1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዶርትሙንድ የጀርመን ሻምፒዮን

ሰኞ፣ ሚያዝያ 15 2004

በጀርመን ቡንደስሊጋ የእግር ኳስ ውድድር የዘንድሮው ሻምፒዮን ማንነት ሁለት ጨዋታዎች ቀደም ብሎ ሰንበቱን ለይቶለታል።

https://p.dw.com/p/14jnx
ምስል picture-alliance/dpa

በጀርመን ቡንደስሊጋ የእግር ኳስ ውድድር የዘንድሮው ሻምፒዮን ማንነት ሁለት ጨዋታዎች ቀደም ብሎ ሰንበቱን ለይቶለታል። ያለፈው ወደደር ወቅት ሻምፒዮን ቦሩሢያ ዶርትሙንድ በአስደናቂ ሁኔታ ድሉን ሲደግመው በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮንም ሬያል ማድሪድ ለሻምፒዮንነት እየተቃረበ ነው። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ደግሞ ባማኒዩ መሰናከል የተነሣ ፉክክሩ መልሶ እየጠበበ መሄዱ አልቀረለትም።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ላ-ሊጋ የአንዴ የአሥር ነጥብ አመራሩ እየመነመነ መጥቶ አራት ደርሶ የነበረው ሬያል ማድሪድ ስንበቱን በባርሤሎናው ኑው-ካምፕ ስታዲዮም ባካሄደው ከባድ ግጥሚያ ሲያሸንፍ በዚህ መልክ መልሶ ይጠናከራል ብሎ ያሰበ ብዙ አልነበረም። አሠልጣኙ ፖርቱጋላዊው ሆሴ ሞሪኞ ቀደም ሲል ቼልሢይን፣ ኢንተር ሚላንንና በመጨረሻም ሬያል ማድሪድን እየመራ በኑው-ካምፕ ባደረጋቸው ግጥሚያዎች ወደመጣበት የተሸኘው ሁሌም በሽንፈት ነበር።                                                        

ሆኖም አሁን ሬያል ባርሤሎናን ያህል ጠንካራ ተጋጣሚውን ለዚያውም በገዛ ሜዳው ላይ 2-1 ለመርታት ሲበቃ አሠላጣኙን ከማስፈንደቁ ባሻገር አመራሩን መልሶ ወደ ሰባት ነጥቦች ማስፋቱ ሰምሮለታል። ሁለቱን ጠቃሚ ጎሎች ያስቆጠሩት የጀርመኑ በሄራዊ ቡድን ተጫዋች ሣሚ ኬዲራና የፖርቱጋሉ ኮከብ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ነበሩ።                                                

ሮናልዶ በነገራችን ላይ 42ኛ ጎሉን በማስቆጠር ከባርሣ ተፎካካሪው ከሊዮኔል ሜሢ በአንድ ሲበልጥ የዘንድሮውን ውድድር ወቅት ክብረ-ወሰኑን ማስፈቱን እንደቀጠለ ነው። የስፓኝ ሻምፒዮና ሊጠናቀቅ ገና አራት ጨዋታዎች ሲቀሩት በመሠረቱ ባርሤሎናም አንደኛ የመሆን ዕድሉ ገና አለው። ይሁንና ሬያል ዘንድሮ ድሉን አሳልፎ መስጠቱ የማይመስል ነገር ነው። እናም ያለፉት ሶሥት ዓመታት ሻምፒዮን ባርሣ በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ላይ ይበልጡን ከማተኮር ሌላ ምርጫ አይኖረውም።

በአንግሊዝ ፕሬሚይር ሊግ ቀደምቱ ማንቼስተር ዩናይትድ ኤቨርተንን በሜዳው፤ በኦልድ-ትሬፎርድ ስታዲዮም ሁለት-ለባዶ ከመራ በኋላ በመጨረሻ 4-4 ሲለያይ  በአምሥት ነጥቦች ዝቅ ብሎ ይከተለው የነበረው ተፎካካሪው ማንቼስተር ሢቲይ እስክ ሶሥት ነጥቦች ልዩነት እንዲቃረበው በር ከፍቷል። ማንቼስተር ሢቲይ በበኩሉ ግጥሚያ ዎልቨርሃምፕተን ወንደረርስን 2-0 ሲያሸንፍ ይህም የፕሬሚየር ሊጉ ሻምፒዮና መጠቃለያ ወቅት ይበልጥ ማራኪ እንዲሆን ነው ያደረገው።                                                                     

በነገራችን ላይ ኔዘርላንዳዊው የአርሰናል አጥቂ ሮቢን-ፋን-ፐርሢ የዓመቱ የሊጋው ድንቅ ተጫዋች በመባል በእንግሊዝ ፕሮፌሺናል እግር ኳስ ተጫዋቾች ማሕበር ተመርጧል። ፋን-ፐርሢ በዚህ የውድድር ወቅት 27 ጎሎችን በማስቆጠር የፕሬሚየር ሊጉ ቁንጮ ነው። የሊጋው ውድድር ሊጠናቀቅ ሶሥት ግጥሚያዎች ብቻ ሲቀሩ የማንቼስተሩ ክለቦች ፉክክር ደጋፊዎቻቸውን ይበልጥ ልብ የሚሰውር እንደሚሆን አንድና ሁለት የለውም።

Fußball Bundesliga Borussia Dortmund - Borussia Mönchengladbach 32. Spieltag
ምስል picture-alliance/dpa

በሌላ በኩል የጀርመን ቡንደስሊጋ የ 2011/2012 ውድድር ወቅት ሻምፒዮንነት በሂደቱ የመጨረሻውን ቀን ሳይጠብቅ በዶርትሙንድ ዳግም-የበላይነት ከወዲሁ ለይቶለታል። ቦሩሢያ ዶርትሙንድ ባለፈው ቅዳሜ ሻምፒዮንነቱን የደገመው ቀላል የማይባል ተጋጣሚውን መንሸንግላድባህን በተለየ ልዕልና 2-0 በመርታት ነበር። ክለቡ ባለፉት 26 የሊጋ ግጥሚያዎች አንዴም ሳይሸነፍ ለዚህ ስኬት ሲበቃ አሠልጣኙን ዩርገን ክሎፕ በተጫዋቾቹ እጅጉን ነው የኮራው።

በዶርትሙንዱ ቬስትፋሊያ ስታድዮም 80 ሺህ ሕዝብ ተገኝቶ ግጥሚያውን በቀጥታ ሲመለከት አያሌ የክለቡ ደጋፊዎች በአደባባይ ደስታቸውን ገልጸዋል። ሁለተኛው ባየርን ሙንሺን በዶርትሙንድ ድል ሻምፒዮን የመሆን ተሥፋውን ከወዲሁ እንዲቀብር ሲገደድ ሁሉንም እንዳያጣ በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ጠቃሚ ግጥሚያው ላይ ማተኮር ይኖርበታል። እርግጥ በሌላ በኩል ሁለቱ የቡንደስሊጋ ቀደምት ክለቦች ባየርንና ዶርትሙንድ በሚቀጥለው ወር በጀርመን ፌደሬሺን ዋንጫ ፍጻሜ ግጥሚያ ይገናኛሉ። ስለ ቡንደስሊጋው ሁኔታ የዶቼ ቬለን የጀርመንኛ ፕሮግራም ክፍል የስፖርት ጋዜጠኛ አርኑልፍ በትቸርን ቀድም ሲል ሳነጋግር በርሱ ዕምነት የወጣቱ ቡድን የስኬት ሚስጥር በተለይም ተጫዋቾቹ የአሠልጣኑን መርህ በሚገባ መከተል መቻላቸው ላይ ነው።

«የስኬቱ ምስጢር እርግጥ የተጫዋቾቹ ግሩምነትና በተለይ ደግሞ የአሠልጣኑ የዩርገን ክሎፕ የተለየ የመቀሰቀስ ችሎታ ነው። ዩርገን ክሎፕ ቡድኑን ከድል ወደ ድል እያሸጋገረ መምጣቱ ተሳክቶለታል። የራሱን የትግል ሰሜት ወደ ተጫዋቾቹ ማስተላለፉ ሲሰምርለት ተጫዋቾቹም የሚለውን ሁሉ ከመከተል ወደ ኋላ አላሉም። በሚገባ በተግባር ተርጉመውታል። ለምሳሌ ግሩሙ አጥቂ ሌቫንዶቭስኪ፣ ገትሰና ሌሎችም! ዶርትሙንድ አሁን ለሁለተኛ ጊዜ ሻምፒዮን እንዲሆን ያበቁት እነዚህ ሁኔታዎች ናቸው»

በሌላ በኩል ዶርትሙንድ ምናልባትም ከባየርን ሌላ የቅርብ ተፎካካሪ አልነበረውም። በተለይ ብሬመን፣ ሃምቡርግ ወይም ሌቨርኩዝን ዘንድሮ ከሚጠበቅባቸው በታች ሆነው ነው የታዩት። እናም ይህ የዶርትሙንድ ጥንካሬ የቡንደስሊጋው ድክመት ውጤት ሊሆን ይችላል ወይ ለሚል ጥያቄ መንስዔ መሆኑ አልቀረም።

«የጀርመን ቡንደስሊጋ ከሌሎቹ የአውሮፓ ሊጋዎች ሲነጻጸር በመሠረቱ ተጠናክሯል። ለምሳሌ በዩኤፋ የአምሥት ዓመት ድልድል መሠረት ኢጣሊያን ከኋላው አስቀርቷል። ግን እርግጥ ባየርን ሙንሺን ብቻ ነው በአውሮፓው ውድድሮች ከሻምዮናው ሊጋ ግማሽ ፍጻሜ ደርሶ የሚገኘው። ዶርትሙንድ ከውድድሩ ቀድሞ ሲወጣ ሻልከና ሃኖቨርም ከአውሮፓ ሊግ ተሰናብተዋል። ዶርትሙንድን በተመለከት በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ የቡድኑ የአጨዋወት ስልት የበሰለ አልነበረም። ለነገሩ መጥፎ ሆነው አይደለም። ግን የሚገባውን ያህል በማጥቃት ባለመጫወታቸው ነው ቀድመው የወጡት። በሚቀጥለው የውድድር ወቅት ግን  የተለየ አቀራረብ እንደሚኖራቸው አምናለሁ»   

ይህን በጊዜው እንደርስበታል፤ አሁን ወደ ኢጣሊያ ሤሪያ-አ እንሻገርና ጁቬንቱስ ቱሪን ሮማን 4-0 በመሸኘት አመራሩን ወደ ሶሥት ነጥቦች ከፍ ማድረጉ ተሳክቶለታል። ለዚህም ምክንያት የሆነው የሁለተኛው የኤሲ ሚላን ከቦሎኛ በ 1-1 ውጤት መወሰን ነው። ሆኖም ውድድሩ ገና አምሥት ግጥሚያዎች ሲቀሩት የሁለቱ ክለቦች ፉክክርም ባለበት ይቀጥላል።                                                             

በፈረንሣይ ሻምፒዮና ሞንትፔሊየር በሁለት ነጥብ አመራሩ ሲቀጥል ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን አሁንም የቅርብ ተፎካካሪው ነው። ውድድሩ ሊጠናቀቅ ገና አምሥት ግጥሚያዎች ቀርተውታል። ከዚሁ ሌላ በኔዘርላንድ አያክስ አምስተርዳምና በፖርቱጋልም ፖርቶ ያለፈውን ሰንበት ግጥሚያቸውንም በስኬት ሲወጡ ለሻምፒዮንነት በጣሙን እየተቃረቡ ነው።

London Marathon
ምስል AP

አትሌቲክስ

የኬንያ አትሌቶች ሶሥት ወራት ገደማ በቀረው በዘንድሮው የለንደን ኦሎምፒክ የማራቶን የበላይነታቸውን ለማሣየት ቆርጠው የተነሱ መሆናቸውን ባለፈው ሰንበት በቦታው አረጋግጠዋል። ኬንያውያኑ ትናንት በተካሄደው የለንደን ማራቶን ሩጫ በወንዶችና በሴቶችም ሲያሸንፉ የበላይነታቸው ባጣሙን ጎልቶ የታየ ነበር። ከዚህ አንጻር የተቀረው ዓለም አትሌቶች በኦሎምፒኩ ማራቶን የተሻለ ዕድል እንዲገጥማቸው ተሻሽለው መገኘታቸው ግድ ነው የሚሆነው።

በትናንቱ የለንደን ማራቶን በወንዶች ዊልሰን ኪፕሣንግ የአገሩን ልጅ ማርቲን ሌልን አስከትሎ በቀዳሚነት ከግቡ ሲደርስ ጸጋዬ ከበደ ከኢትዮጵያ ሶሥተኛ ወጥቷል። በሴቶች ደግሞ ኬንያውያት ከአንድ እስከ አምሥት ተከታትለው ከግባቸው ሲደርሱ ሜሪይ ካይታኒ ለአሸናፊነት በቅታለች። ከኢትዮጵያ ተፎካካሪዎች አበሩ ከበደ ስድሥተኛና አጸደ ባይሣም ዘጠነኛ በመውጣት ከመጀመሪያዎቹ አሥር አትሌቶች መካከል ለመሰለፍ ችለዋል። 

Tennis Australian Open Djokovic Nadal
ምስል dapd

ቴኒስ

የስፓኙ ዓለምአቀፍ የቴኒስ ኮከብ ራፋኤል ናዳል የሰርቢያውን የዓለም አንደኛ ኖቫክ ጆኮቪችን ትናንት በሞንቴ ካርሎ ፍጻሜ ግጥሚያ በለየለት 6-3,6-1 ውጤት በማሸነፍ ለታላቅ ድል በቅቷል። ድሉን ታላቅ የሚያደርግው ናዳል በስባት ፍጻሜ ግጥሚያዎች በጆኮቪች ከተሸነፈ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ለበላይነት መብቃቱ ነው።  ለስፓኙ ተወላጅ የትናንቱ የሞንቴካርሎ ድል በተከታታይ ስምንተኛው መሆኑ ነበር። ሁለቱ ተጫዋቾች በዓለም የቴኒስ ማዕረግ ተዋረድ ላይ አንደኛና ሁለተኛው መሆናቸው ይታወቃል።

Formel 1 Sebastian Vettel 2012 Bahrain Formel Eins Grand Prix
ምስል Reuters

አውቶሞቢል

ባህሬይን ላይ ሕዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ የአገሪቱን ገዢዎች በወጠረበት ሁኔታ ትናንት ተካሂዶ በነበረው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም ጀርመናዊው የሁለት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን ዜባስቲያን ፌትል በዘንድሮው የውድድር ወቅት ለመጀመሪያ ድሉ በቅቷል። ጸጥታ ጠባቂዎች ባሰፈኑት ከፍተኛ ቁጥጥር ተቃውሞው ከእሽቅድድሙ ስፍራ እንዳይደርስ ማድረጉ ተሳክቶላቸዋል።                                                                      

የአገሪቱ ገዢዎች ባለፈው ዓመት የሕዝቡን የለውጥ እንቅስቃሴ ለመቅጨት የሃይል ዕርምጃ ከወሰዱ ወዲህ ውድድሩን ለማስተናገድ መቁረጣቸው ብዙ ተቃዋሚዎችን አስቆጥቶ የቆየ ጉዳይ ነው። ለማንኛውም ፌትል ከትናንት ድሉ በኋላ በአጠቃላይ ነጥብም መሪ ለመሆን በቅቷል። በባሕሬይኑ እሽቅድድም የፊንላንዱ  ኪም ራይኮነን ሁለተኛ ሲወጣ ሶሥተኛ የሆነው የፈረንሣዩ ሮሜን ግሮስዣን ነው።

በእግር ኳስ ለማጠቃለል ነገና ከነገ በስቲያ የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ግማሽ ፍጻሜ ዙር መልስ ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ።  በነገው ምሽት የስፓኙ ባርሤሎና የእንግሊዙን ክለብ ቼልሢይን የሚያስተናግድ ሲሆን ያለፈውን ዓመት የአውሮፓ ሻምፒዮንነቱን ለማስከበር ዕድል እንዲኖረው የግድ ማሸነፍ ይኖርበታል። ባርሣ በመጀመሪያው ግጥሚያ በቼልሢይ ሜዳ 1-0 መሸነፉ የሚታወስ ነው። እናም ቡድኑ በተለይ ስንበቱን በሬያል ተሸንፎ የስፓኝ ሻምፒዮንነት ዕድሉ  በመመንመኑ ብርቱ ትግል እንደሚያደርግ ይጠበቃል።             

በማግሥቱ ረቡዕ በሚካሄደው በሁለተኛው የሻምፒዮና ሊጋ ግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያ ደግሞ ማድሪድ ላይ ሬያልና የጀርመኑ ባየርን ሙንሺን የሚገናኙ ሲሆን ባየርን በመጀመሪያው ግጥሚያ 2-1 በማሸነፉ ቤርናቤው ስታዲዮም የሚገባው በከፍተኛ የራስ መተማመን መንፈስ ነው። የዶቼ ቬለ የሰፖርት ፕሮግራም ክፍል ባልደረባ አርኑልፍ በትቸር እንደሚያምነውም ባየርን ለፍጻሜ የመድረስ ትልቅ ዕድል ነው ያለው።

«ባየርን በሬያል ማድሪድ የሚፈራ ተጋጣሚ ነው። ስለዚህም ትልቅ ዕድል ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ። የመጀመሪያውን ግጥሚያ በማሸነፉ ቅድሚያውን በመጠቀም በማጥቃት መጫወቱ ጎል ለማስቆጠር በጣሙን ይበጀዋል።  በተለይ ጨዋታው ባዶ-ለባዶ ሆኖ በረዘመ ቁጥር ሬያል መክፈት ሰላለበት ባየርን ጎል የማግባት ጥሩ ዕድል ነው የሚኖረው። በጥቅሉ ባየርን በጠባብ ወጤትም ቢሆን ወደ ፍጻሜው እንደሚያልፍ ነው የማምነው» 

በሌላ በኩል ሬያል ማድሪድ በሜዳው አሸንፎ ለፍጻሜ ለመድረስ ከባድ ትግል እንደሚደርግ የማያጠራጥር ነገር ነው። ምናልባትም የአውሮፓው ሻምፒዮና ሊጋ የፍጻሜ ተጋጣሚዎች ሁለቱ የስፓኝ ክለቦች ሬያልና ባርሣ ሊሆኑ ይችላሉ። በትክክል የሚሆነውን ግን እስከ መጪው ረቡዕ ምሽት ጠብቆ መታዘቡ ግድ ይሆናል።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ