1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን እና የአፍሪቃ መብት ተሟጋቾች ጥያቄ

ቅዳሜ፣ የካቲት 22 2006

ጀርመን በአፍሪቃ ብዙም የቅኝ አገዛዝ ታሪክ የሌላት ልትመስል ትችል ይሆናል። የታሪክ መዛግብት የሚያሳዩት ግን ሌላ ነው። ጀርመን እአአ በ1884 ምዕራባውያን ኃይላት አፍሪቃን በመካከላቸው የተከፋፈሉበት ጉባዔ የተካሄደው በርሊን ውስጥ ነበር።

https://p.dw.com/p/1BHii
Namibia deutsche Kolonialgeschichte Kriegsgefangene Herero
ምስል Bundesarchiv, Bild 146-2003-0005/Unknown/CC-BY-SA 3.0

ያኔ ደቡብ ምዕራብ አፍሪቃ ይባል የነበረው ሀገር(የዛሬዋ ናሚቢያ) ለጀርመን ተሰጠ። ዛሬ ከ130 ዓመት በኋላ በርካታ አፍሪቃውያን እና የጀርመን ድርጅቶች ጀርመን ስለዚሁ ታሪኳ በትምህርት ቤቶችዋ ውስጥ ማስተማር እንድትጀምር በመጠየቅ ሰሞኑን በመዲናይቱ በርሊን ተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል።

Aufmarsch gegen aufständische Herero
ምስል dpa

እርግጥ በርሊን ይቅርታ ብትጠይቅም፣ በቅኝ አገዛዙ ዘመን በሄሬሮ ብሔረሰብ እና በኔምባ ብሔር ላይ ለፈፀመችው የጅምላ ጭፍጨፋ ሙሉ ኃላፊነቱን እስካሁን አልወሰደችም።ማርያነ ባሌ ሞዱምቡ በብራንድንቡርግ ጦር ለተሰበሰበው ተቃዋሚ ሰልፈኛ ባሰሙት ንግግራቸው የዘር መጥፋት መፈፀሙ ዕውቅና እንዲያገኝ ጠይቀዋል።

« በጀርመን ቅኝ አገዛዝ ዘመን በሄሬሮ እና በናማ ብሔሮች ላይ የተፈፀመው የዘር ማጥፋት እና የነፍስ ግድያ ሁሉ ዕውቅና ሊያገኝ እና ወንጀሉ እንደተፈፀመ ሊረጋገጥ ይገባል። »

የዘር ማጥፋቱ ጭፍጨፋ የተጀመረው የሄሬሮ እና የናማ ብሔረሰቦች በጀርመን ቅኝ አገዛዝ አንፃር እአአ በ1904 ዓም ባመፁበት ጊዜ ነበር። ጀነራል ሎታር ፎን ትሮታ ዓማፂዎቹን ለመደመሰስ ዕቅድ አወጡ። ዕቅዱ ተግባራዊ በሆነበት ድርጊት እአአ እስከ 1908 ዓም ድረስ 80,000 ሰው ተገድሎዋል። የናሚቢያ ሕዝብ የዘር ማጥፋቱ ጭፍጨፋ ሰለባ የሆኑትን ዜጎቹን እአአ ከ 1932 ዓም ወዲህ በይፋ ማሰብ ጀምራለች። ያም ቢሆን ፣ ጀርመን እአአ እስከ 2004 ዓም ድረስ ስለዚሁ ጉዳይ ከማንሳት ተቆጥባ ነበር የቆየችው። ይሁንና፣ የቀድሞ የጀርመን የልማት ተራድዖ መስሪያ ቤት ሚንስትር ወይዘሮ ሀይደማሪ ቪችሶሬክ ሶይል በቅኝ አገዛዝ ዘመን ለተፈፀመው የዘር ማጥፋት የኃይል ተግባር ይቅርታ ለመጠየቅ እአአ በ2005 ዓም ወደ ናሚቢያ ተጓዙ።

Adrian Dietrich Lothar von Trotha
ምስል picture-alliance/dpa

« የጀርመን ቅኝ ገዢ ኃይላት በአያት ቅድም አያቶቻችሁ ላይ፣ በተለይም፣ በሄሬሮ እና በናማ ሕዝቦች ላይ አስከፊ የኃይል ተግባር የፈፀሙበትን ድርጊት ዛሬ ለማረጋገጥ እፈልጋለሁ። በዚያን ጊዜ የተፈፀመውን የጭካኔ ተግባር፣ ነፍስ ግድያው እና ወንጀሉ በዛሬ ጊዜ የጅምላ ጭፍጨፋ ተብሎ ነው የሚጠረው። በመሆኑም፣ በአምላክ ስም በምንጋራው ፀሎት ላይ እንደተጠቀሰው በደላችንን እና ጥፋታችንን ይቅር እንድትሉን እጠይቃለሁ። »

የሚንስትሯ ይቅርታ መጠየቅ ለብዙ ዘመናት ሥር ሰዶ የቆየውን ታሪካዊ ቁስል ለመፈወስ የተወሰደ ዋነኛው የመጀመሪያ ርምጃ ሆኖ ነው የታየው። ይሁንና፣ ይኸው አስከፊው የጀርመን ቅኝ አገዛዝ ታሪክ እስከዛሬ ድረስ በሀገሪቱ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ አልተካተተም። ጀርመን ስለዚሁ ታሪኳ በማንሳት ገፅታዋን ለማበላሸት እንደማትፈልግ ነው ጀርመናዊው የታሪክ ምሁር እና የአፍሪቃ ጉዳዮች ተመራማሪ ሄኒንግ ሜልበር ያስረዱት።

Symbolbild Entwicklungsministerin Wieczorek-Zeul Afghanistan
ምስል picture-alliance/ dpa

« ጀርመን ስለዚሁ ታሪክ ለማስተማር ያመነታችው ይህንን እንደ ጥሩ አጋጣሚ ለማየት ባለመፈለግ ሳይሆን አሁን የድሮ ታሪክ እንደገና በማንሳት ገፅታችንን ማበላሸት ይሆናል፣ በሚል አስተሳሰብ ይመስለኛል። አሁን በጣም ተሻሽለናል፣ ካለፈው ታሪካችንም ትምህርት ቀስመናል በሚል ሊሆን ይችላል፣ ትምህርት ተቀስሞ ሊሆን ይችላል፣ ግን ስለዚህ ታሪካችን መነገር የለበትም በምል ጉዳዩን ለማንሳት ካልፈለግን እና ካልቻልን ትምህርት ቀስመናል ለማለት አንችልም። እና የሄሬሮን እና የናማን ጉዳይ በተመለከተ የሚታየው ገሀድ ይህ ነው። »

የአፍሪቃ የመብት ተሟጋች ቡድኖችም በጀርመን ቅኝ አገዛዝ ዘመን በሕዝቦቻቸው ላይ የተፈፀመውን የጭካኔ ተግባር ዕውቅና እንዲያገኝ ነው የሚፈልጉት። ይህ አስከፊ የጀርመን ታሪክ በየትምህርት ቤቶች ውስጥ በታሪክ ትምህርት ውስጥ እስኪካተት ድረስ ትግላቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል። ልክ የናዚ ጭፍጨፋ ሰለባ ለሆኑት አይሁዳውያን እና ሮማ እና ሲንቲ ለሚባሉት የማዕከላይ አውሮጳ ነዋሪዎች በበርሊን እንደቆመው መታሰበያ በጀርመን ቅኝ አገዛዝ ዘመን ሰለባ ለሆኑት የሄሬሮ እና የናማ ብሔረሰቦች አፍሪቃውያንም አንድ መታሰቢያ ሀውልት እንዲተከል ይፈልጋሉ።

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ