1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዩክሬን ላይ የጠነከረዉ ጫና

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 23 2004

የቀድሞ የዩክሬይን ጠቅላይ ሚኒስትር ዩሊያ ቴሞሼንኮ እንዲፈቱ ዓለም ዓቀፍ ግፊቱ ቀጥሏል። የአዉሮጳ መሪዎች ኪየቭ ላይ የጀመሩትን ግፊት በማጠናከርም ዩናይትድ ስቴትስ ቴሞሼንኮ ባስቸኳይ ተፈተዉ ህክምና እንዲያገኙ ጠይቃለች። ዓለም ዓቀፍ

https://p.dw.com/p/14nfC
ምስል picture-alliance/dpa

የመብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናልም ታሳሪዋ ፖለቲከኛ ሊፈፀምባቸዉ ይችላል ያለዉን በመጥቀስ መግለጫ አዉጥቷል።

ልጃቸዉ ዬቭጌኒያ ቴሞሼንኮ እናቷ በአሳሪዎቻቸዉ በደረሰባቸዉ እንግልትና በወሰዱት የረሃብ አድማ ምክንያት ጤናቸዉ በአስጊ ሁኔታ ላይ እንደሆነ በድረገጽ ላይ ባሰፈረችዉ መግለጫ ጠቁማለች። ዛሬ ህዝባዊ በዓል በመሆኑም እስረኛዋን ለመጎብኘት አለመቻሉ የቤተሰቡን ስጋታት ከፍ እንዳደረገዉም ተገልጿል። ዘገባዎች እንዳመለከቱት ላለፉት 12 ቀናት በረሃብ አድማ ላይ የቆዩት የቀድሞዋ የዩክሬን ጠቅላይ ሚኒስትር ዩሊያ ቴሞሼንኮ የጤና ይዞታ ያሳሰበዉ የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት የዩክሬን መንግስት ህክምና እንዲፈቅድላቸዉ፤ እንዲሁም እዚያ የሚገኘዉ የአሜሪካን ኤምባሲ ታሳሪዋን መጎብኘት እንዲችል ጠይቋል።

Julia Timoschenko Proteste in der Ukraine
ምስል picture-alliance/dpa

ጀርመን ያቀረበችዉን ዩክሬን ከፖላንድ ጋ በመተባበር በምታስተናግደዉ የአዉሮጳዉያን 2012ዓ,ም የአዉሮጳ እግር ኳስ ዋንጫ ዉድድር ላይ ያለመገኘት ጥሪ የአዉሮጳ መሪዎች እንደተቀበሉት እያመለከቱ ሲሆን አሜሪካን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዛሬ ይፋ ያደረገዉ መግለጫም አዉሮጳ ዩክሬን ላይ ያሳረፈችዉን ግፊት አጠናክሯል። የጀርመን ፖለቲከኞችን አቋም ወደቀዝቃዛዉ ጦርነት የመመለስ አዝማሚያ ሲሉ የተቹት የዩክሬን ባለስልጣናት በበኩላቸዉ ስፖርትን እንደመያዣ ሊጠቀሙበት አልመዋል ሲሉ ተችተዋል። ዩክሬኒያዊዉ የፖለቲካ ተንታኝ ቫዲም ካራስዮቭ እንደሚሉት ከሆነ ፕሬዝደንት ዩኒኮቪች ምንም እንኳን ከዉጭ የሚሰነዘርባቸዉን ትችት ቢሰቀቁም ከዚያ በላይ ቲሞሼንኮን ይፈራሉ፤

«በአጭሩ ለመናገር ከዉጭ የሚሰነዘርባቸዉን ትችት ቢፈሩም ከዚህ የበለጠ ደግሞ ለቴሞሼንኮ ፍርሃት አላቸዉ። ከምንም በላይ ደግም ስልጣናቸዉን እንዳያጡ ይሰጋሉ። በመሠረቱ ዩሮ 2012 በቴሞሼንኮ ምክንያት ሙሉ ለሙሉ ተሳታፊ ያጣል የሚለዉ አያሰጋቸዉም። ምክንያቱም እንዲህ ባለ ምክንያት የእግር ኳስ ጨዋታዉ እንደማይሰናከል ግልፅ ነዉ። መካሄዳቸዉ አይቀርም። እንዲህ ባለዉ ጨዋታ መሳተፍ የማይፈልግ አስቀድሞ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልገዋል።»

የተንታኙን ግምት የሚያጠናክረዉ የጀርመን የእግር ኳስ ፌደሬሽን ኃላፊ ቮልፍጋንግ ኔሪሽባህ ሃሳቡን በይፋ መቃወማቸዉ ነዉ። የዩክሬን ህዝብ እንዲህ ያለዉ የስፖርት ዝግጅት ሊነፈገዉ እንደማይገባ የተሟገቱት ኔሪሽባህ የዘንድሮዉ የአዉሮፓ የእግር ኳስ ሻምፒዮን ዉድድር ወደጀርመን ይመለስ የሚለዉን እንደማይቀበሉት አመልክተዋል። የእሳቸዉን ሃሳብ የተለያዩ የስፖርት ፌዴሬሽኖች እንደሚደግፉ የጀርመን የዜና ወኪል ከበርሊን ሲዘግብ፤ የዓለም ዓቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት የጀርመን ኦሊምፒክ እንቅስቃሴ የበላይ ቶማስ ባህ በበኩላቸዉ ርምጃዉን ዓለም ዓቀፍ ንቀት በማለት ተችተዋል።

Vor dem Olympiastadion Kiew ist ein übergroßer Fußball mit dem Logo der UEFA Euro 2012 in Kiew in der Ukraine aufgestellt
ምስል picture-alliance/dpa

ባህ ሃሳቡ የዩክሬንን ህዝብ ፍላጎት የሚፃረር ብቻ ሳይሆን የተባባሪ አዘጋጅዋን የፖላንድንና የሌሎች የአዉሮጳ ሐገሮችን ብሎም የአዉሮጳ እግር ኳስ ዉድድር አዘጋጅ አካልን አመለካከት ከግምት ያላካተተ እንደሆነም ግልፅ አድርገዋል። የጀርመን ፖለቲከኞች በዩክሬን በሚካሄደዉ የአዉሮጳ ሻምፒዮና ዉድድር አለመገኘት የሚለዉን ሃሳብ ያቀረቡት የኪየቭ አስተዳደር ቲሞሼንኮን ከእስር ለመልለቅ ፈቃደኝነት ባለማሳየቱ ሲሆን፤ ባለፈዉ ዓርብ በአገሪቱ ምስራቃዊ ግዛት በሚገኝ ከተማ የደረሰዉ የቦምብም ተከታታይ ፍንዳታም የፀጥታ ስጋት መኖሩን አመላካች ነዉ ተብሏል። ዩክሬን ግን ፍንዳታዉ ያስከተለዉን ስጋት ለመቅረፍ እና የተመልካቾችን ደህንነት ለመጠበቅ ተገቢዉን ዝግጅት አድርጌያለሁ እያለች ነዉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ