1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ ወደ “የኩሽ ምድር” ይቀየር የሚለው አነጋግሯል

ዓርብ፣ ሰኔ 16 2009

የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች በዚህ ሳምንት ካተኩሩባቸው ውስጥ ኢትዮጵያ ለድርቅ ተረጂዎች ከሚያስፈልገው እርዳታ ጋር በተያያዘ የተነሱ ጥያቄዎችን፣ በኢህአዴግና የተቃዋሚዎች ድርድር እንደዚሁም ብሔር ተኮር ሽኩቻዎችን በተመለከተ በማህበራዊ ድረ ገጽ አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡ 

https://p.dw.com/p/2fI6n
Äthiopien Mitiku Kassa, the State Minister of Food Security
ምስል DW/Getachew Tedla

ድርቅ፣ ድርድር እና የብሔር ሽኩቻ

ለማህበራዊ ድረ-ገጽ ተጠቃሚዎች ሳምንቱ «ፈዛዛ» የሚባል ነበር፡፡ በሌሎች ጊዜያት እንደተለመደው ብዙዎቹን ተጠቃሚዎች ባንድ ወይም በሌላ መልኩ የሳበ አንድ ትልቅ ርዕሰ ጉዳይ አልነበረም፡፡ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት «ሕገ-ወጥ» ያላቸዉ የዉጪ ዜጎች ከሐገሩ እንዲወጡ የሰጠዉ ቀነ-ገደብ ሊጠናቀቅ ዕለታት በቀረበት ባሁኑ ወቅት በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን ለከፋ ችግር መጋለጣቸዉ ለብዙ ኢትዮጵያዉን አሳሳቢ ጉዳይ  ቢሆንም የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ፀሐፊዎችን ትኩረት ግን አልሳበም።

በአንጻራዊነት ትኩረት ስበው ከሰነበቱት ሁለቱ ሳምንት የተሻገሩ ናቸው፡፡ የዚህ ሳምንት ርዕሰ ጉዳይ ሊባል የሚችለው የድርቅ እርዳታ ጉዳይም ቢሆን ከሳምንት በፊት በመገናኛ ብዙሃን ለተሰራጩ ዘገባዎች የተሰጠ ማስተባበያ ያስከተለው ነው፡፡ በዚሁ ጉዳይ እንጀምር፡፡ 

Äthiopien Schlimmste Hungersnot seit 30 Jahren
ምስል Reuters/T. Negeri

ባለፈው እሁድ ለንባብ የበቃው ሪፖርተር ጋዜጣ ከብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ጋር ሰፋ ያለ ቃለ ምልልስ አካሄዶ ነበር፡፡ የቃለ መጠይቁ ማጠንጠኚያ ደግሞ በሀገሪቱ በተከሰተው ድርቅ ለዕርዳታ ፈላጊዎች የሚሰጠው እርዳታ ጉዳይ ነው፡፡ ከሳምንት በፊት የመንግስት ባለስልጣናት እና የግብረ ሰናይ ድርጅት ኃላፊዎችን ያነጋገሩ ጋዜጠኞች ኢትዮጵያ ከመጪው ሐምሌ ወር ጀምሮ ለተረጂዎች የምታቀርበው የምግብ እርዳታ አይኖራትም ሲሉ ዘግበው ነበር፡፡ በወቅቱም ኮሚሽነር ምትኩ ሀገሪቱ ለአስቸኳይ ምግብ እርዳታ የሚሆን አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደምትሻ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ 

ኮሚሽነሩ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “እርዳታ አለቀብኝ” ያለው የዓለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) መሆኑን ጠቅሰው “ጉዳዩን አጮኸዉታል” ብለው መናገራቸው በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች ዘንድ አልተወደደላቸውም፡፡ “የዓለም የምግብ ፕሮግራም ለዕርዳታ ፈላጊዎች መድረስ ካቃተው መቶ በመቶ እኛ እንሸፍናለን” ሲሉ የተናገሩትም ትችት ቀስቀሶባቸዋል፡፡ 

ገረሱ ቱፋ በፌስ ቡክ በጻፈው አጭር አስተያየት “የሀገሪቱን ህዝብ የመመገብ አቅም ካለህ የምግብ እርዳታ የመጠየቁ ፋይዳው ታዲያ ምንድነው? አሳፋሪ ነው” ብሏል፡፡ ያደሳ ቦጂአ በበኩሉ “በኢትዮጵያ በውጭ እርዳታ ላይ ጥገኛ የመሆን ባህል በጣም የተስፋፋ ነው፡፡ ኮሚሽነሩ እዚህ ‘ዓለም ህዝባችንን መመገብ ካቃተው እኛ እናደርገዋለን’ ይላሉ፡፡ ከተሳሳትኩ አርሙኝ፡፡ እንደማስበው እኛ ራሳችንን መመገብ ካቃተን ዓለም እኛን በመመገብ ይረዳናል እንጂ በተገላቢጦሹ አይደለም፡፡ ይህ እኮ ‘ጎረቤቶቼ ቤተሰቦቼን መመገብ ካቃታቸው እኔ እመግባችዋለሁ’ እንደማለት ነው” ሲል በምሳሌ የኮሚሽነር ምትኩን አገላለጽ ተችቷል፡፡

ኒሞና ቦርቶላ የተሰኙ የፌስቡክ ተጠቃሚ የ“ጉድ አገር” ሲሉ ርዕስ በሰጡት አስተየየታቸው “እኔ የምለው ‘መቶ በመቶ’ የመሸፈን አቅም ካለ ሲጀመር ለምን ወደ ልመና ተሄደ? የእርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር እያሻቀበ፣ ገና ለገና ከዓለም የምግብ ፕሮግራም ይገኛል ተብሎ ማስቀመጥስ ሰዎቹ ምን እስከሚሆኑ ነው የሚጠበቀው? ያው መልሱ እስከሚያልቁ ነው የሚሆነው” ብለዋል፡፡ 

ገዢው ፓርቲ እና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ወደሚመለከተው ሁለተኛው ርዕሰ እንሻገር፡፡

ኢህአዴግ እና 16 ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለድርድር ለመቀመጥ እያካሄዱ የሚገኙትን የማራቶን ቅድመ ውይይት አሁንም ማጠናቀቅ አልቻሉም፡፡ ፓርቲዎቹ ባለፈው ሰኞ በነበራቸው ስብሰባ ለድርድር እንዲቀርቡ ከሚፈልጓቸው 13 አጀንዳዎች ውስጥ ስድስቱን ብቻ በስምምነት አጽድቀዋል፡፡ ባላለቁ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር ለነገ ቅዳሜ ቀጠሮ ይዘዋል፡፡ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተጠቃሚዎች ለድርድር ቀረቡ የተባሉ አጀንዳዎችን አንስተው ሲነጋገሩ ከርመዋል፡፡ 

Symbolbild Facebook Ausfall 27.01.2015
ምስል Reuters/D. Ruvic

ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ “ኢህአዴግ በሕገ መንግስቱ፣ በድንበር ጉዳይ፣ በፖለቲካ እስረኞች ዙሪያ እንደማይደራደር ግልጽ አድርጓል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ በፀረ ሽብር ህጉ፣ የበጎ አድራጎት ማህበራት አዋጅ፣ የዴሞክራሲ ተቋማት አጠቃቀም፣ የፍትህ አካላት አደረጃጀት ላይ እንነጋገር እያለ ነው” ሲል በዜና ዘገባዎች ላይ የተመለከተውን በፌስ ቡክ ገጹ ይጠቅስና እነዚህ ሁለቱ እንዴት እንደሚቃረኑ ያስረዳል፡፡ “ተቃዋሚ የተባሉት 16 ፓርቲዎች መደራደሪያ አጀንዳቸው ‘አበል ማስተካከያ’ ካልሆነ ገዢው እንወያይባቸው፣ እንደራደር ያለባቸው ነጥቦች በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ከላይ የካዳቸው እኮ ናቸው፡፡ ዳሩ ለካ ገዢውም፣ ‘ተቆጪ ነኝ’ ባዩም ሹፈት ይዘው ነው” ይላል፡፡  

ተመሳሳይ ሀሳብ ያንጸባረቁት ቶሌራ ፍቅሩ ገምታ በፌስ ቡክ አስተያየታቸው ኢህአዴግ “ወሳኝ በሚባሉ የህገመንግስት ጉዳዮች፣ የፖለቲካ እስረኞች እና የኢትዮጵያ ድንበር” ላይ አልደራደርም ማለቱን ተችተዋል፡፡ “ኢህአዴግ ትኩረት የሚያስቀይሩ ስትራቴጂዎችን በመቀየስ እና የህዝብ ፍላጎት በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሆን ብሎ ለውጥ በማድረግ የታወቀ ነው፡፡ ኢህአዴግ የፓርቲ ኃይሎችን የውይይት መድረክ የከፈተው በበርካታ የሀገሪቱ ክፍሎች፣ በግልጽ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ከታዩ ተቃውሞዎች በኋላ ካጋጠመው አስፈሪ የፖለቲካ ቀውስ ለማምለጥ ነው፡፡ በአፍሪካ ቀንድ ኃይል የተቀላቀለበት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለመከተል እየዳዳ ያለውም ትኩረቱን በውጭ ጉዳዮች ለመጥመድ በማሰብ ነው” ሲሉ ጽፈዋል፡፡ 

የሕገ-መንግስቱን የተለያዩ አንቀጾች ከማሻሻል እስከ ባህር በር ጥያቄ የተካተቱበትን የተቃዋሚዎችን 13 አጀንዳዎች የተመለከተው ሄኖክ ስዩም ደግሞ ተስፋውን በፌስ ቡክ አጋርቷል፡፡ “መንግስት የህገ መንግስቱን የተወሰኑ አንቀጾች አሊያም አዋጆችን ለመቀየር ወይም ለማሻሻል ፍላጎት ካሳየ ይህ ለኢትዮጵያ መልካም ዜና ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዳሴም ሩቅ አይሆንም፡፡ እነሱ ለሀገሪቱ ነቀርሳ የሆኑ፤ ለጠባብነት፣ ግጭት እና ዘረኝነት ማደግ ምክንያት የሆኑ ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ አንቀጽ 39 እና ብሔር ተኮር ፌደራሊዝም” ሲል ጽፏል፡፡ 

ከአጀንዳዎቹ ሁሉ የብዙዎችን ቀልብ የሳበ የሚመስለዉ ግን በገዳ ስርዓት አራማጅ ፓርቲ የቀረበው ነው፡፡ ፓርቲው “ኢትዮጵያ” የሚለው የሀገሪቱ ስያሜ ወደ “ኩሽ ምድር” ይቀየር ሲል በመደራደሪያ አጀንዳነት ማቅረቡ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተጠቃሚዎች መሳለቂያ ሆኗል፡፡ መረር ካሉቱ ስንነሳ ወንድወሰን ቲኢ በሚል ስም ሀሳባቸውን ያሰፈሩ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ እናገኛለን፡፡ “እነ ዶ/ር መረራንና አንዷለም አራጌን አስሮ፣ እነ ብርቱካን ሚደቅሳን እና ዶ/ር ብርሃኑን ከሀገር አባርሮ፣ ህወሓት/ኢህአዴግ በራሱ አምሳል ጠፍጥፎ ከሰራቸው ተለጣፊ ፓርቲዎች ጋራ የሃገሪቷን ስም ከኢትዮጵያ ወደ ‘ኩሽ ምድር’ ይቀየር፣ አይቀየር በሚል አንገብጋቢ ጉዳይ ላይ ለመደራደር አጀንዳ እያጸደቀ እንደሆነ ዘግይቼ ሰማሁ። የሆኖ ሆኖ ይሄን የሞተ ሃሳብ ያቀረበው ተለጣፊ ፓርቲ የሴሜቲክ ቋንቋ ከሺህ ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ፈልቆ ወደ ተቀረው አለም እንደተስፋፋ ያውቅ ይሆን?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

Äthiopien Verhandlungsrunde zwischen Regierung und Opposition
ምስል DW/Y. Geberegziabeher

ማኮ ቢሊ የተሰኙ ግለሰብ “ኢትዮጵያ የሚለው ስም ወደ ኩሽ ምድር ይቀየር ያለውን ፓርቲ አደንቃለሁ፡፡ ኢትዮጵያ የሚለው ቃል መጤ ወይም ባዕድ ነው” ሲሉ ድጋፋቸውን በፌስ ቡክ ገልጸዋል፡፡  ፈገግታ ወደሚያጭሩት እንለፍ፡፡ ማቭሪ ኤቢ “ኢትዮጵያ የሚለው ወደ ኩሽ ምድር ተቀየረ እንበል (እንበል ነው ) ዜግነት ስንጠየቅ በኢትዮጵያዊ ፋንታ "ኩሽ ምድራዊ" ነው የምንለው? በእንግሊዘኛ ደግሞ - Kushlandian?” ስትል ጠይቃለች፡፡ ኤፍሬም እ. ሀይሉ የተሰኙ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ “ኢትዮጵያ የሚለውን መጠሪያ ወደ ኩሽ ምድር ቀይረን ከጨረስን በኋላ ወደ ግለሰብ ስም ቅየራ ስለምንመጣ ለራሳችሁ የሚሆን በነፍስ ወከፍ ሶስት ሶስት አማራጭ ስሞችን ይዛችሁ እንድትጠብቁን እናሳስባለን” ሲሉ ተሳልቀዋል፡፡

ብዙዎች ሲቀባበሉት የታየው ግን ድሬ ቲዩብ  የስም ቅያሬውን አስመልክቶ ተከታታዩችን በጠየቀ ወቅት የተሰጠ መልስ ነው፡፡ ካሌብ ካሌብ በተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ የተሰጠው መልስ ወደ አንድ ሺህ ሶስት መቶ ገደማ ላይክ አግኝቷል፡፡ ብዙዎችም ወደ የገጾቻቸው ወስደው ለጓደኞቻቸው አጋርተውታል፡፡ “እንደኔ እንደኔ ግን ከቀየርነው አይቀር "የጉድ ሀገር" ብንላት ይሻላል፤ ባይሆን የቤት ስሟን "ኩኩሻ" እንላታለን!! ሆሆሆሆ ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም አሉ!” ብለዋል ካሌብ ካሌብ፡፡

የመጨረሻው ርዕሰ ጉዳያችን በኢትዮጵያውያን የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች የሚዘወተረው ብሔር ተኮር ሽኩቻ ነው፡፡ መልኩን እየቀያየረ በየጊዜው የሚያወዛግበው ይህ ጉዳይ በዚህ ሳምንት በገዢዉ ፓርቲ አንጋፋ ፓርቲዎች (በህወሓትና ብአዴን) አባላትና ደጋፊዎች ጎላ ብሎ ተስተውሏል፡፡ ውዝግቡን ጣራ ያስነካው ደግሞ የአማራ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዩች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን በጉዳዩ ላይ በግል የፌስ ቡክ ገጻቸው ያሰፈሩት አስተያየት ነው፡፡ 

አቶ ንጉሡ የ“ሆርን አፌርስ” ድረ-ገጽ ዋና አዘጋጅ ዳንኤል ብርሃኔ በአማራ ክልል፣ በርዕሰ መስተዳደሩ ገዱ አንዳርጋቸው እና ብአዴን ላይ ያነጣጠሩ መልዕክቶችን እና አጀንዳዎችን በተደጋጋሚ እንደሚለቅ ጽፈዋል፡፡ “ጨዋ አንደበት የተዘጉ በሮችን መክፈት ይችላል” በሚል ርዕስ ስር ጠንከር ባሉ ቃላት ረዘም ያለ አስተያየታቸውን ያቀረቡት አቶ ንጉሱ  “እኛን እየነካካችሁ እናንተ ወደ ቆማችሁበት ጭቃ መሬት አታውርዱን፤ ሁላችንም ወርደን ህዝብ አናበጣብጥ። ይልቁንስ ጊዜያችንን፣ ዕውቀታችንን እና ጉልበታችንን የህዝቡን ችግር ለመፍታት እና ህዝቦችንን ወደ አንድነት በሚያመጡ ተግባራት ላይ ብናተኩር ይሻላል” ሲሉ ጽሁፋቸውን ደምድመዋል፡፡ የእርሳቸው ጽሁፍ በርከት ያለ ድጋፍ እና ተቃውሞ አስከትሏል፡፡ የግለሰቦች ጉዳይ ለምን ወደ ብሄር ደረጃ ያድጋል ሲሉ የጠየቁም ነበሩ፡፡ ለኋለኞቹ ማሳያ የሚሆኑት ተስፋኪሮስ ሳህለ ናቸው፡፡ 

Social Media - Facebook
ምስል picture-alliance/dpa/T. Hase

“መጠየቅ ያለበት ጥያቄ በፖለቲካ ሃይሎች መካከል የሚፈጠረው ያለመግባባት ህዝብ ለምን ተሳታፊ እንዲሆን ይፈለጋል? ህወሓትና ብአዴን ስላልተግባቡ የትግራይና የአማራ ህዝብ መቃቃር አለበት? የፖለቲካ ልዩነት ሲኖር ህዝብ ፍረደን ይባላል እንጂ በየትኛው አግባብ ነው የግጭታችን አካል ሁን ተብሎ ለእልቂት የሚጋበዘው? ብአዴንና ህወሓት ህዝብን ሳያጋጩ ለምን ልዩነታቸውን በመሸናነፍ አልያ በመግባባት ለመፍታት አይሞክሩም? ይኸ ለዘመናት ያለምንም ግጭት ተፋቅሮና ተደጋግፎ የኖረን ወንድማማች ህዝብ የልዩነታችሁና የግጭታችሁ አካል አታድርጉት” ብለዋል ተስፋኪሮስ በፌስ ቡክ ባሰፈሩት ረዘም ያለ ጽሁፋቸው፡፡ 

የውዝግቡ አስኳል የሆነው የአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጉዳይ በየጽሁፉ ሲነሳ ተስውሏል፡፡ እንዳላማው አበራ የ“አቶ ንጉሡ ነገር” ሲሉ በሰየሙት ጽሁፋቸው ላይ “አቶ ንጉሡን ለመውቀስ፣ ብሎም ለማስፈራራት ከተሰለፉት መካከል ሰውየው መልስ የሰጡት አቶ ገዱን ለሰደበ ሰው መሆኑን የጠቀሰ አላየሁም፡፡ ትችቶቹን ብቻ ላነበበ አቶ ንጉሡ በድንገት ከእንቅልፋቸው ነቅተው ለጻፉት ነገር መልስ የተሰጠ ነው የሚመስለው፡፡ ከጠባብነት ቅርቃር ሳንወጣ ምንም አይነት ጤነኛ ውይይት ልናካሂድ አንችልም” ሲሉ ተቺዎችን ተችተዋል፡፡ 

የጸጋይ ሐጎስ አጭር የፌስ ቡክ አስተያየት የአቶ ገዱ ተቺዎች አቋም የት ድረስ ሊሄድ እንደሚችል አመላካች ይመስላል፡፡ “ገዱ አንዳርጋቸውን ጀግና አድርጎ የሚቆጥር ሰው እውነተኛውን ጀግና ሳያይ፣ የጀግኖችን የሕይወት ታሪክ ሳያነብ እና ጀግና ሳይሆን ይህቺን ምድር ይሰናበታል” ብለዋል ጸጋይ፡፡ 
  

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ