1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጃፓን፤ የገጠማት ቀውስና የኤኮኖሚው ጉዳት

ረቡዕ፣ መጋቢት 14 2003

ጃፓን ውስጥ የቅርቡ የመሬት ነውጽና ማዕበል ያደረሰው ሃያል ጥፋትና ይህንኑ ተከትሎም በፉኩሺማ የአቶም ሃይል ጣቢያ የተከሰተው ቀውስ አገሪቱን እጅጉን መፈተኑ አልቀረም።

https://p.dw.com/p/RBu1
የቶኪዮ የምንዛሪ ገበያምስል dapd

አደጋው በደረሰበት አካባቢ ወደፊት የሚካሄደው መልሶ ግንባታ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንደሚፈጅ ነው የሚታመነው። በወቅቱ በጥፋቱ መጠን ላይ የተለያዩ አሃዞች ቢቀርቡም የዓለም ባንክ ለምሳሌ በነውጹና በማዕበሉ የደረሰውን ጥፋት በ 235 ቢሊዮን ዶላር ይገምታል። ይህም ግዙፍ ገንዘብ ሲሆን የመልሶ ግንባታው ተግባር መፏጠንና የአምራቹ ኢንዱስትሪ ዘርፍ በፍጥነት መልሶ መንቀሳቀስ በጃፓን ብቻ ሣይሆን በሌሎች ከጃፓን በሚቀርቡ የኤሌክትሮኒክ ወይም የግንቢያ ዕቃዎች ላይ ጥገኛ በሆኑ አገሮች ኤኮኖሚ ላይም ተጽዕኖ የሚኖረው ነው።
የዓለም ባንክ ጃፓን ውስጥ በቅርቡ የመሬት ነውጽና ማዕበል ደርሶ የነበረውን ጥፋት ከሁለት መቶ ቢሊዮን ዶላር በላይ ከፍ አድርጎ አስቀምጦታል። ይህም እ.ጎ.አ. በ 1995 ዓ.ም. በኮቤ የመሬት ነውጽ አድርሶት ከነበረው ጥፋት ሲነጻጸር ከእጥፍ በላይ መሆኑ ነው። በዴካ ባንክ ግምት በጃፓን ብሄራዊ ኤኮኖሚ ላይ የተከተለው ኪሣራ 137 ሚሊያርድ ኤውሮ ይደርሳል። ይሁን እንጂ አብዛኛው የዓለም ኤኮኖሚ ጠበብት አሁንም የሚያስቡት ጃፓን ውስጥ ዝግ ይል እንደሆን እንጂ የኤኮኖሚ ዕድገት እንደሚኖር ነው።
ዴካ ባን’ክ ለምሳሌ ይህንኑ በማጤን በጃፓን ለዚህ ለያዝነው ዓመት ቀርቦ የነበረውን የዕድገት ትንበያ ከ 1,5 ወደ 1 ከመቶ ዝቅ አድርጎታል። የጀርመኑ ኮሜርስ ባንክ ዋና የኤኮኖሚ ባለሙያ ዮርግ ክሬመር ደግሞ የኮቤውን ልምድ ጠቃሚነት በማመልከት የመልሶ ግንባታው ተግባር ዕድገቱን ወደፊት ለማራመድ ይረዳል ባይ ናቸው።

“የኮቤው የጥር ወር 1995 ዓ.ም. የመሬት ነውጽም እጅግ ከባድ ነበር። የኢንዱስትሪው ምርት በጊዜው ቀደም ካለው የታሕሣስ ወር ሲነጻጸር ሁለት ከመቶ ነበር የወደቀው። ሆኖም ወዲያው በተከታዩ የካቲት ወር ኪሣራውን በሙሉ መሸፈን ይቻላል። እንዲህም ሆኖ እርግጥ ኤኮኖሚው ያቆለቁላል። ግን የመሬት ነውጹን ብቻ ከወሰድን የሰዉ መከራ ቢበዛም መልሶ ግንባታው በፍጥነት እንደሚሳካ ነው ልምድ የሚያሳየው”

አሁን በጃፓን እንደሚታየው ከኤኮኖሚው ችግር ባሻገር የአቶም ቀውስም አስጊ እየሆነ ነው። ስጋቱን በፉኩሺማ የአቶም ጣቢያ የሚታዩ አንዳንድ ጥቃቅን ስኬቶችም አያለዝቡትም። ይልቁንም ብዙዎችን ማስጨነቅ የያዘው ትልቁ ጥያቄ የጣቢያው አደጋ ከቁጥጥር ስር ሊውል ባይችል በዓለም ኤኮኖሚ ላይ ምን ያስከትላል የሚል ነው። የስዊሱ ሣራዚን ባንክ ዋና የምጣኔ-ሐብት ባለሙያ ያን ፖዘር የተፈራው አደጋ ቢደርስ ምን ሊከተል እንደሚችል ለመናገር ከደፈሩት ጥቂት የኤኮኖሚ ጠበብት መካከል አንዱ ናቸው።

“በንጥረ-ነገር ማብላያው ውስጥ ቅልጠት ቢደርስ የፉኩሺማን አካባቢ ለአያሌ ዓመታት መኖር የማይቻልበት ማድረጉና ከዚሁ ተያይዞም የአደገኛው ጨረርታ ጉም ወደ ቶኪዮ ቢዘልቅ ኑሮን ለተወሰነም ጊዜ ቢሆን ሊያሰናክል እንደሚችል የሚታሰብ ነው”

በስዊሱ ባለሙያ ስሌት ይህ ከሆነ መልሶ ግንባታው ቀጥ የሚልና የምርት ተግባርም በመላ አገሪቱ በግማሽ የሚቀንስ ነው የሚሆነው። ለዚህም ምክንያቱ ቶኪዮና አካባቢው አርባ በመቶው የጃፓን የኤኮኖሚ አቅም የሚገኝበት መሆኑ ነው። እንግዲህ በረጅም ጊዜ ጃፓን ከአጠቃላይ ብሄራዊ ምርቷ አሥር በመቶውን ልታጣ ትችላለች።

“በወቅቱ ሥራቸውን እንዲያቆሙ የተደረጉት የሃይል ማመንጫዎች ስድሥት በመቶ ድርሻ አላቸው። እና በሰሜን-ምሥራቁ አካባቢ ያለውን ሁኔታ ሲመለከቱት ደግሞ ከብሄራዊው አጠቃላይ ምርት ተጨማሪ አራት በመቶ ድርሻ ይታከላል። ይህም ለዘለቄታው የማይተካ ነው የሚሆነው”

በዓለም ባንክ ገለጻ መሠረት የጃፓን የኤኮኖሚ ዕድገት በቀውሱ ሳቢያ እስከያዝነው ዓመት አጋማሽ ድረስ ተጽዕኖ ይኖርበታል። በሌላ በኩል በመልሶ ግንባታው ጥረት በዓመቱ መጨረሻ ሁኔታው ሻል የሚል ነው የሚሆነው። በነገራችን ላይ መልሶ ግንባታው አምሥት ዓመታት ያህል እንደሚጨርስ ይገመታል።

የሆነው ሆኖ የከፋው ቢከፋ ሁኔታው በዓለም ኤኮኖሚ ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ ውሱን እንደሚሆን አያሌ የኤኮኖሚ ጠበብት ይስማማሉ። የስዊሱ ሣራዚንም ሆነ ዴካ ባንክ የሚጠብቁት ዓለምአቀፉ ዕድገት በአንድ ከመቶ ብቻ ደከም ሊል እንደሚችል ነው። እስካሁን በዓለምአቀፍ ደረጃ የሚጠበቀው ዕድገት በሣራዚን ባንክ ግምት 4,8 ከመቶ ይደርሳል። ያን ፖዘር እንደሚሉት ታዲያ ከዚሁ አንድ ከመቶ ቢቀነስ ....

“.... ከኤኮኖሚ ቀውስ ክልል ውስጥ አይገባም ማለት ነው። ጃፓን ዝግ ሕብረተሰብ ናት ለማለት ይቻላል። ወደ አገር የሚገባው ምርት በአሥር ከመቶ ብቻ የተወሰነ ነው። እናም የጃፓን ኤኮኖሚ በውጩ ዓለም ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ ብዙም ከባድ አይሆንም። በቀላሉ ሊታለፍ የሚችል ነው”

ምናልባት ሁኔታው ለቻይና ለየት ያለ ይሆናል። ኮሎኝ ከተማ ላይ ተቀማጭ የሆነው የጀርመን የኤኮኖሚ ጥናት ኢንስቲቲዩት ባልደረባ ዩርገን ማቲስ እንደሚሉት ቻይና በጃፓኑ ቀውስ በጣሙን ነው የተነካችው። ጃፓን ሃያ በመቶ የሚሆን ምርቷን ወደ ቻይና ስትልክና ከፊሉንም በዚያው በማሰራት በመላው ዓለም እንዲሸጥ ስታደርግ ቆይታለች። ይሄው የወቅቱ ችግር እንግዲህ የዓለም ኤኮኖሚ መንኮራኩር ለሆነችው ለቻይና አስቸጋሪ በሆነ ሰዓት መሰናክል መሆኑ አልቀረም።

ችግሩ በአምራቹ ኤኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ በግልጽ የሚታይ ሲሆን በሌላ በኩል በተለይም በአሜሪካ የአክሢዮንና የምንዛሪ ገበዮች ላይ ያልተጠበቀ ጎጂ ውዥቀትን ሊያጠነክር የሚችል ነው። በምንዛሪው ገበዮች ላይ የሚታየው ውዥቀት ደግሞ ዞሮ ዞሮ በአምራቹ ኤኮኖሚ ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል። ለምሳሌ ይህን መሰሉ ሁኔታ ፍጆታንና የመዋዕለ ነዋይ ዝግጁነትን ሊቀንስ ይችላል። አደጋውን በአሜሪካ የበለጠ የሚያጠነክረው ደግሞ ንብረት በአብዛኛው በአክሢዮን መልክ የሚያዝ በመሆኑ ነው።
ሌላው በአውሮፓው የኤውሮ ምንዛሪ ክልል የዕዳው ቀውስ ሊጠናከር መቻል ነው። የጃፓን መድህን ኩባንያዎችና የመዋዕለ ነዋይ ባለቤቶች በውጭ ብዙ ገንዘብ አከማችተዋል። ይሄው በአውሮፓ ሕብረት ,ውስጥ ብቻ 800 ሚሊያርድ ኤውሮ ይጠጋል። ጃፓን ታዲያ አሁን ለመልሶ ግንባታው ተግባር ብዙ ገንዘብ ትፈልጋለች። እናም ይህን በአውሮፓ የተከማቸ ሃብት ትፈልገዋለች ማለት ነው። ይህም በሕብረቱ ውስጥ ያለው የዕዳ ቀውስ ይበልጥ እንዲጠናከር ነው የሚያደርገው።

እርግጥ ይህም ሆኖ የጃፓን ሁኔታ ዓለምን እንዳለ ከለየለት ቀውስ ላይ የሚጥል አይሆንም። በሌላ በኩል የፉኩሺማ የአቶም ጣቢያ ድራማ ግን የተፈራው ከባድ ፍንዳታ ሳይደርስም ዘላቂ ለውጥን የሚጠይቅ ነው። ስለዚህም ያን ፖዘር እንደሚሉት በተለይም በረጅም ጊዜ የኤነርጂ ፖሊሲ ረገድ ስሌት መደረጉ ከመቼውም ይበልጥ ግድ ይሆናል።

“ጀርመን ከአቶም ሃይል አጠቃቀም በፍጥነት መላቀቅ ስለሚቻልበት ሁኔታ ማሰብ ጀምራለች። ቻይና ራሷ ሳትቀር በአጭር ጊዜ ግንቢያው እንዲቆም ማድረጓ አልቀረም። ይህም አማራጭ የኤነርጂ ምንጮችን የመፈለግ ጥረታችንን እንድናጠናክርና እርግጥ የማዕድን ነዳጆችንም ይበልጥ እንድንጠቀም ያደርገናል ማለት ነው”

በሌላ አነጋገር እነዚህንና አማራጭ የኤነርጂ ምንጮችን በፍጥነት ፍቱን በሆነ መንገድ መጠቀም ካልተቻለ በፖዘር ግምት የአሌክትሪክና የቤንዚን ዋጋ እያደገ ነው የሚሄደው። ይህ በኤኮኖሚ ላይ የሚኖረውን ከባድ ተጽዕኖ መገመቱ ደግሞ ብዙም አያዳግትም።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ