1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደቡብ አፍሪቃ፣ ANC እና ኤኮኖሚዋ

ረቡዕ፣ ጥር 9 2004

የአፍሪቃ ብሄራዊ ሸንጎ ANC የተቋቋመበትን መቶኛ ዓመት በቅርቡ በደመቀ ሁኔታ አክብሯል።

https://p.dw.com/p/13ktz
ምስል dapd

ANC በአፍሪቃ ምድር አንጋፋው የነጻነት እንቅስቃሴ ሲሆን በደቡብ አፍሪቃ ረጅም ጸረ-አፓርታይድ ትግል ታሪክ ውስጥ ወሣኝ ሚና ነበረው። የአፍሪቃው ብሄራዊ ሸንጎ በኔልሰን ማንዴላ መሪነት የውሁዳኑን ነጮች የዘር አድልዎ አገዛዝ አፓርታይድን አስወግዶ ሥልጣን ከያዘ ወዲህ ዛሬ 17 ዓመታት አልፈዋል። ግን በጊዜው የብዙሃኑን የደቡብ አፍሪቃ ጥቁሮች የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የተገባው ቃል ዛሬ የታለመውን ያህል ዕውን አልሆነም።
በርካታ የጥቁሮች መንደሮች ዛሬም የኤሌክትሪክ ብርሃን ለማግኘት አልበቁም፤ የሥራ አጡም ቁጥር በተለይም የወጣቱ እጅግ ከፍተኛ ነው። ለብዙሃኑ ደቡብ አፍሪቃውያን ተሥፋ የነበረው ANC-ም የሥልጣን ትግልና ሙስና ውስጣዊ መለያው ሆኖ ሲቆይ በደጋፊዎቹ ዘንድ ጭምር ቅሬታን እያጠነከረ ሄዷል። ከዚህ አንጻር ታዲያ መቶኛ ዓመት ክብረ-በዓል በሕዝብ ዘንድ ምን ትርጉም ነው የነበረው? በኬፕታውን የጀርመን የንግድ ጋዜጣ የ “ሃንደልስ-ብላት” ወኪል ቮልፍጋንግ ድሬክስለር የአፍሪቃው ብሄራዊ እንቅስቃሴ በቅድመ-አፓርታይዱ ዘመን የነበረውን ታላቅ ሚና በማስታወስ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ግን ባለፈ ታሪኩ ተወስኖ እንደቀረ ነው ያመለከተው።

“ለነገሩ በዓሉ ለደቡብ አፍሪቃ ዜጎች ትልቅ ትርጉም ሊኖረው በተገባ። ANC ለረጅም ጊዜያት በአገሪቱ ዕጣና የፖለቲካ ሂደት ላይ ወሣኝ ሚና ነበረው። አሁን መቶ ዓመት ሞላው። እርግጥ በወጣት ሊጋው፤ በዋልተር ሲሱሉ፣ ኦሊቨር ታምቦና ኔልሰን ማንዴላ አማካይነት በሕዝብ አዕምሮ ውስጥ መቀረጽ የጀመረው በአርባኛዎቹ ዓመታት ነበር። ከዚያም በ 60ኛዎቹ ዓመታት ሲታገድ በዓለምአቀፍ ደረጃ የአገሪቱ ጥቁሮች ትግል ሕጋዊ ተጠሪ በመሆን ሰፊ ዕውቅናን ያገኛል። እንግዲህ እንዲህ እያለ ነበር በዘጠናኛዎቹ አጋማሽ ለሥልጣን የደረሰው። ይሁንና ብሄራዊው እንቅስቃሴ እ.ጎ.አ. በ 1994 ዓ.ም. የአፓርታይዱ አገዛዝ አብቅቶ ሥልጣን ሲይዝ ከነበረው ታሪካዊ ሁኔታ አንጻር የሚያሳዝን ሆኖ ብዙዎች የአፍሪቃ የነጻነት እንቅስቃሴዎች የሄዱበትን ፈለግ ነው የተከተለው። በሥልጣን ትግልና በሙስና በመጠመዱ ፈሩን ስቷል። እና በዓሉም ይሄው የጋረደው ነበር። ከቀድሞው ሞራላዊ ገጽታው የቀረው ጥቂት ነው”
በዕውነትም ብዙዎች ዛሬ በድርጅቱ ደስተኞች አይደሉም። ሃቁ ይህ ሲሆን በሌላ በኩል ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ የ ANC-ን መቶኛ ዓመት በዓል የመላው ደቡበ አፍሪቃውያን ነው ነበር ያሉት። እንደገና ብዙ ቃልም ገብተዋል። ግን እንደሚታወቀው ብዙሃኑ ደቡብ አፍሪቃውያን፤ በተለይም ጥቁሮች ዛሬም በከፋ ድህነት ነው የሚኖሩት። እናም በመንግሥቱ የአስተዳደርና የኤኮኖሚ ፖሊሲዎች እርካታ እንደማይሰማቸው ግልጽ ነው።

“ትክክል ነው። ጄኮብ ዙማ በበዓሉ አከባበር ላይ እንደገና የማይረባ ንግግር ነው ያሰሙት። ንግግሩ ከአንድ ሰዓት ተኩል በላይ ረጅም ሲሆን ተከታዮቹን ሊቀሰቅስ የቻለ አልነበረም። ዲስኩሩ እንዳበቃ ወዲያው ስታዲዮሙ በከፊል ባዶ ነበር የሆነው። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የዕለቱ ጠንካራ ሙቀት ብቻ አልነበረም። የንግግሩ አታካችነት ጭምር እንጂ! እንደተለመደው ሁሉም ነገር እንደሚሻሻል፣ ANC ከሥልጣን ትግሉ እንደሚላቀቅና በሙስና ላይ ጥብቅ ትግል እንደሚደረግ ቃል ተገብቷል። ግን እነዚህ ሁሉ ያላንዳች ለውጥ ለዓመታት ሲባሉ የቆዩ በመሆናቸው ሕዝቡ ሊሰማቸው አይፈልግም። እና በተጨባጭ ድርጅቱ ወዴት ነው የሚያመራው? ይሄ ጨርሶ አይታይም። የቀድሞ ታሪኩና ስኬቱ ብቻ ነው አሁንም የሚነሣው”

በጆሃንስበርግ “ሜይል ኤንድ ጋርዲያን” የተሰኘው ቀደምት የደቡብ አፍሪቃ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የሆኑት ኒክ ዶውስም ANC ብዙ የኤኮኖሚ ፖሊሲዎችን ቢያስተዋውቅም ውጤቱ የተጠበቀውን ያህል እንዳልሆነ ነው የሚናገሩት።

“ዕውነት ነው፤ ለአብዛኞቹ ደቡብ አፍሪቃውያን በኤኮኖሚ ረገድ የተደረገው ዕርምጃ በጣም ቀስተኛ ነው። በብዙ አቅጣጫ የኋልዮሽ ሂደት ነው የተደረገው። በአገራችንና በዓለም ኤኮኖሚ ላይ የተፈጠረው መዋቅራዊ ለውጥም አገሪቱ ከአፓርታይድ በኋላ ዕውነተና ለውጥ ማድረጓን ማክበዱም አልቀረም። ግን ይህ የአስተዳደር ጉድለት አለበረም ማለት አይደለም። የአፍሪቃው ብሄራዊ እንቅስቃሴ በመሠረቱ ብዙ ጠቃሚ የኤኮኖሚ ፖሊሲዎችን አስተዋውቋል። ግን ለውጡን ገቢር ማድረጉ ብዙም አልሰመረለትም። ብዙሃኑ ደቡብ አፍሪቃውያንም ይህን ሙስናና የበላይ ተጽዕኖ ለኑሮ ሁኔታቸው መሻሻል መሰናክል እንደሆነ አድርገው ነው የሚመለከቱት”

የወቅቱ ሃቅ እንግዲህ ይህ ሲሆን ANC በክብረ-በዓሉም ሕዝቡን የሚስብ ወይም የሚያንቀሳቅስ አዲስ ነገር አላቀረበም። የአፍሪቃው ብሄራዊ እንቅስቃሴ የወደፊት ሂደቱን የሚጠቁም ራዕይም ሆነ ግልጽ ያለ ዕቅድ የለውም ቢባል ማጋነን አይሆንም። እናም አገሪቱ ወዴት እንደምትጓዝ ከወዲሁ እንዲህ ብሎ መናገሩ ሲበዛ ያስቸግራል። በተለይ ደጋፊዎቹን እያስቆጣና ከድርጅቱ እያራቀ በመሄድ ላይ ያለውም ይሄው ነው።

“በግምት 25 በመቶው የደቡብ አፍሪቃ ሕዝብ ዛሬ ሥራ አጥ ነው። በወጣቱ ዘንድ እንዲያውም የሥራ አጡ ቁጥር 50 በመቶ ይጠጋል። ከዚሁ ሌላ ከ 350 ሺህ የሚበልጡ ደቡብ አፍሪቃውያን የኤይድስ ሰለቦች ሆነዋል። ANC ለምሳሌ በተለየ ፖሊሲ፤ እንበል ለዘብተኛ በሆነ የሥራ ሕግ ብዙዎችን በሙያ ማሰማራት በቻለ ነበር። ጥሩ በሆነ አጠቃላይ የኤይድስ መከላከያ ፖሊሲም እንዲሁ ብዙዎችን ማትረፍ ባልገደደ! ሌላም ችግር አለ። በትምሕርት ረገድም 80 በመቶው የመንግሥት ትምሕርት ቤቶች የተሟላ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ሆነው አይገኙም። ባለፉት 17 እና 18 ዓመታት እንግዲህ እሢያን ትተን ሌሎች የአፍሪቃ አገሮች እንኳ የተሻለ ስኬት ባገኙ ነበር”

ሆኖም ብዙ የኤኮኖሚ ጠበብት ዛሬ ደቡብ አፍሪቃን በተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገት ከሚራመዱት ብራዚልን፣ ቻይናን፣ ሕንድንና ሩሢያን ከመሳሰሉት በአሕጽሮት ብሪክ በመባል ከሚጠሩት ሃገራት ጋር ነው የሚመድቡት። ደቡብ አፍሪቃ እርግጥ ለተፋጠነ ዕድገት የሚያበቃ የተፈጥሮ ሃብትና ሰፊ የሥራ ጉልበት እንዳላት ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ አገሪቱ እንደ ብሪክ ሃገራት በእርግጥ ከፍተኛ የኤኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ እንድትበቃ መሠረታዊ የኤኮኖሚ ፖሊሲ ለውጥ ማድረጓ ግድ የሚሆን ይመስላል።

“ደቡብ አፍሪቃ ከብሪክ ሃገራት ጋር አብራ መጠቀሷ በግድ አንድ የአፍሪቃ አገርን በስብስቡ ላይ ለማከል በመፈለጉ ነው። ብራዚል በደቡብ አሜሪካ ወይም ሕንድና ቻይና በእሢያ በፍጥነት ነው የሚያድጉት። እያንዳንዱ የእሢያ አገር ከቪየትናም አንስቶ እስከ ታይላንድና ኢንዶኔዚያ ድረስ ዛሬ አፍሪቃ ውስጥ ጠንካራ ከሚባሉት በበለጠ መጠን ከፍተኛ የኤኮኖሚ ዕድገት የሚያስመዘግብ ነው። ደቡብ አፍሪቃ በበኩሏ መዋዕለ ነዋይን በመሳብ ዕድሉን ሳትጠቀምበት ቀርታለች”
በወቅቱ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ማዕድኖችንና ባንኮችን በመንግሥት ዕጅ የማስገባት ክርክር እየተካሄደ ሲሆን ይህ ፖሊሲ ደግሞ የግል ባለሃብቶችን ብርቱ ፍርሃቻ ላይ መጣሉ አልቀረም። ውጤቱም የጀርመኑ የንግድ ጋዜጣ የኬፕታውን ወኪል ቮልፍጋንግ ድሬክስለር እንደሚያመለክተው ጎጂ የሚሆን ነው የሚመስለው።

“ከ 2004/2005 አንስቶ የጥሬ ዕቃው ጥሩ ንግድ ለዘብ እስካለበት እስከ 2008/9 ዓ.ም. ድረስ ሁሉም ጥሬ ሃብት ያላቸው ሃገራት፤ እንበል ቺሌ፣ አውትራሊያ፣ ካናዳ በአማካይ ከአምሥት እስከ ስድሥት በመቶ የኤኮኖሚ ዕድገት አሳይተዋል። ደቡብ አፍሪቃ በአንጻሩ በያመቱ አንድ በመቶ ዕድገት እያጣች ነው የመጣችው። ችግሩ እዚህ ላይ ነው። መዋዕለ-ነዋይን የሚስብ ፖሊሲ ማስፈን አልተቻለም። እናም ደቡብ አፍሪቃ ከሌሎቹ ላይ ለመድረስ ከፈለገች ፖሊሲዋን መለወጡ ግድ ነው የሚሆንባት። ሌላው ነጥብ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የመንግሥት ተቀጣሪዎች ደሞዝ ከመጠን በላይ እያደገ መሄድ ነው። ባለፉት ሶሥት ዓመታት ከኑሮው ውድነት መጠን በላይ ከ 10 እስከ 12 በመቶ ነው ያደገው። በዚሁ ጊዜ ምርታማነት ደግሞ ስምንት በመቶ ቀንሷል። ይህ እንግዲህ ደቡብ አፍሪቃ ከእሢያና ደቡብ አሜሪካ አንጻር ለፉክክር እንድትበቃና ዕውነተኛ የብሪክ አካል እንድትሆን ከተፈለገ መለወጥ ይኖርበታል”

የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት ፖሊሲ ተቺዎች አገሪቱ ከአምራችነት ይልቅ ፍጆተኝነት ያመዘነባት ናት ይላሉ። በሌላ አነጋገር መንግሥት ከምርት ይልቅ የፍጆት ባሕልን እያስፋፋ ነው። ታዲያ ይህ የአገሪቱ የኤኮኖሚ ዕድገት እንዲጠነከር ከተፈለገ የግድ መለወጥ የሚኖርበት ጉዳይ ነው የሚመስለው።

“ትክክል! ቁስሉን በትክክል ነው ያመለከትከው። ደቡብ አፍሪቃ ይበልጥ አምራች የኤኮኖሚ ዘርፍ ያስፈልጋታል። በአንጻሩ ግን ፍጆቱ ነው ዛሬ ጎልቶ የሚታየው። በመሠረቱ ጥሩ ዕርምጃ ያደረጉት ከጥሬ ሃብት የሚያገኙትን ገቢ የሚቆጥቡና መዋዕለ-ነዋይ የሚያደርጉ ሃገራት ናቸው። እዚህ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ግን ይህ የሚገባውን ያህል አልሆነም። ለዚህም ነው የመንግሥት ተቀጣሪዎች ደሞዝ መነሣቱ! እዚህ ላይ ገንዘብ ዝም ብሎ እንዲወጣ ነው የተደረገው። በአንጻሩ መዋቅራዊ ፕሮዤዎችን ለማራመድ የሚገባውን ያህል ቁጠባ አልተደረገም። ችግሩ እንግዲህ ይህ ነው። አምራቹን ዘርፍ፤ ለምሳሌ 60 በመቶውን የውጭ ንግድ ገቢ የሚያስገኘውን የማዕድእን ዘርፍ ማጠናከር ይገባል። ግን በወቅቱ የሚደረገው ተጻራሪው ነው”

እንደ ኒክ ዶውስ ከሆነ ደቡብ አፍሪቃን በተፋጠነ ዕድገት በሚገኙት አገሮች መጠን ለማራመድና ለምሳሌ ሥራ አጥነትን የመሳሰሉ የአገሪቱን ዓበይት ችግሮችን ለመቋቋም ገና ብዙ ነው የሚቀረው።

“የደቡብ አፍሪቃን ዕድገት ሥራ አጥነትን በሚገባ ለመቋቋም ወደሚፈለገው ስድሥትና ሰባት ከመቶ ዕድገት ደረጃ ለማድረስ ብዙ ነገሮች መደረግ አለባቸው። ይህም መዋቅራዊ መሻሻልን፣ ከላይ ወደታች የሚደረግ የፖለቲካ ተጽዕኖንና ከሁሉም በላይ ደግሞ ከአፓርታይድ በኋላ ሰፍኖ የሚገኘውን የትምሕርት ስርዓት ድክመት ማስወገድን ጭምር የሚጠቀልል ነው። የትምሕርቱ ስርዓት በወቅቱ በፖለቲካ ተጽዕኖ ሳቢያ ደካማ ሆኖ ነው የሚገኘው። ከዚሁ ጋር የጤና ጥበቃው ሁኔታም መሻሻልን ይጠይቃል”

የአፍሪቃ ብሄራዊ እንቅስቃሴ ወደፊት አገሪቱን በብልጽግና አቅጣጫ ለማራመድ ከፈለገ አሁኑኑ በውስጡ አስፈላጊውን የተሃድሶ ለውጥ ማድረግ ይኖርበታል። ችግሩ አንዴ ኔልሰን ማንዴላ አገሪቱን ሊያደርሷት ወዳሰቡት ደረጃ ለመምራት ርዕዮቱም ሆነ ቁርጠኝነቱ ያለው መሪ መኖሩ በወቅቱ ጎልቶ አለመታየቱ ነው።

መሥፍን መኮንን


አርያም ተክሌ


ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ