1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደ.ሱዳን፤ የተኩስ አቁም ስምምነት ተፈረመ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 2 2006

በደቡብ ሱዳን ለወራቶች ከዘለቀ ከፍተኛ ግጭትና ጦርነት በኋላ፤ የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና ተቀናቃኛቸዉ የቀድሞዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪኤክ ማቸር የተኩስ አቁም ስምምነት ተፈራረሙ። ይህ ትናንት ምሽት የተደረሰዉ ስምምነት፤ በተፈረመ በ24 ሰዓታት ዉስጥ ተግባራዊ እንደሚሆን ተገልፆአል።

https://p.dw.com/p/1Bxbd
ምስል Reuters

ሁለቱ ተቀናቃኞች በደቡብ ሱዳን ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ መዲና አዲስ አበባ ላይ ተገናኝተዉ የቀጥታ ንግግር ሲያደርጉ ይህ ለመጀመርያ ግዜ መሆኑ ነዉ። ሁለቱ ተቀናቃኞች ከተስማሙባቸው ጉዳዮች መካከል፤ አንድ የሽግግር መንግሥት መመስርትና በጠላትነት መተያየትን ማብቃት የሚሉት ይገኙበታል። በደቡብ ሱዳን በተከሰተዉ የእርስ በእርስ ጦርነት፤ ለተጎዱ ከአንድ ሚሊዮን ለሚበልጡ ነዋሪዎች የሰብዓዊ ርዳታ እንደሚደርስም ተመልክቷል። በተኩስ አቁም ስምምነቱ ላይ የተካተቱትን ነጥቦች ወደፊት ተግባራዊ ለማድረግ፣ በመጪዎቹ ቀናት በሁለቱም ወገን ያሉ መልዕክተኞች የስምምነት ነጥቦቹን አንድ በአንድ በማጥናት ገቢራዊ ለማድረግ እንደሚሰሩ ተነግሯል።

Bruch der Waffenruhe im Südsudan 26.01.2014
ምስል Reuters

በሌላ በኩል የጀርመኑ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር፤ የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች የደረሱትን ስምምነት አስመልክተዉ «በጦርነቱ ዉስጥ ላለዉ ማህበረሰብ የአዲስ ተስፋ ምልክቱ ነዉ» ሲሉ ተናግረዋል።

በደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና በአማጽያኑ መሪ ሪኤክ ማቻር መካከል ባለፈው ታኅሳስ ወታደራዊ ፍልሚያ ተጀምሮ በሺ የሚቆጠሩ መገደላቸውና ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ከቀየው መፈናቀሉ ታውቋል። በእርግጥ ጥር አጋማሽ ላይ ሁለቱ የደቡብ ሱዳን ባላንጣዎች በኢጋድ አደራዳሪነት በሸራተን አዲስ የመጀመሪያውን የሰላም ውል መፈራረማቸው ይታወሳል።

ሆኖም ግን በዓማጺያኑ በኩል የቀድሞው ም/ፕ ሪክ ማቻር ሁሉንም ዓማጺያን አይወክክሉም ከሚለው ስጋት አንስቶ በሁለቱም ወገን የተኩስ አቁም ስምምነቱ ውሎ ሳያድር ነበር የተጣሰው።

አዲስ አበባ ውስጥ እንደገና የሰላም ውይይት እንዲጀመር ያግባቡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙንና የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ጆን ኬሪ ናቸው። ከትናንት በስትያ ማታ አዲስ አበባ የገቡት የቀድሞው የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንትና የአሁኑ የአማጽያን መሪ ሪኤክ ማቻር፣ በቅድሚያ ከ2 ሳምንት በፊት ከእስር የተለቀቁትን 4 ከፍተኛ የፖለቲካ ሰዎች አነጋግረዋል።

Bruch der Waffenruhe im Südsudan 26.01.2014
ምስል Reuters

ማቻር ፣ ሽምግልናውን ከሚያካሂደው የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ሊቀ መንበር ፤ የኢትዮጵያን ጠ/ሚንስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝንም ማነጋገራቸው ተገልጿል። ምንም እንኳን ለአምስት ወራት የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም የትናንቱ ስምምነት ለሁለተኛ ጊዜ ቢሆንም ቀደም ሲል በተካሄደው ስምምነት ወቅት ሁለቱ የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች ተገናኝተው አልተነጋገሩም። በትናንቱ ስምምነት ወቅት ግን ሁለቱ ተቀናቃኞች ፊት ለፊት ለመገናኘት ችለዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ጆን ኬሪ፤ ፕሬዚዳንት ሣልቫ ኪርን ደቡብ ሱዳን ውስጥ አግኝተው ካነጋገሩና ተቀናቃኛቸው የቀድሞዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪኤክ ማቸርን በስልክ ካወያዩ ከአንድ ሣምንት በኋላ ነው ሁለቱ ተቀናቃኞች ፊት ለፊት ተገናኝተው ስምምነቱን የተፈራረሙት። የደቡብ ሱዳን ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት እየተደረገበት እንደሆነ ለማሳየትና ጫና ለማሳደር የተመድ ዋና ፀሐፊ ባን ኪሙንም ደቡብ ሱዳን አቅንተው እንደነበር የሚታወስ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ