1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደቡብ ሱዳን

ሐሙስ፣ ነሐሴ 11 2009

በውጊያ ጦርነቱ መሀል የደቡብ ሱዳን መንግሥት በሰጠው ምህረት መሠረት እስካሁን 30 የፖለቲካ እሥረኞችን ፈቷል። አማጽያን እርምጃውን መልካም ጅምር ሲሉ አወድሰውታል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እንደሚሉት በሺህዎች የሚቆጠሩ ደቡብ ሱዳናውያን አሁንም በህገ ወጥ መንገድ እንደታሰሩ ነው።

https://p.dw.com/p/2iQoh
Südsudan Rebellenführer Riek Machar in Juba
ምስል Reuters/Stringer

ደብብ ሱዳን እና የሰላሙ ተስፋ

በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ዋነኛውን ሚና መጫወት የሚገባቸው የደቡብ ሱዳን መንግሥት እና ህዝብ ናቸው ሲሉ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ አስታወቁ። ተንታኙ ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ  የደቡብ ሱዳን መንግሥት የፖለቲካ እሥረኞችን መፍታቱ የመቀራረብ እና ሰላም የማውረድ ፍላጎት መኖሩን የሚያመለክት እርምጃ ነው ብለዋል። የሐገሪቱ ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ ይፈታል ተብሎ ባይታሰብም ጎረቤት አገራት እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ካለፈው ስህተት ትምሕርት ወስደው የሰላሙን ጥረት መቀጠል እንዳለባቸውም ገልጸዋል። ኂሩት መለሰ 
የደቡብ ሱዳን መንግሥት እና አማጽያን እዚህም እዚያም እየተዋጉ ነው። አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ መፎከራቸውም አልቆመም። በጦርነቱ የሰላማዊ ሰዎች ህይወት ማለፉና እና ዜጎችም ከቀያቸው መሰደዳቸው ቀጥሏል። መንግሥት ከ10 ቀናት በፊት የአማፅያን ጠንካራ ይዞታ የነበረችውን ኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ የምትገኘውን የፓጋክ ከተማን መያዙን አስታውቆ ነበር። አማጽያን ደግሞ ከሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ መልሰው በእጃቸው እንዳስገቧት ከትናንት በስተያ ተናግረዋል። የአማጽያኑ ምክትል ቃል አቀባይ ኮሎኔል ላም ፓውል ጋብርየል ጦራቸው የመንግሥት ወታደሮችን ከሰሜን ምሥራቅዋ ፓጋክ ሲያስወጣ አብዛኛዎቹም ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው እንደተናገሩ አሶስየትድ ፕሬስ ዘግቧል። መንግሥት ግን ለዚህ ዘገባ ማረጋገጫ አልሰጠም። የደቡብ ሱዳን ውጊያ ማብቂያ ማጣቱ የሰላሙ ጥረትም አለመሳካቱ የሀገሪቱ እጣ ፈንታ ምን ይሆናል የሚለውን ጥያቄ ሁሌም ያስነሳል። ዶቼቬለ ስለዚሁ ጉዳይ የጠየቃቸው በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት እና ስልታዊ ጥናት ተቋም የፖለቲካ ተንታኝ አቶ አበበ አይነቴ ችግሩ እስኪፈታ ጊዜ መውሰዱ አይቀርም ይላሉ። 
«ላለፉት 5 እና 6 ዓመታት የታየው ችግር በአጭር ጊዜ የሚፈታ አይደለም። ምክንያቱም ችግሮቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ መልካቸውን እና ይዘታቸውን እየቀየሩ የመጡበት ሁኔታ ነው ያለውና።ጦርነቱን ማካሄዱ እና ችግር መፍጠሩ አንድ ነገር ሆኖ ገና በኤኮኖሚም ያልዳበረ ያልጠነከረ ሀገር ላይ የሚከሰት ግጭት በአጭር ጊዜ ምላሽ አግኝቶ ወደ ሚፈለገው ለማምጣት ትዕግስትም ይጠይቃል። ጊዜም ጉልበትም የሰው ሀብትም የሀገር ሀብትም መብላቱ የማይቀር ነው። እና አሁንም ቢሆን ጊዜ መውሰዱ አይቀርም።»
በውጊያ ጦርነቱ መሀል የደቡብ ሱዳን መንግሥት በሰጠው ምህረት መሠረት እስካሁን 30 የፖለቲካ እሥረኞችን ፈቷል። እሥረኞቹ የተፈቱት ባለፈው ግንቦት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ብሔራዊ ውይይት ለማመቻቸት ባደረጉት ምህረት መሠረት ነው። ሁሉም ማለት ይቻላል የታሰሩት የማጽያኑን መሪ የቀድሞውን ምክትል ፕሬዝዳንት ሪየክ ማቻርን ትደግፋላችሁ ተብለው ነው። አማጽያን እርምጃውን መልካም ጅምር ሲሉ አወድሰውታል። ኪር እነዚህን እሥረኞች ያለአንዳች ቅድመሁኔታ መፍታታቸው ችግሩን በሀገሪቱ ማቆሚያ ያጣውን ግጭት ለመፍታት መቁረጣቸውን ያሳያል ተብሏል። አቶ አበበም እርምጃውን ተስፋ ሰጭ ብለውታል። 
«በጣም ተስፋ ሰጭ ነበር። ምክንያቱም የአማጽያን ኃይሎች ካቀረቧቸው ቅድመ ሁኔታዎች አንዱ የታሰሩብን አባላት እና ደጋፊዎቻቸው ይፈቱ የሚል ነው። ፖለቲከኞቹ ከእስር ይለቀቁ የሚል ነው ሥልጣን ላይ ያለው። የደቡብሱዳን መንግሥት የተቃዋሚዎችን ጥያቄ ተቀብሎ እንደተጠቀሰው የተወሰነ ቁጥር ያላቸውን ተቃዋሚዎች ከእስር ለቋል። ይሄ በሁለቱ በኩል ያለውን የመቀራረብ እና ለመነጋገር ያለውን ፍላጎት የሚያሳይ ነው። በሌላ መልኩ ቀደም ሲል የተናጠል የተኩስ አቁም ማድረጉም ይሄ በራሱ በደቡብ ሱዳን መንግሥት በኩል የአቋም ለውጥ እየታየ ለመምጣቱ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።»
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች 30 ሰዎች ብቻ መፈታታቸው ችግሩን መሸፋፈኛ ነው ሲሉ አጣጥለዋል። እነርሱ እንደሚሉት አሁንም በሺህዎች የሚቆጠሩ ደቡብ ሱዳናውያን በህገ ወጥ መንገድ አሁንም እንደታሰሩ ነውና። 4 ዓመት ሊደፍን ጥቂት ቀናት የቀሩት የደቡብ ሱዳኑ ጦርነቱ ከሐገሪቱ ዜጎች አንድ አራተኛውን ማለትም 12 ሚሊዮኑን አሰድዷል። የማጽያኑ መሪ ማቻርም ዲፕሎማቶች እና የፖለቲካ ምንጮች እንደተናገሩት ደቡብ አፍሪቃ ነው የሚገኙት። የደቡብ ሱዳን የሰላም ጥረት ባለበት እንደቆመ ነው። ከአሁን በኋላ የሰላሙ ተስፋ ምን ሊሆን ይችላል። አቶ አበበ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ቀዳሚው ሚና የህዝቡ ሊሆን ይገባል ይላሉ።
«በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ከጎረቤት አገሮችም ከዓለም አቀፉ ማህበራትም ይበልጥ የሱዳን መንግሥት እና የሱዳን ህዝብ ነው ባለቤቱ ። በቀጥታ ተጎጂውም ተጠቃሚውም የሱዳን ህዝብ እና መንግሥት ነው። በሁለተኛ ደረጃ አማጺው ኃይል ነው። በሦስተኛ ደረጃ ጎረቤት ሀገሮች እና ዓለም አቀፉማህበረሰብ የደቡብ ሱዳንን ችግር ለመፍታት ከመቼውም በላይ ካለፈው ስህተት ካለፈው ጉድለት ተምረው። በቀጣይነት ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በሚያስችል መልኩ መንቀሳቀስ አለባቸው»
ኂሩት መለሰ

Südsudan Symbolbild Konflikt
ምስል Getty Images/AFP/C. Atiki Lomodong
Südsudan Panakuach - Südsudanische Soldaten
ምስል Reuters/G. Tomasevic

ሸዋዬ ለገሠ