1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዮዓኪም ጋውክ የገና ዋዜማ ንግግር

እሑድ፣ ታኅሣሥ 16 2009

የጀርመኑ ፕሬዝዳንት ዮአሂም ጋውክ ሽብር የቀሰቀሰው ቁጣ እና ንዴት ወደ ጥላቻ እና ኹከት እንዳይለወጥ ጥሪ አቀረቡ። ፕሬዝዳንቱ በዓመታዊ የገና ዋዜማ ንግግራቸው «በበርሊን የገና ገበያ የበርካቶች መሞት እና መቁሰል ጥልቅ ፍርሃት እና ረብሻ ፈጥሮብናል።» ሲሉ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/2UrMp
Deutschland Weihnachtsansprache Bundespräsident Gauck
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Schreiber

 

 

የጀርመኑ ፕሬዝዳንት ዮዓኪም ጋውክ ሽብር የቀሰቀሰው ቁጣ እና ንዴት ወደ ጥላቻ እና ኹከት እንዳይለወጥ ጥሪ አቀረቡ። ፕሬዝዳንቱ በዓመታዊ የገና ዋዜማ ንግግራቸው «በበርሊን የገና ገበያ የበርካቶች መሞት እና መቁሰል ጥልቅ ፍርሃት እና ረብሻ ፈጥሮብናል።» ሲሉ ተናግረዋል። «ዜጎች ቁጣ፤ ንዴት እና አቅም ማጣት ተሰምቷቸዋል።» ያሉት ጋውክ ንግግራቸው ሁሉ በበርሊኑ የሽብር ጥቃት የተሞላ ሆኖ ተስተውሏል። ፕሬዝዳንቱ ቁጣ እና ንዴቱ ወደ ጥላቻ እና ኹከት እንዳያድግ ይልቁንም መተባበር እና ርኅራሔ እንደሚያስፈልግ በአፅንዖት ተናግረዋል። ጋውክ በሽብር ጥቃቱ ማግሥት ማሕበረሰቡ እንዳይከፋፈል ፖለቲከኞችም እርስ በርስ ጣት ከመጠቋቆም ሊታቀቡ እንደሚገባም አሳስበዋል። ይህ ሲባል ግን የጥቃቱ መነሾ እና ዳፋ ውይይት ሊደረግበት አይገባም ማለት አይደለም ሲሉም አክለዋል።  ጀርመን በበርሊን የገና ገበያ ላይ ጥቃት ፈጽሟል ተብሎ የተጠረጠረዉ አኒስ አምሪ ጣልያን ዉስጥ በተገደለ ማግሥት ተባባሪዎች ካሉት እያደነች መሆኑን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። መራሒተ-መንግሥቷ አንጌላ ሜርክል ተጠርጣሪው ሌላ ሥጋት ባለመፍጠሩ እፎይታ እንደተሰማቸው ትናንት ገልጠዋል።  የቱኒዝያ አገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒሥትር የተጠርጣሪው አኒስ አምሪ ዘመድ እና ሌሎች ሁለት ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን አስታውቀዋል። እድሜያቸው ከ18 እስከ 27 ነው የተባሉት ተጠርጣሪዎች የህቡዕ የሽብር ቡድን አባላት ነበሩ ተብሏል።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ