1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደቡብ ሱዳን የሠላም ዉልና ተስፋ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 21 2007

የደቡብ ሱዳንን የሠላም ስምምነት የሚቆጣጠረዉና የሚያጣራዉ የኢጋድ መስሪያ ቤት ሐላፊ አምባሳደር ተፈራ ሻዉልም ኪር «ቅሬታ» ያሉትን ለዉስጣዊ ፖለቲካዊ ፍጆታ ካልሆነ በስተቀር ትርጉም የለዉም ይሉታል።

https://p.dw.com/p/1GN2d
ምስል Reuters/J. Solomun

[No title]

የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ሐገሪቱን የሚያወድመዉን ጦርነት ለማስቆም ይረዳል የተባለዉን የሠላም ሥምምነት ትናንት መፈረማቸዉን የተለያዩ መንግሥታትና ድርጅቶች በደስታ ተቀብለዉታል። ኪር ሰነዱን ሲፈርሙ እዚያዉ ጁባ የነበሩት የምሥራቅ አፍሪቃ ሐገራት መሪዎች ትናንትን "ለአካባቢዉ አስደሳች ቀን" ሲሉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ጦርነቱን ለማስቆም መልካም እርምጃ ብለዉታል። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት የፀጥታ አማካሪ እንዳሉት ደግሞ ለሠላም የመጀመሪያ እርምጃ ነዉ። የሰምምነቱን መፈረም የደገፉት ወገኖች በሙሉ ግን የደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች ሥምምነቱን ገቢር እንዲያደርጉ እያሳሰቡም ነዉ።

ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር አጉረጥርጠዉም፤ አንገራግረዉ፤ አመንትተዉም፤ በኢትዮጵያዊዉ ዲፕሎማት በአምባሳደር ተፈራ ሻዉል አገላለፅ ደግሞ «ጮኸዉም፤ ተፈራግጠዉም» የሠላም ሰነዱን ፈረሙ። ትናንት።

ይሁንና ኪር የሰምምነቱ ሰነድ መፅሐፍ-ቅዱስ ወይም ቁርዓን አይደለም ባይ ናቸዉ። መሻሻል አለበት። በሰነዱ ከተካተቱት ሐሳቦች የማይቀበሉ-ወይም ለመቀበል የሚታቀቡባቸዉ ነጥቦችን ለአደራዳሪዎች አቅርበዋልም። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት የፀጥታ አማካሪ ወይዘሮ ሱሳን ራይስ እንዳሉት ግን ሥምምነቱ ከተፈረመ ገቢራዊ ማድረግ እንጂ «ለመቀበል መታቀብ» ብሎ ነገር የለም።

Südsudan - Ankunft von Äthiopiens Premierminister Hailemariam Desalegn
ምስል Reuters/J. Solomun

የደቡብ ሱዳንን የሠላም ስምምነት የሚቆጣጠረዉና የሚያጣራዉ የኢጋድ መስሪያ ቤት ሐላፊ አምባሳደር ተፈራ ሻዉልም ኪር «ቅሬታ» ያሉትን ለዉስጣዊ ፖለቲካዊ ፍጆታ ካልሆነ በስተቀር ትርጉም የለዉም ይሉታል። የኢጋድ አባል ሐገራት መሪዎችም የቅሬታዉን ፅሁፍ አልተቀበሉትም። በኢትዮጵያ ሠላምና ልማት ዓለም አቀፍ ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ አቶ አበበ አይነቴም በዚሕ ይስማማሉ።

የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ሐይላት የሠላም ዉል ሲፈራረሙ ያሁኑ የመጀመሪያቸዉ አይደለም። ተፋላሚዎች ሰምምነቶችን በየጊዜዉ እየተጣሱ ሃያ ወራት እንደተዋጉ ሁሉ ያሁኑን ሥምምነት ሙሉ በሙሉ ማክበራቸዉ አጠራጣሪ ነዉ።

አቶ አበበ እንደሚሉት የእስካሁኑ ሥምምነት እንዳይከበር ከተፋላሚ ሐይላት እንቢተኝነት በተጨማሪ የኢጋድ አባል ሐገራት ከስምምነቱ ይልቅ ለየግል ጥቅማቸዉ መቆማቸዉ አንዱ ምክንያት ነበር።

ኢትዮጵያ፤ ኬንያ፤ ዩጋንዳ፤ ሰሜን ሱዳንም በደቡብ ሱዳን አነሰም በዛ የየራሳቸዉ ጥቅም አላቸዉ። የዩጋንዳን ያክል ከደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ሐይላት አንዱን ደግፎ ጦር እስከ ማዝመት የደረሰ መንግሥት ግን የለም።

የዩጋንዳዉ ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሳቬኒ የእስካሁን አቋማቸዉን በርግጥ ከቀየሩ-የቀየሩበት ምክንያት የፖለቲካ ተንታኝ አበበ አይነቴ እንደሚገምቱት የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ጫና-አንዱ ነዉ። ምናልባት የጦርነቱ መራዘም፤ ወይም የሁኔታዎች መለወጥ-ሌሎቹ።

Südsudan Präsident Salva Kiir
ምስል Reuters/T. Negeri

ትናንት ጁባ የነበሩት፤ አምባሳደር ተፈራ ሻዉል ደግሞ «አሁን የተለየ ነዉ።»-ይላሉ።የኢጋድ አባል ሐገራት፤ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብም የጋራ አቋም ይዘዋል። ምሳሌም አላቸዉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን በቃል አቀባያቸዉ በኩል «አስደሳች» ያሉትን የሠላም ዉል ተፋላሚዎች ገቢር እንዲያደርጉ አደራ ብለዋል። የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት የባራክ ኦባማ ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢይ በፋንታቸዉ ተፋላሚ ሐይላት የፈረሙትን ዉል ተግባራዊ ካላደረጉ፤ የፀጥታዉ ምክር ቤት በማዕቀብ እንዲቀጣቸዉ ዩናይትድ ስቴትስ የምክር ቤቱን አባል መንግሥታት ማስተባበሯን ትቀጥላለች።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ