ዜና | 15.12.2017 | 00:00

ዘሄግ፤ የቀድሞዉ የደርግ ባለስልጣን እስራት ተፈረደባቸዉ

ዘ ሄግ የሚገኘዉ የኔዘርላንድስ ፍርድ ቤት ከቀይ ሽብር ጋር በተገናኘ በተከሰሱት የቀድሞ የደርግ መንግሥት ባለስልጣን ላይ የዕድሜ ልክ እስራት በየነ። የዳች ዜግነት ያላቸዉ ትዉልደ ኢትዮጵያዊዉ የመቶ አለቃ እሸቱ ዓለሙ በጎርጎሪዮሳዊዉ የዘመን ቀመር በ1970ዎቹ ኢትዮጵያ ዉስጥ በስልጣን ላይ በነበሩ ጊዜ በተፈፀመ የጦር ወንጀል ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ብሏቸዋል። ዳኛ ማሪቴ ሬንከንስ «የ63 ዓመቱ እሸቱ ዓለሙ በጦር ወንጀል፤ ዜጎቻቸዉን በጭካኔ እና በተጠና መንገድ የመኖር መብታቸዉን በመንጠቅ የተፈረደባቸዉ የዕድሜ ልክ እሥራት ለድርጊቱ ያለዉ ተመጣጣኝ ቅጣት ይኸዉ ብቻ በመሆኑ እንደሆነ መግለጻቸዉን የፈረንሳይ የዜና ወኪል ከዘ ሄግ ዘግቧል።

ኒያሚ፤ 74 ኤርትራዉያን ተሰዳጆች ከሊቢያ ወደ ኒዠር መግባታቸዉ

የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን በእንግሊዝኛ ምህጻሩ UNHCR ከሊቢያ ለጥቃት የተጋለጡ 74 ስደተኞችን ትናንት ማምሻዉን ለዛሬ አጥቢያ ወደኒዠር አሻገረ። አብዛኞቹ ልጆች እና ሴቶች መሆናቸዉ የተገለፀዉ ወገኖች ከኤርትራ ወደሊቢያ የሄዱ ተሰዳጆች እንደሆኑ ኒያሚ ላይ የተቀበሏቸዉ የUNHCR ወኪል ገልጸዋል። «ከኤርትራ የመጡ 74 ጥገኝነት ፈላጊዎች አዉሮፕላኑ ዉስጥ ይገኛሉ። አብዛኞቹ ልጆች እና ማንም አብሯቸዉ የሌለ ወይም ከቤተሰቦቻቸዉ የተለዩ ሕጻናት ናቸዉ። ኒዠር ለእነሱ መሸጋገሪያ ናት። መልካም አቀባበል ይደረግላቸዋል፤ ድጋፍም ያገኛሉ፤ አሁንም ሕይወት መቀጠል እንደሚችልም ተስፋ ይሰጣቸዋል።»ወደኒዠር የተሻገሩት 51 ልጆችን ጨምሮ 22 ሴቶች እና አንድ ወንድ ናቸዉ። UNHCR ሐሙስ ምሽት ለዓርብ አጥቢያ በአስቸኳይ ያጓጓዛቸዉ ጥገኝነት ፈላጊዎች ሊቢያ ዉስጥ በሚገኝ የእስር ቤት የቆዩ እንደነበሩም የUNHCR ባልደረባዋ አመልክተዋል። ቡድኑ እንዲህ ባለዉ መርሃግብር ኒዠር ዉስጥ የመጣ ሁለተኛዉ መሆኑ ነዉ።

ኒዉ ዮርክ፤ የተመድ የደቡብ ሱዳንን ኃይሎች ማስጠንቀቁ

የተመድ የፀጥታዉ ምክር ቤት በመጪዉ ሳምንት የሚጀመረዉን የደቡብ ሱዳን አዲስ የሰላም ዉይይት የሚያደናቅፉ ዋጋ ሊከፍሉ እና መዘዝ ሊያስከትልባቸዉ ይችላል ሲል አስጠነቀቀ። የፀጥታዉ ምክር ቤት ባወጣዉ መግለጫ በምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ማለትም ኢጋድ አነሳሽነት አዲስ አበባ ላይ ሊካሄድ የታቀደዉን አዲሱን የሰላም ሂደት ልዩ የዕድል መስኮት ብሎታል። እንዲያም ሆኖ ይህ አጋጣሚ ለሁለቱም የደቡብ ሱዳን ኃይሎች ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት በሀገሪቱ ለማምጣት የመጨረሻ ዕድላቸዉ እንደሆነም አስታዉቋል። ከፍተኛ የማደስ መድረክ በሚል በኢጋድ የታለመዉ የደቡብ ሱዳን አዲስ የሰላም ዉይይት የፊታችን ሰኞ በአፍሪቃ ዋና መዲና አዲስ አበባ ላይ እንደሚጀመር አዣንስ ፍራንስ ፕረስ አመልክቷል። ሆኖም ግን እስካሁን እነማን በመድረኩ እንደሚገኙ አልተገለጸም። የፀጥታዉ ምክር ቤት ግን ሁሉም ወገኖች በሂደቱ ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ በአፅንኦት ጠይቋል።

አቡጃ፤ ቦኮ ሃራምን ለመዋጋት 1 ቢሊየን ዶላር መመደቧ

ከነዳጅ ዘይት ከፍተኛ ገቢ የሚያገኘዉ የናይጀሪያ መንግሥት በሀገሪቱ እና አካባቢዋ የሚንቀሳቀሰዉን ፅንፈኛ እስላማዊ ቡድን ቦኮ ሃራምን ለመዋጋት የአንድ ቢሊየን ዶላር በጀት አፀደቀ። አሶሲየትድ ፕረስ እንደዘገበዉ የናይጀሪያ 36 ግዛቶች ሀገረ ገዢዎች ገንዘቡ ወደ ፌደራል መንግሥት ካዝና ለዚሁ ተግባር እንዲገባ አዎንታቸዉን ሰጥተዋል። ገንዘቡ ለፀጥታ ማስከበሩ ዘርፍ አስፈላጊ ቁሳቁሶችን፣ ለስለላ እና ለሎጀስቲክስ እንደሚዉል ነዉ የተገለፀዉ። የኤዶ ግዛት ሀገረ ገዢ ጎድዊን ኦባስኪ፤ ሀገረ ገዢዎቹ ፌደራል መንግሥት ታጣቂዎቹ ላይ የወሰደዉ ርምጃ ባስገኘዉ ዉጤት ደስተኞች መሆናቸዉን ተናግረዋል። እንዲያም ሆኖ ሀገሪቱ ዉስጥ ከዚህ ቀደም ቦኮ ሃራምን ለመዋጋት በሚል የተከናወነ የጦር መሣሪያ ግዢ ከፍተኛ የሙስና ቅሌት ተፈጽሞበታል የሚል ወቀሳ አስከትሏል። የናይጀሪያ የቀድሞዉ የፀጥታ ጉዳይ አማካሪ ለጦር መሣሪያ ግዢ በሚል የወጣ 2,1 ቢሊየን ዶላር ወደሌላ አዙረዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

ሞስኮ፤ ፍርድ ቤት በፑቲን የቀድሞ ሚኒስትር ላይ እስራት በየነ

የሩሲያ ፍርድ ቤት በዛሬ ዕለት የቀድሞዉ የሀገሪቱ የኤኮኖሚ ሚኒስትር አሌክሲ ዑሊዩካይቭ የሁለት ሚሊዮን ዶላር ጉቦ መብላታቸዉን አረጋገጠ። በዚህም መሠረት ስምንት ዓመት ፅኑ እስራት እና 2,2 ቢሊየን ዶላር መቀጮ ፈርዶባቸዋል። ዑሊዩካይቭ በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ከሀገሪቱ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ተጓዳኝ ጉቦ ተቀብለዋል በሚል ክስ የመሠረተባቸዉ አቃቤ ሕግ በአስር ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ነበር የጠየቀዉ። የ61 ዓመቱ አሌክሲ ዑሊዩካይቭ ፑቲን 17 ዓመት ሥልጣን ላይ በቆዩበት ወቅት ለእስር የበቁ ብቸኛዉ ባለስልጣን መሆናቸዉ ተገልጿል። የፕሬዝደንት ፑቲን አማካሪ አሌክሲ ኩድሪን በበኩላቸዉ የፍርድ ቤቱ ዉሳኔ መሠረት የሌለዉ ነዉ ሲሉ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን መግለጻቸዉን ሮይተርስ አመልክቷል።

ብራስልስ፤ የአዉሮጳ ኅብረት ቀጣይ የብሬግዚት ዉይይት

የአዉሮጳ ኅብረት መሪዎች ከብሪታንያ ጋር በብሬግዚት ጉዳይ የሚያደርጉት ድርድር ሁለተኛ ምዕራፍ እንዲጀመር ዛሬ ተስማሙ። የድርድሩ ሁለተኛ ምዕራፍ የሚያተኩረዉ በሽግግሩ ወቅት እና ወደፊት ሊኖር በሚችለዉ የንግድ ግንኙነት ላይ እንደሚሆን ተገልጿል። ከብሪታኒያዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ ጋር ትናንት በቀጣዩ ርምጃ ላይ የተነጋገሩት የኅብረቱ መሪዎች ሜይ ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ ላደረጉት ጥረት አመስግነዋቸዋል። በተቃራኒዉ ሜይ በሀገራቸዉ ፓርላማ የብሪታኒያን ከኅብረቱ አወጣጥ አስመልክቶ ያቀረቡት ዕቅድ ተቀባይነት አላገኘም። በዛሬዉ ዕለት ከተካሄደዉ ዉይይት በኋላ የአዉሮጳ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ዶናልድ ቱስክ የተደረሰበትን ዉጤት እንዲህ ገልጸዋል፤«በመጨረሻም ብሬግዚትን በተመለከተ፤ ሁለተኛዉን የድርድር መድረክ 27ቱ የኅብረቱ አባል ሃገራት ባይተባበሩ ኖሮ፤ የሚሼል ባርንየ ጠንካራ ጥረት እና የጠቅላይ ሚኒስትር ሜይ ገንቢ ሚና ባይኖር አዳጋች ይሆን ነበር። ለወደፊት ግንኙነት መዋቅር ግልጽ ራዕይ ለማግኘት የኅብረቱ 27 ሃገራት የዉስጥ ዝግጅት እና ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር የዉጭ ግንኙነት የሚያደርጉትበት ወቅት ነዉ። በዚህ መመሪያ መሠረትም ድርድራችንን በሚቀጥለዉ ዓመት መጀመር ይኖርብናል። በአዉሮጳ ኅብረት በኩል ያለዉ አንድነት ይቀጥላል ብዬ አምናለሁ።»ጉዳዩን አስመልክቶ ለሁለተኛ ቀን በተካሄደዉ ዉይይትም የዜጎችን መብት፣ የአየርላንድን ድንበር እና ብሪታኒያ ስለሚጠበቅባት ክፍያ የተደረጉ ዉይይቶች ላይ በቂ መሻሻሎች መታየታቸዉም ተገልጿል።

ቤተልሔም፤ የፍልስጤማዉያን ተቃዉሞ እና የእስራኤል ኃይሎች

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ለኢየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማነት የሰጡትን እዉቅና በመቃወም በዛሬዉ ዕለት በሺዎች የሚገመቱ ፍልስጤማዉያን ሰልፍ አካሄዱ። በዚህ ወቅትም እንደ አጥፍቶ ጠፊ የሆነ ነገር የታጠቀ መሆኑ የተጠረጠረ ነዉ የተባለ ፍልስጤማዊ መገደሉን የእስራኤል ፖሊስ አመልክቷል። በተቃዉሞ ሰልፈኞቹ እና በእስራኤል የፀጥታ ኃይሎች መካከል በተካሄደዉ ግጭትም በርካቶች ተጎድተዋል። በተለያዩ የእስልምና እምነት ተከታዮች በሚበረክቱባቸዉ ሃገራትም ተመሳሳይ ተቃዉሞች የቀጠሉ ሲሆን ቱርክ የትራምፕ ዉሳኔ ተቀባይነት እንዳያገኝ የተመድ ግፊት እንዲያደርግ የበኩሏን ጥረት መጀመሯን አስታዉቃለች። SL/AA

Albanian Shqip

Amharic አማርኛ

Arabic العربية

Bengali বাংলা

Bosnian B/H/S

Bulgarian Български

Chinese (Simplified) 简

Chinese (Traditional) 繁

Croatian Hrvatski

Dari دری

English English

French Français

German Deutsch

Greek Ελληνικά

Hausa Hausa

Hindi हिन्दी

Indonesian Bahasa Indonesia

Kiswahili Kiswahili

Macedonian Македонски

Pashto پښتو

Persian فارسی

Polish Polski

Portuguese Português para África

Portuguese Português do Brasil

Romanian Română

Russian Русский

Serbian Српски/Srpski

Spanish Español

Turkish Türkçe

Ukrainian Українська

Urdu اردو