1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ያ ትውልድ» እና ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች

ዓርብ፣ ሚያዝያ 20 2009

በኢትዮጵያ ታሪክ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ ምኅዳር ጉልህ እንቅስቃሴ ያደርጉ የነበሩ የ«ያ ትውልድ» አባላት የማኅበራዊ መገናኛ አውታር እንቅስቃሴያቸው ምን ይመስላል? በቅርቡ ያረፉት አቶ አሰፋ ጫቦን አብነት በማድረግ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ላይ ቅኝት አድርገናል።

https://p.dw.com/p/2c6LL
Assefa Chabo
ምስል DW/D. Nida

«ያ ትውልድ» እና ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች

በቅርቡ በድንገት በጠና የመታመማቸው እና የማረፋቸው ዜና የተሰማው፤ አቶ አሰፋ ጫቦ። በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች በተለይም በፌስቡክ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ከሚጠቀሱ ጥቂት የ«ያ ትውልድ» ዘመነኞች  መካከል አንዱ ነበሩ። ብዙዎቹ የ«ያ ትውልድ» አባላት በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች እምብዛም የማይታዩት ለምንድን ነው? 

ተሰደው በሚኖሩባት ዩናይትድ ስቴትስ ለበርካታ ዓመታት ድምጻቸው ከጠፋ በኋላ፦ ላለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት በተለይ በፌስ ቡክ ንቁ ተሳታፊ ነበሩ፤  አቶ አሰፋ ጫቦ። ያን በዝምታ ያሳለፉበትን ጊዜ እሳቸው  «የጥሞና ጊዜ» ሲሉ ነው የሚጠሩት።  «የጥሞና ጊዜ»ው ከተገባደደ በኋላ ግን የአቶ አሰፋ ብእር በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ በተለይ በፌስቡክ መንተግተግ ያዘ። አቶ አሰፋ ስለ ዘር መድልዎ፤ በስደት ስለሚኖሩበት ሀገር የምርጫ ስርዓት፤ በውጭ ሃገር ስለሚገኙ ኢትዮጵያውያን፤ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ እና ቆየት ያሉ ጉዳዮች ብሎም ሌሎች ነጥቦች በተከታታይ በመጻፍ በርካታ ወጣቶች ዘንድ መድረስ ችለዋል። 

ካለፉት 30 ዓመታት አንስቶ ነዋሪነታቸውን ሲልቨር ስፕሪንግ ሜሪላንድ ውስጥ ያደረጉት አቶ ያሬድ ጥበቡ የአቶ አሰፋ ጓደኛ (እና ዘመነኛ) ናቸው። በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይም በንቃት ይሳተፋሉ።  አቶ አሰፋ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች በስፋት ተሳታፊ ለመኾናቸው ቀደም ሲል ጀምሮ በጽሑፎቻቸው ያደንቋቸው የነበሩ ወጣቶች አስተዋጽኦ እንዳለው ይናገራሉ። «ወጣቱ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት እና ሊሞላው የሚገባው ክፍተት እንዳለ ሲረዳ፤ ይበልጥ [በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች] ንቁ መኾንን መረጠ፤ ሥነ ቴክኒኩንም ተማረው። እናባለፈው ሁለት ዓመት ከወጣቱ ጋር በዓለም አቀፍ ዙሪያ ከጨንቻ እስከ አውስትራሊያ ድረስ ከብዙ ወጣቶች ጋርየሚያገናኘው መስመር እና መረብ ዘጋ በቅቷል። ከዛ ተሳትፎ ጋር በመነጨከተለያዩ የዓለም ማዕዘናት ነው ወጣቶች ሐዘናቸውን የሚገልጡት።» 

በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ላይ ተጠቃሚ ሲኮን የስም ማጥፋቱን እና በሰብእና ላይ የሚከፈተውን ዘመቻ መቋቋም በራሱ «የመንፈስ ጥንካሬ ይጠይቃል» ሲሉ አክለዋል አቶ ያሬድ ጥበቡ። «ብዙ የዕድሜ ጓደኞቼ ኮሌጅ አብረውን የነበሩ፤ በትግሉ አብረውን የነበሩ ይገርማቸዋል። እንዴት ይኽንን ተቀብለህ ትቀጥላለህ አይነት ነገር። ክብር አርፈህ መቀመጥ ስትችል አይነት ነገር ይላሉ» በማለት የዕድሜ አቻዎቻቸው ስጋትን አንጸባርቀዋል። «እኔ እና ጋሽ ሰፋም ከእኛ ትውልድ ወይንም ያ ትውልድ  ከሚባለው በጣም ከጥቂቱ አንዶቹ ነን። ሲመስለን በጣት የምንቆጠር ነን ብዬ ነው የማስበው በንቃት የምንሳተፈውከዛ ትውልድ አባላት መሀከል።» 

Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

በኦሬገን ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሙኒኬሽን የዶክትሬት ጥናታቸውን በማገባደድ ላይ የሚገኙት  አቶ እንዳልካቸው ጫላ ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ሰዎች ወደ ማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች መምጣታቸው እንደኾነ ይናገራሉ  የአቶ አሰፋ ጫቦ የነቃ ተሳትፎን በማስታወስ።  አቶ እንዳልካቸው ካለፉት ሦስት ዓመታት አንስቶ የአቶ አሰፋ ጽሑፎችን በፌስቡክ ተከታታይ ነበሩ።  

ኢትዮጵያ እና አሜሪካንን ጨምሮ በሌላው ዓለም የሚገኙ ዕድሜያቸው ገፋ ያሉ ሰዎች ወደ ማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች መጥተው ተሳትፎዋቸውን የሚጀምሩት «በፌስቡክ ነው» እንደኾነ አቶ እንዳልካቸው  ተናግረዋል። «ሌሎቹ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ትንሽ የአጠቃቀም ችሎታ ወይንም የመገናኛ አውታሮች ዕውቀት ይፈልጋሉ» ሲሉ የዘማናዊ ስልኮች መራቀቅ  በዕድሜ ገፋ ላሉ ተጠቃሚዎች አስቸጋሪነቱ «ጊዜ የሚፈልግ ነገር ስለሆነ ማለት ነው» ሲል አክሏል። «እሱን እስኪለምዱ ድረስ፤ታሪኮችን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እየተመለከቱ እስኪሳቡ ድረስ ጌዜ ፈጅቷል ማለት ነው። አሁን አሁን ግን በአቶ አሰፋ ጫቦም እንዳየነው በርካታ የዛ ትውልድ አባላት ወደ ማኅበራዊ የመገናኛ መስኮች እየመጡ ነው » ብለዋል። 

ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የኾኑ ብዙ ወጣቶች በተለይ ወንዶች በፌስቡክ ተሳታፊ መኾናቸውን ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ መመልከታቸውን ጠቁመዋል። «ያን መስክ ማጣትታሪክን መናገር፤ አለመቻል ማለት ነው» ያሉት አቶ እንዳልካቸው «ድረ-ገጽ እና መጽሐፍ ላይ ብቻ መወሰንታሪካቸው እንዳይነበብእንዲረሱ ያደርጋል» ስለዚህም ያን ዕድል መጠቀም አለብን ብለዋል። 

 ኢትዮጵያ ውስጥ ኾነም በሌላው ዓለም ሰዎች ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን በቁም ነገር መውሰድ የጀመሩት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መኾኑን አቶ እንዳልካቸው አክለው ጠቅሰዋል።  የ«ያ ትውልድ አባላት»ም ኾኑ ሌሎች «ማኅበራዊ ሚዲያን በጥርጣሬ የሚመለከቱ ሰዎች ግን «ቆም ብለው ማሰብ ይገባቸዋል» ሲሉ ጠቅሰዋል። አቶ ያሬድ ጥበቡ በበኩላቸው በርካታ የ«ያ ትውልድ» ዘመነኞቻቸው ወደ ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ያለመምጣታቸውን ምክንያት  ሲያብራሩ፦ «የፖለቲካ ባሕሉ፤ መጎሻሸሙ፤ የስም ማጥፋቱ፤ መዘላለፉ የሚያስፈራቸው እጅግ በጣም ብዙ ሰዎች አሉ» ብለዋል። 

የግሎባል ቮይስ ከሰሃራ በታች ያሉ ሃገራት አርታኢ አቶ እንዳልካቸው  «ወጣቶችን ለማግኘት» በተለይ ከማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቀላል ወደ ኾነው ፌስቡክ መምጣት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ፌስቡክ እና ሌሎች ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እየጨመሩ እንጂ እየቀነሱ ስለማይሄዱ የ«ያ ትውልድ» አባላት መሳተፍ አለባቸው ብዬ ነው የማምነው» ሲሉም ተሳትፎው ሊበረታታ እንደሚገባ ተናግረዋል። 

Symbolbild Social Media
ምስል DW/S. Leidel

 የ«ያ ትውልድ» ዘመነኛ የነበሩት የአቶ አሰፋ ጫቦ ጽሑፎችን ለማስታወስ ያኽል ከማረፋቸው ከአንድ ወር ከ20 ቀን በፊት በፌስቡክ ያሰፈሩትን ዘለግ ያለ ጽሑፍ በአጭሩ እንቃኝ። አቶ አሰፋ ለጽሑፉቸው «የማይዘጋ በር» የሚል ርእስ ሰጥተውታል። 

ጽሑፉ ስለ ትራምፕ የሶሪያ የአየር ላይ ጥቃት፤ ስላለቁት ህፃናት እና ሴቶች፤ ስለሞተው አሜሪካዊ ወታደር እና የአባቱ ቅሬታም ይተነትናል። 33ኛው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ሃሪይ ትሩማን ጠረጴዛ ላይ በእንግሊዝኛ የተጻፈው ወደ ትዝታ ማኅደራቸው እንደመለሳቸውም ይጠቅሳሉ። በፕሬዚዳንቱ ጠረጴዛ ላይ የሚገኘው ጽሑፍ፦ «በእኔ ፕሬዚዳንትነት ስር ለተሠራው ማንኛቸውም ተጠያቄ እኔ ብቻ ነኝ!» የሚል ትርጓሜ ይዟል።  የአቶ አሰፋ ጽሑፍ፦ «አንዴ የካቲት 1966 ጸደይ መጽሔት ላይ ወጥቶ የነበር የሽሙጥ ምስል (Cartoon) አስታወሰኝ» እያለ ይቀጥላል። በትራምፕ ሞገደኝነት የተንደረደረው ጽሑፍ በኢትዮጵያ የ«ያ ትውልድ» ጊዜ ስለተከሰቱ እና አኹን ባለንበት ዘመን ስለሚገኙ ፖለቲከኞች እና የፖለቲካ አዙሪት እያጣቀሰ ይመላለሳል። 

ከ«ያ ትውልድ» ዘመነኞች መካከል በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ጉልህ ተሳትፏቸው በተለይ በወጣቶች ዘንድ ይደነቁ እንደነበሩት እንደ እነ አቶ አሰፋ ጫቦ ሌሎችም ብቅ እያሉ የኑሮ ልምዳቸውን ያካፍሉ ይኾናል? የብዙዎቹ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ጥያቄ አዘል ተስፋ ነው። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ