1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ2015 ዓበይት ክንዉኖች ክፍልI

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 11 2008

በየመን የአል-ቃኢዳ ቅርንጫፍ አባላት ናቸዉ የተባሉት አሸባሪዎች ፓሪስ ላይ የጣሉትን ጥቃት ለመበቀል የሐያሉ ዓለም ዤ ስዊ ሻርሊ (እኔም ሻርሊ ነኝ) እያለ ወደ ደቡብ አረቢያ ሲያማትር ወትሮም ሠላም የራቃት ደሐይቱ አረባዊት ሐገር እርስ በርስ ስትፋጅ አገኛት።

https://p.dw.com/p/1HRL4
ምስል Reuters/Grigory Dukor

[No title]

ከአፍቃኒስታን እስከ ኢራቅ በድል መጠናቀቁ የተነገረለት ፀረ-ሽብር ጦርነት ዳግም ጦር ያስዘመተበት፤በዩክሬን ሰበብ ጦር የተማዘዙ ጠላቶች እንደ ጥሩ ወዳጅ በጋራ የዘመቱበት፤ የሰዉ ልጅን የሚፈጅ፤ የሚያሰድደዉን ጦርነት የሚያግፈጠፍጠዉ ዓለም ለዛፍ፤ዕፅዋት፤ ለከባቢ አየር ደሕነት በጋራ ሊሰራ ቃል የተገባባበት ዓመት የ365 ቀናት ጉዞዉን ሊያገባድድ እነሆ የዘጠኝ ቀን ዕድሜ ቀረዉ።ጊዜዉ ይሮጣል።ሕይወት አጭር ናት።ግን  ቅጥቧ እስኪደርስ ትቀጥላለች።በጎርጎሮሳዊዉ 2015 ከአፍሪቃና አዉሮጳ ዉጪ ባለዉ ዓለም የተከናወኑ አበይት እዉነተቾን በሁለት ክፍል እንቃኛለን።ክፍል አንድን ዛሬ እነሆ።

                            የዩክሬንን ፖለቲካዊ ሥርዓት በበላይነት የመቆጣጠሩ ሽሚያ ከምዕራባዉያን መንግሥታት ጋር ጠመንጃ ካማዘዘ ጠብ የዶላት ሩሲያ የራስዋን ፖለቲካዊ ተፅዕኖ የምታሳርፍበትን ክበብ ለመፍጠር ያደረገችዉ ጥረት፤ የመነመነም ቢሆን ጥሩ ዉጤት ያሳየዉ ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ነበር።

የምስኮ እና የዋሽግተን፤ ብራስልስ ፖለቲከኖች የኪየቭን ቤተ መንግሥት በየታማኞቻቸዉ በኩል ለመቆጣጠር የገጠሙት ፍትጊያ አጓጉል ባርቆ ክሪምን ከሩሲያ አስለጥፎ ምሥራቃዊ ዩክሬንን ከጦርነት ከሞጀረ ወዲሕ ምዕራባዉያኑ ተሻራኪዎች የሞስኮ ባላንጦቻቸዉን ለማንበርከክ ያላደረጉት ከነበረ ምላጭ መሳብ ብቻ ነበር።

Frankreich Stephane Charbonnier Banner Augen
ምስል picture-alliance/dpaF. Von Erichsen

ምዕራባዉያን መንግሥታት የነዳጅ ዘይት ዋጋን ከማርከስ እስከ ምጣኔ ሐብት ማዕቀብ፤ ከዉጊያ ልምምድ፤ ጦር እስከ ማስፈር ከወረራ ዛቻ እስከ ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ የተረባረቡባት ሩሲያ ከአራት ደካማ ግን ሥልታዊ ጎረቤቶቿ ጋር የምጣኔ ሐብት ሕብረት መሠረተች።ጥር አንድ-ማለቱ ነበር።

ሩሲያን ከቤሎሩስ፤ከአርሜንያ፤ከካዛኽስታን እና ከኪርጊስታን ጋር የሚያስተባብረዉ ዩሮኤዥያ የተሰኘዉ ሕብረት የምዕራቦቹን ተፅዕኖ መቋቋም ባይችልምሥነልቡናዊ አቅሙ ቀላል አይደለም።

በየኩሬን ሰበብ የናረዉ የምዕራብዉያን እና-ሩሲያ እሰጥ አገባ ዉጤት አስተጋብኦቱ የሁለቱን ወገኞች ፖለቲከኞች በሚያራዉጥበት መሐል-የአዉሮጳ ሥልጣኔ፤ የዉበት፤ የፍቅር ተምሳሌቲቱ ከተማ ተሸበረች።ፓሪስ።ጥር ሰባት።

ሁለት ወንድማቾች ታጣቂዎች ሻርሊ ኤብዶ የተሰኘዉን የፈረንሳይ ምፀታዊ መፅሔት ቢሮን ወርረዉ የመፅሔቱን አዘጋጆች፤ ባልደረቦችና ፀጥታ አስከባሪዎችን በድምሩ አስራ-ሁለት ሰዎች ገደሉ።ሐዘን፤ዉግዘት፤የበቀል ዛቻ፤ ፉክክራዉ ይንቆረቆር ገባ።ለፕሬዝደንት ፍራንሷ ኦላንድ ግድያዉ በመላዉ ፈረንሳይ ላይ የተፈፀመ ነበር።

«ዛሬ መላዋ ሪፐብሊክ ተጠቃች።ሐሳብን በነፃነት ለመግለፅ፤ለባሕል፤ለሥነ-ጥበብ፤ ለብዝሐነት እና ለዲሞክራሲ የቆመችዉ ሪፐብሊክ (ተጠቃች።) የገዳዮቹ ሊያሳኩ የፈለጉት ይሕ ነዉ።ይሁንና ነፃነት ከአረመኔዎች በላይ ጠንካራ ናት።ፈረንሳይ እሴትዋን ለማስከበር በጋራ እስከቆመች ድረስ ጠላቶችዋን ሁሌም ታሸንፋለች።ሥለዚሕ ሁላችሁም በጋራ እንድትቆሙ እጠይቃለሁ።መልሳችን ይሕ መሆን አለበት።»

ነብዩ መሐመድን የሚያንቋሽሽ ሥዕል አትሟል በተባለዉ መፅሔት አዘጋጆች ላይ የተፈፀመዉ ግድያ ፓሪሶችን ለበቀል ሲያንተከትክ አንድ ሌላ ታጣቂ እዚያዉ ፓሪስ ከሚገኝ አንድ የአይሁድ የምግብ ሸቀጥ መደብር ገብቶ በትንሹ አራት ሰዎችን ገደለ።ገዳዮቹ በሙሉ ተገድለዋል።

Jemen Protest gegen saudi-arabische Militäroperationen
ምስል picture-alliance/dpa/Y. Arhab

የመጀመሪያዉ ጥቃት በተፈፀመ በአራተኛዉ ቀን የአርባ ሐገራት መሪዎችና ከሁለት ሚሊዮን የሚበልጡ የፓሪስና የአካባቢዋ ነዋሪዎች ግድያዉን አዉግዘዉ ከፈረንሳይ ጎን መቆማቸዉን በሠልፍ አረጋገጡ።የጀርመንዋ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል እንዳሉት ያን ያሕል መሪና ሕዝብ አደባባይ መዉጣቱ ጀርመንን ጭምር የሚያኮራ ነዉ።

«ይሕ የሚያመለክተዉ የነፃነት፤ የእኩልነት እና የወንድማማችነት አስተሳሰብን የሚያጠናክሩ ብዙ ሰዎች መኖራቸዉን ነዉ።እና እኛ ዛሬ እንደ ጀርመን ፌደራላዊ መንግሥት ይሕንን እንደምንደግፍ እና የፈረንሳይ ታሪካዊ ወዳጅ እንደመሆናችን መጠን በዚሕ ክፉ ሰዓት ከመላዉ ፈረንሳዊ ጎን መቆማችንን ስንናገር ኩራት ይሰማናል።ፅናቱንም እንመኝላችኋለን።»

በየመን የአል-ቃኢዳ ቅርንጫፍ አባላት ናቸዉ የተባሉት አሸባሪዎች ፓሪስ ላይ የጣሉትን ጥቃት ለመበቀል የሐያሉ ዓለም ዤ ስዊ ሻርሊ (እኔም  ሻርሊ ነኝ) እያለ ወደ ደቡብ አረቢያ ሲያማትር ወትሮም ሠላም የራቃት ደሐይቱ አረባዊት ሐገር እርስ በርስ ስትፋጅ አገኛት።

የሐገሪቱን መንግሥት የሚወጉት የሁቲ አማፂን ርዕሠ-ከተማ ሰነዓን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠሩ።አንዴ ታግቻለሁ፤ ሌላ ጊዜ ሥልጣን ለቅቄያለሁ፤ ሲሉ የነበሩት ፕሬዝደንት አብድ ረቦ መንሱር ሐዲ ወደ ትዉልድ ግዛታቸዉ ደቡብ የመን ሸሹ።ጦርነቱም ጋመ።

የሰነዓዉ ወኪላችን ግሩም ተክለ ሐይማኖት።ጥርም አበቃ።የካቲት ሰባት የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ፔትሮ ፖሮሾንኮ ቴሌቪዥን ካሜራ ፊት ቀርበዉ የተናገሩት ሐገራቸዉን የሚያወድመዉን ጦርነት፤ግጭት ሽኩቻ ለማርገብ የሚደረገዉን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ጨርሶ ያዳፍነዋል አሰኝቶ ነበሩ።

Russland Syrien Militärhilfe
ምስል Reuters/Ministry of Defence of the Russian Federation

ፕሮሼንኮ ከተማረኩ ወይም ከተገደሉ የሩሲያ ወታደሮች የተገኘ ያሉትን የሩሲያ ፓስፖርት እያገላበጡ ሐያል ጎረቤታቸዉን የወነጀሉትን ከሕዳር 2013 የጀመረዉን የዩክሬን ቀዉስ ለማርገብ በተለይም ምሥራቃዊ ዩክሬንን የሚያወድመዉን ጦርነት ለማስቆም የሚረዳ ሥምምነት ይፈረማል ተብሎ በሚጠበቅበት መሐል ነበር።

«2014 የምዕተ-ዓመታትን ቢቀር የአስርታትን ጊዜ የኋሊት አሽከርክሮታል።ጎረቤታችን ዓለም አቀፍ ሕግን ጥሳ የግዛታችንን አካል ከግዛትዋ ቀይጣለች።ዛሬ የቀድሞዋ ስልታዊ ወዳጃችን በሉዓላዊት ሐገራችንና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መስራች ሐገራችን ላይ ሁሉን አቀፍ ጦርነት ከፍታብናለች።በሁለቱ የቀድሞ ወዳጅ ሐገራት መካካል በተገነባዉ የጥላቻ ግንብ ላይ የዉሸትና የፕሮፓጋንዳ ክምር እየተደፈደፈ ነዉ።ባንድ ወቅት ሸቀጦችን ለማጓጓዢያ፤ሐገር ጎብኚዎችን ለማመላለሾያ ያገለግሉ የነበሩት የድንበር መንገዶች ዛሬ የሩሲያ ታንኮች፤መድፎች፤ሮኬት ማወንጨፋ የቻኑ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች ይርመሰመሱባቸዋል።»

የቸኮሌት ነጋዴዉ ቱጃር ፖለቲከኛ ወቀሳ፤ዉግዘት ሞስኮዎችን ብዙ አላበሳጨም።እንዲያዉም ዉግዘት፤ወቀሳ፤ ክሱ በተሰማ በአምስተኛዉ ቀን ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን፤ ከአዉጋዥ ከሳሻቸዉ ጋር ሥለተኩስ አቁም ይነጋገሩ ገቡ።ሁለቱ መሪዎች የቤሎሩስ፤የጀርመን እና የፈረንሳይ አቻዎቻቸዉን አክለዉ ሺዎችን የገደለዉን ጦርነት ለማስቆምም ተስማሙ።የካቲት 12

በምዕራባዉያን በሚደገፈዉ በዩክሬን መንግሥት እና ሩሲያ በምትረዳቸዉ አማፂያን መካካከል ተኩስ አቁም ሲፈረም የየካቲት አስራ-ሁለቱ 139ኛዉ ነበር።ከሞላ ጎደል እስካሁን ገቢራዊ የሆነዉም ይኸዉ ነዉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 2015«የብርሐን እና የዓፈር ዓመት ብሎ ሰይሞት ነበር።» የድርጅቱ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ያኔ አዲስ በነበረዉ ዓመት ካሳለፋቸዉ ዉሳኔዎች ቀዳሚዉ ግን አፈርን መጠበቅ ወይም ብርሐንን ማዳራስ የሚል አልነበረም።«እንዋጋ» የሚል እንጂ።ማንን? አሸባሪን።

ዉሳኔ ቁጥር 2199 በፀደቀ በሁለተኛዉ ሳምንት፤ የአሸባሪነት ሥም ዝናዉ የናኘዉ፤ እራሱን የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግሥት (ISIS) ብሎ የሚጠራዉ ቡድን ኒምሩድ፤ሐትራ፤ዱር ሻሩኪን የተባሉትን የኢራቅ ጥንታዊ ከተሞች ማዉደሙ ተዘገበ።የናጄሪያዉ አሸባሪ ቡድን ቦኮ ሐራምም የISIS አባል መሆኑን አወጀ።መጋቢት 12

መጋቢት ሐያ-አምስት።ሳዑዲ አረቢያ መራሹ የአረብ ሐገራት ጦር የመንን በጦር ጄት መደብደብ ጀመረ።አብዛኛዉን የመን የሚቆጣጠሩትን የሁቲ አማፂያንን ለማጥፋት የዘመቱት የተባባሪዎቹ ሐገራት የጦር ጄቶች ድብደባ ጥፋት ለኢትዮጵያዉን ስደተኞች ተርፎም ነበር።እንደገና ግሩም ተክለ ሐይማኖት።

Nepal Hubschrauber Militär
ምስል Reuters/U.S. Marine Corps/R. Morales

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀዉ ከመጋቢት እስካሁን በቀጠለዉ ጦርነት ስድስት ሺሕ ሰዉ ተገድሏል።መቶ ሺዎች ቆስለዋል።ሚሊዮኖች ተሠደዋል።ትናንት ከወደ ዤኔቭ የደረሰን ዘገባ እንደሚጠቁመዉ አቅሙም፤ ገንዘቡም፤ ሞራሉም የተመናመነባቸዉ የተፋላሚ ሐይላት አዛዦች ታማኞቻቸዉ የሠላም ዉል እንዲፈራረሙ ሳይፈቅዱ አልቀሩም።

ሚያዚያ ሐያ አምስት-ካታማንዱ ኔፓል።-------እና መሬቱ ሰመጠ፤ ሕንፃ፤ ቤቱ፤ አጥሩ፤ ግንቡ ሁሉም ተደረመሠ።የሒማሊያዋ ተራራ ሐገር ሕዝብ ተፈጥሮም፤ ፈጣሪዉም ጨከነበት።8857 ሰዉ አለቀ።በሬክተር መመዘኛ 7,8 የተለካዉ መሬት መንቀጥቀጥ ሕንድ፤ ቻይን፤ ባንግላዴሽም ተሻግሮ አንድ መቶ ስልሳ ሰዉ ገድሏል።በሁለተኛ ሳምንቱ እንደገና ኔፓል ተመልሶ ከመጀመሪያዉ መቅሰፍት የተረፉ 218 ሰዎችን አጠናቀቀ።ግንቦትም አበቃ።የቀሪዉን መንፈቅ አበይት እዉነት ሳምንት ለመቃኘት ያብቃን።ለዛሬዉ መልካም ምሽት።

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ