1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደቡብ ሱዳን-የተስፋ ጭላጭንጭል?

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 14 2008

የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች በነሐሴ ወር የተፈራረሙትን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በዋና ከተማዋ ጁባ ተገናኝተዋል። ለሁለት አመታት የዘለቀውን የርስ በርስ ጦርነት እና ቀውስ ለመፍታት የተፈረመው ስምምነት በጥቂት ወራት ውስጥ የሽግግር መንግስት የመመስረት እቅድ አለዉ።

https://p.dw.com/p/1HTTS
Bildkombo Südsudan Riek Machar und Salva Kiir
ምስል Getty Images/Zacharias Abubeker/Ashraf Shazly/Montage

[No title]

ባለፈዉ ሰኞ የፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ተቀናቃኞች የሽግግር መንግስት በመመስረት የደቡብ ሱዳንን የፖለቲካ ውጥንቅጥ ለመፍታት ያለመውን የሰላም ስምምነት ተግባራዊነት ለመጀመር ከዋና ከተማዋ ጁባ መድረሳቸው ተሰምቷል። በቀድሞው የአገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪየክ ማቻር የሚመራው አማፂ ቡድን ዋና ተደራዳሪ ታባን ደንግ ጋይ «ወደ ጁባ መምጣታችን የጦርነቱ ፍጻሜ ነው። ህዝቡም ሊቀ-መንበሬና የጦር አዛዥ ዶ/ር ሪየክ ማቻር በጥር እንደሚመጡ መጠበቅ አለበት።» ሲሉ መናገራቸውን ሬውተር ዘግቧል። አምባሳደር ተፈራ ሻውል በኢጋድ የደቡብ ሱዳን የሠላም ዉል የተቆጣጣሪና አጣሪ ቡድን ዋና ኀላፊ ናቸው።

Konflikt im Südsudan Regierungssoldat 30.12.2013
ምስል Reuters

የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች በምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት አማካኝነት ልዩነቶቻቸውን ለመፍታት እና የተኩስ አቁም ለማድረግ ባደረጓቸው ድርድሮች የገቧቸውን ስምምነቶች በተደጋጋሚ ሲጥሱ እርስ በርስም ሲወነጃጀሉ ነበር። አሁን ለደቡብ ሱዳን ቀውስ መፍትሔ የማበጀት ተስፋ የተጣለበት የሁለቱ ወገኖች ግንኙነት በአደራዳሪዎቻቸውም ይሁን በቀጣናው አገራት በጎ እርምጃ ተደርጎ ይታያል። ነገር ግን ጥርጣሬ እና ስጋትም ይደመጣል። አምባሳደር ተፈራ ሻውል የካሁን ቀደም የተፈጸሙ ስምምነቶችን ተግባራዊ ማድረግ ያልተቻለው በሪየክ ማቻር የሚመራው ተቃዋሚ ወደ ዋና ከተማዋ መግባት ባለመቻሉ እንደሆነ ይናገራሉ።

የደቡብ ሱዳን ነጻ አዉጪ ንቅናቄ (SPLM)ን ለሁለት የሰነጠቁት የፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና ተቃዋሚያቸው ሪየክ ማቻር ኃይሎች ጎሳን ያማከለ ግድያ በመፈጸም፤ህጻናትን ለውትድርና በመመልመል እና በመግደል፤የአስገድዶ መድፈር፤ ዜጎችን ቁም ስቅል በማሳየት እና ከመኖሪያ ቀያቸው በማፈናቀል ይወነጀላሉ። ይሁንና የደቡብ ሱዳንና ዜጎቿ የነገ እጣ ፈንታም በእነዚሁ የቀድሞ የነጻነት ትግል ጓዶች የዛሬ ባላንጣዎች እጅ ላይ ወድቋል። በአጭር ጊዜ የሽግግር መንግስት ምስረታን ቀዳሚ ዓላማ ያደረገውን የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት አምባሳደር ተፈራ ሻውል የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ-መንግስታት ትልቅ ስኬት እንደሆነ ያምናሉ። ለስምምነቱ መደረስም ሆነ ተግባራዊነት ክፍለ አህጉራዊው ድርጅትና የቀጠናው አገራት መሪዎች ከፍ ያለ ሚናመቻወታቸውንም ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል። አምባሳደሩ በደቡብ ሱዳን አሁንም ግጭቶች ቢኖሩም የሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች በጁባ መገናኘት ግን ለዘላቂ መፍትሔ ጉልህ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ይናገራሉ።

Südsudan Mehr als 30.000 Menschen laut UNO vom Hungertod bedroht
ምስል Getty Images/AFP/T. Karumba

የደቡብ ሱዳን ቀውስ 2.3 ሚሊዮን ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ሲያፈናቅል 4.6 ሚሊዮኑን ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ጠባቂ አድርጓል። ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪየር በጎርጎሮሳዊው 2013 ዓ.ም. ምክትላቸው ሪየክ ማቻር መፈንቅለ መንግስት እየጠነሰሱ ነው በሚል ውንጀላ ከመንበራቸው ሲያባርሩ በተቀሰቀሰው ቀውስ መነሾ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል። የፖለቲካው ውጥንቅጥ ዳፋ በነዳጅ ዘይት የበለጸገችውን አገር ኢኮኖሚም አሽመድምዶታል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ