1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጋና እና ሕ/ወጡ ማዕድን የማውጣት ችግር

ቅዳሜ፣ ሰኔ 8 2005

ምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ጋና ማዕድኑን ወርቅ በንግድ ወደ ወጭ በመላክ በአፍሪቃ ከደቡብ አፍሪቃ ቀጥላ ሁለተኛውን ቦታ ይዛለች። ይሁን እንጂ፣ ካለፉት ጥቂት ጊዚያት ወዲህ ይኸው ዘርፍ ማዕድኑ ወርቅ በሕገ ወጡ መንገድ በሚወጣበት አሰራር ትልቅ ችግር ገጥሞታል።

https://p.dw.com/p/18qKQ
ምስል picture-alliance/Valeriy Melnikov/RIA Novosti

በሕገ ወጡ ተግባር የተጠረጠሩ ብዙ ሰዎች፣ ቻይናውያን ጭምር ታስረዋል። የጋና መንግሥት በሕገ ወጥ የወርቅ ማዕድን ማውጣት ስራ ተሰማርተዋል በሚል ከጠረጠራቸው ቻይናውያኑ መካከል አንዳንዶቹ ወደ ሀገራቸው የተባረሩ ሲሆን፣  የሚባረሩበትን ቀን እየተጠባበቁ ነው። ሆኖም፣ የጋና ኢሚግሬሽን ኃላፊዎች እንዳስታወቁት፣  አንዳቸም የወንጀል ክስ አይመሠረትባቸውም።

ሀብት ለማካበት በማሰብ ወደ ጋና የሄዱት ቻይናውያኑ ተጠርጣሪዎች ለጋናውያን ብቻ በተመደበው ንዑሱ የማዕድን ስራ ተሰማርተው ነው የተገኙት። አስፈላጊው ማዕድን የማውጣት ፈቃድ ሳይኖራቸው በዚሁ ስራ በተሰማሩበት ድርጊት የጋናን ሕግ መጣሳቸውን ባለሥልጣናት አስረድተዋል። ቻይናውያኑ በአካባቢ ባህላዊ መሪዎች መካከል የሚካሄዱ ውዝግቦችን እንዳባባሱ፣ የውኃ አቅርቦትን እንዳጠፉ፣ እንደበከሉ፣ በዚህም ያካባቢ ነዋሪዎችን ሕይወት አደጋ ላይ እንደጣሉ የጋና የመሬት እና የተፈጥሮ ሀብት ሚንስቴር ያወጣው ዘገባ በግልጽ ማሳየቱን ባለሥልጣናቱ አክለው አስረድተዋል። ከዚህ ሌላም አንዳንዶቹ ቻይናውያን ተጠርጣሪዎች ካካባቢ ነዋሪዎች ጋ የተኩስ ልውውጥ ማካሄዳቸው ነው የተገለጸው።

Goldgewinnung Ghana
ምስል DW

ከ150 የሚበልጡት ቻይናውያን ተጠርጣሪዎች ባለፉት ሁለት ሣምንታት ውስጥ የታሰሩት የወርቅ ማዕድን በሚካሄድባቸው ማዕከላይ እና ምሥራቃዊ ጋና፣ እንዲሁም፣ በአሻንቲ አካባቢዎች ነው። የጋና መንግሥት ቻይናውያኑ ፈፀሙት ባለውና ለሀገር ስጋት ሆኖ ባገኘው ርምጃ አንፃር ፈጣን ውሳኔ እንዲወሰድ ያደረገው የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ጆን ማሀማ ያቋቋሙት የሚንስትሮች ግብረ ኃይል ነው። የግብረ ኃይሉ ሊቀ መንበርም የሆኑት የጋና የመሬት እና የተፈጥሮ ሀብት ሚንስቴር አልሀጂ ኢኑሳህ እንዳስረዱት፣ ቻይናውያኑ ላካባቢ ጥበቃ በደቀኑት ችግር የተነሳ ነው የተባረሩት።

የሚንስትሮቹ ግብረ ኃይል ግን በዚሁ ተግባሩ ወቅት አላስፈላጊ የኃይል ተግባር ከመውሰድ ሊቆጠብ እንደሚገባ በምክር ቤት የተወከሉት የተቃዋሚ ፓርቲ እንደራሴ ያው ፍሪምፖንግ አዶ አሳስበዋል። የግብረ ኃይሉ አባላት በሕገ ወጡ ተግባር ተሰማርተዋል ያሉዋቸውን ቻይናውያንን በማባረር ስም ያካባቢ ነዋሪዎችንም  እንዳጉላሉ እና ንብረታቸውንም እንዳጠፉባቸው ነው አዶ የገለጹት።
« ሕገ ወጦቹ ቻይናውያን መውጣት አለባቸው፤ ግን የማልስማማበት ጉዳይ የፀጥታ ኃይላት ከመዲናይቱ አክራ ሥልጣናቸውን ያካባቢ ባለሥልጣናትን ሳያማክሩ ወደካባቢ እያስፋፉ ያሉበትን ድርጊት ነው። ይህ በኔ አመለካከት የተሰጣቸውን ተልዕኮ አልፎ የሄደ ይመስለኛል። »
የጋና መንግሥት በሕገ ወጡ የማዕድን ማውጣት ስራ በተሰማሩት ግለሰቦች አንፃር ዘመቻ ከጀመረ ወዲህ ወደ ሁለት መቶ የሚጠጉ ቻይናውያን በገዛ ፈቃዳቸው ጋናን ለቀው ለመውጣት ዝግጁነታቸውን በመግለጽ፣ ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበትን ሂደት እንዲያፋጥንላቸው ኢሚግሬሽንን መጠየቃቸው ተሰምቶዋል። የጋና ኢሚግሬሽን ማዕከል ባለሥልጣናት የቻይናውያኑን ዜግነት ባፋጣኝ ካጣሩ በኋላ ጥያቄአቸውን እንደሚቀበሉ አስታውቀዋል። የጋና ኢሚግሬሽን ማዕከል ኃላፊ ፍራንሲስ ፓምዴቲ ተጠርጣሪዎቹ ቻይናውያን አሁን በማዕከሉ ማረፊያ ቤቶች እንደሚገኙ ቢገልጹም፣ በቻይናውያኑ አንፃር በውጭ ዜጎች ጥላቻ ሰበብ በደል ተፈፅሞዋል በሚል በመሥሪያ ቤታቸው ላይ የተሰነዘረውን ወቀሳ ሀሰት ሲሉ አስተባብለዋል።
« እኛ በውጭ ሀገር ዜጎች አንፃር ጥላቻ እንደሌለን ግልጽ ማድረግ አስፈላጊ ይመሰለኛል። እና ጋና የወጭ ዜጎች፣ ቻይናውያን ጭምር ሊሄዱባት የማይቻልባት ቦታ መታየት አይኖርባትም። ችግራችን ያለው በሀገራችን ውስጥ በሕገ ወጥ ተግባር ከሚንቀሳቀሱ የቻይና ዜጎች ጋ ነው። ብዙዎቹ በንዑስ ደረጃ ለጋና ዜጎች ብቻ በተመደበው የማዕድን ማውጣት ስራው ዘርፍ በመሰማራታቸው ይህንን ሕገ ወጥ ተግባራቸውን በቸልታ አናልፈውም፤ አስፈላጊውን ርማጃ በመውሰድ እናስወጣቸዋለን። »
የጋና መንግሥት ሕገ ወጡን የማዕድን ማውጣት ተግባርን ለማብቃት የጀመረው ጥረቱ ይሳካለት መሆን አለመሆኑ እንግዲህ ወደፊት የሚታይ ይሆናል። 

North Mara Gold Mine in Tansania
ምስል DW/J. Hahn

አርያም ተክሌ

መሥፍን መኮንን