1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን እና አዲሱ የአፍሪቃ ጽንሰ-ሀሳብዋ

ሐሙስ፣ ሰኔ 9 2003

የጀርመን መንግስት ለመጀመሪያ ጊዜ ጠቅላላ የአፍሪቃን አህጉር የሚያጠቃልል የአፍሪቃ ጽንሰ-ሀሳብ የተባለ አዲስ መርሃግብር አወጣ።

https://p.dw.com/p/RTyj
ምስል dapd

የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጊዶ ቬስተርቬለ ከብዙ ክርክር በኋላ የተዘጋጀውን ሰነድ ትናንት በይፋ አቅርበዋል። ብዙዎቹ የሀገሪቱ ሚንስቴሮች ጽንሰ-ሀሳቡ በተረቀቀበት ስራ ላይ ተሳታፊዎች ነበሩ። በአዲሱ የአፍሪቃ መርሀግብር ዝግጅት ላይ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ጠበብት ምክር በማካፈል የበኩላቸውን አስተዋጽዖ አበርክተዋል።

በጥምሩ መንግስት ምስረታ ጊዜ እንደሚወጣ የተነገረለት አዲሱ የጀርመን የአፍሪቃ ጽንሰ-ሀሳብ ዝግጅት ከአንድ ዓመት በላይ የፈጀ ሲሆን፡ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ፡ የትምህርት እና የተፈጥሮ አካባቢ፡ እንዲሁም፡ የኤኮኖሚ ትብብር ሚንስቴሮች በጋራ ያረቀቁት ሰነድ ነው። በዚሁ ሀያ ስምንት ገጾች በያዘው እና የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጊዶ ቬስተርቬለ ትናንት በይፋ ባቀረቡበት ሰነድ ውስጥ አፍሪቃን በጠቅላላ የሚመለከት አዲስ የፖለቲካ መርሀግብር ተቀይሶዋል።

Merkel Afrika-Konzept
ምስል dapd

« ከጎረቤታችን አህጉር ጋ ባለን ግንኙነት ላይ አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት እንፈልጋለን። እያደገ የመጣው የአፍሪቃ ትርጓሜ እና አፍሪቃም ለራስዋ ጉዳዮች በይበልጥ ኃላፊነቱን እየወሰደች የመጣችበት ሁኔታ ፍሬ እንዲያስገኝ እንፈልጋለን። »

በሰሜን አፍሪቃ የተነቃቃው ዓብዮት ለመላው አህጉር ላይ ተጽዕኖ እንዳለው የገለጹት ቬስተርቬለ፡ በአፍሪቃ የሚኖረው ህዝብም ልክ በሌላው ዓለም እንደሚታየው ሁሉ ነጻነት፡ የህግ የበላይነት፡ ዴሞክራሲ እና የሰብዓዊ መብት ጥሙን ማርካት እንደሚፈልግ ማሳየቱን አረጋግጦዋል። በመሆኑም፡ ይላሉ ቬስተርቬለ፡ ጀርመን አፍሪቃውያን መንግስታት ሰላማዊ እና ነጻ የወደፊት ዕድል ለመፍጠር የጀመሩትን ጉዞ ለማበረታት ዝግጁ ናት።

« አፍሪቃን ለወዳጅነት እንጋብዛለን፤ በእኩልነት ላይ ለተመሰረተ ወዳጅነት። ዘመን ካለፈበት የርዳታ ሰጪና ተቀባይነት ግንኙነት ባለፍ። የእኛ ዓላማ የአፍሪቃውያኑን ጥረት እና ኃላፊነትን ለመሸከም የሚወስዱትን ርምጃ ማበረታታት ነው። በእኩዮች መካከል የሚፈጠር በራስ መተማመን ላይ የተመሰረተ የእኩልነት እንዲኖር እንፈልጋለን። ዋናው መነሻችን፡ በእኩልነት ላይ ለተመሰረተ ወዳጅነት የተሰኘው ነው። ምክንያቱም የአህጉሮቻችንን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ከናንተ ጋ ባንድነት በእኩልነት ላይ በተመሰረት ወዳጅነት መገንባት እንፈልጋለንና። »

ቻይና እና ህንድን የመሳሰሉ ሌሎች ሀገሮችም ከአፍሪቃ ጋ ግንኙነታቸውን አጠናክረው። ጀርመን በአፍሪቃ ጊዚያዊ ስኬቶችን የማስመዝገብ ዓላማ አላቸው በምትላቸው በነዚህ ሁለት ሀገሮች አንጻር ዘላቂነት የሚኖረው እና አፍሪቃውያንንም ጭምር ተጠቃሚ የሚያደርግ አጋርነትን መፍጠር ነው የምትፈልገው። እና የጀርመን ኤኮኖሚንም እና የአፍሪቃን ህዝብ የሚጠቅም አንድ የኃይል ምንጭ እና የጦሬ አላባ አጋርነትን ማቋቋም ፍላጎት እንዳላት የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቬስተርቬለ አስረድተዋል።

« ዓላማችን በመካከላችን ሊኖር የሚችለውን ትብብር በወዳጅነት ላይ በተመሰረተ ዘዴ እንድንጠቀምበት ነው። ይህ በአፍሪቃ ለሚኖረው ህዝብ ብልጽግና ብቻ ሳይሆን፡ መረሳት የሌለበትም ለራሳችንም ብልጽግና እና ጥቅምም የሚበጅ መሆኑ ነው። »

በዚሁ ነጥብም ላይ ነው አሁን ጀርመናውያኑ የተቃውሞ ፓርቲዎች በአዲሱ የመንግስቱ የአፍሪቃ ጽንሰ-ሀሳብ ላይ ነቀፌታቸውን እየሰነዘሩ ያሉት። በፌዴራዊው ምክር ቤት፡ ቡንድስታግ የግራ ፓርቲ አንጃ እንደራሴ ኒየማ ሞፋሳት እንዳኣኣስረዱት፡ የጀርመን መንግስት የአፍሪቃን አህጉር እንደ ጥሬ አላባ መጋዘን በመመልከት፡ ለዘብተኛውን የገበያ መርህ ስር የተጀመረውን የልማት ትብብር የሚጎዳ ነው።

የጀርመውያኑ የአፍሪቃ ጽንሰ-ሀሳብ በተለይ የወደፊቱን የጀርመንን ጥቅም ብቻ እንዲያስጠብቅ ሆኖ የተዘጋጀ በመሆኑ የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ መሪ ክላውዲያ ሮትም ቅር እንደተሰኙ ገልጸዋል። አዲሱ የአፍሪቃ ጽንሰ-ሀሳብ በጋራለአፍሪቃ በሚል መጠሪያ ከሚታወቀው መንግስታዊ ካልሆነው ድርጅትም ሂስ ተሰንዝሮበታል።

ቤቲና ማርክስ

አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሐመድ