1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ያገረሸው የኦሮሞ ወጣቶች ተቃውሞ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 4 2008

ሰዎች ከመሞታቸው፤ከመቁሰልና መታሰራቸው በፊት ዛሬ መላ ኦሮሚያን ያዳረሰው ባህር ተሻግሮ አውሮጳና አሜሪካ የተደመጠው የተቃውሞ ድምጽ መጀመሪያ ብቅ ያለው ከወደ ጊንጪ ነበር።

https://p.dw.com/p/1HMlM
Berlin Demonstration von Oromo-Aktivisten
ምስል DW/H. Kiesel

ያገረሸው የኦሮሞ ወጣቶች ተቃውሞ

መነሻው ደግሞ «የጪሊሞ ደን ለግለሰብ ተሸጧል፤ለጊንጪ ትምህርት ቤት የተከለለ መሬትን የካቢኔ አባላት ተከፋፍለውታል» በሚሉ የተቃውሞ ድምፆች ናቸው። ተቃውሞው ግን በተቀሰቀሰበት አልበረደም። በተጀመረበት መፍትሔ አላገኘም።መካከለኛውእና ምዕራብ ኦሮሚያአምቦ፤ነጆ፤ጉሊሶ፤ደምቢዶሎ፤ነቀምት፤ጊምቢና ሌሎች ከተሞችን አዳረሰ። ሐሮማያ፤ዲላ፤አዲስ አበባ፤ወሎን ወደ መሳሰሉ ሌሎች በርካታ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ተዛመተ። በተቃውሞው እስከ አርብ ታኅሳስ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ 20 ሰዎች መታሰራቸውን ከ150 በላይ መቁሰሉንና ከ 500 በላይ መታሰሩን የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ የአመራር አባል አቶ በቀለ ነጋ ተናግረዋል።

«በነጆ የተጀመረዉ በመሰናዶ ትምህርት ቤት ሰኞ እለት ነበር። ማክሰኞ ከመጀመርያ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ድረስ ያሉት አንድ ላይ ሆነው ወደ አደባባይ ወጡ።» የሚለው ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የአይን እማኝ «የአድማ በታኞች ተኩክስ ቢጀምሩም ሕዝብ በመሃል በመግባት ተማሪዎቻችን ሊሞቱ አይገቡም በማለት ተቋዉሞዉን ቀጥሏል።» ሲል ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል። ተቃዋሚዎች «ሕዝብ ከመሬቱ ሊመፈናቀል አይገባም፣ ፊንፊኔ እምብርታችን ነዉ፣ ሕዝብ ካለ እብርቱ መኖር አንደማይችል ሁሉ ኦሮሞ ያለ ፍንፊኔ ሊኖር አይችልም።» የሚል መፈክር ማሰማታቸውንም ገልጧል።

Enset-Pflanze in Äthiopien
ምስል DW/J. Breyer

«በአምቦ የመሰናዶ ትምህርት ቤት እና በድሬ እንጭኒ ተማሪዎች ለሰለማዊ ሰልፍ ወጥተዉ ነበር።» የሚለው ሌላ የአይን እማኝ ተቃውሞውን ተከትሎ ፖሊስ ተማሪዎች ማሰር መጀመሩን ያስረዳል።«ሕዳር14 ዘጠኝተማሪዎችታስረዋል።» የሚለው ወጣት «ይህን እስር አምልጠዉ ወደ ፊንፊኔ የሸሹ ተማሪዎች እንዳሉ ሰምቼ ነበር።» ሲል ተናግሯል።

36 ከተሞችና 17 ወረዳዎችን የሚዘውና አሁን የኦሮሚያ ልዩ ዞን ተብሎ የሚጠራው አካባቢ በኢትዮጵያ መንግስት በልማት የማስተሳሰር እቅድ «ግዛቱን ብቻ ሳይሆን ከስልጣን ወሰን ወጥተው በአዲስ አበባ ከተማ ስር ይተዳደራሉ።» የሚል ጥያቄ ከተቃዋሚቹ እንደሚሰማ የሚናገሩት የሜልቦርን የዩኒቨርሲቲ የሕግ ምሩቁ ዶ/ር ፀጋዬ አራርሳ ናቸው። አዲስ አበባን ያስተሳስራል በተባለው እቅድ በልማት ስም የአካባቢውን ገበሬዎች ያፈናቅላል፤የገበሬዎች ፈቃድኝነት፤ተገቢ የካሳ ክፍያ አለመከፈል በተቃውሞው ከሚነሱ ጥያቄዎች የሚጠቀሱ ናቸው። «የመሬት ጉዳይ የመኖር ህልዉና ጉዳይ ነዉ።የኦሮሞ ሕዝብ እየተቸገረ ስለሆነ ይህ የመሬት ዘረፋ በአስቸኳይ እንዲቆም እንፈልጋለን።» የሚሉት አቶ በቀለ ነጋ «የጨፌ ኦሮሚያ ያወጣዉ ከተሞች መቀላቀልና አንድ ማድረግ ይችላሉ የሚለዉ ሕግ ባህሉንና ቋንቋዉን የሚያጠፋ ሆኖ ስለታየን፣በጽሑፍም ጠይቀናል።ይህ አዋጅ መቆም አለበት እንላለን።» ሲሉ ይናገራሉ። የአካባቢው ገበሬዎች በልማት ስም የሚነሱ ቢሆን እንኳ«ያ ልማት እሱን መጥቀም አለበት።ያም ማለት መሬቱን ይዞ ካለዉ አካል ጋር እንደ ግለሰብ አክስዮን ኖሮት የሚቋቋመዉ ኢንዱስትሪ ዉስጥ ሚና ሊኖረዉ ይገባል ነዉ የምንለዉ።» ሲሉ ይሞግታሉ።

Berlin Demonstration von Oromo-Aktivisten
ምስል DW/H. Kiesel

የአዲስ አበባ እና ኦሮሚያ ልዩ ዞኖች የተቀናጀ ማስተር ፕላን ተቃውሞ ሲቀሰስቅስ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ከሁለት ዓመታት በፊት መንግስት በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ ከተሞችን በልማት ለማስተሳሰር አወጣሁት ያለው እቅድ በገጠመው ተቃውሞ የሰው ሕይወት ጠፍቷል። የአካል ጉዳት፤የንብረት ውድመትም ደርሷል። የአዲስ አበባንና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞችን የ10 ዓመትና 25 ዓመት የልማት ዕቅዶች ይዟል የተባለው የጋራ ማስተር ፕላን ግን በርካታ ጥያቄዎች ተነስተውበታል። ጥያቄው ሲንከባለል የከረመ ይመስላል። «አንቀጽ 49 ንዑስ ቁጥር 5 ላይ አዲስ አበባ የፌድራል መንግስት መቀመጫ ነች። ኦሮሚያ መሐል እንደመገኘቷ ግን የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ይከበርላታል። የሚል አንቀጽ» በሕገ-መንግስቱ ውስጥ መኖሩን የሚናገሩት የህግ ባለሙያው ዶ/ር ፀጋዬ አራርሳ የአዲስ አበባ ቻርተር በተዘጋጀበት ወቅት የተባለው ልዩ ጥቅም አለመካተቱን ይናገራሉ። ከዚያም በኋላ የአዲስ አበባንና ኦሮሚያን ልዩ ጥቅም የሚተረጉም ህግ አለመውጣቱንም አስረድተዋል። የክልሉ መንግስት ጉዳዩን ለህገ-መንግስት አጣሪ ጉባዔ ባቀረበበት ወቅትም «ልዩ ጥቅም ውስጥ አይካተትም የሚል ክርክር ተነስቶባችሁ ክስ ይዛችሁ ስትመጡ ነው ህገ-መንግስቱ ልዩ ጥቅም ሲል ምን ማለቱ ነው የሚለውን የምንተረጉምላችሁ» የሚል ምላሽ ማግኘታቸውን ዶ/ሩ ጨምረው አስረድተዋል። የክልሉ መንግስት የአዲስ አበባ ከተማን ህጋዊ ያልሆነ መስፋፋት ለመግታትና ከከተማዋ የሚወጣውን የቆሻሻ አወጋገድ ደንብ ለማስያዝ አቶ አባዱላ ገመዳ የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር በነበሩበት ወቅት ጨፌ ኦሮሚያ አሁን ልዩ ዞን ተብለው የሚጠሩትን በህግ ማቋቋሙን ዶ/ር ፀጋዬ አራርሳ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

Demonstration in London gegen das Regime in Äthiopien
ምስል DW/H. Demisse

በአዲስ አበባ በኦሮምኛ የሚያስተምር ትምህርት ቤት፤ የኦሮሞ የባህል ውክልና በጥያቄው ውስጥ ከተካተቱት መካከል እንደሚገኙበት ዶ/ር ፀጋዬ አራርሳ ተናግረዋል። ከተሞቹን በልማት ያስተሳስራል በተባለው እቅድ፤በአተገባበሩ ላይ እና በተቃሰቀሰው ተቃውሞ ላይ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግንው ጥረት ፍሬ አላፈራም።ከእቅዱ ውስን መረጃ የደረሳቸው ዶ/ር ፀጋዬ አራርሳ መንግስት ከሁለት ዓመት በፊት ጥያቄ ሲነሳ ያስተናገደበት መንገድ ውጥረቱን እንደጨመረው ይናገራሉ። «ፕላኑ የተሰራበት እና የተገለጠበት መንገድ ከላይ ወደ ታች ስለሆነ ፕላኑን በተመለከተ ተቃውሞ በተነሳ ጊዜ የመንግስት ባለስልጣናት ደጋግመው ብትወዱም ባትወዱም ይፈጸማል እያሉ ይዝቱ» ልዩነቱ ውጥረት እንደነገሰበትም ጨምረው አስረድተዋል።

ተቃውሞው ከተቀሰቀሰ ሦስተኛ ሳምንቱን ቢያስቆጥርም እሳካሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በይፋ በጉዳዩ ላይ ያሉት ነገር የለም። ለመንግስት ቅርበት ያላቸው መገናኛ ብዙኃን ተቃውሞውን «የፀረ-ሰላም ኃይሎች» ድርጊት እያሉ ሲኮንኑት ተደምጧል። በባለስልጣናቱ አንደበትም ይሁን በመገናኛ ብዙኃኑ «የፀረ-ሰላም ኃይሎች» ማንነት ግን አልተጠቀሰም። ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ሙክታር ከድር በረቂቅ ደረጃ ይገኛል ያሉት እቅድ «ሕዝቡሳይስማማበትእንደማይተገበር» አስታውቀዋል። እስከዚያው ግን ተማሪዎች ጥቁር ለብሰው፤እጃቸውን አጣምረዉ ከማጅራታቸው በመጫንተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው። የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ የአመራር አባል የሆኑት አቶ በቀለ ነጋ መንግስት ለወጣቶቹ ተቃውሞ የሰጠውን ምላሽ አብዝተው ይኮንናሉ።

በእቅዱ ላይ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ተማሪዎች ቅድሚያውን ይዘዋል። ጥይት፤ዱላ፤እስር እና እንግልቱም የበዛው ግን እነሱ ላይ ነው። ፌስቡክን መሰል ማህበራዊ ድረ-ገጾች ከአነስተኛ ቀበሌ እስከ ትልቅ ከተሞችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተከሰቱ ድርጊቶችን በዓለም ዙሪያ አሰራጭተዋል። ማህበራዊ ድረ-ገጾቹ መልሰው የመንግስትን እርምጃ ለመውቀስ ለወጣቶቹ አጋርነት ለማሳየትም ላቅ ያለ ሚና ተጫውተዋል። ዶ/ር ፀጋዬ አራርሳ ተቃውሞው በአንድ ፓርቲ የበላይነት የተያዘው የፖለቲካ ምህዳር መገለጫ እንደሆነ ያስረዳሉ።

Berlin Demonstration von Oromo-Aktivisten
ምስል DW/H. Kiesel

የአቶ በቀለ ነጋ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ፓርቲን በአባልነት ያቀፈው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ በዕለተ-ቅዳሜ በአዳማ ጠርቶት የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ ሳይሳካ መቅረቱ ተሰምቷል። የኢትዮጵያ መንግስትም አዳማ፣ቡራዩናጅማን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በእቅዱ ላይ ከሕዝብ ጋር ውይይት መጀመሩን ለመንግስት ቅርበት ያላቸው መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። አለመግባባቱን በዘላቂነት ለመፍታቱ ግን ማረጋገጫ የለም።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ