1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመንና የአታላንታ ተልእኮ፣

ዓርብ፣ ግንቦት 3 2004

አታላንታ በሚል ስያሜ ፣ ከአውሮፓው ኅብረት የተውጣጣው የባህር ኃይል፣ በሁለት ዐበይት ዓላማዎች ሳቢያ ከሶማልያ ጠረፍ ፈንጠር ብሎ በአደን ባህረ-ሰላጤ፣ ከተሠማራ 2 ዓመት ሆኖታል። የመጀመሪያ ዓላማው ፣ በድርቅና ረሃብ ለተጎዳው የሶማልያ

https://p.dw.com/p/14u8p
ምስል picture-alliance/dpa

አታላንታ በሚል  ስያሜ ፣ ከአውሮፓው ኅብረት የተውጣጣው የባህር ኃይል፣ በሁለት ዐበይት ዓላማዎች ሳቢያ ከሶማልያ ጠረፍ ፈንጠር ብሎ በአደን ባህረ-ሰላጤ፣  ከተሠማራ  2 ዓመት ሆኖታል። የመጀመሪያ ዓላማው ፣ በድርቅና ረሃብ ለተጎዳው የሶማልያ ህዝብ ፣ ዓለም አቀፍ እርዳታ እንዲደርሰው ማብቃት ሲሆን  ፣ ሁለተኛው፣  በየዕለቱ አያሌ የንግድ መርከቦች የሚመላለሱበትን የባህር መሥመር አስተማማኝ  ማድረግ  ነው። በዚያው በአደን ባህረ ሰላጤ 340 የባህር ኃይል ወታደሮች ያሠማራችው ጀርመን የኅብረቱ ባህር  ኃይል  በዚያ እንደተሠማራ የሚቆይበትን ጊዜ ፣ ፓርላማዋ ትናንት  በድምጽ ብልጫ እንዲራዘም አድርጓል። የባህር ኃይሉ እርምጃ፣  በባህር ላይ ውንብድናን መታገል ብቻ ሳይሆን፣ ከጠረፍ አልፎ ፣ በየብስ 2 ኪሎሜትር ድረስ ዘልቆ በመግባት  የወንበዴዎችን ምሽጎች በማጥቃት ጭምር  ያተኩራል። ስላአከራካሪው ውሳኔ ፤ የቀረበውን ዝግጅት ተክሌ የኋላ እንደሚከተለው ሰብስቦታል።
የጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት(ቡንደስታኽ) ትናንት ውሳኔ ባሳለፈበት ዕለት፤ አንድ ፣

Einsatz Atalanta zur Bekämpfung der Piraterie am Horn von Afrika
ምስል picture-alliance/dpa

ንብረትነቱ የግሪክ የሆነና 135,000 ሜትሪክ ቶን ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት የጫነ መርከብ ፤ ከዖማን በስተምሥራቅ 480 ኪሎሜትር ገደማ  ርቀት ላይ  ተጠልፏል። የሶማልያ የባህር ላይ ወንበዴዎች፤ ባለፈው 2011 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ብቻ 230 ጊዜ ነው ጥቃት የሠነዘሩት። የአውሮፓው ኅብረት የአታላንታ ተልእኮ አድሚራል፤  ብሪታንያዊው ዳንከን ፖትስ፤ የአታላንታ የ ሁለት ዓመታት ተግባር  በአመዛኙ አዎንታዊ እንደነበረ ነው የገለጹት። ባለፈው ዓመት ፤ ከጥር እስከ ሃምሌ፤  የባህር ላይ ወንበዴዎቹ  28 ጊዜ የጠለፋ እርምጃቸው ቢሳካላቸውም ፣ ከሃምሌ እስከ ታኅሳስ  ግን 3 ጊዜ ብቻ ነበረ ማከናወን የቻሉት። የአታላንታ ተልእኮ ይበልጥ ቢስፋፋ የተሻለ ውጤት እንደሚገኝ ፣ የአውሮፓው ኅብረት አባል መንግሥታት፤ እዚህም ላይ የጀርመን መንግሥት የሚያምንበት እንደመሆኑ መጠን ፤ በፓርላማ በሰፊው ከተከራከረበት በኋላ፣ የአታላንታ ሥምሪት እንዲራዘም በድምፅ ብልጫ ወስኗል። በጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ም/ቤት(ቡንደስታኽ)የሶሺያል ዴሞካራቱ ፓርቲ የህዝብ ተወካዮች የመከላከያ ጉዳዮች ቃል አቀባይ ራይነር አርኖልድ፤


1,«ጥያቄው ተጠናክሮ የቀረበው፣ ከብሪታንያ ተባባሪዎቻችን በኩል ነው። ብሪታንያዊው አዛዥ፣  አድሚራል ፖትስ፣   እንደሚያሰላስሉት፤ የአታላንታን ተልእኮ ማስፋፋቱ፤ በባህር ላይ ወንበዴዎቹ ላይ የሥነ ልቡና ተጽእኖ የሚያሳድር ነው።»
ራይነር አርኖልድ፣ ብቻ አይደሉም የጊዜውን መራዘም የተቃወሙ። አረንጓዴዎችና   የግራ ፈለግ ተከታዮችም የአታላንታን  ተልእኮ መራዘም ፣ ሊቀበሉት የሚገባ ጉዳይ አይደለም ነው ያሉት።  
የባህር ላይ ወንበዴዎችን በባህር ላይ ብቻ ሳይሆን በአየርም መከታተል እንደሚቻልና ጠረፍ አካባቢ በየብስ 2 ኪሎሜትር ያህል ዘልቆ በመግባት የወንበዴዎቹን ተቋማት ፤ የቤንዚን ማካመቻ ማዕከላትና ጀልባዎች ዒላማ በማድረግ  ስንቅና ትጥቅ እንዳይኖራቸው መጣሩ ያን ያህል አይገድም በማለት የ ክርስቲያን ኅብረት(CDU)ፖለቲከኛ ፊሊፕ ሚስፌልደር እንዲህ ብለዋል።
3,«መረጃው አለ። በከፊል በአየር አሰሳ በማድረግ መረጃውን መሰብሰብ አያዳግትም። በሌላ መረጃ ማግኛ ዘዴም፤ ጠረፍ አካባቢ የባህር ላይ ወንበዴዎቹን  ምሽጎች፣  ጀልባዎቻቸውና መርከቦቻቸውም የት እንዳሉ  ለይቶ ማወቅ ይቻላል።»

Piraterie Bildergalerie
ምስል picture-alliance/dpa


በለንደን ኪንግስ ኮሌጅ፤ በአፍሪቃው ቀንድ የፀጥታ ጉዳይ ምርምር የሚያደርጉት EVA STRICKMANN በአውሮፓው ኅብረት ከሁለት ጎራ የተከፈ ቡድን መኖሩን  ሲገልፁ--
«በአታላንታው ተልእኮ በመሳተፍ ላይ ከሚገኙት፣ የአውሮፓው ኅብረት አባል መንግሥታት መካከል ኔደርላንድ፤ ፈረንሳይና ብሪታንያ፤  በባህር ላይ ብቻ ሳይሆን በየብስም እርምጃ መውሰድ ተገቢ ነው የሚል ጽኑ አቋም ያላቸው ሲሆን፤ ጀርመንን የመሳሰሉ መንግሥታት ደግሞ ፤ በዚህ ጥያቄ ላይ ለዘብ ያላ አቋም ነበረ ሲያሰሙ የቆዩት።»
ኤቫ እሽትሪክማን እንደሚሉት ከወታደራዊ እርምጃ አኳያ ጠንከር ያለ እርምጃ እንውሰድ የሚሉት ትክክል ሊሆኑ ይችላሉ። በሌላ በኩል ፣ የባህር ላይ ወንበዴዎቹ ፣ ስልታቸውንም ምሽጋቸውንም  መቀያየር የሚችሉ መሆናቸውን መዘንጋት አይገባም ባይ ናቸው።  የባህር ላይ ወንበዴዎቹ ሌላም እርምጃ መውሰድም አይሳናቸውም ። የባህር ላይ ወንበዴዎቹ ፣ይላሉ ኤቫ፤

Piraterie Bildergalerie
ምስል picture-alliance/dpa


«  በጠረፍ የሚኖረውን ህዝብ፤ ሊያስተባብሩት ይችላሉ። የጠረፉን ቦታ ጠንቅቀው ነው የሚያውቁት። በቀጥታ በባህር ላይ ውንብድናው የማይሳትፉ ሰዎችንም በተለያዩ ጠቃሚ ትብብሮች ማሳተፍም ሆነ መጠቀም ይችላሉ። »
እሽትሪክማን ከዚህ ጋር በማያያዝ፣ የአሸባብ ሚሊሺያ ጦረኞች፣ በተለይ በፑንትላንድና በሰሜን ምሥራቅ ሶማሊያ ይበልጥ በመንቀሳቀስ የአካባቢውን የማረጋጋት እርምጃ መቅኖ ሊያሳጡት ይችላሉ ነው የሚሉት።
ግራም ነፈሰ ቀኝ ፤  አካባቢውን ለዘለቄታው ለማረጋጋት፣ ሶማልያ ወደፊት ሥርዓት ያለው መንግሥት መመሥረት ይኖርባታል። የአውሮፓው ኅብረት እ ጎአ  ከ 2008 ዓ ም አንስቶ ለልማት 400 ሚሊዮን ዩውሮ ያህል ገንዘብ ሰጥቷል። እንደ ኤቫ እሽትሪክማን ግምገማ፤ የፖለቲካ ው ሥራ  ነው የበለጠ  ትርጓሜ የሚኖረው። በሶማሊላንድና ፑንትላንድ የተሻለ አካባቢያዊ አስተዳደር የተዘረጋ ሲሆን ፤ ይህን  ከአካባቢያዊ  ወደ ብሔራዊ ደረጃ እንዲሸጋገር ማድረግ ይበልጥ ይበጃል።

Deutsches Marineschiff Bayern unterwegs nach Afrika
ምስል picture-alliance/dpa

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሰ