1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን፤ በአዉቶቡስ አደጋ 18 ሠዎች ሞቱ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 27 2009

ጀርመን ፈጣን አዉራ ጎዳና ላይ ይጓዝ የነበረ አዉቶቡስ ላይ በደረሰ የግጭት አደጋ 18 ተሳፋሪዎች ሞቱ ፤ 30 ሰዎች ደግሞ ቀላልና ከባድ ጉዳት ደረሰባቸዉ። ከተሳፋሪዎቹ አብዛኞቹ በእድሜ የጠኑ ስለነበሩ ቃጠሎዉን ለማምለጥ ጥረት ማድረግ እንዳልቻሉም ተዘግቦአል።

https://p.dw.com/p/2fr1q
Deutschland Unfall Reisebus in Münchberg
ምስል picture-alliance/dpa/B. Schackow

18 Tote nach Busunfall in Bayern - MP3-Stereo

 

ዛሬ ማለዳ ጀርመን ፈጣን አዉራ ጎዳና ላይ ይጓዝ የነበረ አዉቶቡስ ላይ በደረሰ የግጭት አደጋ 18 ተሳፋሪዎች ሞቱ ፤ 30 ሰዎች ደግሞ ቀላልና ከባድ ጉዳት ደረሰባቸዉ።  ጡረተኛ አገር ጎብኝዎችን አሳፍሮ ከዛክሰን ወደ ባቫርያ ግዛት በመጓዝ ላይ የነበረው ይኽው አውቶብስ ሽታምባህ በተባለችው ከተማ  ከሌላ ተሽከርካሪ ጋር ከተጋጨ በኋላ በተነሳ እሳት ሙሉ በሙሉ መውደሙን ፖሊስ አስታውቋል። የጀርመን ፕሬዚዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየርና የጀርመንዋ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል  በደረሰዉ አስደንጋጭ አደጋ ኃዘናቸዉን ገልፀዋል።  በአደጋዉ ሕይወታቸዉን ካጡት ቤተሰቦች ጋር ነን ያሉት ፤ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል፤ የአደጋ ጊዜ ደራሾችን ሥራም አመስግነዋል።

« ከፍተኛ ቁጥር ተሳፋሪዎች መሞታቸዉን ፤ እንዲሁም በርካቶች ጉዳት የደረሰባቸዉ እንዳሉም ሰምተናል። በዚህ ሰዓት በአደጋዉ ሕይወታቸዉን ካጡት ቤተዘመዶች ጋር ነን። በአደጋዉ የተጎዱት ሰዎች ጤናቸዉ ቶሎ እንዲመለስ እንመኛለን። የአደጋ ጊዜ ፈጥኖ ደራሾች በዚህ ከባድ ጊዜ የሚፈጽሙት ርዳታ ሚዛን የሚደፋ ነዉና እናመሰግናቸዋለን።» 

የጀርመን የመንገድ ትራንስፖርት ጉዳይ ሚኒስትር  አሌክሳንደር ዶብሪዲንት አደጋዉ በደረሰበት ቦታ ላይ ተገኝተዉ እንደተናገሩት አዉቶቡሱ በፍጥነት በእሳት የጋየበት መንስኤ ምን እንደሆነ አይታወቅም። ከተሳፋሪዎቹ አብዛኞቹ በእድሜ የጠኑ ስለነበሩ ቃጠሎዉን ለማምለጥ ጥረት ማድረግ እንዳልቻሉም ተዘግቦአል።

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሠ