1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ያገረሸው የኮንጎው ውዝግብ፣

ዓርብ፣ ሐምሌ 12 2005

የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ጦር ሠራዊት M-23 በሚል መጠሪያ በሚታወቀው አማጺ ኅይል ላይ መልሶ የማጥቃት ዘመቻውን አጠናክሯል። በታንክ፣ በሄሊኮፕተር ፤ አዳፍኔና ከባድ አውቶማቲክ ጠብመንጃ ፣ ወታደሮቹ ከጎማ ከተማ በስተሰሜን ፣ የአማጽያኑን ምሽግ መደብደባቸውን የዜና አውታሮች አስታውቀዋል።

https://p.dw.com/p/19Ayr
ምስል AP

ካለፈው ኅዳር ወዲህ ፤ ባለፈው እሁድ ፣ በጦር ሠራዊቱና በመንግሥት ወታደሮች መካከል በተካሄድ ከባድ ውጊያ ፣ ቢያንስ 130 ሰዎች ሳይገደሉ አልቀሩም።

Kongo M23 Rebellen ziehen aus besetzen Gebieten
ምስል AP

የኮንኮ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ጦር ሠራዊት በወሰደው መልሶ የማጥቃት ዘመቻ፤ የተማረኩ የM -23 አባላትን በግፍ እርምጃ ማሰቃየቱን በውጊያ የተገደሉትን አስከሬንም አደባባይ በመዘርጋት ከብረ ነክ ተግባር የመፈጸሙ ዜና፤ ውግዘትን አስከትሎበታል። ይህን ድርጊት ቀድመው ካወገዙት መካከል የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን ይገኙበታል። ባለፉት 20 ዓመታት ከግጭት ቀጣናነት ባልተላቀቀው በተለያዩ የማዕድን ክምችቶች በታወቀው ምሥራቅ ኮንጎ ፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ሲሆን ህይወቱን ያጣው፤ ካኅዳር ወዲህ እንደገና ባገረሸው ብርቱ ውጊያም ፤ 10 ወታደሮችን ጨምሮ ቢያንስ 130 ሰዎች ናቸው ህይወታቸውን ያጡት።

የመንግሥትን ጦር ፣ ጠንክሮ ሲፋለም የቆየው M-23 ፣ የተቋቋመው፣ አምና፣ በሚያዝያ ወር ፣ ከኮንጎ ጦር ሠራዊት አፈንግጠው በወጡ የቱትሲ ብሔረሰብ ተወላጆች በሆኑ ወታደሮች ነው። በዓለም አቀፍ ተጽእኖ ለቀው ከመውጣታቸው በፊት ፤ M-23 አማጽያን ጎማን ፣ ለ 10 ቀናት በቁጥጥራቸው ሥር አውለው እንደነበረ የሚታወስ ነው። ያም ሆኖ፤ ባለፈው የካቲት በድርጅቱ መካከል በተፈጠረ የሥልጣን ፉክክር፤ ሱልታኒ ማኬንጋ የበላይነቱን ሲቀዳጁ፣ እስከቅርብ ጊዜ የአማጽያኑ ድርጅት የፖለቲካ መሪ የነበሩት ዣን ማሪ ሩኒጋ፣ከተከታዮቻቸው ጋር ወደ ሩዋንዳ ኮብልለዋል። M-23 አማጽያን፣ ጀርመን ውስጥ ፤ በባይሮት ዩንቨርስቲ የውዝግቦች ተመራማሪና ፕሮፌሰር ፣ ማርቲን ዶዖቨን ሽፔክ እንደሚሉት፣ የጦር መሣሪያ ችግር አጋጥሞአቸው አያውቅም።

«መታወቅ ያለበት፤ M-23 አማጽያን ባለፈው ኅዳር ጎማ ላይ የዘረፉት ከባድ ጦር መሳሪያ አሁንም ያላቸው መሆኑ ነው። የውስጥ መከፋፈሉ በዚህ ረገድ ያጎደለባቸው ሁኔታ የለም። ለጥቂት ዓመታት የሚበቃቸውን ያህል አግኝተዋል። »

Kämpfe im Ostkongo
ምስል Phil Moore/AFP/Getty Images

ከሰሞኑ ፣ በኮንጎ ወታደሮችና በ M-23 አማጽያን መካከል በተካሄደው ብርቱ ውጊያ፤ የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ኃይሎች፤ በሩዋንዳ መንደሮች ላይ ተኩሰዋል ስትል ኪጋሊ ያሰማችውን ክስ፣ ሰላም አስከባሪው ኃይል ትናንት ሐሰት ሲል አስተባብሏል።

በምሥራቃዊው ኮንጎ ውጊያው ማገርሸቱ፤ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባን ሸምጋይነት ፤ ባለፈው የካቲት ፤ 11 የአፍሪቃ መንግሥታት ፤ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎና ሩዋንዳ ጭምር የፈረሙትን የሰላም ውል ከንቱ የሚያስቀር እንዳይሆን ሥጋት ማሳደሩ አልቀረም።

ባለፈው መጋቢት ፤ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃው ም/ቤት፣ በምሥራቅ ኮንጎ ፣ እንዲሠማራ የመደበው 3,000 ጠንካራ ጦር ፣ አማጽያንን ትጥቅ እንዲያስፈታ ሥልጣን የተሰጠው መሆኑ ቢታወስም ፤ በተግባር እስከምን ድረስ ይሣካለታል ፤ ውሎ አድሮ የሚታይ ጉዳይ ይሆናል። M- 23 አማጽያን ፣ በምሥራቅ ኮንጎ በአሁኑ ጊዜ ሰላም እንዲሠፍን ሳይሆን ፤ እንዲናጋ ነው የተቻላቸውን ሁሉ የሚያደርት። ጥያቄው ፤ አሁን ያላቸው አቅም እስከምን ድረስ ነው? ነው። የዓለም አቀፍ ውዝግቦች አጥኚው ድርጅት (ኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ) ባልደረባና የማዕከላዊው አፍሪቃ ጉዳዮች ተከታታይ ባለሙያ ፣ ቲዪሪ ቪርኩሎን

«M-23 አማጽያን፣ መዳካመቻው ከቶውንም የሚያጠያይቅ አይደለም። የኮንጎ ጦር ሠራዊት ደግሞ እስካንጫው ነው የታጠቀው። ታዲያ M-23 የምሥራቅ ኮንጎ አማጽያን፤ ከውጭ ተጨማሪ እርዳታ ካላገኙ በስተቀር፣ ብቻቸውን የኮንጎን ጦር ሠራዊት መክተው እንዲያፈገፍግ የሚያስችል ኃይል የላቸውም። »

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ