1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ድርቅ ያጠቃቸው የአፍሪቃ ሃገራት

ሐሙስ፣ የካቲት 17 2008

ኤሊኞ የተባለው የአየር ንብረት በበርካታ የአፍሪቃ ሃገራት ጉዳት አስከትሏል ። ዓመታት እየጠበቀ የሚከሰተው ኤሊኞ አንዳንድ ሃገራትን ለድርቅ ሲያጋልጥ የተወሰኑትን ደግሞ ለውሃ ማጥለቅለቅ ዳርጓል ። ኤሊኞ ከባድ ጉዳት ካደረሰባቸው የአፍሪቃ ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ ሞዛምቢክ አንጎላ ዚምባብዌ ማላዊ እና ደቡብ አፍሪቃ ይገኙበታል ።

https://p.dw.com/p/1I2S4
Hunger Dürre Kinder Afrika
ምስል picture-alliance/dpa/S. Morrison

[No title]

በኢትዮጵያ የተመድ እንዳስታወቀው ከ10 ሚሊዮን በላይ ህዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልገዋል ። የእርዳታ ፈላጊው ቁጥር በቅርቡ በእጥፍ ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል ። መንግሥት ፈጣን የምጣኔ ሃብት እድገት ማስመዝገቡን በሚያስታውቅበት በአሁኑ ሰዓት ብብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ለምግብ እጥረት መጋለጡ እያነጋገረ ነው። የኤሊኞ የአየር ንብረት ለውጥ ሰዎችን ለምግብ እጥረት እስከሚያጋልጥበት ደረጃ ድረስ መጠበቅ አልነበረበትም የሚሉ አሉ ። ሆኖም ኢትዮጵያ አሁን ከ1980ዎቹ በተሻለ ድርቁ ያስከተለውን ችግር ለመቋቋም አስፈላጊ ዝግጅት ማድረጓን ቦን በሚገኘው የልማት ጥናት ማዕከል ተመራማሪ ኦሊቨር ኪሩ ያስረዳሉ ።
«የኢትዮጵያ መንግሥት በበርካታ ለጋሾች እርዳታ ድርቁን በተሻለ ሁኔታ ለመቋቋም አስፈላጊ እርምጃዎችን ወስዷል ። ካለፈው በተሻለ መንግሥት በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች አንድ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ ለማከፋፈል አቅዷል ። ድርቁ ሊያስከትላቸው የሚችሉ ችግሮችን ለመቋቋም ከቀድሞው የተሻለ ዝግጅት አድርጓል ።»
ቢርጊት ሞርገንራት እንደዘገበችው በአንዳንድ ሩቅ በሚባሉ አካባቢዎች በቅርቡ መንገዶች በመሠራታቸው በድርቅ ወደ ተጎዱት አካባቢዎች በቀላሉ እርዳታ ማድረስ ይቻላል ። ሆኖም የተመድ በኢትዮጵያ በተከሰተው ድርቅ ለተገዱ መርጃ የሚውል 1.4 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ቢያሳውቅም መንግሥት እስከ አሁን ከለጋሾች ያገኘው ገንዘብ ወደ 590 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ብቻ መሆኑ አሳስቧል ።
ሞዛምቢክ ደግሞ ከወራት አንስቶ ጽንፍ በያዙ ሁለት ዓይነት የአየር ንብረቶች ችግር ውስጥ ወድቃለች ። በደቡብ ሞዛምቢክ ግማሽ ሚሊዮን ያህል ህዝብ በከፋ ድርቅ ሲሰቃይ ሰሜናዊው ክፍል ደግሞ ከባድ ዝናብ ጉዳት አስከትሎበታል ።እስካሁን ጎርፍና መብረቅ የ45 ሰዎች ህይወት አጥፍቷል ።በመላ ሞዛምቢክ ቁጥሩ 77 ሺህ የሚጠጋ ህዝብ ለምግብ እጥረት ተጋልጧል ። የሞዛምቢክ ሚኒስትሮች በተፈጥሮ አደጋ ችግር ውስጥ ለወደቁ ሰዎች መርጃ የአንድ ቀን ደሞዛቸውን ሰጥተዋል ።መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በመላ ሃገሪቱ ችግሩን ለመቋቋም ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ናቸው ።በማላዊ 2.8 ሚሊዮን ሰዎች ለከፋ ረሃብ ተጋልጠዋል ። በሃገሪቱ በጎርፍ ምክንያት ባለፈው ዓመት ሰብል አልያዘም ። የተመ የህጻናት መርጃ ድርጅት UNICEF እንደሚለው መንግሥት ችግሩን መቋቋም አልቻለም ። ኦክስፋም የተባለው የእርዳታ ድርጅት ባልደረባ ክሌር ሲዋርድም የማላዊ መንግሥት እየጣረ ቢሆንም ችግሩን መቋቋም ተስኖታል ይላሉ ።
« በማላዊ መንግሥት ለችግሩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል ። በማቀድና በቅድሚያ ማስጠንቀቂያ በኩል አስቀድሞ ተዘጋጅቷል ። ሆኖም ሙሉ በሙሉ ለችግሩ መድረስ አልቻለም ። ግን ካለፉት ዓመታት በተሻለ ሁኔታ አቅደዋል ።»
ወደ አንጎላ ስንሻገር በደቡባዊ አንጎላ ከድርቅ ጋር የሚካሄደው ትግል አራተኛ ዓመቱን አስቆጥሯል ። በአንጎላ ወደ 750 ሺህ ያህል ሰዎች በድርቅ ተጎድተዋል ። ህጻናት ግንባር ቀደም ተጠቂዎች ናቸው ።በአንጎላ ድርቅ ያስከተለውን የምግብ እጥረት ለመቋቋም ፣ የተመድና የአውሮጳ ህብረት ከ12 ሚሊዮን ዩሮ በላይ መለገስ እንዳለባቸው ተዘግቧል ።በዚምባብዌም በሃገሪቱ የቅርብ ጊዜ ታሪክ አስከፊ የተባለ ድርቅ ገብቷል ። ከህዝቡ አንድ አምስተኛው ወይም 13 ሚሊዮን የዚምባብዌ ዜጎች በምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ነው ። በዚህ የተነሳም የፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ መንግሥት እህል በብዛት ከውጭ እየሸመተ ነው ። መንግሥት የ1.5 ሚሊዮን ዶላር ዓለም ዓቀፍ እርዳታ ጠይቋል ።
ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በተከሰተው ድርቅ ሰበብም ወደ 50 ሺህ የሚጠጋ ህዝብን ለድህነት መዳረጉ ተነግሯል ። ሃገሪቱን የመታው ድርቅ በመቶ ዓመት ታሪኳ እጅግ የከፋ ተብሏል ። መንግሥት ችግሩን ለመቋቋም የሚውል 20 ሚሊዮን ዩሮ መድቦ ነበር ።አሁን ደግሞ ተጨማሪ 60 ሚሊዮን ዩሮ ለማውጣት አቅዷል ። በሃገሪቱ ከፍተኛ የውሃ እጥረት ተከስቷል ። ችግሩ ሰው ሰራሽ ነው ሲሉ የሚከራከሩ አሉ ።

Simbabwe Dürre
ምስል picture-alliance/AP Photo/T. Mukwazhi
Simbabwe Dürre Hilfslieferungen
ምስል Reuters/P. Bulawayo

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ