ ፍሰት ላይ የሚያደርሰዉን ተፅዕኖ በገለልተኛ ተቋማት ማስጠናት አንዱ ነበር።ኢትዮጵያዊ የምሥራቅ አፍሪቃ ፖለቲካ አጥኚ አቶ አቤል አባተ።

መጋቢት ነበር ወሩ።ለግንቦት በታቀደዉ ምርጫ ሰበብ የተቃዋሚ ፓርቲዎችና የገዢዉ ፓርቲ- ኢሕአዴግ፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎችና «የኢሕአዴግ ተቀፅላ» ተብሎ የሚታማዉ ምርጫ ቦርድ ዉዝግብ የናረበትም ወር ነበር-መጋቢት።

የአንድነት ፓርቲ መሪዎች ለሁለት ተከፍሉ በሚል ሰበብ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በርካታ መሪዎች የነበሩበትን ቡድን አግዶ-ለሁለተኛዉ እዉቅና የሰጠዉ በዚሕ ወር ነበር።«የቀድሞዉ የምክር ቤት እንደራሴ» ለመባል ቀናት የቀራቸዉ የያኔዉ የአንድነት ፓርቲ ምክርትል ፕሬዝደንት አቶ ግርማ ሠይፉ በምርጫ «እንዳንወዳደር አንችላችሁም» ብለዉ ፈሩን፤ አገዱን።ብለዉ ነበር።

ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎም ምርጫ ቦርድን እንደወቀሱ፤ ኢሕአዴግን እንዳማረሩ ነበር።የሰማያዊ ፓርቲ አንዱ ነዉ።የፓርቲዉ ፕሬዝደንት ኢንጂነር ይልቃል ተመስገን።የምርጫ ቦርድ ምክትል ሐላፊ አቶ ወንድሙ ጎላ እንዳሉት ግን ምርጫ ቦርድ እስከዚያ ድረስ የጎላ ቅሬታ አልደረሰዉም።ኢትዮያ፤ ግብፅና ሱዳን በተስማሙት መሠረት የሕዳሴ ግድብን ሥራና የዉሐ ፍሰት ያጠናሉ የተባሉት ኩባንዮችን ለመቅጠር የሰወስቱ ሐገራት ሚንስትሮች ተስማሙ።

የኢትዮጵያ የዉሐና ሐይል ሚንስትር አቶ አለማየሁ ተገኑ።ሚያዚያ ሁለት።የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ስምምነቱን ለማጤን፤የመግባባት መንፈሱን እንዴትነት ለማስተንተን ጊዜ አላገኘም።ደቡብ አፍሪቃ የተሰደዱ ኢትዮጵያዉያን፤ ወሮበሎች በለኮሱት በእሳት ጋይተዉ መሞታቸዉ አሳዝኖት ሳያበቃ ሊቢያ ዉስጥ ሰላሳ ኢትዮጵያዉን የመገደላቸዉ መርዶ ያንገበግበዉ ገባ።ISIS በሚል እንግሊዘኛ ምሕፃረ-የሚጠራዉ አሸባሪ ቡድን ገሚሱን ኢትዮጵያዉያን በካራ፤ የተቀሩትን በጥይት መግደሉ ሐዘን ቁጣዉን ድርብ አድርጎት ነበር።መስቀል አደባባይ-ሠልፍ።

የቁጣ-ሐዘኑ ሰልፍ መንግሥትን በመቃወም፤ተቃዉሞዉ በግጭት ድብደባ እስራት ነዉ ያሳረገዉ።

ግንቦት ምርጫ ተደረገ።ከ36 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ድምፅ የሠጠበት፤ ሐምሳ ስምት የፖለቲካ ፓርቲዎች የተወዳደሩበት ምርጫ ባብዛኛዉ ሠላማዊ ነበር።ዉጤቱም-ብዙ አልዘገየም።ሰኔ አጋማሽ ይፋ የሆነ።የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና።

Äthiopien Addis Abeba Anti ISIS Protest
ምስል Getty Images/AFP/Abubeker

የቀሩትን የምክር ቤት ወንበሮች ደግሞ የኢሕአዴግ አጋር የሚባሉት ፓርቲዎች አሸንፈዋል።ድምር ዉጤት፤ ኢሕአዲግ መቶ፤ ተቃዋሚ ዜሮ።ተቃዋሚ ፓርቲዎች የምርጫዉን ሒደትና ዉጤት መቃወም፤ ማዉገዛቸዉ ግን ዛሬም እንደ ቀጠለ ነዉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ግን በምርጫዉ ዉጤት ማግስት ትልቅ ዕንግዳዉን ለመቀበል ሽር ጉድ ይል ገባ።የዩናይትድ ስቴትሱን ፕሬዝደንት ባራክ ኦቦማን።ኦባማ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ካቀዱበት ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚዎች እና ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾች ጉብኝቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ያደርሰዋል ላሉት የሰብአዊ መብት ረገጣ ይሁንታ ከመስጠት ይቆጠራል በማለት ሲቃወሙት ነበር።ሑዩማን ራይትስ ዋች አንዱ ነበር።

የድርጅቱ አጥኚ ጀፍሬይ ስሚዝ ነበሩ።ኦባማ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ማቀዳቸዉን በመቃወም ከኢትዮጵያ ዉጪ የሚደረገዉ ሰልፍ፤የደብዳቤ አቤቱታ፤ የመገናኛ ዘዴዎች ትችት በደመቀበት መሐል ኢትዮጵያ ዉስጥ ሁለት ትላልቅ፤ ላንዳዶች አስገራሚ አዉነቶች ተከወኑ።በአሸባሪነት ተከሰዉ ሰወስት ዓመት ግድም የታሰሩት የሙስሊሞች መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ መሪዎችና አባላት ከሰባት እስከ 22 ዓመት የሚደርስ ቅጣት ተፈረደባቸዉ።ከጠበቆቻቸዉ አንዱ-

ከአስራ-ስምንቱ ስድስቱ በምሕረት መለቀቃቸዉን ባለፈዉ አርብ ሰምተናል።ብዙዎችን ብዙ ያስገረመዉ በይግባኝ ሙግት አምስት ዓመት እስራት ተፈርዶባት የነበረችዉ መምሕርትና ፀሐፊ ርዕዮት ዓለሙ ድንገት መለቀቋ ነዉ።የተለቀቀችበትን ምክንያት-እንኳን ጋዜጠኞች እሷም አላወቀችዉም

Äthiopien vor der Wahl Merga Bekana in Addis Abeba
ምስል picture-alliance/dpa/C. Frentzen

የተፈረደበት እስረኛ የፍርድ ዘመኑን ሳይጨርስ፤ ምሕረትም፤ አመክሮም፤ይቅርታም ሳይደረግለት ድንገት በመለቀቅ ርዕዮት፤ በመልቀቅ ኢትዮጵያ የመጀመሪዎቹ፤ ሁለት ሺሕ ሰባት ልዩዉ ዘመን ሳይሆኑ አልቀሩም።

ርዕዮት በተለቀቀችበት ዕለት ጋዜጠኛ ተስፋ ዓለም ወልደየስና አራት ባልደረቦቹም ድንገት ተለቀዋል።ምክንያት።እሱም አያዉቀዉም።ተስፋዓለምና ከሱ ጋር የተለቀቁት አራት ባልደረቦቹ ከሌሎች አራት ባልደረቦቻቸዉ ጋር በድምሩ ዘጠኝ ሆነዉ መንግሥትን ለመናድ ወይም ካሸባሪ ጋር በመተባበር ወንጀል ተጠርጥረዉ ታሰረዉ፤ ተከሰዉ የፍርድ ቤት ቀጠሮ እየጠበቁ ነበር።

የርዕዮተ-ዓለሙና የነተስፋ ዓለም መለቀቅ ብዙ እንዳነጋገረ አንዳዶችን «ለኦባማ ጉብኝት እጅ መንሻ» እንዳሰኘ፤ የትልቂቱ ሐገር ትልቅ መሪ በናይሮቢ አድርገዉ አዲስ አበባ ገቡ።ሐምሌ ማብቂያ ነበር።

ጉብኝቱን የተከታተለዉ የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ጌታቸዉ ተድላ ሐይለ ጊዮርጊስ ከዘገበዉ የቀነጨብነዉን እናስታዉሳችሁ።

Äthiopien Blue Party Führung Pressekonferenz SCHLECHTE QUALITÄT
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

ፕሬዝደንት ኦባማ ኢትዮጵያን አወደሱ፤ የአፍሪቃ መሪዎችን ወቀሱ።በሰወስተኛ ቀናቸዉ ወደ ሐገራቸዉ ተመለሱ።በስልጣን ላይ ያለ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ኢትዮጵያን ሲጎበኝ-ኦባማ የመጀመሪያዉ ናቸዉ።ሐምሌም ብዙ አልቆየም።ተሰናበተ።ነሐሴ የቀድሞዉ የኢትዮያ ጠቅላይ ሚንስትር የአቶ መለስ ዜናዊ ሰወስተኛ ሙት ዓመት ተዘክሮበት፤ የኢሕአዴግ አስረኛ ጉባኤ ተስተናግዶበት፤ የኢትዮጵያዊያን ሴት አትሌቶች ድል ከቤጂግ ተዘግበበት ተጠናቀቀ።ጳግሜ።አስራ-ሰወስተኛዋ ወር። ኢትዮጵያዉያኑን በኑሮ ዉድነት፤ በዋጋ ንረት፤ በበዓል ሸመታ እንዳባተለች በስድስተኛ ቀንዋ ለሁለት ሺሕ ስምንት ቦታ ለመልቀቅ ተገደች።ነጋሽ መሐመድ ነኝ።መልካም አዲስ ዓመት።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ