1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን ዳግም ሊጨቃጨቅ ነው

እሑድ፣ መስከረም 14 2010

የዛሬው ምሽት ምርጫ ለጀርመን አንዳች መልእክት አለው። ቀኝ ጽንፈኛ ፖለቲከኞች ለመጀመያ ጊዜ ምክር ቤት ሲገቡ፤ አንጌላ ሜርክል ሽንፈት ቀምሰዋል። የዶይቸ ቬለዋ ኢነስ ፖል የሚከተለውን ጽፋለች።

https://p.dw.com/p/2kctn
Ines Pohl
ምስል DW/P. Böll

ይኽ ምርጫ ግልጽ መልእክት አለው፤ እንዲያ መቀጠል የለም። ሁለት ተሸናፊዎችም አሉት፤ የሶሻል ዲሞክራቶቹ ፓርቲ እና አንጌላ ሜርክል። የሶሻል ዲሞክራቶቹ ፓርቲ ታሪካዊ በሆነ መሽቆልቆል ወደ 20,8 ከመቶ ጥልቅ ወርዷል። የመራኂተ መንግሥቷ ፓርቲ ክርስቲያን ዲሞክራቲክ ኅብረት ወደ ስምንት ከመቶ ያህል ድምፅ አጥቷል። አንዳች የመሬት መንሸራተት። በደህናው ጊዜ ሥልጣን ለመልቀቅ የማሰላሰያ ሰበብ በነበር። ሆኖም ጊዜው ከጀርመኖች ሁኔታ አንጻር ደህና የሚባል አይደለም። የምርጫው ውጤት መጤ ጠሉ አማራጭ ለጀርመን (AfD) ፓርቲ በ13 ከመቶ ድምጽ ምክር ቤት መግባት መቻሉን ብቻ አይደለም የሚያሳየው። ይልቁንስ የፌዴራል ጀርመን ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ለመጀመሪያ ጊዜ እጅግ ወደ ቀኝ ያዘመመ ፓርቲ  ምክር ቤት መግባት የቻለበት ጊዜ ነው። 

ሀገሩ ሌላ መልክ ይዟል።


ነገሮች የተገለባበጡበት ታሪካዊ ወቅት። በዛሬው የእሁድ ምርጫ ሀገሩ መልኩን ቀይሮ ሌላ ኾኗል። አነስተኛ በሆነ መልኩ አይደለም። አንዳች ውድቀትም አይደል። ይኼ አንዳች መገዳደር ነው። በዚህም አለ በዚያ ግን ዲሞክራሲ። ከዓለም አንጻር ደግሞ ጀርመን ይህን መገዳደር በሚገባ ትማርበታለች፤ ትወጣዋለችም ብሎ ማሰብ ይበጃል። በምክር ቤትም ክርክሩ እጅግ መጦፉ አይቀር። ተቃዋሚ በታጣበት ምክር ቤት ኃያሏ መራኂተ-መንግሥት እንዳሻቸው መምራታቸውም ያከትምለታል።    

 
ይኽም የዚህ ምሽት ሌላ አንዳች መልእክት ነው። 


ዋናው ሊታሰብበት የሚገባው ነገር  ዲሞክራሲያዊ ፓርቲዎች በሆይሆይታ እዚህ በደረሰው አማራጭ ለጀርመን ፓርቲ (AfD) ዲሞክራሲያዊ ውይይታቸው እንዳይሰናከል ማድረጉ ነው። በቀኝ ዘመሙ ፓርቲ ብዥታ የተዋጠ መፍትኄ ተብዬ ተግዳሮቶችን መጋፈጥ ይገባቸዋል፤ ያም ብቻ አይደለም ከፊት ለተደቀነው ችግር እውነተኛ መፍቴን መሻት ይጠበቅባቸዋል። እናም በስተመጨረሻ በበርካታ ሰዎች ዘንድ ስደተኞች የገዛ ሀገራችን ሊቀይሩ ነው በሚል የሰረጸው ስጋት የምር ሊወሰድ የሚገባው ጉዳይ  ነው።ጀርመን በውይይት ባሕሏ ይህን ጉዳይ የምር ልታስብበት ይገባል። ስጋቶችን እያድበሰበሱ ለመቅበር መሞከር የቀኝ ፖለቲከኞችን ይበልጥ ያጠናክራቸዋል።   


ይኽም የዚህ ምርጫ አንዱ መልእክት ነው።


ሶሻል ዲሞክራቶች (SPD) ተቃዋሚ ይኾናሉ


ቀዳሚው እና ዋነኛው ተግዳሮት የሚሆነው መንግሥት የመመስረቱ ጉዳይ ነው። ሶሻል ዲሞክራቶቹ ተቃዋሚ ለመሆን በፍጥነት አቋም የመውሰዳቸው ነገር ብልህነት ነው። እንዲያ በማድጋቸውም ነው ራሳቸውን ማደስ እና ምናልባትም የወደፊት ተስፋቸውን ማጠናከር የሚችሉት። እነሱ እንደዛ በመወሰናቸው ከምንም በላይ ደግሞ በምክር ቤቱ አማራጭ ለጀርመን ፓርቲ ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ መሆኑ ይቀራል።  

በዚህ የተወሳሰበ ድርድር አንጌላ ሜርክል ከባድ ምት ይጠብቃቸዋል። ጫንቃቸው ላይ ከተጫነው ሸክም የጎላው ግን የስደተኞች መርኃቸው ለፓርቲው ከፍተኛ ድቀት ሰበብ ነው ሲሉ የገዛ ፓርቲያቸው አባላት ተጠያቂ የማድረጋቸው ነገር ነው። በሌላው መልኩ ደግሞ ምንም ውጤት ያግኙ ምንም የምዕራቡ ዓለም ቁንጮ መሪነታቸው ቀጥሎ በዓለም መድረክ ሀገራቸው ጀርመን የተረጋጋ ሆና እምነት የሚጣልበት ወዳጅ በመሆን ይቀጥላል ሲል መላው ዓለም ተስፋ ጥሎባቸዋል። በእርግጥም ሀገራቸው ጀርመን ግልጽ የሆነ እጅግ ዲሞክራሲ የዘለቀበት ሀገር ሆኖ ይቀጥላል በሚልም ነው ተስፋው።   

ለዚያ ደግሞ ከምንም በላይ በጀርመን ሕገ-መንግሥትም የሚደገፍ ነው። ለሁሉም የሚሠራው ለአማራጭ ለጀርመንም (AfD) ይሠራል። አንቀጽ 1፤ «የሰው ልጅ ክብር በምንም መልኩ የማይገሰስ ነው።»  

 ኢነስ ፖል/ ማንተጋፍቶት ስለሺ