1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዮዌሪ ሙሴቬኒ፤ 30 ዓመት በሥልጣን ላይ

ቅዳሜ፣ ጥር 21 2008

የዩጋንዳ ፕሬዚደንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ ሀገራቸውን በርዕሰ ብሔርነት ሲመሩ በዚህ ሳምንት ሰላሳ ዓመት ሆናቸው። ሙሴቬኒ በአፍሪቃ በስልጣን ላይ ከተቀመጡ ሰላሳ እና ከዚያ በላይ የሆናቸውን ሌሎቹን አምስት ርዕሳነ ብሔርን ቡድን ተቀላቅለዋል።

https://p.dw.com/p/1Hm28
Yoweri Museveni Präsident Uganda
ምስል picture-alliance/AP Photo/E. Hoshiko

ዮዌሪ ሙሴቬኒ፤ 30 ዓመት በሥልጣን ላይ


እነርሱም የኢኳቶርያል ጊኒ ፕሬዚደንት ቴዎዶር ኦቢያንግ ንጌማ፣ የአንጎላ አቻቸው ኾዜ ኤድዋርዶ ዶስ ሳንቶሽ፣ በዚህ በተያዘው የየካቲት ወር 92 ዓመት የሚሆናቸው የዚምባብዌ ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤን እና የካሜሩንኑ ፖል ቢያን ናቸው።

ብዙኃኑ የዩጋንዳ ዜጎች ከሙሴቬኒ በስተቀር ሌላ ፕሬዚደንት አያውቅም፣ ምክንያቱም ከ35 ሚልዮኑ የዩጋንዳ ሕዝብ መካከል ሶስት አራተኛው ሙሴቬኒ ስልጣን ሲይዙ ገና አልተወለደም ነበር። ይኸው ሁኔታም ፣ በዩጋንዳ መዲና ካምፓላ የሚገኘውን የጀርመናውያኑን የፍሪድሪኽ ኤበርት ተቋም ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት እንደሚመሩት የፖለቲካ ተንታኝ ማራይከ ለ ፔሌ አስተያየት፣ ይህ ሕዝቡን አማራጭ እያሳጣው ሳይሄድ አልቀረም።
« ትልቁ ችግር ሕዝቡ አማራጭ ይኖራል የሚለው የሕዝቡ ተስፋ እየጠፋ መሄዱን ነው። ፕሬዚደንቱ በፍፁም ስልጣን፣ ጫና በማሳረፍ አገዛዛቸውን ቀጥለዋል። ስለሆነም፣ ብዙዎች ሌላ አካሄድ ሊኖር ይችላል ብለው አያምኑም። »
በስልጣን ላይ ለሶስት አሰርተ ዓመታት በቆዩት ሙሴቬኒ እና «ብሔራዊ ተቋቋሚ ንቅናቄ» ፓርቲያቸው እና በሀገሪቱ መንግሥት መካከል ልዩነት መኖር የሚገባው ልዩነት እየጠፋ ሄዷል ለማለት ይቻላል። ፕሬዚደንቱ ይህንን ሁኔታ ለራሳቸው ጥቅም እያዋሉት መሆኑን ማራይከ ለ ፔሌ ይናገራሉ።
« ፕሬዚደንቱ የሀገሪቱ ገንዘብ ሁሉ የርሳቸው የሆነ ያህል እንደሚሰማቸው በተደጋጋሚ ከማጉላት ወደኋላ አላሉም። በምርጫ ድምፃቸውን ለርሳቸው የማይሰጡ በሚኖሩበት አካባቢም ልማት ሊያራምዱ እንደማይችሉም ነው ግልጽ ያደረጉት። ገንዘብ የምታገኙት እኔን እና መንግሥቴን ስትመርጡ ብቻ ነው። ይህም በገዚው ፓርቲ እና በመንግሥት መካከል ልዩነት አለማድረግ ወይም አንድ አድርጎ እንደመመልከት ይቆጠራል። ሕዝቡ በዚህ ቅር ተሰኝቶዋል፣ ግን፣ ይኸው አሰራር ማንኛውም ለውጥ የሚመጣበትን ሁኔታ አዳጋች አድርጎታል። »
ዩጋንዳውያን ከአንድ ወር በኋላ አዲስ ምክር ቤት እና አዲስ ፕሬዚደንት ይመርጣሉ። ሙሴቬኒም ለመጀመሪያ ጊዜ ጠንካራ ተፎካካሪ ቀርቦባቸዋል። የፊታችን የካቲት 18፣ 2016 ዓም በሚደረገው በፕሬዚደንታዊው ምርጫ ላይ ሰባት እጩዎች የሙሴቬኒን አገዛዝ ለማብቃት ቢነሳሱም፣ ሙሴቬኒ ይሸነፋሉ ብለው የሚገምቱት ጥቂቶች ናቸው።
በተለይ ሶስት ጊዜ ሞክረው ከተሸነፉት የተቃዋሚው የ«ዴሞክራሲያዊ ለውጥ መድረክ» ፓርቲ እጩ ኪዛ ቢሲጌይ፣ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር እና ከ« ጎ ፎርዎርድ» የተሰኘው አዲስ ፓርቲ እጩ አማማ ምባባዚ ጠንካራ ፉክክር እንደሚጠብቃቸው ይታመናል። ይሁንና፣ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት፣ የሁለቱ ዋነኛ ተቃውሞ ፓርቲዎች እጩዎች ቀድሞ በገዢው ፓርቲ ውስጥ ከፍተኛ ባለስልጣናት የነበሩ በመሆናቸው ፣ ራሳቸው በፈጠሩት እና ጥቅም ባገኙበት ስርዓት አንፃር የሚቆም አሳማኝ አማራጭ ለማቅረብ በመታገል ላይ ናቸው። የዩጋንዳ ዜጎች ሀገሪቱ ነፃነት ካገኘች ወዲህ በምርጫ የስልጣን ለውጥ አይተው ስለማያውቁ በመጪው ምርጫም የተለየ ውጤት መገኘቱን አጠያይቀዋል።
በምርጫው የሚሳተፉ እጩዎች በጠቅላላ ፖሊስ የኃይል ርምጃ እየፈጸመ ነው፣ የተቃዋሚ ቡድኖችም ሚሊሺያዎችን እያደራጁ ነው፣ ይህም በሀገሪቱ ሁከት እንዳያስነሳ እና ውጥረቱን እንዳያካርር መስጋታቸውን እየገለጹ ነው።
በሚልተን ኦቦቴ መንግሥት አንፃር በህቡዕ ከተንቀሳቀሱ በኋላ በ1986 ዓም ተሀድሶ የማራመድ ዓላማ ይዘው በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን ላይ የወጡት ሙሴቬኒ፣ በዚያን ጊዜ ስልጣንን የሙጥኝ በሚሉ ፕሬዚደንቶች ላይ ጠንካራ ወቀሳ ነበር የሰነዘሩት። እጎአ በ1986 ዓም ት ፣ በሀገሪቱ ይካሄድ የነበረውን ደም አፋሳሽ ውጊያ እና የፖለቲካ አለመረጋጋት አብቅተዋል። እርግጥ፣ በመጀመሪያዎቹ የስልጣን ዓመታት ሰላም ማውረድ ተሳክቶላቸዋል፣ የሀገሪቱ ኤኮኖሚም እንዲያንሰራራ አድረገዋል። ይሁን እንጂ፣ በሀገሪቱ የመጀመሪያው ምርጫ ያካሄዱት ስልጣን ከያዙ ከአስር ዓመት ገደማ በኋላ በ1996 ዓም ነበር።
አዲስ በተረቀቀ ሕገ መንግሥት አማካኝነትም፣ ሀገሪቱ የአንድ ፓርቲ ስርዓት እንድትተዳደር ቢያደርጉም እና እንደገና ከአስር ዓመት በኋላ በሕገ መንግሥቱ ላይ ባስደረጉት ለውጥ አማካኝነት ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገሪቱ እንዲንቅሳቀሱ ቢፈቅዱም፣ የፕሬዚደንቱን ስልጣን በሁለት ዘመን የሚገድበውን አንቀጽ ሻሩ። በአንድ ወቅት በመንግሥት አንፃር በማመፅ ትግል ያካሄዱት ሙሴቬኒ ፣ የብሔራዊ ተቋቋሚ ንቅናቄ ፓርቲያቸውን ትግል ዓላማ በመተው፣ አሁን ራሳቸውን እንደ ተቋም መመልከት ይዘዋል። ሙሴቬኒ ከሚልተን ኦቦቴ እና ከቲቶ ኦኬሎ አገዛዝ በኋላ በ1986 ዓም ስልጣን ከጨበጡ ወዲህ ውጊያ ላይ እንዳሉ ነው የሚናገሩት።
« የጀመርኩትን ሁሉ አቋርጬ ጥዬ እንድሄድ ነው ወይ የሚፈለገው? » ሲሉ ያጠያይቃሉ።
ሙሴቬኒ የመድብለ ፓርቲን ስርዓት ካስተዋወቁ በኋላ በመጀመሪያ በ1980 ዎቹ ዓመታት በሰሜናዊ ዩጋንዳ እና ባካባቢው ጎረቤት ሀገራት የሽብር ተግባር ባስፋፋው የ«ሎርድ ሬዚዝስተንስ አሚሶም» ፣ ከዚያም በአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ጓድ፣ «አሚሶም » ተልዕኮ ስር በሶማልያ ዓማፂ ቡድን አሸባብ አንፃር ውጊያ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
ከኒው ዮርክ የአሸባሪዎች ጥቃት በኋላ ሙሴቬኒ በተለይ በአፍሪቃ ቀንድ በፀረ ሽብሩ ትግል ላይ ያሳዩት ትብብር ቀና አመላካከት አትርፎላቸው፣ በጎረቤት «ዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ እና በቡሩንዲ ውዝግቦች ላይ በሸምጋይነት ሚና ተጫውተዋል። እንደ ጀርመናዊቷ የፍሪድሪኽ ኤበርት የፖለቲካ ጥናት ተቋም ኃላፊ ለፔሌ ትዝብት፣ ሙሴቬኒ ይህንኑ ሚናቸውን በሀገራቸው ችግር እንደሌለ ለማስመሰል አዘውትረው ይጠቀሙበታል።
« ብዙ የዩጋንዳ ዜጎች በ1970 እና 1980ኛዎቹ ዓመታት የተካሄዱትን ጦርነቶች አያስታውሱም። ጦርነቱ ካበቃ በኋላ የተወለዱት የሀገሪቱ ዜጎች በወቅቱ ትኩረትታቸውን ያሳረፉት ባለፈው ታሪክ ላይ ሳይሆን፣ እንደሚታወቀው፣ የስራ ቦታ ማግኘት ጉዳይ ነው። በሀገሪቱ ተጓድሎ የሚገኘው የስራ ቦታ ባፋጣኝ ካልተፈጠረ፣ የወጣት ዩጋንዳውያን ቅሬታ እያደገ መሄዱ አይቀርም። »
የዩጋንዳ መሰረታዊ መብቶችን እና የፖለቲካ ነፃነትን በተመለከተ ካለፉት ሰላሳ ዓመታት ወዲህ ይህ ነው የሚባል የተሀድሶ ለውጥ እንዳልታየ ተንታኞች ይናገራሉ። በአንድ ወቅት በጣም ነፃ ይባል የነበረው የሀገሪቱ ፕሬስ ባለፉት ዓመታት ጠንካራ ገደብ አርፎበታል።

14.06.2014 DW Karte Online Uganda neu
Uganda ehemaliger Premierminister Amama Mbabazi
ምስል Getty Images/AFP/R. Bosch
Uganda Wahlen 2016
ምስል Simone Schlindwein

ፊሊፕ ዛንድነር/አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ