1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርት

ድህነቱ አንገት ያስደፋው ግን ያላሸነፈው ተማሪ ታሪክ

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 6 2010

የዛሬው የወጣቶች ዓለም እንግዳችን አንድ በዝቅተኛ ኑሮው ምክንያት ተምሮ ጥሩ ቦታ ለመድረስ ብዙ ፈተናዎችን ማለፍ የነበረበት ወጣት ታሪክ ነው። በልጅነቱ ብዙ ትንኮሳ ፣ ስድብ እና መገለል ስለደረሰበት ትክክለኛ ስሙን ባይገልፅልን መርጧል። ለዚህ ዘገባ ግን ትዕግስቱ እያልን እንጠራዋለን።

https://p.dw.com/p/2p9Mk
Figur Straße
ምስል Fotolia/giz

ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው። ትምህርቱንም በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ተከታትሎ እንደጨረሰ ከአዲስ አበባ ዮንቨርስቲ በመምህርነት ተመርቆ ዛሬ በተመረቀበት የሙያ መስክ በማገልገል ላይ ይገኛል። እዚህ ቦታ እስኪደርስ ግን መንገዱ እጅግ ፈታኝ ነበር። « አባቴ ልጅ እያለ ነው የሞተው። እናታችን ጥጥ እየፈተለች፣ ቆሎ እየሸጠች ያሳደገችን። ሀይ ስኩል እየተማርኩ ሁሉ በባዶ እግሬ ነበር ትምህርት ቤት የምሄደው።»

የችግሩም ሁኔታ ትምህርቱ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ፈጥሮበት ነበር። ትግስቱ ብዙውን ጊዜ ቁርስ ሳይበላ ነበር ጠዋት ትምህርት ቤት የሚሄደው። ቁርስ አለ የተባለ ቀን ደግሞ ወይ ቆሎ ወይ ቂጣ አፉ ላይ አድርጎ ነው ከቤት የሚወጣው።  « አንዳንዴ ምሳችንም ቆሎ ሊሆን ይችላል።እንጀራ የሚባል 15 ዓመት እስኪሆነኝ ድረስ እቤታችን ውስጥ አይቼ አላውቅም ነበር»

ትግስቱ ከሁለት ታላላቅ እህቶቹ ጋር ነው ያደገው። እናታቸው በደርግ ጊዜ ይሰጥ ከነበረው መሰረተ ትምህርት በስተቀር ትምህርት አልተማሩም። ቢሆንም ሶስቱም ልጆቻቸው ጠንክረው እንዲማሩ ይደግፏቸው እንደነበር ልጃቸው ትግስቱ ይናገራል።

Stadtansicht von Addis Abeba, Äthiopien
ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው።ምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

አዲስ አበባ ዮንቨርስቲ እስኪገባ ድረስ በድህነቱ ምክንያት ብዙ ፈተናዎችን ያሳለፈው ትግስቱ፤ ሌሎቹ የበሉትን ፣ሌሎቹ የጠጡትን እና የለበሱትን አድሮጎ ለማደግ ትምህርቱን ማቋረጥ እንደ አማራጭ ያሰበበትም ጊዜ ነበር። ይሁንና አላቋረጠም። ዛሬ መምህር ሆኖ ያገለግላል። አቅሙ የፈቀደውን ያህል እንደሱ በችግር ውስጥ ሆነው የሚማሩ ተማሪዎችን ይደግፋል። ልጅ እያለ ከትምህርቱ ጎን መስራቱም እንደጠቀመው ይናገራል። ለቤተሰቡ ኃላፊነት ተሰምቶች ሳይሆን እሱ እንደሚለው ድህነት ያስተማረው ቀናነት ነው።

ትግስቱ ዛሬ ባለ ትዳር እና የአንድ ልጅ አባት ሆኗል። ተምሮ ራሱን እና ቤተሰቡን ማስተዳደር እስከሚችል ድረስ ያለፈበትን ህይወት ስላካፈለን እናመሰግናለን። እናንተም ሌሎች ወጣቶችን ያጠነክራል፣ ያበረታታል፣ ወጣቶች ሊወያዩበት ይገባል የምትሉትን ጉዳይ ፃፉልን። መድረካችን ክፍት ነው።

ልደት አበበ