1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዩጋንዳ ምርጫና ዉዝግብ

ሐሙስ፣ የካቲት 24 2008

በዩጋንዳ ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ እንዳሸነፉ የተገለፀበት ምርጫ ዉዝግብ ወደፍርድ ቤት ሊያመራ መሆኑ እየተነገረነዉ። የሙሴቪኒን የ30 ዓመታት የስልጣን ጉዞ ለመግታት ያለሙት ተፎካካሪያቸዉ ኪዛ ቤሲጄ ተፈፅሟል ባሉት ማጭበርበር ምክንያት መንግሥት ዉጤቱን የሚፈትሽ ገለልተኛ አጣሪ ኮሚቴ እንዲሰይም ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ጫና እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

https://p.dw.com/p/1I6b3
Uganda Präsidentschaftswahlen Kizza Besigye
ምስል Reuters/E. Echwalu

[No title]

በዩጋንዳ ፖለቲካ ታሪክ ከጎርጎሪዮሳዊዉ 1970ዓ,ም ጀምረዉ በንቃት ተሳትፈዋል። በኢዲ አሚን ዘመነ ስልጣን በስደት የቆዩት ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ አሚንን ለመገልበጥ በተካሄደዉ ንቅናቄም ተካፍለዋል። ሚልተን ኦቦቴ ሥልጣን ከመያዛቸዉ አስቀድሞ በተቋቋመዉ የሽግግር መንግሥት የመከላከያ ሚኒስትር ሆነዉ ያገለገሉት ሙሴቪኒ ከኦቦቴ ጋር ባለመስማማታቸዉ ለአምስት ዓመታት በአማፂነት ዱር ቤቱ ብለዉ ተዋግተዋል። በጎርጎሪዮሳዊዉ 1986 ካምፓላን ተቆጣጠሩና የፕሬዝደንትነት መንበሩንም ያዙ። ከዚያን ጊዜ አንስተዉም ምርጫ በተካሄደ ቁጥር የሚያሸንፉት እሳቸዉ ናቸዉ። ዘንድሮም ደገሙት፤ ለቀጣይ አምስት ዓመታትም የዩጋንዳ ፕሬዝደንት እንደሆኑና እንደተባሉ ሊቀጥሉ። የዩጋንዳ ብሔራዊ የምርጫ ኮሚሽን ሙሴቪኒ በ61 በመቶ ድምፅ ማሸነፋቸዉን የቅርብ ተፎካካሪያቸዉ ቤሲጄም 35 በመቶ ድምጽ አግኝተዉ ሁለተኛ መሆናቸዉን ይፋ አድርጓል። ዉጤቱን እንዳተቀበሉት በይፋ ያስታወቁት ቤሲጄ አቤቱታቸዉን ለፍርድ ቤት አቀርባለሁ እያሉ ነዉ። አቤታቸዉን ለማቅረብ የሚረዳቸዉን መረጃ በእጃቸዉ ለማስገባት ግን ከምርጫዉ ዕለት አንስቶ ከቤታቸዉ እንዳይነቃነቁ በቁም እስር ላይ መሆናቸዉ እንቅፋት እንደሆነባቸዉ ተገልጿል። ጉዳዩን ወደፍርድ ቤት ለመዉሰድ ተፈላጊዉን ማስረጃ ማሰባሰብ ባይቻል እንኳ በሰላማዊ መንገድ ዉዝግቡን ለመፍታት የምርጫ ዉጤቱን የሚያጣራ መርማሪ ኮሚቴ እንዲሰየም መድረክ ለዴሞክራሲያዊ ለዉጥ የተሰኘዉ ፓርቲያቸዉ ፕሬዝደንት ሙጊሻ ሙንቱ ጠይቀዋል።

Uganda Wahlen 2011 Yoweri Museveni
ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቪኒምስል Getty Images

«ለየካቲት አስሩ ምርጫ ገለልተኛ መርማሪ ኮሚቴ እንዲቋቋም እንጠይቃለን። የምርጫ ኮሚሽኑ በገለፀዉ ዉጤት እና እኛ ከመላ ሀገሪቱ ባሰባሰብነዉ መካከል ግልፅ ጉልህ ልዩነት አለ። በሀገሪቱ ተሸንፈዋል የተባሉት ፕሬዝደንታዊ እጩ ማሸነፋቸዉን የሚያሳዩ ሁኔታዎች አሉን። ይህም በገለልተኛ መርማሪ ብቻ ነዉ በሰላማዊ መንገድ ሊፈታ የሚችለዉ።»

በሌላ ወገን ተመሳሳይ ጥያቄ የቀረበዉ በምርጫዉ መሸነፋቸዉ ከተገለፀዉ የፓርቲዉ እጩ አማማ ማባባዚ ሲሆን እሳቸዉ በሰዓቱ ይህን የሚያሳይ ፊርማ አሰባስበዋል። የማባባዚ ጠበቃ ሴቬሪኖ ትዊኖቡሲንጌ እንደሚሉት አቤቱታቸዉ፤ የሙሴቪኒ እጩ ተወዳዳሪዎች መራጮችን በጉቦ ደልለዋል፤ የምርጫ ዉጤቱም ወደምርጫ ኮሚሽን የደረሰዉ ግልፅ ባልሆነ ስልት ነዉ የሚል ነዉ።

«ለምሳሌ ጉቦን በተመለከተ ተናግሬያለሁ፤ ለመሆኑ እንዴት 18 ሚሊየን መቆፈሪያ ለመራጮች በነፃ አከፋፍላለሁ ይባላል? ዉጤቶች የሚሰባሰቡበት ማዕከል ሳይኖር እንዴት ነዉ ዉጤቱን ለቅሜያለሁ ማለት የሚቻለዉ? እንዲህ ያሉትን ጉዳዮች ነዉ ለፍርድ ቤት ሰጥተው እንዲያብራሩ የምንፈልገዉ። እነዚህ ሁሉ የተፈፀሙ ወንጀሎች እና ከሕጉ ጋር የማይጣጣመዉ አካሄድ ዉጤቱ ላይ ተፅዕኖ አድርጓል፤ በዚህ ምምክንያት ፍርድቤቱ ሊሰርዘዉ ይገባል።»

የዩጋንዳ የፍትህ ሚኒስቴር የበላይ አካል ይህን አቤቱታ የሚያዳምጡ እና የቀረበዉን መረጃ የሚመረምሩ ከፍተኛ ዳኞች የተካተቱበት ቡድን ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ ዩጋንዳዉያን ኪዛ ቤሲጄ ላይ ይፈጸማል ባሉት ያልተገባ አያያዝ ምክንያት ባለስልጣናቱን ተችተዋል። በተለይም ፖሊስ ከቤታቸዉ እንዳይወጡ በቁም እስር ማቆየቱ ፖለቲከኛዉ ለፍርድ ቤት የሚያስፈልጋቸዉን መረጃ እንዳያሰባስቡ እንቅፋት ስለሆነባቸዉ ማዘናቸዉንም ገልጸዋል።

Uganda Mbabazi Anwälte Registrierung Petition
ማባባዚ አቤቱታቸዉን ሲያቀርቡምስል DW/E. Lubega

«የተያዙበት ሁኔታ፤ እንዳይንቀሳቀሱ መታገዳቸዉ፤ በቤታቸዉ ብቻ መገደባቸዉ፤ በዚያም ላይ ፖሊስ በየተራ ምክንያት እየመጣ እንዳይወጡ ማገዱና የመሳሰሱት ሁሉ አሉ፤ እናም ተንቀሳቅሰዉ ጉዳዩን ካላሰባሰቡ እንዴት አድርገዉ ነዉ ለፍርድ ቤት መረጃ ማቅረብ ይችላሉ?»

«ዉጤቱ በወጣ ጊዜ ምርጫዉ ነፃ እና ፍትሃዊ እንዳልነበረ በጣም ይሰማን ነበር። ስለዚህ ሁላችንም ጉዳዩን ወደሕግ ይመሩታል የሚል ተስፋ ነበረን፤ ምክንያቱም ማንም በዚህች ሀገር ጦርነት አይፈልግም። ወደሕግ ጉዳዩን ማቅረብ ሳይቻል ሲቀር አስደንጋጭ ነዉ የሆነዉ። ትልቁ ጥያቄ ቀጣዩ ምንድን ነዉ የሚል ነዉ።»

«መንግሥት ቤሲጄ መዋቅሩ እና ድጋፉ ስላላቸዉ በቂ መረጃዎች ሰብስበዉ አቤቱታቸዉን እንዳያቀርቡ እና ከፍተኛ ፍርድ ቤቱም የሙሴቪኒን ድል እንዳይሰርዝ መንግሥት የተጠቀመበት ስልት ነዉ ብዬ አስባለሁ።»

በርካታ የሲቪል ድርጅቶች ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቪኒም ሆኑ ተቀናቃኛቸዉ ኪዛ ቤሲጄ ይህን ዉዝግብ ለመፍታት ሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲጠቀሙ ጥሪ እያቀረቡ ነዉ። በዚህ ምርጫ ተወዳድረዉ መሸነፋቸዉን የተቀበሉት ሌሎቹ እጩ ተፎካካሪዎችም ዉይይት እንዲካሄድ እያሳሰቡ ነዉ።

አሌክስ ጊታ/ ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ