1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጋዛ-የጥፋትና የዳግም ግንባታ ዑደት

ሰኞ፣ ጥቅምት 3 2007

ገንዘቡ እንደ ቃሉ ሁሉ ይንዥቀዠቅ ይሆናል።ለጋዛ ነዋሪዎች ሲሚንቶ፤ ብርድ ልብስ፤ የዱቄት ወተት ይገዛ-ይታደልበት ይሆናልም።ለወደፊቱ ተስፋና ዋስትና መሆኑ ግን ወይዘሮ አል ሔሉዉ እንደሚሉት ሲበዛ አጠራጣሪ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1DV5i
ምስል Reuters/M. Abd El Ghany

የዓለም-ሐያል፤ ሐብታም ሐገራት ፖለቲከኞች የተገነባዉን ማፍረስ ያዉቁበታል።አጥፊዎች ሲፈርስሱ አይቶ እንዳላየ ማለፍ ወይም አፍራሾችን መደገፉንም እንደበጎ ፈሊጥ ተክነዉበታል።ሲያፈርሱ ወይም ሲያስፈርሱ ቀጪ፤ተቆጪ የላቸዉም። ያስፈረሱትን ዳግም ለማስገንባት ግን የሚቀጡ-የሚቆጡትን ዓለም ማስተባበሩን ይችሉበታል።ከሥልሳ ዘመናት በላይ እያስፈረሱ-የሚያስገቧት ጋዛን ዘንድሮም-እንደእስከዘንድሮዉ አስፈርስዉ ዳግም ሊያስገነቧት ትናንት ቃል ገቡ፤ቃል አስገቡም።የተገባዉ ቃል ምንነት፤ የጋዛ ነዋሪዎች ተስፋ የለሽ ሕይወት ትኩረታችን ነዉ ።

እስራኤልና ምዕራባዉያን መንግሥታት «አሸባሪ» የሚሉትን የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ሐማስን ለማጥፋት የዘመተዉ የእስራኤል ጦር ጋዛን በሚያወድምበት መሐል-ባለፈዉ ነሐሴ ከዋሽግተን-ብራስልስ በተደጋጋሚ ከሰማናቸዉ መልዕክቶች አንዱ ይሕ ነበር።

«እስራኤል፤ ከሮኬቶች እራስዋን የመከላከል መብቷን እንደግፋለን።እስራኤል፤ አንድ ወጣት አሜሪካዊና ሁለት እስራኤላዊ ወጣቶችን የገደሉ ሰዎችን ለመያዝ ጥረት ከጀመረች በኋላ ሮኬት የመተኮሱን ሒደት የጀመረዉ ሐማስ ነዉ።እና አሳፋሪ ነዉ።አዎ ከባድ ነዉ።እንዲሕ አይነት (ወታደራዊ) ዘመቻ ማድረግ ከባድ ነዉ።ወጣቶችንና ሰላማዊ ሰዎችን በተመለከተ የሰጠሁት አስተያየት ማንም ሰዉ የሚሰጠዉን ነዉ።ይሁንና ጦርነት ከባድ ነዉ።ይሕን በግልፅ ተናግሬያለሁ።አሁንም እደግመዋለሁ። እስራኤል እነዚያን ዋሻዎችን ለማግኘት የምታደርገዉን ማድረጓን እንደግፋለን።»

Zerstörung im Gaza-Streifen
ምስል DW/S. al Farra

የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ ነሐሴ-2014 (ዘመኑ በሙሉ እንደጎር ጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ)።ኬሪ «ሐማስ ጀመረዉ» ባሉት የሮኬት ጥቃት ስልሳ-ሰባት የእስራኤል ወታደሮችና ስድስት ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።

እስራኤል ባንጻሩ የሐማስ ዋሻዎችን ለማጥፋት በሚል ሰበብ በከፈተችዉና ዩናይትድ ስቴትስ በደገፈችዉ ወታደራዊ ዘመቻ 2100 ፍልስጤማዉያን ተገድለዋል።በብዙ ሺሕ የሞቆጠሩ አካላቸዉ ጎድሏል።ብዛኞቹ ሠላማዊ ሰዎች ናቸዉ።አብዛኛዉ የጋዛ ሕዝብ ቤት ንብረቱ ወድሟል።18 000 መኖሪያ ቤቶች ጨርሶ ወድመዋል።ከሰባ ሺሕ የሚበልጡ ቤቶች በከፊል ፈራርሰዋል።

ዓለም ፕሬዳንት ዑመር ሐሰን አል-በሽርን ከሱዳን፤ ፕሬዝዳንት ኡሑሩ ኬንያታን ከኬንያ፤ የሚከስ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አላት። ላይቤሪያ እና ኮትዲቯርን በየዘመናቸዉ የመሩ ፖለቲከኞችን ከያሉበት እየያዘ የሚያስር ፍርድ ቤትም አላት።ፍልስጤም እና እስራኤል ላይ ለደረሰዉ ጥፋት ግን ተጠያቂዎችን መክሰስ፤ማሰር፤ ፍርድ ቤት ማቅረብ አይደለም «ተጠያቂ» ለማለት እንኳ የፈለገ-የሐየል ዓለም-ፖለቲከኛ የለም።ሌላዉ ጭራሽ አልደፈረም።

Bildergalerie Kinder der Welt Gaza
ምስል Mohammed Abed/AFP/Getty Images

በጋዛ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ተወካይ ስኮት አንደርሰን እንደሚሉት ባለፈዉ ሐምሌና ነሐሴዉ ጦርነት ቤት-ንብረቱ የወደመበት ሕዝብ ሁለት መሠረታዊ ነገሮች ይፈላጋል።

«የመጀመሪያዉ መሠረታዊ ነገር ሕዝቡ ለክረምቱ በቂ መጠለያ እንዲያገኝ ማድረግ ነዉ።ክረምቱ ተቃርቧል።በአራትና በስድስት ሳምንታት ዉስጥ የጋዛ አየር መቀዝቀዝ ይጀምራል።ሥለዚሕ ሕዝቡ ክረምቱን የሚኖርበት አስተማማኝ መጠለያ እንዲያገኝ ማድረግ አለብን።በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ግን ሕዝቡ የሚያስፈልገዉ ተስፋ እና ወደፊት በኑሮዉ የሚሆነዉን ማወቅ ነዉ።አብዛኛዉ ሕዝብ ይሕ የመጨረሻዉ ግጭት ለመሆኑ፤ እንዲሕ አይነቱ ግጭት ላለመደገሙ ተስፋ እንዲሰጠዉ ይፈልጋል።

እንደ ተስፋ ቢስነቱ ሁሉ ጥፋቱ ዳግም ላለመደገሙም ምንም ዋስት የለም።ከ1948 ጀምሮ በየጊዜዉ-እየወደመች ግን ጨርሶ እንዳትጠፋ ዳግም የምትገነባዉን ጋዛን ዳግም ለመገንባት ግን ዓለም ከስልሳ አምስት ዓመታት በላይ እንደለመደዉ እደገና ካይሮ ላይ ታደመ።ትናንት።

የጉባኤዉ አስተባባሪና መሪ ነሐሴ ላይ መንግሥታቸዉ የእስራኤልን ወታደራዊ ዘመቻ እንደሚደግፍ ያረጋገጡት የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ ናቸዉ።

«ከዚሕ ጉባኤ የሚጠበቀዉ ገንዘብ ብቻ አይደለም።የእስራኤልያዉያን፤ የፍልስጤማዉያን እና የሁሉንም የአካባቢዉ ሕዝብ ጉጉት የሚያሳካ ሠላም ለማስፈን ሁሉም ቃሉን እንዲያድስ ጭምር እንጂ።ይሕን ለማሳካት ፕሬዝዳንት ኦባማ፤ እኔ እራሴ እና ዩናይትድ ስቴትስ አበክረን እንደምጥር ቃል እገባላችኋላሁ።»

Portraitserie über Familien aus Gaza Rabia
ምስል DW/T. Krämer

የሠላም-ጥረቱ ቃል በርግጥ አስደሳች-ተስፋ ሰጪም ነዉ።ግን ባለፉት ስልሳ-አምስት ዓመታት ከተሰማዉ ቃል፤ ከተሰጠዉ ተስፋ የተለየ አለመሆኑ እንጂ ቀቢፀ-ተስፋዉ።በየዘመኑ የሠላም ቃል እየተገባ ለሁለተኛ ትዉልድ የቀጠለዉ ጦረነት ነዉ።እልቂት።ስደት፤ጥፋት።እንደገና ሌላ ጥፋት።

በኬሪ መሪና አስተባባሪነት ካይሮ ላይ የታደሙት ጉባኤተኞች በተጨባጭ ቃል የገቡትም ገንዘብ ለማዋጣት እንጂ-ተጨባጭ ሠላም ለማዉረድ አይደለም።ጋዛን ለማጥፋት ሐምሳ-ሁለት ቀናት ነዉ የፈጀዉ።ወትሮም በእስራኤል ከበባ የተዳከመችዉ ግዛት ከሐምሌዉ አጋማሽ ጦርነት በፊት ወደነበረችበት ደረጃ እስክትመለስ ድረስ፤ ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ዛሬ ለአካለመጠን ያልደረሰ ልጅ-ለማደግ፤ ለማግባት-ለመዉለድ፤ ለመዳር ከታደለ የልጅ ልጅ ያያል።

በፍርስራሽ ክምር ተዉጣ የካይሮ ጉባኤተኞችን ቃል ለምታዳምጠዉ ለጋዛዋ ወይዘሮም የነበረዉ በቅፅበት እንዳልነበረ የሆነበት ጥፋት የሚለወጥበትን ሰበብ-ምክንያት ለፈጣሪ መተዉን መርጣለች።ነዋል አል ሔሉዉ ነዉ ስሟ።

« ይሕ ቤትና የአትክልት ሥፍራዉ ለኔ የምድር ላይ ገነት ነበሩ።እንዲሕ ሆኖ ማየት በጣም ያሰቅቀኛል።ይሕ ሁኔታ እስኪለወጥ ደረስ የሚፈጀዉ ጊዜ ፈጣሪ ብቻ ነዉi የሚያዉቀዉ።ዓመት፤ሁለት ዓመት አስር ዓመት?ለመገንባት ከባድ ነዉ። እኛ ቤቱን ለመገንባት ሃያ-ስድስት አመት ለፍተናል።ባንድ ጊዜ ሁሉም ወደመ።»

የወይዘሮ አል ሔሉዉ ባለቤትም የሚስታቸዉን ፍርሐት-ሥጋት ለማስወገድ የሚሰጧት ተስፋ የለም።እንደ መኖሪያ ቤታቸዉ ሁሉ ይሰሩበት የነበረዉ አካባቢም ወድሟል።እና ሰዉዬዉ ሥራ የላቸዉም።ጋዛን የሚያስዳድረዉ ሐማስ በጦርነቱ ቤታቸዉ ለወደመባቸዉ ቤተሰቦች ለየቤተሠቡ 1500 ዩሮ አከፋፍሏል።

Geberkonferenz für den Wiederaufbau von Gaza Kerry und Sabah Al-Khalid al-Sabah
ምስል Reuters/C. Kaster

ገንዘቡን ሥራ ፈተዉ የተቀመጡት አክረም አል-ሔሉዉ ከቀለብ ወይም ከመጠለያ ቁሳቁስ አልፎ ቤት ለመገንቢያ ሊያዉሉት ከቶ አይቻላቸዉም ነበር።አሁን ደግሞ ከቦምብ-ጥይት የተረፉትን የጋዛ ነዋሪዎች ብርድ ሊያኮማትራቸዉ ነዉ።ክረምቱ ተቃርቧል።

«ክረምት ሊገባ ነዉ።ምሕረት አያዉቅም።ከለበስኩት ሸሚዝ ሌላ-የለኝም።የምቀይረዉ ምንም የለኝም።ለማሕሙድ አባስ ለሌሎቹም የዓለም ፖለቲከኞች የምናገረዉ-እዚሕ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆናችንን እንዲያዉቁት ነዉ።»

አያዉቁት ይሆን? ጠንቅቀዉ ያዉቁታል።ጠንቅቀዉ የሚያዉቁትን ጥፋት ለማስቆም ግን አልፈለጉም።ወይም አልቻሉም።ጠንቅቀዉ የሚያዉቋትን የወደመችዉ ጋዛን መልሶ ለመጠገን 4,3 ቢሊዮን ዩሮ ለማዉጣት ቃል ገብተዋል።

ከዚሕ ዉስጥ የዓለም አንደኛ ሐብታም፤ ልዕለ ሐያል ሐገር ዩናይትድ ስቴትስ 212 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብታለች።ዩናይትድ ስቴትስ ISIS በሚል ምሕፃረ-ቃል የሚጠራዉን አክራሪ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ለመደብደብ በትንሽ ግምት በሳምንት መቶ ሚሊዮን ዶላር ታወጣለች።28 ሐገራትን በአባልነት ያቀፈዉ የአዉሮጳ ሕብረት አራት መቶ ሐምሳ ሚሊዮን ዩሮ ለመስጠት ቃል ገብቷል።ከተቀረዉ ከ3,3 ቢሊዮን ዩሮ መሐል አብዛኛዉን ለማዋጣት ቃል የገቡት የአረብ ሐገራት ናቸዉ።

ገንዘቡ እንደ ቃሉ ሁሉ ይንዥቀዠቅ ይሆናል።ለጋዛ ነዋሪዎች ሲሚንቶ፤ ብርድ ልብስ፤ የዱቄት ወተት ይገዛ-ይታደልበት ይሆናልም።ለወደፊቱ ተስፋና ዋስትና መሆኑ ግን ወይዘሮ አል ሔሉዉ እንደሚሉት ሲበዛ አጠራጣሪ ነዉ።

«የወደፊቱ ሁሌም ያስፈራኛል።ከዋሻዋ ማዶ የሚታየኝ ብርሐን የለም።ነገሮች ይለወጣሉ ብዬ አላምንም።ይሕ ቤቴ አይደለም።ቤቴ ወድሟል።የት ነዉ የምገባዉ።ነገ የሚሆነዉ መዓልት ወሌት እንዳስጨነቀኝ ነዉ።ሁሌም ምንም ተስፋ አይታየኝም።»

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን የሚያቁቱትን ጥፋት፤ ተስፋ ካጡት ፍልስጤማዉን አንደበት ለመስማት ነገ ጋዛን ይጎበኛሉ።

Zerstörung im Gaza-Streifen
ምስል DW/S. al Farra

«የወደፊቱን ለመመልከትና ለወደፊቱ የተሻለ ነገር ለመመሥረት ለሚደረገዉ ጥረት እስፍራዉ ተገኝቶ መመልከት አስፈላጊ ነዉ ብዬ አምናለሁ።ለዚሕም ነዉ ከሕዝቡ በቀጥታ ለመስማት፤ በገፅ ተገኝቼ ሁኔታዉን ለመቃኘትና የገንባታ ጥረታችንን ለማበረታት ማክሰኞ ጋዛን እንደምጎበኝ ያስታወቅሁት።»

ከዚያስ? የሚሆነዉ ሲሆን ለመስማት ያብቃን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ