1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዩክሬን ዉዝግቧና ምጣኔ ሐብቷ

ሐሙስ፣ መጋቢት 25 2006

«ዩክሬን ለወደፊቱ የትልቅ ገበያ ትስፋ አላት።»ተስፋዉ በርግጥ አማላይ ነዉ። የዩክሬን እዉነታ ከሚባለዉ መቃረኑ እንጂ ቀቢፀ-ተስፋዉ። የዩክሬን ሕዝብ የነብስ ወከፍ ገቢ የሞንጎሊያን እንኳን አያክልም። 3800 ዶላር። ኢንዱስትሪዎችዋ-አሮጌ ናቸዉ። ብልጣብልጥ፤ አታላይ፤አጭርበርባሪ ነጋዴ ፤ደላላ፤ ባለሥልጣናት ከብረዉባታል።

https://p.dw.com/p/1BbK4
ምስል picture-alliance/ITAR-TASS

ዩክሬንን በበላይነት ለመቆጣጠር ሩሲያና ምዕራባዉያን ሐገራት የገጠሙት ዉዝግብ እና አንዱ ሌላዉን የመቅጣት እርምጃ አሁንም እንደቀጠለ ነዉ። የሁለቱ ተቀናቃኝ ሐይላት ሽኩቻ የሥልታዊቱን ሐገር ምጣኔ ሐብታዊ፤ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ጉዞ አነጋጋሪ አድርጎታል። ካለፈዉ የካቲት ወዲሕ የኪየቭን የመንግሥትነት ሥልጣን የያዙትን ሐይላት የሚደግፉት ምዕራባዉያን ሐገራት የዩክሬንን ምጣኔ ሐብት ለመጠገን በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ዩሮ ማዉጣት አለባቸዉ። ሩሲያ ባንፃሩ ለዩክሬን በምትሸጠዉ ጋዝ ላይ የ 44 በቶ ጭማሪ አድርጋለች። ፖለታካዊዉ አለመረጋጋት፤ ወታደራዊ ፍጥጫም እንደቀጠለ ነዉ። መፍትሔዉ ምን ይሆን?-ይጠይቃል የአሎይስ ቤርገር ዘገባ።

የርዳታ-ብደሩ ቃል ከብራስልስ-ዋሽግተን ወደ ኪየቭ ይጎርፋል። የአዉሮጳ ሕብረት 1,6 ቢሊዮን ዩሮ ዩናይትድ ስቴትስ ስምንት መቶ ሚሊዮን ዩሮ፤ የዓለም ገንዘብ ድርጅት ከ15 እስክ 18 ቢሊዮን ዶላር እንስጣለን እያሉ ነዉ። ምዕራባዉን ለዩክሬን የሚረዱ-የሚሰጡትን የገንዘብ መጠን ሥታሠላ የቆየችዉ ሞስኮ ባንፃሩ ለዩክሬን በምትሸጠዉ ጋስ ዋጋ ላይ ባንዴ-44 ከመቶ ጭማሪ አድርጋለች።

የምዕራባዉያኑ ዓላማ ዩክሬንን ከሩሲያ ጥገኝነት ለማላቀቅ ከሆነ ለጋስ መግዢያ ተጨማሪ ገንዘብ መመደብ፤ በተዘዋዋሪ እንደ«ጠላት» ለሚያዩዋት ሞስኮ አዲስ የጋዝ ገበያ መክፈት ግድ ይላቸዋል፤ ያዋጣ ይሆን?

Ukraine Minensuchboot Donuslaw Versuchter Ausbruch
ምስል picture-alliance/ITAR-TASS

«46 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ዩክሬን ጠቃሚ (ገበያ) አላት። ለጀርመን የአዉቶሞቢል ኢንዱስትሪም የተለያዩ መሳሪዎች አቅራቢም ናት።» ይላሉ በኪየቭ የጀርምን የኢኮኖሚ መልዕክተኛ፤ አሌክሳንደር ማርኩስ። በአዉሮጳ ሕብረት ምክር ቤት የሊብራል ፓርቲ ተወካይ አልክሳንደር ግራፍም በሐገራቸዉ ልጅ አባባል ይስማማሉ።

«ዩክሬን ለወደፊቱ የትልቅ ገበያ ትስፋ አላት።»ተስፋዉ በርግጥ አማላይ ነዉ። የዩክሬን እዉነታ ከሚባለዉ መቃረኑ እንጂ ቀቢፀ-ተስፋዉ። የዩክሬን ሕዝብ የነብስ ወከፍ ገቢ የሞንጎሊያን እንኳን አያክልም። 3800 ዶላር። ኢንዱስትሪዎችዋ-አሮጌ ናቸዉ። ብልጣብልጥ፤ አታላይ፤አጭርበርባሪ ነጋዴ ፤ደላላ፤ ባለሥልጣናት ከብረዉባታል።

ሶቪየት ሕብረት የዛሬ ሃያ ዓመት ግድም በተፈረካከሰች ማግሥት መንግሥት ይቆጣጠራቸዉ የነበሩ የማምረቻና የማከፋፋያ ተቋማት ወደ ግል ይዞታ ሲለወጡ ተቋማቱን በርካሽ የገዙ፤ ወይም ባቋራጭ የያዙ ጥቂት ሰዎች ዛሬ የሐገሪቱን ምጣኔ ሐብት ብቻ ሳሆን ፖለቲካዉንም ባሻቸዉ ዘዋሪ ናቸዉ። ነፃ ዉድድርን ዘግተዉታል። የጀርመኑ የዓለም ምጣኔ ሐብት ጥናት ተቋም ተመራማሪ ራይነር ሽቫይከርት እንደሚሉት የጥቂቶችን አድራጊ ፈጣሪነት ለማስቀረት መንግሥት የነፃ ዉድድርን ሕግ መደንገግ ብቻ ሳይሆን፤ በጥብቅ መቆጣጠርም አለበት።

«ምክንያቱም ለምጣኔ ሐብቱ ዕድገት አብይ አስተዋፅኦ የሚያደርጉትን መካከለኛና አነስተኛ ተቋማትን ማስፋፋትና ማጠናከር የሚቻለዉ በዚሕ መንገድ ብቻ ነዉ።»

ዩክሬን በምግብ እህል ምርት ከዩናይትድ ስቴስና ከአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት ቀጥሎ ከዓለም ሰወስተኛዉን ደረጃ የያዘች ናት። ይሁንና ምዕራባዉያኑም ሆኑ ሩሲያ እራሳቸዉ በገፍ የሚመርቱትን ስንዴ ከዩክሬን ለመግዛት የሚሻሙበት ምክንያት ብዙም የለም። አንድ ጠቃሚ ነገር ግን አላት። የጦር መሳሪያ ኢንዱስትሪዋ። ከሶቪየት ሕብረት የወረሰችዉ በተለይም የሔሊኮፕተር ሞተሮች ማምረቻ ኢንዱስትሪዎችዋ ለሩሲያ በጣም ጠቃሚ ናቸዉ። አብዛኞቹ የሩሲያ ተዋጊ ሔሊኮፕተሮች የዩክሬን ሞተር የተገጠመላቸዉ ናቸዉ። የይክሬኑ የምጣኔ ሐብት አማካሪ ቦሪስ ኩሽኒሩክ ሩሲያ የዩክሬንን የጦር መሳሪያ ቁሳቁሶች ካጣች ጦሯ መተኮስም መብረርም አይችልም ባይ ናቸዉ።

«በጦር መሳሪያዉ ምርት ከዩክሬይን ጋር ተባብሮ መሥራቱ ለሩሲያ ጠቃሚ ነዉ። አለበለዚያ ካለዩክሬን የሩሲያ ጦር መብረርም መተኮስም አይችልም።»

Symbolbild Russland Krim Krise
ምስል picture-alliance/dpa

ሞስኮ-ሥልታዊቷን፤ የጦር ማከማቻ፤ ማስፈሪ፤ የጦር ጀልባና መርከብ ማምረቻይቷን ግዛት ክሪሚያን ከቀላቀለች ወዲሕ የኩሽኒሩክ ትንታኔ-ሰሚ የለዉም። በክሪሚያ ሠበብ የሞስኮና የኪየቭ ወታደራዊ ትብብር ተቋርጧል። ኩሽኒሩክ «መተኮስም፤ መብረርም አይችልም» ካሉት የሩሲያ ጦር 40 ሺሕዉ ከተረፈችዉ ዩክሬን ድንበር ላይ ለዉጊያ እየተለማመደ፤ ጠመንጃዉን-እንደወደረም ነዉ።

የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጦር አዛዥ ጄኔራል ፊሊፕ ብሪድላቭ ትናንት እንዳሉት የሩሲያ ጦር ከክሬሚሊን ከታዘዘ በአስራ-ሁለት ሰዓታት ዉስጥ የዩክሬንን ጦር ደፍልቆ-አድርግ የተባለዉን ማድረግ ይችላል። ኔቶ ዩክሬንን አባል ማድረጉን ያልፈለገዉም የክሬምሊኖች ቁጣ ከእስካሁኑ በላይ ከናረ-መዘዙን ሥለሚያዉቀዉ ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ

 

 

 

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ