1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን ፣ ተገን ጠያቂዎችና ፣ የወሲብ ጥቃት

ማክሰኞ፣ ጥር 3 2008

አዲሱን 2016 ዓም ለመቀበል በኮሎኝና በሌሎችም የጀርመን ከተሞች በዋዜማው አደባባይ በወጡ ሴቶች ላይ የደረሰዉ ወሲባዊ ጥቃትና ዝርፊያ እዚህ ጀርመን እያወዛገበ ነው ። ወንጀሉን በመፈፀም ከተጠረጠሩት አብዛኛዎቹ ተገን ጠያቂዎች መሆናቸው ፓሊስም ጥቃቱን መከላከል አለመቻሉ ማነጋገሩ ቀጥሏል ።

https://p.dw.com/p/1Hc6G
Deutschland Silvesternacht vor dem Hauptbahnhof in Köln
ምስል picture-alliance/dpa/M. Böhm

በጎርጎሮሳዊ 2016 ዋዜማ በኮሎኝና በሌሎችም ትላላቅ የጀርመን ከተሞች በሴቶች ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ ከዚያም አልፎ ወሲባዊ ጥቃት እንዲሁም ዝርፊያ መፈፀሙ ጀርመን ውስጥ አብይ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ ከርሟል ። በዚሁ ጊዜ በተለይ በኮሎኝ ከተማ በአዲስ ዓመት ዋዜማ በደረሰው ጥቃትና ዝርፊያ ከ1ሺህ በላይ የሚሆኑ ወጣት ወንዶች መሳተፋቸው ሲታወቅ ከመካከላቸው 32ቱን ተጠርጣሪዎች መለየቱን የፌደራል ጀርመን ፖሊስ አስታውቋል ። የኮሎኝ ፖሊስ እንደገለፀው ደግሞ የ19ኙን ተጠርጣሪዎች ማንነት ደርሶበታል ። ከመካከላቸው 14 ቱ ከሞሮኮ እና ከአልጀሪያ እንደመጡ 10 ሩ ደግሞ ተገን ጠያቂዎች መሆናቸው ከነርሱም ውስጥ 9ኙ ጀርመን በህገ ወጥ መንገድ እንደገቡ የጀርመን ዜና አገልግሎት DPA ዘግቧል ። በጎርጎሮሳዊው 2015 ዓም ከ1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን ባስገባችው በጀርመን በተገን ጠያቂዎች የተፈፀመው ይህ ጥቃትና ዝርፊያ ብዙ ጥያዌዎችን አስነስቷል ። የህግ ባለሞያና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ ለዶቼቬለ በሰጡት አስተያየት ድርጊቱ ያልተጠበቀ በመሆኑ ህብረተሰቡን ፖለቲከኞችንና ህግ አስከባሪዎችን ማስደንገጡን ገልፀዋል ። የህግ የበላይነት ባለበት በጀርመን የተፈፀመው ይህ ጥቃትም በአፋጣኝ ውሳኔ ሊያገኝ እንደሚገባም ጠቁመዋል ።
ኮሎኝና ሃምቡርግን በመሳሰሉ የጀርመን ትላልቅ ከተሞች በሴቶች ላይ ወሲባዊ ጥቃቱ መድረሱ ብቻ ሳይሆን ፖሊስም በወቅቱ ችግር ውስጥ ለወደቁት ፈጥኖ መድረስ አለመቻሉ ብዙ አወዛግቧል ። ፖሊስ ጥቃቱን ባለመከላከሉ መንስኤ የኮሎኝ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ከሃላፊነታቸው እስከመነሳት ደርሰዋል ።ኮሎኝ የምትገኝበት የኖርድ ራይን ቬስትፋለን ፌደራዊ ክፍለ ሃገር የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር በዚያ ምሽት ፖሊስ ለጥቃቱ ሰለባዎች መድረስ አለመቻሉን፣ ተቀባይነት የሌለው ሲሉ ተችተዋል ።ፖሊስ ጥቃቱን መከላከል አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ ጉዳይ አድበስብሶ ለማለፍ መሞከሩም ሌላው ስህተት ነበር እንደ ዶክተር ለማ ።ፖሊስ በኮሎኝ ብቻ በአዲስ አመት ዋዜማ የደሩሱ ጥቃትና ዘረፋዎችን የተመለከቱ 516 አቤቱታዎች ደርሰውታል ።ከመካከላቸው 237ቱ ማለትም 40 በመቶው የወሲባዊ ጥቃቶችና ትንኮሳዎች ክሶች ናቸው ።ከመካከላቸው ሁለት የአስገድዶ መድፈር ክሶች ይገኙበታል ።107ቱ የዝርፊያ ፣የተቀሩት ደግሞ የአካላዊ ጥቃቶች አቤቱታዎች መሆናቸው ተነግሯል ።በሌላዋ የጀርመን ትልቅ ከተማ በሀምቡርግም 133 ተመሳሳይ ጥቃቶች መድረሳቸው ተዘግቧል ። በፍራንክፈርትም ጥቂት መሰል አቤቱታዎች ቀርበዋል ። ተቃዋሚዎች ቢኖሩም ብዙሃኑ ስደተኞችን እንኳን ደህና መጥታችሁ ብሎ በተቀበለበት ሃገር ይህን መሰል ጥቃት በተገን ጠያቂዎች መፈፀሙ የህዝቡንም ሆነ የመንግሥትን ሃሳብ ሊያስቀይር ይችላል የሚል ስጋት ያደረባቸው አልጠፉም ። ዶክተር ለማ ግን ይህ ይሆናል ብለው አይጠብቁም ።
ሆኖም በአሁኑ ጊዜ የውጭ ዜጎች ጀርመን መግባታቸውን የማይቀበሉ ፣ጀርመን ለጀርመናውያን ብቻ የሚል አቋም ያላቸው እንዲሁም በአውሮፓ የእስልምናን መስፋፋት እንቃወማለን የሚሉ ቡድኖች እና ደጋፊዎቻቸው ይህን አጋጣሚውን እንደ ማሳያ ከመጠቀም ወደ ኋላ እንደማይሉ ይታመናል ።በአዲስ ዓመት ዋዜማ በጀርመን ከተሞች የደረሰው ጥቃት ጀርመን ስደተኞችን የመቀበል ሃላፊነት እንዳለባትና አቅሙም እንዳላት ደጋግመው በሚያሳስቡት በመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ፓርቲ ላይም ተፅእኖ ሊሳድር እንደሚችል ይገመታል ። ሆኖም ዶክተር ለማ እንደሚሉት ትልቅ የተባለ ችግር ግን ሊያስከትል አይችልም ። መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ወንጀል የፈሙ ወደ ሃገራቸው መመለስ እንዳለባቸው ተናግረዋል ።ወንጀል መፈጸማቸዉ የተረጋገጠ ተገን ጠያቂዎችን ወደ መጡበት ሃገር መመለስ በሚያስችል የህግ ማሻሻያ ላይም የጀርመን መንግሥትና ምክር ቤት ይመክርበታል።

Hauptbahnhof Köln Sylvester Ausschreitungen Menschenmassen
ምስል picture-alliance/dpa/M. Böhm

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሀመድ