1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን እና ተገን ጠያቂዎች

ማክሰኞ፣ ግንቦት 9 2008

የፌደራል ጀርመን የተገን ጠያቂዎችና የስደተኞች ጉዳይ መስሪያ ቤት በጎርጎሮሳዊው 2016 ከአንድ ሚሊዮን ለሚበልጡ የተገን ጥያቄ ማመልከቻዎች ውሳኔ መስጠት ይጠበቅበታል ። በቀደሙት አመታት ውሳኔ ላላገኙ የተገን ጠያቂዎች ማመልከቻዎችም መልስ ለመስጠት አቅዷል ። መስሪያ ቤቱ በታሰበው ጊዜ ያለውን ተግባራዊ ማድረግ መቻሉ እያነጋገረ ነው

https://p.dw.com/p/1IpIE
Paderborn Bundesamt für Migration und Flüchtlinge
ምስል DW/S. Pabst

ጀርመን እና ተገን ጠያቂዎች

በጎርጎሮሳዊው 2015 ዓም ጀርመን የገቡት ስደተኞች ቁጥር ወደ 1.1 ሚሊዮን ይጠጋል ። ይህም ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ወዲህ በአውሮጳ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ክስተት ተብሏል ። በተለያዩ የጀርመን ከተሞች የሚገኙት እነዚህ ስደተኞችም የተገን ጥያቄ ማመልከቻ እስኪያስገቡ ድረስ ወራት ሊወስድ ይችላል ።የእያንዳንዱ ተገን ጠያቂ ማመልከቻ ታይቶ እና ተመርምሮ ጀርመን ተገን ሊሰጠው ይገባል ወይም አይገባም የሚል ውሳኔ ላይ ለመድረስም እንዲሁ ብዙ ጊዜ ይጠይቃል ። ከአንድ አመት ወዲህ ጀርመን የገቡት ተገን ጠያቂዎች ቁጥር ከእስከዛሬው እጅግ ከፍተኛ መሆን የጀርመን የተገን ጠያቂዎች እና የስደተኞች ጉዳይ መስሪያ ቤት ፣ለተገን ጠያቂዎች ማመልከቻዎች ከቀድሞው በፈጠነ አሠራር መልስ እንዲሰጥ አስገድዷል ። የመስሪያ ቤቱ ሃላፊ ፍራንክ ዩርገን ቪዘ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ እንደተናገሩት በጎርጎሮሳዊው 2016 አም መስሪያ ቤታቸው ቢያንስ ለአንድ ሚሊዮን ስደተኞች ጉዳይ ውሳኔ መስጠት አለበት ።
«በ2016 አም አንድ ሚሊዮን ውሳኔዎችን መስጠት ይኖርብናል ። ይህም በአሁኑ ጊዜ ወደ ጀርመን ከሚገቡት ተገን ጠያቂዎች ቁጥር ማነስ ጋር የተያያዘ አይደለም ። የመቀበል አቅማችንን ለማዘጋጀት ወሳኙ ምን ያህል ሰዎች ይመጣሉ የሚለው ነው ። ሁለት ፣ ሶስት ወይስ አራት መቶ ሺህ ወይስ አሁን የገቡት 500 ሺሁ ብቻ ናቸው ። ይህ ደግሞ የሚታወቀው በአመቱ መጨረሻ ነው ።»
ጀርመን ፍራንክፈርት ነዋሪ የሆኑት የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና የህግ ባለሞያ እንዲሁም የጀርመንኛ ቋንቋ መምህር እና አስተርጓሚ ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ ግን በጎርጎሮሳዊው 2016 ለአንድ ሚሊዮን የተገን ጠያቂዎች ማመልከቻዎች ውሳኔ መስጠቱ የሚሳካ አይመስላቸውም ። እርሳቸው እንደሚሉት ከልምድ እንደሚያውቁት የእያንዳንዱ ስደተኛ ጉዳይ በሚሰማበት አሰራር ይህ ተግባራዊ መሆኑ አጠራጣሪ ነው ።
የጀርመን የተገን ጠያቂዎችና የስደተኞች ጉዳይ መስሪያ ቤት ሃላፊ ባለፈው ሳምንት እንደተናገሩት
መስሪያ ቤታቸው የደረሱትን ማመልከቻዎችን እያየ ነው ። ሆኖም ሂደቱን ያጓተተው የስደተኞቹ ቁጥር መብዛት ብቻ ሳይሆን በየገቡባቸው ከተሞች የተመዘገቡ ስደተኞች በሙሉ የተገን ጥያቄ ማመልከቻቸውን ለመስሪያ ቤታቸው ሳይስገቡ መቅረታቸው ሳይሆን አይቀርም ነው ።
«በየማዘጋጃ ቤቶች እና በፌደራል ክፍለ ግዛቶች ከ3 እስከ 4 መቶ ሺህ ተገን ጠያቂዎች ተመዝግበዋል ፣ እስካሁን ግን እነዚህ ተገን ጠያቂዎች ለኛ ማመልከቻ አላስገቡም ብለን እናስባለን ። እኛ በአሁኑ ጊዜ ከ300 ሺህ በታች የሆኑትን ተገን ጠያዊዎች ጉዳይ መመልከት ጀምረናል ። ይህም እኛ ጋ የደረሱትንና የምንመረምራቸውን ማመልከቻዎች ቁጥር በአሁኑ ጊዜ ወደ 430 ሺህ ከፍ አድርጎታል ።በየፌደራል ክፍላተ ሃገር ካሉት ጋር በአጠቃላይ ሲደመር ከ700 ሺህ እስከ 800 ሺህ ይደርሳል ።እዚህ ላይ ደግሞ በ2016 አም ጀርመን የገቡት አዳዲስ ተገን ጠያቂዎች ሲጨመሩ ቁጥራቸው ከአንድ ሚሊዮን በላይ ይደርሳል ።»
ስደተኞች ከአስቸጋሪ እና አደገኛ ጉዞ በኋላ ጀርመን መድረሳቸው ለነርሱ ትልቅ እፎይታ ቢሆንም ጀርመን መቆየት መቻል አለመቻላቸውን ሳያውቁ ለብዙ ወራት በስጋትና በፍርሃት መቆየታቸው ደግሞ ለተለያዩ ችግሮች እያጋለጣቸው መሆኑ ይነገራል ። ከመካከላቸው የቤተሰብ አባላቸውን ፣ባል ሚስት አለያም ልጆችን ሃገራቸው ጥለው ለመጡት ደግሞ ችግሩ የከፋ ነው የሚሆነው ይላሉ ዶክተር ለማ
ዩርገን ቪዘም ተገን ጠያቂዎች ለቃለ መጠይቅ እስኪቀርቡ ድረስ ብዙ መጠበቃቸው ችግር ሊያስከትል በመቻሉ ይስማማሉ ።
«አንድ ስደተኛ ጀርመን ከገባ ከ12 ወራት በኋላ ጉዳዩ መታየት ሲጀምር ስለ ጉዞው ከሃገሩ ስለወጣበት ምክንያት እና አላማው እንዲሁም ስለ አጠቃላዩ ሁኔታ እንዴት ትክክለኛ መረጃ መስጠት እንደሚችል አላውቅም ። ስደተኛው እዚህ የሚደርሰው ከጭንቀት ጋር ነው ። እዚህ ከደረሰ በኋላ ደግሞ ጉዳዩ እስኪታይ መጠበቅ ይኖርበታል። ይህ ደግሞ ሌላው ጭንቀት ነው ።ከዚያ በኋላ ነው ቃለ መጠየቅ የሚደረግለት ። »
እነዚህንና ሌሎች ሁኔታዎችንም ከግምት ውስጥ በማስገባት ሃላፊው ፍራንክ ዩርገን ቪዘ እንደሚሉት ካለፉት አመታት ወደ ዚህ አመት የተንከባለሉ እንዲሁም አዳዲስ የተገን ጥያቄ ማመልከቻዎች የሚታዩበትን ሂደት ለማፋጠን ታቅዷል ። ባለፈው ሚያዝያ መስሪያ ቤቱ ከ60 ሺህ በላይ የተገን ጥያቄ ማመልከቻዎችን ተቀብሏል ። ይህም ባለፈው አመት በተመሳሳይ ወር ከደረሱት ማመልከቻዎች ጋር ሲነፃጸር በ 125 ፐርሰንት ጨምሯል። ከአመልካቾቹ ውስጥ 25,791 ሶሪያውያን ሲሆኑ ከኢራቅ ከአፍጋኒስታን እና ከኢራን የመጡ ተገን ጠያቂዎችን ይገኙበታል። እስከ 2016 መጨረሻ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የስደተኞች ማመልከቻዎች ውሳኔ ይሰጥባቸዋል የሚለው የጀርመን የተገን ጠያቂዎችና የስደተኞች ጉዳይ መስሪያ ቤት እቅዱን ለማሳካት የሰው ኃይሉን ለማጠናከር አቅዷል ። በ2015 የመስሪያ ቤቱ ሠራተኖች ቁጥር 2300 ነበር ። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ወደ 6700 ከፍ ብሏል ። ወደ ፊት ይህን ቁጥር ወደ 7300 ለማሳደግ አስቧል ። ዶክተር ለማ ግን ይህም ቢደረግ በተለመደው አሠራር ሂደቱ እንደተፈለገው ሊፋጠን አይችልም ይላሉ ።
ድምፅ ዶክተር ለማ 3
ጀርመን ተገን የሚጠይቀው ቁጥር ቢጨምርም ከ2016 አንስቶ ወደ ጀርመን የሚመጡ ስደተኞች ቁጥር ግን እየቀነሰ ነው ።የጀርመን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ባለፈው ሰኞ እንዳስታወቀው በሚያዚያ ወር የመጡት አዳዲስ ስደተኞች ቁጥር ወደ 16 ሺህ ይጠጋል ። በቀደመው በመጋቢት ወር 21 ሺህ ፣በየካቲት 61 ሺህ ፣በጥር ደግሞ 92 ሺህ ስደተኞች ናቸው ጀርመን የገቡት ።ወደ ጀርመን የሚመጡት ስደተኞች ቁጥር እየቀነሰ የሄደው ስደተኞች ብብዛት ወደ አውሮጳ የሚገቡበት የባልካን መስመር ከመጋቢት አንስቶ በመዘጋቱ ነው ።የስደተኞች ቁጥር እየቀነሰ መሄድ የተገን ጠያቂዎችና የስደተኞች ጉዳይ መስሪያ ቤት ጫናን ያቃልላል ተብሎ ይጠበቃል።ይሁንና የመስሪያ ቤቱ ሃላፊ ዩርገን ቪዘ እንደሚሉት የታቀደው ካልተሳካ የአንዳንዶቹ ውሳኔ ወደ ሚቀጥለው አመት ሊገፋም ይችላል ።
« ምን ያህል እንደሚመጡ እናያለን ። ከ2016 መጀመሪያ አንስቶ እኛ ጋ የመጡት 190 ሺህ ተገን ጠያቂዎች ናቸው ።በዚህ አመት የ500 ሺሁን ጉዳይ መመልከት እንችል ይሆናል ። ሊታይ ያልቻለው ደግሞ ወደ 2017 አም ይሸጋገራል ። »
በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ የተገን ጥያቄ ማመልከቻዎች ቶሎ ውሳኔ ያገኛሉ ። ለምሳሌ ጦርነት ከሚካሄድበት ከሶሪያ የሚመጡ ስደተኞች ጉዳይ በአንድ ሳምንት ውስጥ ውሳኔ ሊያገኝ ይችላል ። ሆኖም ሰዎች የሚሰደዱበት ምክንያት ግልፅ ካልሆነባቸው ሃገራት የሚመጡ የሌሎች ስደተኞችን ጉዳዮች ማጣራት እና ውሳኔ መስጠት ደግሞ ከ3 እስከ 6 ወራት ሊወስድ ይችላል ።

Bundesamt für Migration und Flüchtlinge Asylbewerber Warteschlange Warten Wilmersdorf
ምስል picture-alliance/dpa/S.Stache
Ankunftszentrum Trier Deutschland Registrierung Datenaufnahme BAMF
ምስል picture-alliance/dpa/H.Tittel
Deutschland Wiese PK zur Flüchtlingskrise
ፍራንክ ዩርገን ቪዘምስል Reuters/F. Bensch

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ