1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ2008 ዓበይት ፖለቲካዊ ክንዉኖች

Negash Mohammedሰኞ፣ መስከረም 2 2009

እስረኞች መፈታታቸዉ ለየተፈቺዉ፤ ለወላጅ-ወዳጅ፤ ዘመዶቻቸዉ በርግጥ አስደሳች ነዉ።የ2008 ጥቅል ሒደትን ለተከታተለ ግን ዓመቱ ለአብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ የሰላምም፤ የደስታ ዘመን መሆኑን ሲበዛ መጠራጠሩ አይቀርም

https://p.dw.com/p/1K0qP
Frankfurt Demonstrationen Äthiopier
ምስል Anagaw Yewondwesen

የ2008 ዓበይት ፖለቲካዊ ክንዉኖች

2008 ላይመጣ ሔደ።የኢድ አል-አድሐ በዓልም ተከበረ።አዲስ ዓመት ።2009።እንኳን አደረሳችሁ።ከዚያስ።የአዲሱ ዓመት አጀማመር ማጣቀሻች፤ የአሮጌዉ ዓመት ፖለቲካዊ ሒደት ትኩረታችን ነዉ።

እያሉ ቀጠሉ።የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ሙላቱ ተሾመ።የልማዳዊ አባባል ተጽዕኖ ወይስ በርግጥ ኢትዮጵያዉን በሰላም ደረሱ። እሳቸዉ ጤናን ጨምረዉ በሰላም አደረሳችሁን ደገሙት የኢትዮጵያ ኦርተዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ማትያስ።ቅዳሜ።

ከቃጠሎ፤ ከጥይት ሩምታ ተርፈዉ የኢትዮጵያ መንግሥትን ምሕረትን ያገኙ እስረኞች መፈታታቸዉ ለየተፈቺዉ፤ ለወላጅ-ወዳጅ፤ ዘመዶቻቸዉ በርግጥ አስደሳች ነዉ።የ2008 ጥቅል ሒደትን ለተከታተለ ግን ዓመቱ ለአብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ የሰላምም፤ የደስታ ዘመን መሆኑን ሲበዛ መጠራጠሩ አይቀርም ።በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብቸኛዉ የተቃዋሚ ፓርቲ እንደራሴ የነበሩት አቶ ግርማ ሰይፉ ለየት ያለ ግን አጭር ግምገማ አላቸዉ።2008ን።

የእነ አቶ ግርማን የፖለቲካ ፓርቲ ያፈረሰዉ፤ከምክር ቤት ወንበር ተጋሪነትም ያሰናበተዉን ምርጫ ዉጤት መቶ በመቶ የጠቀለለዉ የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ኢሕአዴግ 2008 መጣሁ፤ መጣሁ ሲል ከወደ ዩናይትድ ስቴትስ ጠንካራ ድጋፍ አግኝቶ ነበር።

Brasilien Olympische Spiele Rio 2016 21 08 - Marathon Feyisa Lilesa
ምስል Getty Images/AFP/O. Morin

ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተናገደቻቸዉ አሜሪካዊ መሪ ባራክ ኦባማ ለኢትዮጵያ መንግሥት የሰጡት ድጋፍ ለገዢዉ ፓርቲ አስደሳች፤ለአገዛዙም መልካምነት ወይም ተወዳጅነት ዓለም አቀፍ «ስርቲፊኬት» ከማግኘት የሚቆጠር ነበር።

የሟቹ ጠቅላይ ሚንስትር የመለስ ዜናዊ የቅርብ ወዳጅ የነበሩት የፕሬዝደንት ባራክ ኦቦማ ልዩ ረዳት ወይዘሮ ሱዛን ራይስ ሳቅ ግን በመቶ-በመቶዉ ምርጫ ዉጤት ላይ ሥላቅ መምሰሉ አልቀረም ነበር።

የፕሬዝደንት ኦባማ ጉብኝ፤ ንግግር፤ለኢትዮጵያና ለአፍሪቃ የሰጡት ድጋፍ፤ ያስከተለዉም ትችት የኢትዮጵያና ሥለ ኢትዮጵያ በሚዘግቡ መገናኛ አብይ ርዕስነቱ ሳይቀዛቀዝ 2008 ባተ።መስከረም አንድ 2008።ለኢትዮጵያ መንግሥት ሌላ ድል።ሞላ አስገዶሞ የመራቸዉ አማፂያን ግንቦት ሰባት አርበኞች ግንባር የተባለዉ አማፂ ቡድን ከድተዉ ከኤርትራ ኢትዮጵያ ገቡ።

Karte Äthiopien Amhara, Tigray, Oromia Deutsch

መስከረም 23 ኢሕአዴግና አጋር ፓርቲዎቹ የተቆጣጠሩት አዲሱ ምክር ቤት ተመሠረተ።በማግስቱ አዲሱ መንግሥት።ብዙ የኢሕአዲግ ነባር ፖለቲከኞች የጠቅላይ ሚንስትሩ ልዩ ረዳት በሚል ማዕረግ የተሾሙበት የአዲሱ መንግስት አወቃቀር እስከዚያ ዘመን ድረስ ከሚታወቀዉ ለየት ያለ ነበር።

መሪዉ ግን ያዉ የመሪነቱን ሥፍራ በዉርስ ያገኙት አሮጌዉ ነበሩ።ጠቅላይ ሚንስትር ሐይለ ማርማያም ደሳለኝ።

ሹማምንቱ ምክር ቤት አዳራሽ ሲመክሩ 2008 ለኢትዮጵያዉን የጥሩ ዘመን ሚልኪ እንደሌለዉ በተለይ በኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢዎች በግልፅ መታየት ጀምሮ ነበር።ድርቅ።አብዛኛዉን የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመታዉ ድርቅ በኢትዮጵያ የ50 ዓመት ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ቁጥር ያለዉ ሕዝብ ለረሐብ አጋለጠ።

የአደጋ መከላከያና ዝግጁነት መስሪያ ቤት የበላይ ሐላፊ አቶ ምትኩ ካሳ ድርቁ ለረሐብ ያጋለጠዉን ሰዉ ለመርዳት መንግስታቸዉ መዘጋጀቱን አስታዉቀዉ ነበር።

የመንግስት ጥረት፤ዝግጅት፤የሐገሪቱ የምጣኔ ሐብት እድገትም በረሐብ ሰበብ የብዙ ሰዉ ሕይወት እንዳይጠፋ ለመካለክል ጠቅሟል።በሐምሳ ዓመት ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ቁጥር ያለዉን ሕዝብ ከመራብ ለማዳን ግን ጥረቱም እድገቱም አልተከረም።ኢትዮጵያ እንደለመደችዉ የለጋሾችን ርዳታ ከመማፀንም አላወጣትም።በርካታ እንስሳት፤ ቁጥሩ ይነስ እንጂ የሰዉ ይሕወትንም ከሞት አላዳነም።

የምግብ ርዳታ የሚያስፈልገዉ ሕዝብ ቁጥር ጥቅምት ስምንት ሚሊዮን ነበር።ዓመቱ ሲገባደድ እስራ-ሁለት ሚሊዮን መድረሱ ተዘገበ።ድርቁ ያስከተለዉ ጉዳት መጠን፤ የርዳታ ፈላጊዉ ቁጥር ሥንትነት፤ ከዉጪ የሚላከዉ ርዳታ መድረስ አለመድረሱ እንዳነጋገረ ጥቅምት በሕዳር ተተካ።

የድርቅ ርሐቡ አደጋም አብይ ርዕስነቱን ለሌላ መልቀቅ ግድ ሆነበት።የአደባባይ ሰልፍ-ተቃዉሞ፤ ግጭት፤ ግድያና እስራት።መነሻዉ የአዲስ አበባ የተቀናጀ ማስተር ፕላን የተባለዉ የኢትዮጵያ መንግሥት ዕቅድ ነበር።

Äthiopien Barack Obama Hailemariam Desalegn PK
ምስል Getty Images/AFP/S. Loeb

እቅዱ መንግሥት እንደሚለዉ የአዲስ አበባ መስተዳድርን የሚያዋስነዉን የኦሮሚያ መስተዳድር ልዩ አዉራጃ ወይም ዞንን ከርዕሰ-ከተማይቱ ጋር በማቀናጀት አብሮ ለማልማት ያለመ ነበር።የልዩ አዉራጃ ወይም ዞኑ ነዋሪዎች፤ የመብት ተሟጋቾችና አንዳድ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችም ዕቅዱን በሌላ ነበር የተረጎሙት።

በልማት ስም የአካባቢዉን ገበሬዎች የእርሻ መሬት ለመቀማት ያለመ ነዉ በማለት ዕቁን ተቹት።እንዲሰረዝም ጠየቁ።ተማፀኑም።መንግሥት እቢኝ አለ።አንዳድ የመንግሥት ሹማምንት እቅዱ ይሰረዝ የሚለዉን ሐሳብ ከመቃወምም አልፈዉ በግድም በግድም ገቢራዊ ይሆናል እያሉ ወትሮም የታመቀዉን ቅሬታ ለማቀጣጠል ቤንዚን አከል ነዉ-የሆነዉ።

አዲስ አበባ ዙሪያ የተቀጣጠለዉ ተቃዉሞዉ ተቃዉሞ ድፍን ኦሮሚያን አዳርሶ-አዉሮጳ ለመድረስ ሁለት ሳምንት በቂዉ ነበር።ሕዳር ማብቂያ ለንደን ላይ የተደረገዉ የአደባባይ ሰልፍ ዘጋቢያችን ድልነሳ ጌታነሕ እንዲሕ ገልጾት ነበር።

ግጭት ግድያዉ ተጨማሪ ቁጣ ተቃዉሞን እየወለደ ዳፋዉ ታሕሳስ ላይ ለሰላማዊ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችም ተረፈ።የካቲት 2007 ከእስር የተለቀቁት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ እና 21 የፓርቲዉ ባለሥልጣናት ታሰሩ።

የኦፌኮ ከፍተኛ ባለሥልጣን አቶ ገብሩ ገብረ-ማርያም በቅርቡ እንዳሉት እስረኞች እንዲፈቱ የፓርቲዉ ፖለቲከኞችም የተቃዉሞ ሰልፈኞችም ጩኸት ሰሚ አላገኘም።

ጥር ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ለተቃዉሞዉ የተንበረከከ መሠለ።የአዲስ አበባ የተቀናጀ ማስተር ፕላን የተባለዉን ዕቅዱን ሰረዘ።ዉሳኔዉ ከመዘግየቱ ጋር ግድያ፤እስራት እንግልቱን ለማስቆም የፈየደዉ የለም።

ተቃዉሞዉ ተቃዉሞዉን ለመደፍለቅ የሚወሰደዉ የሐይል እርምጃም ተካርሮ ቀጠለ።ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት ሑዩማን ራይትስ ዋች ሰኔ ላይ እንዳስታወቀዉ ሕዳር በተጀመረዉ ግጭት የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከ400 በልጧል።በሺ የሚቆጠሩ ቆስለዋል።በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ተደብድበዋል።በአስር ሺሕ የሚቆጠሩ ደግሞ ታስረዋል።የፀጥታ ሐይላት የገደሏቸዉን ወጣቶች፤ ሴቶችና አዛዉንቶችን አስከሬን በየማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዉ ከተለጠፎ ቪዲዮዎች እና ፎቶ ግራፎች መመልከት የዕለት-ከዕለት ክስተት ሆነ።

የኢትዮጵያ ሁለተኛ ሁለተኛ ደረጃ ማጠናቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ከፈተናዉ በፊት ሾልኮ ወጣ።ግንቦት።ፈተናዉ አሾልከዉ ያወጡት የኦሮሚያ ተቃዉሞ አደራጅ የተባለዉ ስብስብ አባላት መሆናቸዉን አስታዉቀዋል።እርምጃዉ እነሱ እንዳሉት የተቃዉሞዉ አካል ነዉ። በተቃዉሞዉ ምክንያት ያላጠኑ ተማሪዎች በቂ የማጥኚያ ጊዜ እንዲሰጣቸዉ በጠየቁት መሠረት የኢትዮጵያ መንግሥት የፈተናዉ ጊዜ ለማረዘም ተገደደ።

በተቃዉሞ፤ግጭት፤ግድያ፤ እስራቱ መባባስ የሰጋዉ ኢትዮጵያዊ ሰኔ ላይ ለለዉጥ ያክል ሌላ ዜና ቀረበለት። ይኸኛዉም ግን ያዉ ስጋት ነዉ።የጦርነት ስጋት።ከ1992 ጀምሮ ከድንበር ማዶ-ለማዶ የተፋጠጠዉ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጦር ፆረና ግንባር በተባለዉ አካባቢ ተጋጨ።ግጭቱ በርግጥ አዲስ አይደለም።መጠኑ ግን ጠንከር፤ ጥፋቱም እስከ ሰኔ ከነበሩት ሁሉ ከበድ ያለ ነዉ።የኤርትራ መንግሥት ጦሩ በመቶ የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች መግደሉን አስታዉቋል።የኢትዮጵያ የኮሚኒኬሽን ጉዳይ ፅፈት ቤት ሚንስትር አቶ ጌታቸዉ ረዳ ግን የሟች ቁስለኞች ቁጥርን መዘርዘር አልፈለጉም።

ክረምቱ ሲበረታ፤ የረመዳን ፆም ሲጠናቀቅ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በናይሮቢ አድርገዉ አዲስ አበባ ገቡ።

የኢትዮጵያ ታሪክ ከመቶ ዓመት አይዘልም በሚባልበት ቤተ-መንግሥት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ሥለ ሁለቱ ሐገራት ግንኙነት የተናገሩት ባስተናጋጆቻቸዉ ዘንድ ያሳደረዉን ስሜት ሳናዉቅ ሐምሌ ተገባደደ።ታሪካዊቱ ከተማ ጎንደር ላይ ሌላ ታሪክ ሳይታይ ግን ወሩ አላበቃም።የወልቃይት ጠገዴ ወረዳ ከትግራይ ይልቅ በአማራ መስተዳድር መተዳደር አለበት የሚለዉ የረጅም ጊዜ ጥያቄ ምክንያት ሆኖ ጎንደር ላይ በረጅም ጊዜ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የተቃዉሞ ሰልፍ ተደረገ።

Äthiopien Addis Ababa Benjamin Netanjahu Staatsbesuch Hailemariam Desalegn
ምስል DW/Y. Gebereegziabahre

የሰልፈኛዉ ብዛት ብቻ ሳይሆን ሰልፉ በሰላም ተጀምሮ በሰላም መጠናቀቁ፤ ሰልፈኛዉ ከአካባቢዉ ርቆ ለኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ድጋፍ መስጠቱ ብዙዎችን ያስደነቀ፤ጎንደሮችን ያስመሰገነ፤ወልቃይቶችን በሳቸዉ ቋንቋ ያኮራ ነበር።

የጎንደሩ ሰልፍ በሳምንቱ ባሕርዳርም እዚያዉ ጎንደርም፤ በሌሎች ትናንሽ ከተሞችም ሲደገም ግን አስከሬን ያስቆጥር፤ ሐብት ንብረት ያጠፋ ያዘ።አንዳድ የመብት ተሟጋቾች እንደገመቱት ፀጥታ አስከባሪዎች ከሰኔ አጋማሽ እስከ ነሐሴ አጋማሽ በኦሮሚያና በአማራ መስተዳድር በወሰዱት የሐይል እርምጃ ወደ ሰዎስት መቶ የሚጠጉ ሰዎች ተገድለዋል።

ነሐሴ ሌላ መዘዝ አስከተለ።ቂሊንጦ እስር ቤት በእሳት ጋየ።በሚንቀለቀለዉ እሳት መሐል የፀጥታ አስከባሪዎች ጥይት ይንፈቀፈቅ ያዘ።ቢያንስ 23 እስረኞች ተገደሉ።እነማን ይሆኑ? የሚያዉቁት የመንግሥት ሹማንቶች ናቸዉ።እስካሁን ግን ከእስረኞቹ ጠበቃ አንዱ ዛሬ እንዳሉት ባለስልጣናቱ በይፋ አልተናገሩም።ዓመቱ ግን ሔደ።ጣጣ-መከራዉን መቀጠሉ እንጂ ክፋቱ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ። መልካም አዲስ ዓመት።ኢድ ሙባረክ።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ