1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደቡብ ሱዳን፤ ዳግም ለጦርነት?

ረቡዕ፣ መስከረም 18 2009

ሱዳን የሚገኙት የቀድሞዉ የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንት ሬክ ማቻር በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር በሚመራዉና ጁባ በሚገኘዉ መንግሥት ላይ ይፋዊ ጦርነት አዉጁ። ከካርቱም ሱዳን በወጣዉ መግለጫ መሠረት፤ ሬክ ማቻር ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር የሚመራዉ የደቡብ ሱዳን መንግሥት ሕገ ወጥ መሆኑን  ማወጅ ይፈልጋሉ።

https://p.dw.com/p/2Qhtw
Südsudan Rebellenführer Riek Machar in Juba
ምስል Reuters/Stringer

Südsudan_Machar ruft zu Krieg gegen Südsudans Regierung auf/mmt - MP3-Stereo

 

 

በሌላ በኩል ቀደም ሲል ሽምቅ ተዋጊና የአማፅያን መሪ ከነበሩት ከፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር የመጣዉ መልስም ለዉግያዉ ዝግጁ መሆናቸዉን የሚያመለክት ነዉ ።

በደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪርና በተቀናቃኛቸዉ ሬክ ማቻር መካከል ለበርካታ ወራት  ከዘለቀዉ ጦርነት በኋላ በማገገም ላይ ባለችዉ አዲሲትዋ አፍሪቃዊት ሀገር ደቡብ ሱዳን ዳግም የጦርነት ዳመና እያስገመገመ ነዉ። እስካሁን በተካሄደዉ ጦርነት ከሦስት መቶ ሺህ በላይ ሕዝብ አልቋል። እንደ ተመ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን «UNHCR» ግምትም አንድ ሚሊዮን ነዋሪዎች ሀገራቸዉን ለቀዉ ወደ ጎረቤት ሃገራት ተሰደዋል።  በቅርቡ የተመ የፀጥታዉ ምክር ቤት በደቡብ ሱዳን የሚገኙ ሲቪሎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ተጨማሪ 4000 ወታደሮችን እንደሚያሰማራ ቢገልጽም እስካሁን ደቡብ ሱዳን አልደረሱም። እነዚህ ኃይላት ወደ ደቡብ ሱዳን ከገቡ በሀገሪቱ የሚገኘዉን የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታ ኃይል በቁጥር ወደ 17 ሺህ ያደርሱታል።  የደቡብ ሱዳን ነዋሪዎች የፀጥታ ኃይላቱን ወደ ሃገሪቱ መግባት በጉጉት በሚጠባበቁበት በአሁኑ ወቅት ፤ የደቡብ ሱዳን የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ሬክ ማቻር ፤ ለአምስት ሳምንት የቆዩበትን ፀጥታ ሰብረዉ ጁባ በሚገኘዉ በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር መንግሥት ላይ ጦርነት አዉጀዋል። የሬክ ማቻርን የጦርነት አዋጅ በተመለከተ በካርቱም የሚገኙት የማቻርን ቃል አቀባይ ጋዴት ዳክ ለዶይቼ ቬለ እንደገለፁት

Südsudan Rebellenführer Riek Machar
ምስል Reuters/G. Tomasevic

« ይህ ለመቋቋም የተደረገ ርምጃ ነዉ። ሳልቫ ኪር በኛ ላይ ጦርነት አዉጀዋል። ለመመከት እየተዘጋጀን ነዉ ።»  የሳልቫ ኪር ወታደሮች ባሉባቸዉ ቦታዎች ነዉ ጥቃት የምትጥሉት ወይስ ወደ ጁባ ነዉ የምትገቡት ለሚለዉ ጥያቄ?

«ወደ ጁባ ዘልቀን ለመግባት የምንወስንበት ጊዜ ይመጣል። አሁን ግን በመከላከል ላይ እንገኛለን።» ነዉ ያሉት ቃል አቀባዩ። ሪክ ማቻር በጁባዉ መንግሥት ላይ ጦርነት ማወጃቸዉ ተከትሎ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ለዉግያዉ ዝግጁነታቸዉን በመግለፅ ፈጣን መልስ ሰተዋል።

« የፈለገዉን ያህል ኃይል ይዞ ይምጣ ፤ እዚህ ያለዉን ኃይል ይገጥማል።  ሰላም ይኖራል ፤ ይህ ሰላም ደግሞ እንደ ዶክተር ማቻር አይነቱንና ሌሎችን ማካተት ይኖርበታል ብዬ አላስብም።  ማንም ጁባን አይወርም።»  ፕሬዚዳንት ኪር ስልጣን እንደማይለቁ ተናግረዋል ። ስልጣን ከለቀቁ ግን ሀገሪቱ ከ 20 ዓመታት በፊት በሩዋንዳ እንደታየዉ የጅምላ ግድያና ዘር ማጥፋት ይከሰታል ይላሉ።

 « ይህን መንበር ዛሬ ብለቅ ፤ የምታወሩት በደቡብ ሱዳን ስለተፈጸመ የዘር ማጥፋት ነዉ»  ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ስለዘር ማጥፋት የተናገሩት፤ የእሳቸዉ በሆነዉ በዲንቃ ጎሳና በተቀናቃኛቸዉ ሬክ ማቻር  ጎሳ በሆነዉ ኑዌር  መካከል ይከሰታል ስላሉት ግጭት ነዉ።

Südsudan Salva Kiir Mayardit
ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርምስል Getty Images/AFP/M. Sharma

የቃላት ጦርነቱና ጥቃቱ መባባሱን የተመለከቱ በርካታ የፖለቲካ ምሑራንም ምናልባትም በደቡብ ሱዳን ዳግም የርስ በርስ ጦርነት ሳይቀሰቀስ እንደማይቀር ያምናሉ። አብዛኛዉ የደቡብ ሱዳን ዜጋ ደግሞ ይህን አይሻም።  አንድ ደቡብ ሱዳናዊ ፤

« ለመሪዎቻችን እና ለሀገሬ ዜጎች መናገር የምፈልገዉ ነገር አለ፤ ደቡብ ሱዳናዉያን ለስልጣን ያላቸዉን ፍቅር አስወግደዉ ለሀገራቸዉ የፍቅር ኃይል እንዲኖራቸዉ ምኞቴ ነዉ ።»

 ሲል በአፅንኦት ገልጿል።

 

ጀምስ ሽማኑኤላ /  አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ