1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

'ያተኮሰው' የእስራኤል ምክር ቤት ምርጫ

ሰኞ፣ መጋቢት 7 2007

120 መቀመጫዎች ላሉት እና 'ክነሰት' በመባል ለሚታወቀው የእስራኤል ምክር ቤት ነገ ምርጫ ይካሄዳል።በምርጫው 26 የፖለቲካ ፓርቲዎች ይሳተፋሉ። ለረጅም አመታት ስልጣን ላይ የቆዩት ቤኒያሚን ኔታንያሁ ከስልጣንና ከፓርቲ ካባረሯቸው ዚፒ ሊቭኒ እና ከኢዝሃቅ ሄርዞግ ጠንካራ ፉክክር ገጥሟቸዋል።

https://p.dw.com/p/1ErhA
Israel Wahlen 2015 Netanjahu Rede in Har Homa
ምስል picture-alliance/epa/A. Sultan

ለስድስት ዓመታት የጠቅላይ ሚኒስትርነት መንበሩን የተቆናጠጡት ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ራሳቸውን እስራኤልን ከኢራን እና የእስልምና አክራሪዎች መታደግ የሚችሉ ብቸኛው ሰው አድርገው ይቆጥራሉ የሚል ትችት ይሰነዘርባቸዋል። ከ5.8 ሚሊዮን በላይ እስራኤላውያን በስልሳ አምስት አመቱ ፖለቲከኛ እጣ ፈንታ ላይ ሊወስኑ ነገ ድምጽ ይሰጣሉ። በነገው ምርጫ ሰውየው «ይሸነፋሉ» የሚል ቅድመ ትንበያ ቢሰማም በስልጣናቸው የመቆየት እድላቸው ግን የሰፋ ነው።

ባለፈው ሳምንት በተሰሩ ቅድመ ትንበያዎች ቤንጃሚን 'ቢቢ' ኔታንያሁ እና የሊኩድ ፓርቲያቸው ምርጫውን መንግስት መመስረት በሚያስችል ደረጃ ማሸነፍ አይችሉም። ዋንኛ ተፎካካሪያቸው ደግሞ በሌበር እና ሃትኑህ ፓርቲዎች ጥምረት የተፈጠረውና ኢዝሃቅ ሄርዞግ የሚመሩት ግራ-ዘመሙ የጽዮናውያን አንድነት ትብብር ነው። ትብብሩ ምርጫው አሸንፎ መንግስት ከመሰረተ ከአራት የስልጣን ዘመናት ውስጥ ሁለቱን የሌበሩ ሄርዞግ ቀሪውን ሁለት አመታት ደግሞ የሃትኑህ ሊቀ-መንበር የሆኑት ዚፒ ሊቭኒ በጠቅላይ ሚኒስቴርነት ሊመሩ ወስነዋል። ትብብሩም ይሁን መሪው ኢዝሃቅ ሄርዞግ ከቀኝ ዘመሙ ኔታኒያሁ እና ፓርቲያቸው በተለየ ለማህበራዊ ፍትህ እና የእስራኤል ፍልስጤም ፍጥጫ ትኩረት ለመስጠት ማቀዳቸው ለተቀባይነታቸው ምክንያት ነው ተብሏል። ኢዝሃቅ ሄርዞግ ለአንገብጋቢው የቤት እጦት ጉዳይ መፍትሄ ለመስጠትም «የመኖሪያ ቤት እጥረትን መፍትሄ ሊያበጅለት የሚችለው ጠቅላይ ሚኒስትር ብቻ ነው። እንደ ጠቅላይ ሚኒስቴር የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለመቅረፍ ቃል እገባለሁ።»ብለዋል።

Israel Isaac Herzog Kandidat der Opposition
ምስል Reuters/R. Zvulun

የእስራኤል ክነሰት(ምክር ቤት) ምርጫን አስመልክቶ በተሰራው የቅደመ-ትንበያ መሰረት ግራ ዘመሙ የጽዮናውያን አንድነት ትብብር (Zionist Union )25 ወይም 26 መቀመጫዎችን ሊያገኝ ይችላል ተብሏል። የቤኒያሚን ኔታኒያሁ ሌበር ፓርቲ 21 ወይም 22 መቀመጫዎችን ያገኛል የሚል ቅድመ-ትንበያ ተሰምቷል። የሪፐብሊካን ፓርቲ አወዛጋቢ ግብዣ በአሜሪካን ምክር ቤት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብርን ከእስራኤል ደህንነት ጋር አገናኝተው ከተናገሩ በኋላ ያገግማሉ ተብሎ የነበረ ቢሆንም የተለወጠ ነገር የለም። ባለፈው ሳምንት መገባደጃ አርብ ቻናል 10 የተባለ የአገሪቱ የቴሌቭዥን ጣቢያ ይፋ ባደረገው ሌላ ቅድመ-ትንበያ የጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ሊኩድ ፓርቲ 20 መቀመጫዎችን ብቻ ያገኛል ብሏል። ይሁንና ሊኩድ ፓርቲ በአገሪቱ ምክር ቤት ምርጫ ቢሸነፍ እንኳ ከሌሎች የቀኝ ዘመም ፓርቲዎች ጋር በመሆን ጥምር መንግስት ይመሰርታል፤ቤኒያሚን ኔታኒያሁም በጠቅላይ ሚኒስትርነት ይቀጥላሉ ተብሏል። በምርጫው ተፎካካሪ የሚባሉት እና እጅጉን በተቃራኒ ጽንፍ የቆሙት ፓርቲዎች አንዱ ሌላውን ይከሳሉ። የሚያቆራቁሳቸው ጉዳይ ግን ከአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ይልቅ የውጭ ግንኙነት ሆኗል። ጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንን በእየሩሳሌም የዶይቼ ቬለ ወኪል ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤኒያሚን ኔታንያሁም ቢሆኑ በነገው ምርጫ ሽንፈት ሊገጥማቸው እንደሚችል አልሸሸጉም። ነገር ግን እስራኤል አለባት ከሚሉት የኢራን እና የእስልምና አክራሪዎች ስጋት መታደግ የሚችሉ ብቸኛ ሰው ራሳቸውን አድርገው ይቆጥራሉ ሲሉ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ። በሂብሪው ዩኒቨርሲቲ የኮምዩንኬሽን እና ፖለቲካ ፕሮፌሰር የሆኑት ታሚር ሼፈር ‘ለመሆኑ እስራኤል አሁንም ጠንካራ ሰው (strongman) ያስፈልጋታል?’ ሲሉ ይጠይቃሉ። ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ አስተያየታቸውን የሰጡት ፕሮፌሰር አሁን እስራኤል የምትፈልገው ከኔታንያሁ ይልቅ 'ግርማ ሞገስ ያለው ችግር ፈቺ መሪ' መሆኑን ተናግረዋል። ግን ደግሞ ኢዝሃቅ ሄርዞግ ያ ሰው ለመሆናቸው ማንም እርግጠኛ አይደለም። በቴላቪቭ የባርላን ዩኒቨርሲቲ ሃላፊ እና የፖለቲካ ተንታኙ ኢታን ጊልቦአ የሄርዞግን ነገር ከሚጠይቁት አንዱ ናቸው።

Israel Wahlkampf Netanjahu Plakate Banner
ምስል Getty Images/MENAHEM KAHANA

«የሄርዞግ ድምፅ ቀዝቃዛ ነዉ። ግርማ ሞገስም የላቸውም።ድምጻቸው ደካማ ነው።ንግግር በሚያደርጉበት ወቅት ለአድማጫቸው ስልጣናቸውንና በራስ መተማመናቸውን አያንፀባርቅም። ይንን ለማሻሻል ጥረት ያደርጉ የነበረ ቢሆንም ምንም ዓይነት መሻሻል አላየሁበትም»

ኢዝሃቅ ሄርዞግ እና ዚፒ ሊቭኒ ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በፍልስጤም ላይ ያላቸው አቋምም ሆነ የሚወስዷቸውን እርምጃዎች አጥብቀው የሚኮንኑ ፖለቲከኞች ናቸው። 'ቡጊ' በሚል ቅጽል ስማቸው የሚታወቁት ሄርዞግ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ፍልስጤማውያንን ችላ ብለዋል በማለት ይወቅሳሉ። ዚፒ ሊቭኒም ቢሆኑ አገራቸው ከፍልስጤም አስተዳደር ጋር በመተባበር ለዘመናት የዘለቀውን ቀውስ መፍታት አለባት በሚለው አቋማቸው ይታወቃሉ። የሁለቱ ፖለቲከኞች ተቀባይነት ማግኘት ችግሩን እንደማይፈታ ዜናነህ መኮንን ይናገራል።

በቴላቪቭ የባርላን ዩኒቨርሲቲ ሃላፊ እና የፖለቲካ ተንታኙ ኢታን ጊልቦአም ቢሆኑ ሄርዞግ እና የጽዮናውያን አንድነት ትብብር የፍልስጤምን ጉዳይ ከምርጫ ግብዓትነት ባለፈ በተግባር የሚለውጡት ነገር እንደሌለ ያምናሉ።

« ሄርዞግ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተመረጡ እስራኤል አዲስ ምዕራፍ መክፈት ትችላለች፤ዛሬ ከሌበር ፓርቲ ጠቅላይ ሚኒስትር ከተመረጠ ነገ ደግሞ ከፍልስጤማውያን ጋር መግባባት ይቻላል የሚለው ግምት በተለይ በአውሮጳውያን ዘንድ የሚታየው ተስፋ ሙሉ በሙሉ ውሸት ነው። ግምቱ በታሪክ ላይ ያልተመሰረተ እና ከግጭት አፈታት ጽንሰ ሃሳብ ፈጽሞ የራቀ ነው።»

ምርጫው ከመድረሱ በፊት በእስራኤል መገናኛ ብዙሃን የተሰሩ ቅድመ-ትንበያዎች ለቤኒያሚን ኔታንያሁ ራስ ምታት ሆነዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቅዳሜ ለት በፌስቡክ ማህበራዊ ገጻቸው የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን፤መንግስታዊ ያልሆኑ፤ድርጅቶች እና ከበርቴዎች ኢዝሃቅ ሄርዞግ እና ዚፒ ሊቭኒን ወደ ስልጣን ለማምጣት ከውጭ መንግስታት ጋር እያሴሩ ነው ሲሉ ወንጅለዋል። ዬድዮዝ አህሮኖዝ (Yedioth Ahronoth) የተባለውን ጋዜጣ እና አሳታሚውን ኖኒ ሞዘስ (Noni Mozes) በስም ጠቅሰው ከተቃዋሚዎቼ ጋር እያሴሩብኝ ነው ያሉት ኔታንያሁ ተባባሪ ያሏቸውን መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ሃገራት ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል። የፖለቲካ ተንታኙ ኢታን ጊልቦአ የቅድመ-ትንበያው በተለያየ መንገድ ሊቀየር እንደሚችል ይናገራሉ።

Israel Wahlkampf Zionistische Unionspartei Tzipi Livni
ምስል Getty Images/AHMAD GHARABLI

«አሁንም ከውሳኔ ያልደረሰ እና የሚንሳፈፍ ከፍተኛ የሆነ ድምጽ አለ። ይህ ከአጠቃላይ መራጮች ከ12 እስከ 15 በመቶ ይደርሳል። ከእነዚህ አሁንም ማንን መምረጥ እንዳለባቸው ካልወሰኑት መካከል ከምርጫ ቀን በፊት አሊያም በምርጫው ቀን አንዳች ውሳኔ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ።»

ጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንን ከሰላሳ አመታት በፊት ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል የተጓዙት ቤተ-እስራኤላውያን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴያቸው የተወሰነ ሆኖ መቆየቱን ተናግሯል። በነገው ምርጫ ይሳተፋሉ ተብለው ከሚጠበቁ ተወዳዳሪዎች የተወሰኑት መሟላት የሚገባቸውን ባለማሟላታቸው አፈግፍገዋል ብሎናል። አሁን ለቤተ-እስራኤላውያኑ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ፍትህ የሚሰጥ ፍለጋ በምርጫው እንደሚሳተፉ ዜናነህ መኮንን ይናገራል።

የነገው ምርጫ ከምንጊዜውም በተለየ እስራኤላውያንን ከፋፍሏል።የፖለቲካ ተንታኞች ከህዝበ ውሳኔ ጋር አመሳስለውታል። የፖለቲካው ትኩሳት ማዕከል ግን የፍልስጤምን ጉዳይ ችላ ብለው የኢራን ኒኩሌር ፕሮግራም ያሳሰባቸው ኔታንያሁ ናቸው። በአሜሪካን ፕሬዝዳንት ፊት ተነፍገው በምክር ቤቱ ንግግር ያደረጉት ለረዥም አመታት ስልጣን ላይ የከረሙት ሰው።በምርጫው ቢሸነፉ እንኳ ከተቃዋሚው ኢዝሃቅ ሄርዞግ ጋር የጥምር መንግስት ለመመስረት እምብዛም ፈቃደኛ ያልሆኑት ኔታንያሁ። ሁሉም ነገር ነገ ይለይለታል።

እሸቴ በቀለ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ