1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመናዊዉ ማርቲን ሉተር ዓለም እንዴት ቀየረ?

ዓርብ፣ ኅዳር 2 2009

የዛሬ 500 ዓመት የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስትያን ሕግጋቶችን በመቃወም 95 ጭብጥ የዝርዝር ሃሳቦችን ያቀረበዉ ጀርመናዊ ማርቲን ሉተር በካቶሊክ ቤተክርስትያን ላይ ተኃድሶን አድርጎ ፕሮቴስታንት የተሰኘዉን ኃይማኖት የመሰረተበት ዓመት እየታሰበ ነዉ።  

https://p.dw.com/p/2SVN9
Deutschland Geschichte Reformation Luthers Thesenanschlag Ferdinand Pauwels
ምስል picture-alliance/akg-images

የማርቲን ሉተር ማንነት

 

 «መተባበር አለብን በሚል አንደኛ በጀርመናዊነታቸዉ ሁለተኛ በኃይማኖትም በሚለያየን ላይ ሳይሆን አንድ በሚያደርገዉ ማተኮር አለብን በሚል ሁሉም የሚያዩት በጥሩ በጎዉ ነዉ»  

የዛሬ 500 ዓመት በሮማ ቤተ ክርስትያን ላይ ትልቅ ለዉጥን ማካሄዳቸዉ ስለሚጠቀሰዉ ስለ ማርቲን ሉተር በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን የኑረንበርግ ቅ/ሥላሴ አጥቢያ ኃላፊ መሪጌታ ዳዊት ከፍያለው የሰጡን አስተያየት ነበር።  የዛሬ 500 ዓመት በካቶሎካዊት ቤተ - ክርስትያን ላይ ከፍተኛ ተሃድሶ በማድረጋቸዉ ሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስትያ ለሁለት ተከፍላና የፕሮቴስታንትን እምነት በመመሥረታቸዉ የሚታወቁት  ጀርመናዊዉ የሥነ-መለኮት  ፕሮፊሰር ፤ ማርቲን ሉተር፤ 95 ጭብጦች የያዘዉና ለተኃድሶ መንስዔ የሆነዉን የከፍተኛ ተቋም መመረቅያ ጥናታቸዉን ያቀረቡበት 500 ኛ ዓመት ጀርመንን ጨምሮ በተለያዩ የአዉሮጳ ሃገራት ካለፈዉ የጎርጎሪዮሳዊዉ የዘመን አቆጣጠር ጥቅምት 31  ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች እየታሰበ ነዉ። ይህ ለአንድ ዓመት የሚዘልቀዉ  የተለያዩ ዝግጅቶችን ያካተተዉ ሥነ-ስርዓት በሚቀጥለዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ጥቅምት 31፤  2017 ዓ,ም ተሃድሶዉ የተካሄደበትን 500 ኛ ዓመት በማክበር እንደሚጠቃለል ታዉቋል። ለመሆኑ ጀርመናዊዉ የሥነ-መለኮት ትምህርት ፕሮፊሰር ማን ናቸዉ? 

Gutenberg Museum in Mainz
በማርቲን ሉተር በ15 ኛዉ ክፍለ ዘመን ከላቲን ቋንቋ ወደ ጀርመን የተተረጎመዉ መጽሐፍ ቅዱስምስል picture-alliance/dpa/dpaweb

የዛሬ 500 ዓመት በጎርጎሪዮስ የዘመን ቀመር ጥቅምት 31፤ 1517 ዓ,ም ጀርመን ቪተንበርግ ከተማ ዉስጥ ነበር። በቤተ-ክርስትያኒቱ የተካሄደዉ ይህ ዉይይት ግን በጀርመን፤ በአዉሮጳ ብሎም በዓለም ዙሪያ እንደ የቤተ-ክርስትያን ተኃድሶ ነዉ የተወሰደዉ።  በቤተ-ክርስትያኒትዋ በተካሄደዉ የመጨረሻ  ዉይይት ላይ ደግሞ የሉተር 95 አቅጣጫ አስያዥ ጭብጦች በጀርመንኛዉ « Thesen »ይፋ ሲሆኑ ከፍተኛ ዉዝግብ ተቀስቅሶ ነበር። እንደ ታሪክ ማኅደራት አሁን እነዚህን ዉዝግቦች ለመረዳት የዚያን ጊዜዉን ሁኔታ ተመልሶ መቃኘትና መረዳት ያስፈልጋል። ማርቲን ሉተር  ማንም የማይደፍራቸዉን የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን ተጠሪን አልፈዉ ይህን ጥያቄ ያነሱ የማይደፈረዉንም ባህል የደፈሩ፤ ብሎም በጥያቄያቸዉ መሠረትም ምንኩስናዉን የተዉ አብዮተኛ መሆናቸዉን፤ በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን የኑረንበርግ ቅ/ሥላሴ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ኃላፊ መሪጌታ ዳዊት ከፍያለው ያስረዳሉ።

« በዝያን ጊዜ የማይደፈረዉን የካቶሊክ ሊቃነ-ጻጻሳትን ፤ የቤተክርስትያኒትዋን ባህልና ተለምዶ ዉሉ ሁሉ ወደ ጎን ገሸሽ በማድረግ ትልቅ አብዮት ያካሄደ ነበር። ለጀርመናዉያን በተለይ የፕሮቴስታንት እምነትን ለሚከተሉት ማርቲን ሉተር ኩራታቸዉ ነዉ። ለዚህም ነዉ ዘንድሮ የማርቲን ሉተር በቤተ-ክርስትያንዋ ተኃድሶ ያደረገበትን ጭብጥ ጽሑፎች ያቀረበበትን 500 ኛ ዓመት እያከበረና እየታሰበ የሚገኘዉ። በአጠቃላይ ካቶሊክ ቤተ-ክርስትያን ይዛዉ ያለችዉን ማለትም በምንኩስና ብቻ ሕጋዊ ክህነትን መቀበል አስፈላጊ አይደለም የሚሉና ሌሎችንም የተለያዩ 95 ጭብጦች በጽሑፍ ይፋ ያደረገበት ወቅት ነዉ። ይህ ዓይነቱ በእምነት ላይ የተደረገ አብዮት በዝያን ጊዜ የሚታሰብ አልነበረም። የአሁኖቹም የወንጌላዊት ቤተ-ክርስትያን አማኞች ቢሆኑ ማርቲን ሉተርን እንደ ተምሳሌት ነዉ የሚያዩት። ማርቲን ሉተርን የካቶሊኩም ሆነ የኦርቶዶክሱ እምነት ተወካይ ይቃወመዋል፤ ነገር ግን በፕሮቴስታንቱ ዓለም የማይደፈረዉን ደፍሮ አጠቃላይ የሚለያይንና አገልግሎትም እንዳይስፋፋ የሚያደርግ እገዳን አድርጎለታል። ለምሳሌ ክህነት ያላገባና ድንገላዊ የሆነ የሚለዉን አሁንም የካቶሊክ ቤተክርስትያን ተግባራዊ የሚያደርጉትን ሕግ ዉድቅ ያደርጋል። የካቶሊክ ቤተ-ክርስትያን ይህን ሕግ አለማሻሻልዋ የካህን እጥረት አላቸዉ። እና ይህን ማርቲን ሉተር እስቀድሞ ከ 500 ዓመት በፊት ደፍሮ በአደባባይ ተቃዉሞታል። ከዝያም የነበረበትን የካቶሊክ እምነት የምንኩስና ሕይወት ትቶ አንዲት መነኩሴ ሴትንም ከምንኩስናዋ እንድትለቅ አድርጎአል። ይኸዉም ሕጋዊነት ኃጥያት አይደለም  ሲል ነበር የሚናገረዉ። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ቃል እንደገባን እናስፋፋለን ሲል አብዮት አካሄደ።  ይህ አብዮት የተካሄደበትን ዓመት በማስታወስ ማለት የዛሬ 500 ዓመቱን በማስታወስ በተለያዩ ከተማዎች በተለያዩ አብያተ ክርስትያናትም የሱ መታሰብያ እየተደረገለት ነዉ። »

Lutherstadt Eisleben Luthers Geburtshaus
ማርቲን ሉተር ተወልደዉ ያደጉበት ቤት በጀርመን አይዝሌብን ከተማ ይገኛል። ምስል picture-alliance/dpa/P. Endig

ከዝያን ጊዜ ወዲህ ይሆን ፕሮቴስታንት የሚለዉ ኃይማኖት የመጣዉ?   የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን የኑረንበርግ ቅ/ሥላሴ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ኃላፊ መሪጌታ ዳዊት ከፍያለው አዎ ሲሉ ይመልሳሉ፤

« አዎ ከዝያ በኋላ ነዉ። ፕሮቴስታንት የሚለዉ ቃል የመጣዉ «protest»  ተቃዉሞ ከሚለዉ የመጣ ነዉ ። ፕሮቴስታንት ኃይማኖት ከመጣ በኋላ ለክርስትና አዳዲስ ቅርንጫፍ እየተፈጠረ መጣ። እዚህ ላይ ትልቁ ስህተት መጽሐፍ ቅዱስን ከመንፈሳዊ አኳያ ማንኛዉም የመሰለዉ ጋዜጠኛዉ ሁሉም የሚተረጉመዉ ቃል አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊ ስለሆነ በፀሎትና ከእግዚአብሔር ጋር በመገናኘት የሚገለጥ ነዉ እንጂ፤ እንደዉ በምርምር የሚገኝ አይደለም። ማርቲን ሉተር ግን ሁሉ ሰዉ በተረዳዉ በሚፈለገዉ መንገድ መከተል ይችላል ስላለ ፤ ሁሉም በተረዳዉ መልክ እየተነሳ አንዱ በዚህ መልክ ሌላዉም በዝያ መልክ እያለ ዛሬ ብዙ ብዙ ቅርንጫፍ በተለያየ ስም የሚጠሩ የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስትያናት ይገኛሉ።  ይህ በእዉነቱ በእምነቱ ላይ ያመጣዉ ትልቁ ጉድለት ነዉ። »            

አዲሱ ዘመን ከመጀመሩ በፊት በመካከለኛዉ ዘመን ማብቂያ ላይ እምነትን በሚመለከት ለየትኛዉም ጥያቄ ማንኛዉንም ዓይነት መልስ የምትሰጠዉም ሆነ ጫና ማሳረፍ የምትችለዉ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ነበረች። እንደ ታሪክ መዛግብት ካቶሎክ የሚለዉ ቃል ሲተረጎም « ሁሉን ያቀፈ ሁሉን የያዘ»  እንደማለት ነዉ። ጀርመናዉያን ማርቲን ሉተርን ታሪክን የለወጡ በማለት ይገልጿቸዋል  ያሉን ምሥራቅ በርሊን ውስጥ ተማሪ የነበሩት እና ጀርመን ሲኖሩ ከ31 ዓመት በላይ ያስቆጠሩት አቶ መስፍን አማረ፤

Lucas Cranach der Ältere: Martin Luther als Mönch (Ausschnitt)
ማርቲን ሉተር ካቶሊካዊ መነኩሴ ሳሉምስል picture-alliance/akg-images

« ጀርመናዉያን ማርቲን ሉተርን ታሪክን የለወጠ ሲሉ ነዉ ያሚያምኑት። በዝያን ጊዜ የነበረዉን የካቶሊክ ቤተ-ክርስትያንን ስርዓት በመቃወም ክርስትና ታሪክ ዉስጥም ለዉጥን አምጥቶአል። የወንጌላዊት ቤተ-ክርስትያንን የመሰረተዉ ሰዉ እሱ ነዉ። ዛሬ በጀርመን ሃገርም ሆነ በተለያዩ የዓለም ሃገሮች የወንጌላዊት ቤተክርስትያን ተብለዉ ያሉት እምነቶች እንዲሁም በሚሊዮን የሚቆጠሩ አማኞች የሚከተሉትን መንገድ የጣለ ሰዉ ነዉ። እናም ጀርመናዉያን ዜጋቸዉ ስለሆነ እንደማንኛዉም የእምነት ሰዉም ሆነ ፈላስፋ ያከብሩታል፤ ስለዚህ በጀርመን ታሪክ ዉስጥ ትልቅ ሚናን ይጫወታል» 

የማዕድን ማዉጫ ከነበራቸዉ ቤተሰብ በጎርጎረሳዉያኑ 1483 ዓ,ም በጀርመን አይስሌብን በተባለች ከተማ የተወለዱት ማርቲን ሉተር ገና ከልጅነታቸዉ ጀምሮ ብሩህና በሳል አዕምሮ እንደነበራቸዉ ይነገራል። ማርቲን ሉተር ወደ ከፍተኛ ተቋም ለመግባት የሚያዘጋጃቸዉን ትምህርት ኤርፉርት ዩንቨርስቲ አራት ዓመታት ከተከታተሉ በኋላ በዩንቨርስቲ የሕግ ትምህርትን መማር ጀመሩ። በዚሁ ዩንቨርስቲ ዉስጥ ሳሉ ማርቲን ሉተር በሕይወታቸዉ አንድ ትልቅ የሚሉት ነገር ተከሰተ። ይኸዉም በጎርጎረሳዉያኑ ሐምሌ፤ 1505ዓ,ም ከፍተኛ ዉሽንፍርና መብረቅ የቀላቀለዉ ዝናብ ገጥሞአቸዉ፤ የመብረቅ ኃይል ወርዉሮ ከጣላቸዉ በኋላም፤ በሕይወታቸዉ ገጥሞአቸዉ የማያዉቅ ፍርሃት እንዳደረባቸዉ እሞታለሁ ብለዉ ስጋት እንዳደረባቸዉም ታሪካቸዉ ያሳያል።  

እንደ ታሪክ መዝገባቸዉ ከዝያም ጊዜ በኋላ ቤተሰቦቻቸዉ የማዕድን ድርጅት ዉስጥ የሚሰሩትን ሰራተኞች ትጠብቃለች ተብላ ለምትታመነዉ ለቅድስት ሃና እንድትረዳቸዉና ከረዳቻቸዉም መነኩሴ እንደሚሆኑ ተሳሉ። በተሳሉ በ12ኛዉ ቀን ጀርመን ኤርፉርት ከተማ የሚገኘዉን አጉስቲነር የተባለዉን ገዳም በር ማንኳኳታቸዉ ተዘግቦላቸዋል። እዚህ ላይ ማርቲን ሉተር በመጀመርያ ወደ ምንኩስና ዓለም እንዲሄዱ ያበቃቸዉ ፍራቻ እንደሆነ ፤ ቀደም ሲልም የምንኩስና ሕይወትን መኖር ከፈጣሪ ምህረት ይገኛል የሚል እምነት ነበራቸዉም ተተርኮአል። ማርቲን ከምንኩስናዉ ሕይወት የወጡት ራሳቸዉ መሆናቸዉን የሚናገሩት መሪጌታ ዳዊት ከፍያለው፤

Papstbesuch Erfurt Lutherzelle Augustinerkloster Flash-Galerie
ማርቲን በመነኩሴ ሕይወት የኖሩባት ክፍልምስል DW

« ማርቲን ሉተር ከሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን የወጡት ራሳቸዉ ናቸዉ፤ ተባረዉ አይደለም። ቤተ-ክርስቲያኒትዋም ለየቻቸዉ እሳቸዉም በራሳቸዉ ወገን ደጋፊያቸዉን አበጁ ፤ በታያቸዉ መንገድም ወንጌልን እሰብካለሁ ብለዉ፤ ወንጌልን በራሳቸዉ መንገድ ማስተማር ጀመሩ ብዙ ተከታይም አገኙ። አብያተ-ክርስትያናትም አብረዉ ተከትለዉት ስለነበር ፤ ቤተ-ክርስትያኖችን ግማሹን ለነሱ እያደረጉ መጠቀም ጀመሩ። በተለይ በምስራቁ ክፍል የሚገኘዉ የካቶሊክ ቤተ-ክርስትያናት ሁሉ በማርቲን ሉተር ተከታዮች ተወስደዋል፤ እስከ ዛሬም የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች የሚያመልኩበት ስፍራ ነዉ።»  

ጀርመናዉያን ማርቲን ሉተርን እንዴት ይገልፁታል?   

ማርቲን ሉተር እና ጀርመናዉያን ለመናገር በኃይማኖት በኩል ለይተን መናገር ያስፈልገናል። ጀርመናዉያን ስንል ካቶሊካዉያን አሉ ጀርመናዉያን ስንል ፕሮቴስታንቶች አሉ። እንደተባለዉ ለፕሮቴስታንቶቹ ኩራት ስለሆነ እንደታላቅ ሰዉ አድርገዉ ነዉ የሚያዩዋቸዉ። ለዚህም ነዉ እንግዲህ  «EKD» የሚባለዉ በጀርመን አቀፍ የወንጌላዊት አብያተ-ክርስትያናት ኅብረት ታላቅ በዓል አድርጎ የተለያዩ የክርስትና እምነት ተከታዮች በበዓሉ ላይ እየተገኙ ንግግር እያደረጉለት ነዉ። ስለዚህ እምነቱን በይፋ ተቃዉሞ አይደረግበትም በፊት ግን የተወገዘ ነበር።  አሁን ግን መወጋገዝ ሳይሆን ልዩነትን አስወግዶ አንድነትን በሚያመጣዉ ላይ አብረን መተባበር አለብን በሚል፤ አንደኛ በጀርመናዊነታቸዉ ሁለተኛ በኃይማኖቱም አንድ በሚያደርገዉ ላይ በመካከር ሁሉም በቀና ነዉ የሚያዩት»    

በአሁኑ ሰዓት ለአጭር ጉብኝት ቦን በሚገኘዉ የዶይቼ ቬለ ዋና ስቱድዮ የሚገኘዉ የስቶክሆልሙ ወኪላችን ቴድሮስ እንደገለችልን ደግሞ ማርቲን ሉተር በካቶሊካዊት ቤተ-ክርስትያን ላይ ተኃድሶ ያደረገበትና ተገንጥሎ የወጣበትን 500ኛ ዓመት በማስመልከት የሮማዉ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስትያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ወደ ስዊድን መጥተዉ ለ 500 ዓመታት ተራርቀዉ የቆዩት አብያተ-ክርስትያናት ልሉነታቸዉን ለማስወገድ ጥረት በማድረግ አብረዉ ለመስራት ዝግጁነታቸዉን  በፊርማ አጽድቀዋል ሲል ነግሮናል።

Deutschland Augustinerkloster in Erfurt
ማርቲን ሉተር የነበሩበት ኤርፉርት ጀርመን የሚገኘዉ አጉስቲነር ገዳምምስል picture-alliance/dpa/M. Schutt

የኃይማኖት ሳይንስ ምሁሩ ማርቲን ሉተር ከምንኩስናዉ ዓለም ወጥተዉ አዲስ ኪዳንን ወደ ጀርመንኛ ተርጉመዋል። ትርጉሙ ደግሞ ቤተ-ክርስትያኒትዋ እንደምትናገረዉ ወይም እንደምትገልፀዉ አንድ በአንድ በመዉሰድ የተተረጎመ ሳይሆን ሕዝቡ በሚነጋገርበት ማለትም ሕዝቡ በሚገባዉ መንገድ በመተርጎሙ፤ ማርቲን ሉተርን በመከተል ከሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስትያን እምነት የወጣዉ ምዕመን ጥቂት እንዳልነበር በታሪክ ማኅደራቸዉ ሰፍሮአል። ማርቲን ሉተር አዲስ ኪዳንን ሲተረጉም የጠቀመበት ቋንቋ ለአሁኑ ዘመን ጀርመንኛ መሻሻል እና እድገት ትልቅ አስተዋጽዖ ማድረጉ ይጠቀሳል።

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ