1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ድህረ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ሁከት በጋቦ

ዓርብ፣ ነሐሴ 27 2008

በጋቦ መዲና ድህረ ፕሬዚደንታዊውን ምርጫ ተከትሎ ሁከት ከተፈጠረ ወዲህ፣ 26 የተቃዋሚው ቡድን ፖለቲከኞች የተቃዋሚውን ዋና ጽሕፈት ቤት ለቀው እንዳይወጡ ተከለከሉ።

https://p.dw.com/p/1Jugk
Gabun Libreville Ausschreitungen nach Wahlen
ምስል Reuters/Life Africa TV

በጋቦ ፕሬዚደንት አሊ ቦንጎ ያለፈው ቅዳሜ ምርጫ አሸናፊ መሆናቸው ከትናንት በስቲያ ይፋ ከሆነ በኋላ በመዲናይቱ ሊብረቪል ለተካሄደው ሁከት የተቃዋሚው ቡድን መሪ ዦን ፒንግ ተጠያቂ ናቸው ሲሉ የመንግሥት ቃል አቀባይ አላ ክሎድ ቢሊ ቢ ንዜ ወቀሳ አሰሙ። ቢሊ ቢ ንዜ ለራድዮ ፍራንስ አንተርናስዮናል እንዳሉት፣ በፕሬዚደንታዊው ምርጫ በጠባብ የድምፅ ብልጫ የተሸነፉት ፒንግ ከምርጫው በፊት አስቀድመው ያዘጋጁትን ሕዝቡ አደባባይ እንዲወጣ የነደፉትን የሁከት እቅድ ተግባራዊ አድርገዋል። ውጤቱ ይፋ ከሆነ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ የፒንግ ደጋፊዎች በሀገሪቱ ምክር ቤት ዙርያ የሚገኙ መደብሮችን ሰባብረዋል፣ አካባቢውንም እሳት አጋይተዋል፣ በእሳት ከጋዩት መካከል የምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ፖል ቢዮግሄ ምባ መኖሪያ ቡት ይገኝበታል። የፀጥታ ኃይላት በሁለት ቀኑ ሁከት ከ1,100 የሚበልጡ ሰዎችን ፣ ከነዚህም ወደ 800 የሚጠጉት በመዲናይቱ፣ የተቀሩት 300 ገደማ ደግሞ በሌላ የሀገሪቱ አካባቢዎች ማሰራቸውን የጋቦ ሀገር አስተዳደር ሚንስትር ፓኮም ሙቤሌ አስታውቀዋል። ከዚህ በተጨማሪም የፀጥታ ኃይላቱ ዛሬ ንጋት ላይ በሊብረቪል የሚገኘውን የተቃዋሚውን ቡድን ዋና ጽሕፈት ቤት ባጠቁበት ድርጊት ሁለት ሰዎችን መግደላቸውን እና በርካቶችን ማቁሰላቸውን የፈረንሳይ ዜና ወኪል አስታውቋል። ሽንፈታቸውን እንደማይቀበሉ ያስታወቁት የ73 ዓመቱ ዦን ፒንግ ምርጫውን በተከተሉት የመጀመሪያ ቀናት ገለልተኛ ባሉት የድምፅ ቆጠራ መሰረት አሸናፊ መሆናቸውን ገልጸው ነበር። የጋቦ አስመራጭ ኮሚሽን ትናንት ይፋ ባደረገው ውጤት መሰረት፣ ፕሬዚደንት አሊ ቦንጎ 49,8% የመራጭ ድምፅ በማግኘት ለተጨማሪ የስልጣን ዘመን ተመርጠዋል። 48,2% ድምፅ ያገኙት የተቃዋሚው ቡድን ተፎካካሪያቸው ዦን ፒንግ መንግሥት ምርጫውን አጭበርብሮዋል በሚል ውጤቱን ውድቅ አድርገውታል። የፈረንሳይ ፕሬዚደንት ፍራንስዋ ኦሎንድ ድህረ ፕሬዚደንታዊው ምርጫ ሁከት አውግዘው ፣ ሕዝቡ እንዲረጋጋ ጥሪ አቅርበዋል።

አርያም ተክሌ

አዜብ ታደሰ