1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን በናሚቢያ ፤ የፈጸመችው ግፍ

ሐሙስ፣ መጋቢት 20 2004

እ ጎ አ ከ 1884-1915 የጀርመን ቅኝ ግዛት በነበረችውና በ 1990 ነጻነቷን በተጎናጸፈችው ናሚቢያ፣ ከ 70,000 በላይ የሄሬሮ፤ እንዲሁም 10,000 የናማ ብሔረሰብ አባላት የተገደሉበት ድርጊት፤ የጀርመንን የህዝብ እንደራሴዎች ም/ቤት

https://p.dw.com/p/14Uwp
ምስል ullstein bild

አሁንም፣ በማከራከር ላይ ነው።   

ጀርመን ለምንድን ነው በቅኝ ገዥነት ታሪኳ ይህን የታሪክ ሃቅ መቀበል የሚከብዳት? የዶይቸ  ቨለ ባልደረባ፣ ዮሐና ሽሜለር ያቀረበችውን ዘገባ ተክሌ የኋላ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል።

«በጀርመን  ዳር-ድንበር ግዛት ውስጥ፣ እያንዳንዱ ሄሬሮ፣ ጠብመንጃ ያዘ-አልያዘ፤ ከብቶች ይኑሩት-አይኑሩት፣ በጥይት ይገደላል። ከእንግዲህ ሴቶችንና ህጻናትን  አልቀበልም። እንደገና ከወገኖቻቸው ጋር እንደዲቀላቀሉ አድርጉ፤ ወይም በጥይት በሏቸው!»

Berlin Rückgabe der Schädel aus Namibia
ምስል picture-alliance/dpa

ይህ፤  ከጀርመናዊው ጀኔራል ሎታር ፎን ትሮታ እ ጎ አ  ጥቅምት 2 ቀን 1904 ዓ ም የተላለፈ ትእዛዝ ነበር። ትእዛዙ ፣ በጀርመን የቅኝ ግዛት ታሪክ፣ የዘግናኝ ድርጊት መርኅ ነበር ማለት ይቻላል። የቅኝ ግዛቱ ዘመን ካለፈ ወዲህ፤ የጀርመንን የያኔ ተግባር መለስ ብሎ የሚመረምር ተጣማሪ ቡድን ፣የተሰኘው ድርጅት ባልደረባ ክርስቲያን ኮፕ፤---

«የህዝብ ጭፍጨፋ የሚለው ቃል መጠቀስ ይገባዋል ተብሎ ተነስቷል። የያኔው መመሪያ ያመላክታልና!  ሄሬሮዎችንና  ናማዎችን ከገጸ-ምድር ለማጥፋት ግልጽ የሆነ አመለካከት እንደነበረ የአዛዡ ጀኔራል ትእዛዝ ያስረዳል።»

ባለፈው የካቲት ወር ማለቂያ ገደማ ላይ፣ የጀርመን  የግራ ፈለግ ተከታይ ፓርቲ  የህዝብ እንደራሴዎች ለፓርላማው ማመልከቻ ፣ በፓርቲው የህዝብ እንደራሴዎችመሪ ኒማ ሞቫሳት በኩል ቀርቦ ነበር።

«በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎችተሠቅለዋል። በጥይት ተደብድበዋል። ወደ በረሃ እንዲጓዙ ተገደው የውሃ ምንጮችም በኃይል ተይዘውባቸውና ተክልክለው በጥም እንዲያልቁ ተደርጓል። በታጎሩበት ጣቢያ ከባድ ሥራ ማከናወን ግዴታቸው ነበር። ስለዚህ፤ ለዚህ ሁሉ ድርጊት፣ ኀላፊነት መሸከም ተገቢ ነው። የህዝብ ጭፍጨፋ የተካሄደበትን  ግልጽ ታሪክ እስካሁን አምኖ መቀበል አልተፈለገም። ይፋ ይቅርታም አልተጠየቀም። »

Namibia Geschichte Aufmarsch gegen aufständische Herero
ምስል picture-alliance/dpa

በሄሬሮዎች ላይ  ጭፍጨፋ የተካሄደው  በ 1904 እና 1905 ዓ ም መካከል ነው። የናሚቢያ ጉዳዮች ተመራማሪ ባለሙያ፤ በአሽቶክሆልም ፣እስዊድን የዳግ ሐመርሾልድ ድርጅት ባላደረባ ፣ Henning Melber –

«ቅኝ  ገዥዎች የነበሩ መንግሥታት ሁሉ  ለሌላው ወገን ስሜት ፍጹም  ደንታ አልነበራቸውም። በደቡብ ምዕራብ አፍሪቃ(ናሚቢያ) የጀርመንን አያያዝ የተለዬ የሚያደርገው በግልጽ ጦርነት በማካሄድ በዛሬው ዘመን መለኪያ፤ የህዝብ ጭፍጨፋ መካሄዱ ነው። ድርጊቱ፤ በድብቅ የተከናወነ አልነበረም። በያኔው የጀርመን ንጉሣዊ መንግሥት፤ደቡብ ምዕራብ አፍሪቃ ትባል የነበረችው ቅኝ ግዛት ጉዳይ ዋና ርእሰ-ጉዳይ  ሆኖ ነበረ የቀረበው። የአገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃውያንም  ሄሬሮዎችንና ናማዎችን ከገጸ-ምድር ለማጥፋት በይፋ ተናግረው እርምጃ ተወስዷል። »

በ 2004 (እ ጎ አ) ጭፍጨፋው የተካሄደበት 100ኛ ዓመት ሲታሰብ፤ ያኔ ወደ ናሚቢያ ተጉዘው በዚያ የተገኙት ፣ የጀርመን የሶሺያል ዴሞክራቱ ፓርቲ አባልና የልማት ተራድኦ ሚንስትር የነበሩት ወ/ሮ ሃይደማሪ ቪቾሬክ ሶይል፣ አቤቱ በደላችንን ሁሉ ይቅር በለን---»የሚለውን የአቡነ ዘበሰማያት ጸሎት መሰል ልብ የሚነካ፣ ፀፀት አዘል ንግግር አሰምተው ነበር። ይሁንና ፣ንግግራቸው መንግሥትን የሚወክል ሳይሆን የግል አቋም ነው ተባለ።

Namibia Hererofrau mit traditionellem Kopfputz
ምስል picture-alliance/dpa

ለናሚቢያ፤ ሰፊ የልማት እርዳታ መስጠት እንጂ«ካሣ» የሚለው ቃል በአመዛኙ እንዲጠቀስ የሚደለግ አይመስልም። የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ የህዝብ እንደራሴ Egon Jüttner  ደግሞ፣ የተለየ አቋም ነው ያላቸው። 

« በህዝብ ጭፍጨፋ ሳቢያ ቅጣት እንዲሰጥ ዓለም አቀፍ ስምምነት የተደረገው በ 1948 ዓ ም ነው። ጀርመን ፤ የውሉን ደንብ ተቀብላ አባል የሆነች በ 1955 ነው። እናም የጀርመን ፌደራል  መንግሥትበናሚቢያ የተካሄደውን የህዝብ ጭፍጨፋ በይፋ አምኖ አይቀበለውም። እርግጥ ለናሚቢያ አንድ ነገር ማድረግ ተገቢ ነው። ካሣውን በከፍተኛ የልማት እርዳታ ማካካስ ነው። አሁንም ቢሆን በነፍስ- ወከፍ ከተገመገመ ፣ እጅግ ላቅ ያለውን የጀርመን የልማት እርዳታ የምታገኝ አገር ናሚቢያ ናት።»

በ ናሚቢያ ረዘም ላለ ጊዜ የተቀመጡት ሄኒንግ ሜልበር፤ የናሚቢያው የቅኝ ግዛት ዘመን የታሪክ ምዕራፍ ገና እልባት አልተደረገለትም ነው የሚሉት።

Gerda Meuer, Direktorin der DW Akademie Windhoek, Namibia
ምስል Julian Funk

«በናሚቢያ የጋራ የሆነ፣ ያለፈውን የህዝቡን ታሪክና የተሠራበትን ግፍ የሚያስታውስ ንቃተ-ኅሊና አለ። በቃል የተላለፈው ታሪክ፣ በህዝቡ ልቡና ውስጥ አለ። በዚያ ዘመን የተፈጸመው ድርጊት፤ ሰለባዎች የሆኑ  ሰዎች፣ የተናገሩት፣ በቃል እየተላለፈ እስከዛሬ ድረስ ህያው ሆኖ ነው የሚተረከው።» 

ተክሌ የኋላ

ሒሩት መለሰ

አርያም ተክሌ