1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዩክሬን ከማይዳን አብዮት እስከ ባይደን ጉብኝት

ሰኞ፣ ኅዳር 15 2007

ከቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍፃሜ ወዲሕ በተለያዩ ሐገራት የተለያዩ የአደባባይ ሠልፍ-አመፆች ተደርገዋል።አስር ዓመት ባልሞላ ጊዜ ሁለት መንግሥት በአደባባይ አመፅ የፈረሰባት ሐገር ግን አንድ ናት።ዩክሬን።ዛሬም ቢያንስ ምሥራቃዊ ግዛቷ ደም በሚያራጭ አመፅ እየወደመች፤ ምስራቅ ምዕራቦችን ከ25 ዓመት በኋላ ዳግም እንዳፋጠጠች ነዉ።

https://p.dw.com/p/1DsKr
ምስል Reuters/Valentyn Ogirenko

የዩክሬኒያዉ ጋዜጠኛ ሙስጠፋ ነየም የዚያን ቀን ከጓደኛ ባልደረቦቹ ጋር ያደረገዉ እስከ ዛሬና ዛሬ ለሆነና ለሚሆነዉ ይደርሳል ብሎ አላሳበም።ግን አደረገዉ።«እኛ ማይዳን አደባባይ ልንሰለፍ ነዉ፤ አብሮን የሚሠለፍ አለ» የምትለዋን መልዕክት ከፌስ ቡክ ገፁ ለጠፈ።ሕዳር 21 2013(ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ።» እነ ኢንጂነር ፔትሮ ሩንኪቭ መልዕክቱን እንደሰሙ ወደ አደባባዩ ተመሙ።ባለፈዉ ሳምንት አርብ አንድ ዓመት ደፈነ።የማይዳን አብዮትም በባይደን ጉብኝት ተዘከረ።የአብዮቱ፤ ዉጤት ናየወደፊት ሒደቱ ግን የያኔዉን ጋዜጠኛ በደስታ-ሐዘን፤አቃርጠዉታል።ኢንጂነሩን በቁጭት ለሌላ አብዮት አዝቶታል።ለሌሎችስ? የማይዳኑ አብዮት አደኛ ዓመት መነሻ፤ ሒደት፤ ዉጤት፤ አስተጋብኦቱ መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

ጥንታዊ ናት።ሰዉ ከሰፈረባት ከ44 ሺሕ ዘመናት በላይ አስቆጥራለች።ከሥልጣኔ ምንጮች አንዷ ናት።ሰዉ ፈረስን ለቤት እንስሳት ገርቶባትል።ዛሬ ከስሜንና ከምሥራቅ ለምታዋስናት ሐያል ጎረቤትዋ-ሥልጣኔን ብቻ ሳይሆን መጠሪያ ስሟንም አጋርታለች።ሩሲያ-የሚለዉ ሥም የወጣዉ-ዩክሬን እስከ 16ኛዉ መቶ ክፍለ-ዘመን ትጠራበት ከነበረዉ ኪየቭ-ሩስ ከሚለዉ ስሟ ነዉ።ገናንም ነበረች።ርዕሠ-ከማዋ ኪየቭ በዘጠነኛዉ እና ባስረኛዉመቶክፍለ-ዘመናት የምሥራቅ አዉሮጳ የፖለቲካና የባሕል ማዕከል ነበረች።

ጥንታዊነት፤ የስልጣኔ ምጭነት፤ የድሮ ገናናነት እንደዛሬዎቹ ቻይኖች፤ ቱርኮች፤ሕንዶችከዉድቀት ለመነሳት ለሚፍጨርጨር ትዉልድ ታሪካዊ-መሠረት፤ በራስ የመተማመን ሥነ ልቡናዊ ጉልበት፤ መንፈሳዊ ብርታት ሊሆን ይችላል፤ ታሪክ-አፈታሪክን እየጠረቁ ነበርን ሙጥኝ ላሉ-ግን እንደ ኢትዮጵያ መደሕያ፤ እንደ ሞንጎሊያ ማንቀላፊያመሆኑ አይቀርም።ለሚጃጃሉት ደግሞ እንደ መካከለኛዉ ምሥራቅ-የመተላለቂያ ሰበብ ምክንያት።

ዩክሬን እርግጥ ነዉ-እንደ መካከለኛዉ ምሥራቅ ለዝንተ-ዓለም ባይቀጥልም ባሁኑ ወቅት ግጭትን ታስታግዳለች።ከሁሉም ይበልጥ ምዕራብና ምሥራቅን በየዘመኑ ታሻኩታለች።ዛሬም ብሶባታል።

Ukraine Euromaidan Gedenken 21.11.2014
ምስል picture-alliance/dpa/Tatyana Zenkovich

«ሐገራት የጎረቤቶቻቸዉ ዉሳኔ ሥላላስደሰታቸዉ ብቻ፤ ድንበርን ዳግም ማካለል እና በጦር ሐይል ጣልቃ መግባት በ21ኛዉ ክፍለ-ዘመን አዉሮጳ ዉስጥ፤ ሌላም ሥፍራ ቢሆን ተቀባይነት የለዉም።ይሕ እስከቀጠለ ድረስ ሩሲያ የሚደርስባት ኪሳራ እና መገለል ይጠናከራል።»

የዩናይትድ ስቴትሱ ምክትል ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን።ኪየቭ ባለፈዉ አርብ።የሩሲያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አፀፋ-የቃላት ምት ምዕራባዉያንን«አትቃዡ» የሚል ዓይነት ነበር።«ምዕራባዉያን (በሩሲያ ላይ የሚወስዱትን) ቆንጣጭ ርምጃ በተመለከተ የሩሲያ ፌደሬሽንን መርሕ የመቀየር ዓላማ እንደሌለዉ ግልፅ አድርገዋል።-ይሕ በራሱ ቅዠት ነዉ።የሥርዓት ለዉጥ ለማድረግ ይፈልጋሉ።ይሕንን ማንም አይክድም።»

የዩናይትድ ስቴትሱ ምክትል ፕሬዝዳንት ሩሲያን ዳግም ለማስጠንቀቅ ኪየቭ ድረስ የሔዱት አፍቃሬ ምዕራባዉያን ፖለቲከኞች ያደራጁት አብዮት ወይም አመፅ በተጀመረበት አንደኛ ዓመት ክብረ-በዓል ላይ ለመገኘት ነበር።የኪየቮች ታላቅ እንግዳ በዓሉ በይፋ በሚከረበት የነፃነት አደባባይ (ማይዳን) ለመገኘት የነበራቸዉ ዕቅድ ግን ሠረዙ።ምክንያት-ተቃዉሞ ሥለገጠማቸዉ።ፕሬዝዳንት ፔትሮ ፖሮሼንኮ ግን ተቃዉሞዉን ከመጋፈጥ ሌላ ምርጫ አልነበራቸዉም።

«ለተሰዉት ምን ተደረገ----አሳፋሪዎች---ለዩክሬን ምንአደረጋችሁ።»

ተቃዋሚዎቹ በአብዮቱ ሒደት የተገደሉ ሰዎች ቤተሰቦች ናቸዉ።ፖሮሼንኮ ተቃዉሞዉን ሽሽት ቀዝቀዝ ባለ ሥርዓት አበባ ጉጉን አኑሮዉ ምንም ሳይተነፍሱ ካካባቢዉ ፈትለክ አሉ።ከአንድ መቶ የሚበልጡ ሰልፈኞችን የገደሉት ወገኞች ማንነት እስካሁን አልተጣራም።ገዳዮች ለፍርድ አልቀረቡም።የሟች ቤተሰቦችም ካሳ አላገኙም።ከንቱ ደም።ምናልባትም የሌላ አመፅ-ተቃዉሞ ሰበብ።

የዩክሬን መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ ሥልታዊ ነዉ።ወደ ሜድትራንያንባሕር ለመዉረድ፤ ወደ ሰሜን-ምሥራቅ ለመዉጣት ጠቃሚ ናት።ከምሥራቅ አዉሮጳ ወደ መካከኛዉና ሩቅ ምሥራቅ እስያ ለመሻገርም አመቺ ናት።ካንዱ ወደሌላዉ መተላለፊያ ነት-እንደ ስዊዘርላንድ ለታደለ መክበሪያ፤ እንደ ፓናማ አንገቱን ለደፋ መተዳደሪያ ነዉ።

ከሁለቱ አንዱን ላላወቀ፤ ወይም ላልታደለ ግን የጡንቸኞች መጓሸሚያ፤ የሕዝብ እልቂት ነዉ-ትርፉ።ዩክሬን እንዲያ ነበረች።ነችም።

Ostukraine Angriffe 1.8.2014
ምስል picture-alliance/dpa

«ከ2001 ጀምሮ ኔቶ-ሁለት የመስፋፋት ማዕበሎች አስነስቷል።ማለቴ በ2004 የኔቶ ማዕበል ሰባት ሐገራትን አጥለቅልቋል።ስሎቬንያ፤ስሎቫኪያ፤ቡልጋሪያ፤ሩሜንያ እና ሰወስቱ የቦልቲክ ሐገራት፤-ኢስቶኒያ፤ላቲቪያ፤ሉቱዌኒያን።በ2009 ደግሞ ኔቶ ሁለት ተጨማሪ ሐገሮችን አባሉ አድርጓል።ይሕ የመልከዓ-ምድራዊ ፖለቲካዊ ሚዛኑን በእጅጉ ለዉጦቷል።»

የሩሲያዉ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን።በምዕራባዉያን የሚደገፉት የዩክሬን አብዮተኞች ሥልታዊቱን ሐገር ከሩሲያ ጉያ መንጭቀዉ ከምዕራቡ እጅ ሲዶሉ-ሞስኮዎችን «ምን ተረፈን» ማሰኘቱ አልቀረም።ብለዉ አልቀሩም ትልቂቱን ሐብታሚቱን ግዛት ክሪሚያን ከዩክሬን አስገንጥለዉ ከሩሲያ ቀየጡ።

የኪየቮች-ቁጣ የምዕራባዉያን ዛቻ ሲነጠናከር ደግሞ አብዮቱ ያስከፋቸዉን የምሥራቅ ዩክሬን አማፂያንን ይደግፉ ገቡ።

ምዕራባዉያን ባንፃሩ የጦር ሐይል፤የገንዘብ፤ የዲፕሎማሲ ድጋፋቸዉን ለአዳዲሶቹ የኪየቭ መሪዎች ያንቆረቁሩ ያዙ፤ አሜሪካ መራሹ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጦርም ሩሲያ ድንበር አካባቢ ይርምሰመስ ገባ።

የዋሽግተን ብራስልስ ጠንካራ የገንዘብ ጡንቻ በሩሲያ ምጣኔ ሐብት ላይ አረፈ።ማዕቀብ።የተጨማሪ እርምጃ ዛቻ-ማስጠንቀቂዉ ዛሬም አላባራ።እንደገና ምክትል ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን።«ሕገ ወጥ የጦር ክምችትን፤ የጦር መሳሪያና ተዋጊዎችን አሁኑኑ ያንሱ፤ታጋቾችን በሙሉ ያስለቅቁ።ይሕ የሚስተር ፑቲን ሐላፊነት ነዉ።እስካሁን ግን አንዱም አልተፈፀመም።»

ባይደንመንግስታቸዉ ለኪየቭ መንግሥት ተጨማሪ ወታደራዊ እርዳታ እንደሚስጥም ቃል ገብተዋልም።ለምሥራቅ ዩክሬን ሕዝብ ግን አንዱም የተከረዉ የለም። ግዛቱ ወድማለች።ከአራት ሺሕ የሚበልጡ ወገኖቹ ሞተዋል።ብዙ ሺዎች አካላቸዉ ጎድሏል።ሌሎች ከቤት ንብረታቸዉ ተፈናቅለዋል።

የአምናዉ ጋዜጠኛ ሙስጠፋ ነየም ያቺ ፅሁፉ «ዉለታ» ሆናዉ ዛሬ የምክር ቤት እንደራሴ ነዉ።የተከበሩ የፓርላማ አባል።ለዚሕ ማዕረግ በመቃታቸዉ በአብዮቱ ዉጤት ደስተኛ ናቸዉ።የዩክሬን ገሚስ ግዛት በጦርነት በመዉደም መመሰቃቀሉ ግን- ያዝናሉ።

«ዉጤቱ ትንሽ ቢሆንም ዋናዉ ጉዳይ በየትኛዉ አቅጣጫ መጓዝ እንዳለብን መወሰን መቻላችን ነዉ።ዩክሬን ከእንግዲሕ በሌለኛዉ አቅጣጫ አትጓዝም።ሥለሌላዉ አጠቃላይ ጉዳይ ለመናገር ጊዜዉ ገና ነዉ። አለመታደል ሆኖ የማይዳኑ ንቅናቄ ጦርነት አስከትሏል።አሁን የሚታየዉ በሙሉ የዚሕ አሳዛኝ ጦርነት ዉጤት ነዉ።»

ማርና ሬት።

Ukraine Flüchtlinge
ምስል DW/F.Warwick

ዩክሬን፤ አየሯ ተስማሚ ነዉ። ተራራን፤ ከሜዳ ያጣመረች።ለእርሻም፤ ለኢንዱስትሪም የተመቸችነች።ከርሰ-ምድሯ የብረት፤የከሰል፤ የታንታነም፤ የሜርኩሪ የሌሎችም ማዕዳት ቋት ነዉ።ተስማሚ አየር የተፈጥሮ ሐብት እዉቀት-ብልሐት ከታከለበት እንደ ብራዚል፤ሩሲያዎች መበልፀጊያ፤ መጎልበቻ ነዉ።ስግብግብ-አጎብዳጆች ከተቆጣጠሩት ግን እንደ አረቦች አንድም የገዢዎች አለያም የገዢዎቹ ገዢዎች መንደላቀቂያ፤ ወይምእንደ ናጄሪያ መተላለቂያ ነዉ-የሚሆን።

ሶቭየት ሕብረት ተፈረካክሳ ነፃነቷን ካወጀች ወዲሕ የዩክሬን ሐብት፤ ንብረት በሙስና የተዘፈቁ ባለሥልጣናት መንደላቀቂያ፤ የብልጣብልጥ ነጋዴዎች፤ የጮሌ ደላሎች መበልጸጊያ እንጂ ለአብዛኛ ሕዝቧ የተረፈ የለም።25 ዓመት። ዛሬም አልተለወጠም።

የጥንታዊቱ፤ የታሪካዊቱ፤ የሥልታዊቱ፤ የሐብታሚቱ ሐገር ሕዝብ ግን በአንድ ነገር ከብዙ ብጤዎቹ ይለያል።አመፅ።አቀማመጥ ሐብቷ አማልሎት ሐገሩን የተቆጣጠረ የዉጪ ሐይልን ይሁን፤ የራሱ ገዢዎች የሚያደርሱበትን ግፍ በደል በመቃዉም ሁሌም ያምፃል።አመፅ ተቃዉሞዉን የሚያጋግምለት ሐይልም-ሁሌም አያጣም።

ዳሲያኖች፤ሰመሪያኖች፤ ግሪኮች፤ታይረሶች፤ሮሞች፤ ቤዛንታኖች፤ሞንጎሎች፤ቱርኮች፤ ካዛክስታኖች አዘርበጃኖች፤ ሩሲያዎች፤ ፖላንዶች በየተራ በተፈራረቁበት ቁጥር ያ ሕዝብ ያለመፀበት-ወይም የገዢዉ ጠላት አዲስ ገዢ ለመሆን አመፅ ያላቀጣጠሉበት ጊዜ አልነበረም።

የዩክሬን ሕዝብ ሐገሩን ከ1569 ጀምሮ በተቆጣጠሩት በካቶሊኮቹ የፖላንድ-ሉቱዌንያ ጥምረት አገዛዝ ላይ-በ1653 ሲያምፅ-የሩሲያ ኦርቶዶክስ ገዢዎች ሁለንተናዊ ድጋፍ አልተለየዉም ነበር።አመፁ በሩሲያ በሚደገፉት ሐይላት ድል ሲጠናቀቅን ግን ሐገሪቱ የሞስኮዎች ጥገኛ ሆና ቀረች።

በ1853 ካቶልክና ፕሮቴስታቶቹ ብሪታንያ፤ፈረንሳይ፤ሳርዲንያ (ኢጣሊያ) ከሙስሊሚቱ ቱርክ ጋር አብረዉ ከኦርቶዶክሶቹ ሩሲያ፤ግሪክና ሠርቢያ ጋር ክሪሚያ የገጠሙት ጦርነት-የፖላንዶችን ሽንፈት ለመበቀል ነበር።ጦርነቱ እስከዚያ ዘመን ድረስ ከነበረዉ ጦርነት ሁሉ እጅግ አስከፊ ነበር።ዩክሬንን ከሩሲያ ጉያ መፈልቀቅ ግን አልተቻለም።

እንዲያዉም በ1917ቱ የሩሲያ አብዮት ማግሥት ያቺ ሐገር የሶቭየት ሶሻሊስ ሪፕብሊክ ፌደሬሽንን ተቀይጣ ሙሉ በሙሉ በሞስኮ የብረት መቀነት ተቋጠረች።-ከ1945 እስከ 1989 ድረስ እንደ ዩክሬን ሁሉ በሞስኮ ተፅዕኖ ሥር የነበረችዉ የቀድሞዋ የዩክሬን ካቶሊካዊት ገዢ ፖላንድ ዛሬ ሠልፏን ከምዕራቦች ጋር አሳምራ-ሞስኮዎችን አዉጋዥ-ኮናኝ ሆናለች።ዉጪ ጉዳይ ሚንስር ራዶስላቭ ዚኩርቭስኪ ግንባር ቀደሙ ናቸዉ።

Ostukraine Angriffe 31.7.2014
ምስል picture-alliance/dpa

«ከክሬምሊን የተሰጠዉን መግለጫ በይፋ ከመዉጣቱ በፊት አይተነዉ ነበር።ፕሬዝዳንት ፑቲን ከችግር ማምለጫ ታክቲክ የሚጠቀሙ ፖለቲከኛ መሆናቸዉን መዘንጋት የለብንም።ችግራቸዉ እኛ በሳቸዉ ላይ እምነት ማጣታችን የሚስከትልባቸዉን ኪሳራ አሳንሰዉ ማየታቸዉ ነዉ።

ከቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍፃሜ ወዲሕ በተለያዩ ሐገራት የተለያዩ የአደባባይ ሠልፍ-አመፆች ተደርገዋል።አስር ዓመት ባልሞላ ጊዜ ሁለት መንግሥት በአደባባይ አመፅ የፈረሰባት ሐገር ግን አንድ ናት።ዩክሬን።ዛሬም ቢያንስ ምሥራቃዊ ግዛቷ ደም በሚያራጭ አመፅ እየወደመች፤ ምስራቅ ምዕራቦችን ከ25 ዓመት በኋላ ዳግም እንዳፋጠጠች ነዉ።

ለአማፅ የማይቦዝነዉ ሕዝብ ኪየቭንም ላይ አልተረጋጋም።ኢንጂነር ፔትሮ-ሩንኪቭ አንዱ ናቸዉ።የ58 ዓመቱ መሐንዲስ አምና ይኸኔ እነ ጋዜጠኛ ሙስጠፋ በፃፉት ማስታወቂያ ተማርከዉ ባለቬታቸዉን፤ልጆቻቸዉን ሥራቸዉንም ትተዉ ከምዕራባዊ ዩክሬን ኪየቭ የከተሙ ተቃዋሚ ነበሩ።የአመፁ አንደኛ ዓመት በቀደም ሲከበር ግን «ተበሳጭተናል።» አሉ ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬሱ ጋዜጠኛ«ምንም አልተለወጠም። እዚሕ የመጣነዉ ለመንግሥታችን ለማሳሰብ ነዉ።ለዉጥ ካልተደረገ አስጠነቀቁ መሐንዲሱ «ሌላ ማይዳን (አመፅ) እንጠራለን።»ዉላጅ፤ ዘመድ-ወዳጅ የሞተባቸዉን ቅሬታ ሲታከል---የዩክሬን ጉዞ፤ የቀድሞ-ጋዜጠኛ የዛሬ እንደራሴዋ ባሉት አቅጣጫ-ይቀጥል ይሆን? ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ