1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ድንበር ጥበቃዋን ያጠናከረችዉ አዉሮጳ

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 6 2008

የአዉሮጳ ኅብረት በየአባል ሃገራት መካከል ያለዉ ነፃ እንቅስቃሴ እንዳይሰናከል አጠቃላይ የአዉሮጳን የድንበር ጥበቃ ለማጠናከር አልሟል። ትናንት በጉዳዩ ላይ የመከረዉ ኅብረቱ ይፋ ያደረገዉ አዲሱ የየብስ እና ባህር ጠረፍ ጥበቃ የየትኛዉንም አባል ሀገር ይሁንታ ሳይጠብቅ ተግባራዊ እንዲሆን ወስኗል።

https://p.dw.com/p/1HOOY
Mitglieder von Frontex auf einem Schiff vor der Insel Lesbos Griechenland
ምስል picture-alliance/AP Photo/A.Palacios

[No title]

ዉሳኔዉ በተሰናባቹ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2015 አንድ ሚሊየን ገደማ ጥገኝነት ፈላጊዎች ወደኅብረቱ ሃገራት መግባታቸዉ የፈጠረዉ ግርታ ያስከተለዉ ዉዝግብ ነዉ። በአዲስ መልክ እንደሚጠናከር የተገለጸዉ ፍሮንቴክስ የተሰኘዉ ድንበር ጠባቂ ኃይል የስደተኞች ብዛት ከአቅማቸዉ በላይ ወደሆነ የኅብረቱ አባል ሃገራት ጣልቃ የመግባት መብት ተሰጥቶታል።

Europa Grenze Ungarn Serbien Flüchtlinge Migranten Ankunft Menschenmenge
ምስል Reuters/L. Foeger

የአዉሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት የየብስም ሆነ የባህር ድንበሮቻቸዉን በአግባቡ መጠበቅ ካልቻሉ ኅብረቱ ይህን የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ነዉ ትናንት በጉዳዩ ላይ በመከረዉ የኅብረቱ ጉባኤ የተገለጸዉ። የአዉሮጳ ኅብረቱ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ዣን ክላዉድ ዩንከር አስቀድመዉ ገና በመስረም ወር ነበር የጠናከረ የድንበር ጥበቃ አዉሮጳ እንደሚያስፈልጋት ያሳሰቡት። ለዚህም ፍሮንቴክስ የተሰኘዉ የኅብረቱ የድንበር ጠባቂ ኃይል ተጠናክሮ የአዉሮጳን የየብስ እና የባህር ድንበር እንዲጠብቅ ታቅዷል። በእቅዱ መሠረትም አሁን 500 ሠራተኞች ያሉት ፍሮንቴክስ በቀጣይ አምስት ዓመታት ዉስጥ ተቀጣሪዎቹን በእጥፍ ይጨምራሉ። በየብስ እና የባህር ድንበር ጥበቃ ላይ ለሚሠማራዉ ኃይልም ፈጥኖ የሚደርስ 1,500 ድንበር ተቆጣጣሪ ኃይልም በደጀንነት እንዲዋቀር ታስቧል።

Flüchtlingsschiff Ezadeen vor italienischer Küste 02.01.2015
ምስል picture-alliance/dpa/Icelandic Coast Guard

የአዉሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝደንት ፍራንስ ቲመርማንስ ለአዉሮጳ ፓርላማ ትናንት የድንበር ቁጥጥር እቅዱን ሲያቀርቡ እንደተናገሩት ካለፈዉ ታኅሳስ ወር መጨረሻ አንስቶ ተገቢዉ የይለፍ እና የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸዉ ወይም ለጥገኝነት ጥየቃ ሳይመዘገቡ፣ 1,5 ሚሊየን የሚሆኑ ስደተኞች ወደአዉሮጳ ኅብረት ሃገራት ገብተዋል። ይህ ግን በዚህ መልኩ መቀጠል እንደሌለበት ነዉ ቲመርማንስ ያመለከቱት፣

«ይህ በድንበሮች አጠባበቃችን ላይ የሠራነዉን ስህተት በግልፅ ያሳያል። ሕገወጥ አገባቦቹ በመላ የአዉሮጳ ኅብረት ላይ ተፅዕኖ አሳድረዋል። በርካታ አባል ሃገራት የየግል ድንበር ክልልን ዳግም የመቆጣጠር ርምጃን ወስደዋል። በዉጭዉ ድንበር ላይ የመጣዉ ችግር የሸንገን ሥርዓትን ጥያቄ ላይ ጥሎታል። ሸንገንን ይዘን መቆየት ከፈለግን በዉጭዉ የጋራ ድንበር አጠባበቅ ላይ ያለዉን አሠራር ማሻሻል ይኖርብናል።»

እስካሁን ግን እያንዳንዱ አባል ሃገር በተናጠል በአዉሮፕላን ማረፊያዎችም ሆነ የባህር ወደብን ጨምሮ ድንበሮቻቸዉ ላይ ቁጥጥር የማካሄድ ኃላፊነት ነበረባቸዉ። ለምሳሌ ዳር ላይ ከሚገኙት ሃገራት ግሪክ ስትታይ በበርካታ ስደተኞች ተጥለቅልቃለች፤ በየጊዜዉም የሚገቡት ብዙዎች ናቸዉ። ግን ለረዥም ዓመታት ርዳታ ሳታገኝ ቆይታለች። ይህ ግን ከእንግዲህ ይለወጣል። አንድ አባል ሃገር በዉጭዉ ድንበር በቂ ቁጥጥር ሳያደርግ ቀርቶ፤ ተጠይቆም ያንን ካላደረገ ፈጥኖ ወደዚያ የሚሠማራ ኃይል ይኖራል። በዚህ ላይም የአዉሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ከ28ቱ አባል ሃገራት ጋር መክሮ ይወስናል። ይህን ከወዲሁ ፖላንድ ተቃዉማለች። ርምጃዉ ለፍሮንቴክ ተልዕኮ ሲባል የሉዓላዊነትን አሳልፎ መስጠት ነዉ ሲሉ የተቹት አዲሱ የሀገሪቱ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቪቶል ቫስቼኮቭስኪ፤ የኮሚሽኑ እቅድ አስገራሚና ዴሞክራሲያዊ መቆጣጠሪያ የሌለዉ ነዉ ብለዉታል። በአዉሮጳ ፓርላማ የአረንጓዴዎቹ የዉስጥ ፖለቲካ ተንታኝ ፍራንሲስካ ኬለርም እቅዱን ይተቻሉ፤

Europa Tschechien Drahonice Migranten Flüchtlinge Internierung VARIANTE
ምስል picture-alliance/dpa/L. Zavoral

«በዚህ ምክንያት አባል ሃገራት ስደተኞችን በማስገባታቸዉ ይቀጣሉ ማለት ነዉ። ኮሚሽኑ አባል ሃገራት ሙሉ በሙሉ መዘጋታቸዉን እርግጠኛ መሆን ይፈልጋል። ይህ የአዉሮጳን ሕግ ይቃረናል እንዲሁም ከሰብዓዊ መብት አኳያም ፍፁም ተቀባይነት የለዉም። በተግባርም ሲታይ ምንም ትርጉም አይሰጥም፤ ምክንያቱም ፍሮንቴክስ ከአባል ሃገራት ጋር በቦታዉ ተባብሮ መሥራት ይኖርበታል። ፍሮንቴክስ ከአባል ሃገራት ፍላጎት ዉጭ ወደዚያ የሚላክ ከሆነ ደግሞ ይህ ሊሆን አይችልም ።»

የሉዓላዊነት ጉዳይ አባል ሃገራትን ያሳስባል። ይህን በአግባቡ የሚረዳዉ የኅብረቱ ኮሚሽን በረቂቅ ሕጉ ላይ የፍሮንቴክስ ኃይል እንዲህ ባለዉ አጋጣሚ በሚገባበት ሀገር የሚቆየዉ ለተወሰኑ ቀናት ብቻ ሊሆን እንደሚችል በግልፅ አስፍሯል። እስካሁን የኅብረቱ ሃገራት ዜጎች ከቦታ ቦታ ሲጓዙ የጉዞ ሰነዳቸዉ ጊዜዉ ያላለፈ መሆኑ ብቻ ነበር የሚታየዉ፤ ከእንግዲህ ግን ለዉጦች ይኖራሉ። እያንዳንዱ የጉዞ ሰነድ በኮምፕዩተር መረጃዎች አማካኝነት በስልት ይጣራል። በሸንገን ዉል መሠረት ይህ አልነበረም፤ የኅብረቱ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝደንት ፍራንስ ቲመርማንስ የተጠርጣሪ አሸባሪዎችን እንቅስቃሴ ከመከታተል ጋር በተገናኘ ይህን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል። የጥገኝነት ጥያቄያቸዉ ተቀባይነት ያላገኘ ስደተኞችም የሚሰጣቸዉ ሁሉም አባል ሃገራት የሚያዉቁት የተለየ ወረቀት ለማዘጋጀትም ታቅዷል።ኅብረቱ ከ17 ሃገራት ጋር ጥገኝነት ያልተሰጣቸዉን ስደተኞች ለመመለስ ተስማምቷል። በዓመት 500,000 ተመላሾች እንዲላኩ ቢታቀድም እስካሁን 40 በመቶዉ ብቻ ተግባራዊ መሆኑን የገለፀዉ ኮሚሽን ተግባራዊነቱን ተችቷል። እንዲህ ያሉ ጥገኝነት ያላገኙ ስደተኞቹን በመመለሱ ተግባርም ፍሮንቴክስ እንዲሳተፍ ታቅዷል።

በርን ሪገርት/ ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ