1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደም እና ባሕሪያቱ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 14 2008

በሰዉነታችን ዉስጥ ለመኖር አስፈላጊ የሆነዉን ኦክስጅንን እንዲሁም ሌሎች ንጥረነገሮችን ከሳንባ እና ከሌላ የሰዉነታችን ክፍሎች በማመላለስ ትልቅ ሚና ይጫወታል ደም። በሰዉነታችን ላይ በተለያዩ ምክንያቶች አንዳች ጉዳት ደርሶ ቁስለት ሲፈጠር ያ ለከፋ አደጋ አሳልፎ እንዳይሰጠን ሰዉነትን የሚከላከሉ ንጥረነገሮችንም ያመላልሳል።

https://p.dw.com/p/1JApg
Symbolbild Bluttransfusion
ምስል Fotolia

ደም እና ባሕሪያቱ

ብዙ ደም እንዳይፈሰን ፍሰቱ የሚገታበትን ቅመም አመንጪዉም ይኸዉ ደም ነዉ። በሰዉነታችን ዉስጥ የሚገኘዉን ቆሻሻ ወደኩላሊት እና ጉበት አምጥቶ እንዲጣራ የሚያደርገዉ ደም ነዉ። ከዚህም ሌላ የሰዉነታችንን ሙቀት ሚዛናዊ አድርጎ የመቆጣጠር ኃላፊነቱም የእሱ ነዉ። አንድ ሰዉ በሰዉነቱ ዉስጥ የሚኖረዉ የደም መጠን እንደክብደቱ እና ርዝመቱ ይለያያል። በአማካይ ግን በአዋቂ ዕድሜ ደረጃ የሚገኝ ወንድ 5 ሊትር ደም እንዳለዉ እና በተመሳሳይ ዕድሜ እንዲሁም የሰዉነት ክብረትና ርዝመት ያላት ሴት ደግሞ 4 ,5 ሊትር እንዳላት መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ ልዩነት ከምን መጣ የሚለዉን የዉስጥ ደዌ እና የደም በሽታዎች ልዩ ሃኪም ዶክተር ፍሰሃጽዮን ታደሰ በዝርዝር አብራርተዉታል።

Symbolbild Gesundheit Test - Blutstropfen auf Fingerkuppe
ምስል picture-alliance/blickwinkel/McPhotos

በቂ የብረት ወይም አይረን ንጥረነገር ያላቸዉን መግቦች በተመጣጠነ የአመጋገብ ሥርዓት በመዉሰድ ደምን ቶሎ መተካት ይቻላል ቢባልም ግን ዶክተር ፍሰሀጽዮን እንዳሉት ቶሎ ቶሎ ግን ደምን መሰጠት አይቻላም። አንድ ጤናማ ሰዉ በዓመት አራት ጊዜ ብቻ በሦስት ወራት ልዩነት ነዉ ደም መለገሥ የሚችለዉ። ይህ የሚደረገዉ በቂ የብረት ክምችት በሰዉነቱ እንዲኖር ነዉ። የደም ማነስ የሚባለዉ የጤና ችግር መንስኤ የብረት እጥረት መሆኑን የሚያስረዱት የዉስጥ ደዌ እና የደም በሽታዎች ልዩ ባለሙያ ብረት ወይም አይረንን ይብዛም ይነስ ከሁሉም የምግብ ዓይነት ማግኘት እንደሚቻል ነዉ የሚናገሩት።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ