1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢጋድ ጅቡቲ ያቀረበችውን ጥያቄ አጽድቋል

ሰኞ፣ ሰኔ 26 2009

ጅቡቲ እና ኤርትራን በሚያወዛግባቸው ድንበር ላይ ሰፍሮ የነበረው የኳታር ሰራዊት አካባቢውን ለቅቆ ከወጣ በኋላ በስፍራው ውጥረት ሰፍኗል፡፡ ትናንት አዲስ አበባ ላይ ስብሰባቸውን ያካሄዱት የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) አባል ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጅቡቲ ያቀረበን ጥያቄ ተቀብለው አጽድቀዋል፡፡

https://p.dw.com/p/2fqxl
Karte Eritrea Djibouti DEU
ምስል DW

Djibouti requests AU peacekeepers to fill Vacuum - MP3-Stereo

በዓመት ሁለቴ ለሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት መደበኛ ጉባኤ አዲስ አበባ የተገኙት የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ትላንት እሁድ ለስብሰባ ተቀምጠው ነበር፡፡ የስብሰባቸው ዋና አጀንዳ የነበረችው ጦርነት እና ረሃብ እያመሰቀላት የምትገኘው ደቡብ ሱዳን ብትሆንም በጅቡቲ እና በኤርትራ መካከል የተፈጠረውን ውጥረትም ተመልክተዋል፡፡

በድንበር ይገባኛል የሚወዛገቡት ጅቡቲን እና ኤርትራን ለመሸምገል የሞከረችው የባህረ ሰላጤዋ ኳታር ውጥረቱን ለማርገብ ሰራዊቷን በሁለቱ ሀገራት ድንበር ላይ አሰፍራ ቆይታለች፡፡ ኳታር ሰራዊቷን ከሁለት ሳምንት በፊት በድንገት ካስወጣች በኋላ አወዛጋቢውን የራስ ዱሜራ ተራራ የኤርትራ ወታደሮች ተቆጣጥረውታል ስትል ጅቡቲ ይፋ ክሷን ለአፍሪካ ህብረት አቅርባ ነበር፡፡

በትናንቱ የአዲስ አበባ ስብሰባ ደግሞ የኳታር ሰራዊት አካባቢውን ከለቀቀ በኋላ የተፈጠረውን ክፍተት የአፍሪካ ህብረት እንዲሞላው ጥያቄ አቅርባለች፡፡ የኢጋድ የሰላምና የጸጥታ ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ተወልደ ገብረመስቀል ለዶይቸ ቨለ እንደተናገሩት ጥያቄው ጁቡቲ የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል ወደ ቦታው እንዲልክ ፍላጎቷን ያሳየችበት ነው፡፡

“የጅቡቲ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይሄን ጉዳይ አንስተው የኢጋድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሙሉ ለሙሉ ተቀብለውት በኢጋድ ኮሚዩኒኬ መልክ እንዲወጣ ተወስኗል” ሲሉ በስብሰባው ስለተላለፈው ውሳኔ ያስረዳሉ፡፡

በጅቡቲ እና በኤርትራ መካከል የሰፈነውን ውጥረት ከማባባስ ሁለቱም ወገኖች እንዲቆጠቡ ያሳሰበው የአፍሪካ ህብረት የእውነት አፈላላጊ ቡድን ወደ አካባቢው እንደሚልክ አስታውቆ ነበር፡፡ ስለዚህ ጉዳይም በስብሰባው መነሳቱን አምባሳደር ተወልደ ይነገራሉ፡፡

“የኳታር ሰራዊት ከቦታው ወዲያውኑ እንደለቀቀ ጅቡቲ ለአፍሪካ ህብረትም፣ ለዓለም ህብረተሰብም አቤቱታ አቅርባ ነበር፡፡ እርሱን በተመለከተ ደግሞ የአፍሪካ ህብረት እዚያ ሄዶ ጥናት የሚያደርግ ኮሚቴ በጀቡቲ በኩል ላከ፡፡ በኤርትራም በኩል ተመሳሳይ ነገር ለማድረግ የኤርትራ መንግስት መልስ ስላልሰጠ እውነት አፈላላጊ ተልዕኮው በጅቡቲ በኩል ሄዶ ነው እስካሁን ያለውን ሪፖርት ያደረገው፡፡”

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኤርትራ ቆንስል አቶ ነቢል ሰይድ በትዊተር ገጻቸው ዛሬ ባሰፈሩት መልዕክት የጅቡቲን ክስ አስመልክቶ ኤርትራ ለአፍሪካ ህብረት ዝርዝር መረጃ ሰጥታለች ብለዋል፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ

ኂሩት መለሰ